17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ መካሄዱ ይታወሳል። በኢንተርኔትና ከኢንተርኔት ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚመክረው ይህ ጉባኤ በማዘጋጀት በርካታ ጠቀሜታዎችን ማግኘት እንደሚቻል ሲጠቆም የነበረ ሲሆን፣ እንደተባለውም ኢትዮጵያም ከጉባኤው ብዙ ማትረፏ እየተገለጸ ይገኛል።
ጉባኤው የብዙ አገራትን ልምዶች መቅስም የተቻለበት እና የተገኙ ልምዶችም ኢትዮጵያ በዲጅታሉ ዘርፍ እያከናወነች ለምትገኘው ተግባር አጋዥ መሆኑም ታምኖበታል፤ ይህንን ልምድ ወደ ፖሊሲ በመቀየር መስራት እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። በተለይ ዲጂታል ኢኮኖሚውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመገንባት ትልቅ መሳሪያ መሆኑንም ይናገራሉ።
የጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄድ ለኢትዮጵያ በርካታ ፋይዳዎች ያሉት ስለመሆኑ ከጉባኤው በፊትም በሁዋላም በመንግስትም በኩል በተደጋጋሚ ተገልጧል። በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጉባኤው ለቀጣይ የበይነ መረብ አስተዳደር ግብአት የሚሆን ሀሳብ መለዋወጥ የተቻለበት መሆኑን አስታውቀዋል። በጉባኤው የተነሱት ሀሳቦች ለሁሉም አገሮች ጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፣ አገሪቱም ስኬታማ ጉባኤ ማካሄድ መቻሏን ተናግረዋል።
ጉባኤው በዘርፉ ባለሙያዎችም አድናቆት ተችሮታል። የግሎባል ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያው አቶ አበበ በቀለ የጉባኤው ተሳታፊ ነበሩ። እሳቸው እንደሚሉት፤ ለ17ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄደው የበይነመረብ ጉባኤ በኢትዮጵያ በመካሄዱ ብዙ ጥቅሞች ተገኝተውበታል።
የአገሪቷን ገጽታ ከመገንባት አኳያ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፤ ብዙ ኢትዮጵውያን ልምድ የቀሰሙበት መድረክም ነው። ይህንን እድል ሳያገኙ ቀርተው ወደ ውጭ አገር ሄደው ስብሰባውን መካፈል የማይችሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን እዚህ በመካሄዱ በአካልም ሆነ በርቀት ሆነው እንዲሳተፉ ማድረግ ያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
የዓለምን የምጣኔ ሀብት ልህቀትና የሰዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ከሚያቀላጥፉት ነገሮች መካከል ዋንኛው ኢንተርኔት መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢንተርኔት ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ አቶ አበበ አስታውቀዋል፤ በእኛ አገር ኢንተርኔት ተደራሽ ለማድረግ ያለውን ውጣ ውረድ ለመፍታት ብዙ ርቀት መሄድ እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፤ እንደዚህ አይነቶቹ ጉባኤዎች መካሄዳቸው የሌሎች አገራት ተሞክሮ የሚንሸራሸር እንደመሆኑ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚመላከትበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ጉባኤውን ሊሳተፉ ከመጡ ዓለም አቀፍ አገራት ተሳታፊዎች ጋር በኢንቨስትመንት፣ በእውቀት እንዲሁም ቴክኒካል በሆኑ በርከት ባሉ ጉዳዮች ላይ የእርስ በእርስ ግንኙነት የተፈጠረበት መድረክ እንደሆነም አንስተዋል። በተለይ በጉባኤው ተሳታፊ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ብዙ ልምድ አግኝተዋል ብለው እንደሚያምኑ ነው የገለጹት። ያገኙት ልምድ የሚጠቀሙበት እንደሆነና ለወደፊትም ሥራቸው መልካም እድል ይከፍታል ብለው እንደሚያመኑም ተናግረዋል።
‹‹እኔ በግሌ ብዙ ተጠቃሚ ሆኛለሁ›› የሚሉት አቶ አበበ፣ በጉባኤው ከተገኙ ከሠላሳ በላይ አገራት ተሳታፊዎች ጋር ከመተዋወቅ ባለፈ አብረን ተወያይተናል፤ በዚህም የልምድ ልውውጥ አድርገናል፤ እኔም ብዙ ልምድ አግኝቻለሁ ሲሉ ያብራራሉ። ‹‹ከእኔ ጋር ከተለያዩ አገራት የመጡ ተሳታፊዎች ብሄራዊ ሙዚየምን፣ ሳይንስ ሙዚየም እና የኢንቨስትመንት ቢሮን እንዲጎበኙ በማድረግ ከአገር ገጽታ ግንባታ አኳያም የራሴን አስተዋፅኦ አበርክቻለሁ ››ሲሉም ተናግረዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የነበራቸው አመለካከትና እዚህ መጥተው ከተመለከቱ በሁዋላ ያላቸው አመለካከት በእጅጉ መለያየቱንም ገልጸዋል። በተመለከቱት ነገር ደስተኛ መሆናቸውን ሲገልጹ መስማታቸውንም ባለሙያው ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ሰላም፣ በህዝቡ እንግዳ ተቀባይነትና የምግብ መጣፈጥ እጅግ በጣም መደነቃቸውን ሲናገሩ መስማታቸውንም ነው የገለጹት።
ስለኢትዮጵያ በውጭ ሚዲያዎች በሀሰት ሲሰራጩ የነበሩ መረጃዎች ሀሰት መሆናቸውን ተሳታፊዎቹ እንዲገነዘቡ ማስቻሉንም ተናግረዋል። ከጉባኤው ኢትዮጵያ እንደ አገር ብዙ ተጠቅማለች የሚሉት አቶ አበበ፣ በተለይ ከአገር ገጽታ አንጻር አሁን ያላትን የሰላም ሁኔታ፣ የቱሪዝም መስህቦቿን እንዲሁም እያከናወነች ያለቻቸው ተግባራት እንዲታወቁ ያደረገችበት እንደነበርም አመላክተዋል። እንግዶቹም ኢትዮጵያ አሁን ላይ እያሳየች ያለችውን እድገት በማየት ከአምስት ዓመት በኋላ ተመልሰን ስንመጣ ላናውቃት እንችላለን፤ ከእነ ጃፓን የማታንስ አገር ሆና ነው የምናያት እስከማለት የደረሱ እንዳሉም ነው የጠቆሙት።
ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት እንደዚህ አይነት ዓለም አቀፍ ጉባኤ አካሄዳ በሰላም ማጠናቀቋ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቅሰው፣ ስለአገሪቱ የተሳሳተ አመለካከት የያዙ የዓለም አገራትን አመለካከት መለወጥ የሚያስችል እንደሆነም አመላክተዋል። በተጨማሪም ከኢኮኖሚ ፋይዳም አንጻር በተገኘው የዶላር ገቢ አገር ተጠቃሚ መሆኗን ተናግረዋል።፡
አቶ አበበ እንደሚሉት፤ በ17ኛው ዓለም አቀፉ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ላይ ለውይይት የቀረቡት አምስት አጀንዳዎች ወሳኝና ጠቀሜታቸው የጎላ ነው። ከእነዚህም በኢንተርኔት ዙሪያ የሚያጠነጥኑት አጀንዳዎች አንደኛው ሁሉንም ሰው በማገናኘት ሰብዓዊ መብቶችን መጠበቅ የሚመለከት ሲሆን ሁለተኛው ተጠያቂነት በሚያስከትል መልኩ ደህንነትን በመጠበቅ ነው፤ ሦስተኛው መረጃዎች በአግባብ ማስተዳደር የግል ሚስጥር መጠበቅ ሲሆን አራተኛው አርተፊሻል ኢንተለጀንሲን ጨምሮ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ማድረግ ይመለከታል። የመጨረሻውና አምስተኛው የኢንተርኔት መቋራረጥ እንዳይኖር ተጠያቂነት በሰፈነ መልኩ እንዲካሄድ ማድረግ የሚመለከቱ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች ተካሂደዋል።
በተለይ የኢንተርኔት መቋራረጥ የሚከሰተው በተለያዩ ምክንያቶች ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰው፤ በአሁኑ ላይ ኢንተርኔት የለም ማለት ሥራ የለም ማለት እንደሆነም ነው ያመለከቱት። ምክንያቱም ባንኮች ሆነ ሌሎች መሠረተ ልማቶች በአብዛኛው ሥራቸውን የሚሰሩት በኢንተርኔትና በኢንተርኔት አማካኝነት ነው ይላሉ። ስለሆነም በእኛም አገር በዲጅታል ዘርፉ የተጀመሩት ሥራዎች በእጅጉ አበረታች መሆናቸውን ባለሙያው ጠቅሰው፣ ወደፊት ደግሞ በተሻለ መልኩ ሰርቶ ተምሳሌት ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
‹‹ኢትዮጵያ አሁን ላይ በኢንተርኔት ተደራሽነቱም ሆነ ተጠቃሚነት ረገድ የተሻለ አገልግሎት እየሰጠች ነው›› የሚሉት አቶ አበበ፤ ለአብነት ከውጭ አገራት ከመጡ ከጉባኤው ተሳታፊዎች ጋር ወደ ከተማ ወጣ በማለት ኢንተርኔት እንዲጠቀሙ አድርገናል ሲሉም ተናግረዋል። ተሳታፊዎቹ በዚያ ባገኙት የኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነት ሲያደንቁ ተመልክቻለሁ ሲሉ አብራርተዋል። በእነሱ አገር እንኳን እንደዚህ ብዙ የማይቋራረጥ ኢንተርኔት አቅርቦት እንደሌለ በመናገር አድናቆታቸውን ሲቸሩ ማስተዋላቸውን ያስረዳሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ኢንተርኔት ከብዙ ነገሮች ጋር የሚያያዝ በመሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች የኢንተርኔት መቋራረጥ አያጋጥምም ማለት አይደለም፤ በተለይ እንደኛ አገር ሁኔታ በኢንተርኔት ላይ የሚደርሰውን መቋራረጥ በኛ አገር ብቻ መቆጣጠር አንችልም፤ ምክንያቱም ኢንተርኔት አገር የለውም፤ አባት የለውም፤ አስተዳደር የለውም። ለዚህምነው ይህ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ያስፈለገበት ምክንያት። የዓለም አገራት በአንድ መድረክ ተሰብስበው ከመምከርም በላይ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት የሚሆን ምክረ ሀሳብ የሚያቀርቡትም ለዚህ ነው ሲሉ አቶ አበበ የሚናገሩት።
አሁን ላይ ያለው የኢንተርኔት ተደራሽነት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአገራችን ሲሰራበት በቆየው ሁኔታ ኢትዮ ቴሌኮም ብቻ ይዞ ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ አይችልም ነበር ሲሉ ያስገነዝባሉ። ተደራሽነትን ማስፋት ፋይናንስ፣ እውቀት እንዲሁም ምቹ አስተዳደር ይፈልጋል ይላሉ። የቴሌኮም ዘርፉ ለግል ሴክተርም መፈቀዱ ተደራሽነቱን በጣም ያሰፋዋል ነው ያሉት።
ኢንተርኔት ለሁሉም ነገር መሠረት ነው የሚሉት አቶ አበበ፤ ኢንተርኔትን ተደራሽ ማድረግ የአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።
የእኛ አገር ቴክኖሎጂ በሌሎች አገራት ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ሲፈልጉ ይሰጡናል፤ ሲፈልጉ ሊከለክሉንም ይችላሉ ያሉት አቶ አበበ፣ ለወደፊቱ ግን ራሳችንን የምንችልበትን መንገድ ለማመቻቸት መሥራት ይገባል ይላሉ። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ቴክኖሎጂ፣ ፋይናንስ እና እውቀት አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመዋል፤ በአንድነትና በትብብር በመሥራት ሁላችንም የሚጠበቅብንን ኃላፊነት መወጣት ከቻልን በበይነ መረብ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ህብረተሰቡን አሁን ካለበት የቴክኖሎጂ ግንኙነት በማውጣት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማድረስ ይጠበቅብናል ብለዋል።
እንደዚህ አይነት ጉባኤዎች በሚዘጋጁበት ጊዜ የአገር ገጽታ ፣የህዝብን ባህልና እሴቶች በማውጣት በደንብ መሥራት ይገባል ያሉት አቶ አበበ፤ በመንግሥት በኩል ለአገር የሚያመጣውን ፋይዳ በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሥራት እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት። ሚዲያዎች በዚህ ዙሪያ ሰፋ ያለ መረጃ በመዘገብ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ከዚህ በላይ ተባብረን በአንድነት ከሰራን አገራችንን ማሳደግ እንችላለን ብለዋል።
የበይነ መረብ /ኢንተርኔት/ ባለሙያው አቶ ሀብታሙ ዳምጤ በበኩላቸው የ17ኛው የበይነ መረብ ጉባኤ ኢትዮጵያ ብዙ አትርፋለች በማለት የአቶ አበበን ሀሳብ የሚያጠናክር ሀሳብ ሰንዝረዋል። የበይነ መረብ ጉባኤው በዘርፉ መሠራት ላለባቸው በርካታ ሥራዎች በር ከፋች መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ሀብታሙ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ብቻ በመታገዝ ብዙ ዶላር ወደ አገር ማስገባት ትችላለች፤ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ለተመለከተ ሌሎች የኢንተርኔት አይነቶችን ሳይጨምር ከዩቲዩብ ብቻ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ሊገኝ ይችላል። ኢትዮጵያም ቡና፣ ሥጋ እና ሌሎች የምርቶች አይነቶች ወደ ውጭ ልካ ከምታገኘው ገቢ የማይተናነስ ገቢ በዩቲዩብ ብቻ በመጠቀም ማግኘት ይቻላል።
ይህንን ለማድረግ አሁን ላይ ያለው ነገር በቂ ስላለሆነ በመንግሥት ደረጃ በፖሊሲ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ታይተው መስተካከል እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ለአብነት አሜሪካ ከ50 ሚሊዮን በላይ በዩቲዩብ እይታ ያላቸው ሰዎች ቁጭ ብለው ነው ዶላሩን የሚያገኙት። ኬንያም በቴክኖሎጂ መስክ በብዙ መልኩ ተጠቃሚ መሆኗንም ይጠቅሳሉ።
በኢትዮጵያም ከቀረጥ ነጻ ካሜራ እያስገቡ በኢትዮጵያ ፊልም፣ ሙዚቃ እየሰሩ በጣም ብዙ አሳታሚዎች፣ ፕሮዲውሰሮች ተጠቃሚ እንደሆኑም ጠቅሰው፣ አንድ ዶላር ግን ለኢትዮጵያ ጠብ እየተደረገላት እንዳልሆነ ጠቁመዋል። ይህም የሆነው ምንም አይነት አስገዳጅ ሕግ ባለመኖሩ በቀላሉ ማግኘት የሚቻለውን ዶላር ማግኘት አልቻልንም ሲሉ አስረድተዋል።
ይህ የበይነመረብ አስተዳደር ጉባኤ ብዙ ልምዶችንና ተሞክሮዎች የተቀሰመበት መሆኑንም ተናግረው፣ የተገኘውን ተሞክሮ ወደእኛ አገር በማምጣት ተግባራዊ በማድረግ ብዙ ማትረፍ እንደሚቻልም ተናግረዋል። ዘርፉ ትልቅ ዘርፍ እንደሆነና በጣም ቢሰራበት የገቢ ምንጭ መሆን እንደሚችልም አመልክተዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በዚህ ዘርፍ ወደፊት ለመውጣት የሚያስፈልገው ሥራና ሥራ ብቻ ነው፤ በዘርፉ የተለያዩ ሰምምነቶች ማድረግና ዘርፉን ለማጠናከር የሚረዱ ሥራዎች መሥራት አለባቸው። በአብነትም ህንዶችን ይጠቅሳሉ፤ ህንዶች አሥር ላብቶፕ ላይ ዩቲዩብ ከፍተው ይቀመጣሉ፤ ለዚህ ምክንያታቸው ብዙ ተመልካች አግኝተው ዶላር ወደ አገራቸው ለማስገባት ነው ሲሉ ያብራራሉ።
በኛ አገር ብዙ መሥራት እየቻልን እንዳንሰራ የሚያደርጉ አሠራሮች አሉ ሲሉ ጠቁመው፣ ይህን በማስወገድ ብዙ መሥራት የምንችልበትን ሁኔታ መመቻቸት አለበት ይላሉ። አገሪቱ በዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚመለከተው አካል ኃላፊነቱን በመውሰድ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4 /2015