በአራት አመታት ጊዜ ውስጥ 20 ቢሊየን የዛፍ ችግኞችን ለመትከል ዓላማ በማድረግ በመላ አገሪቱ የተከናወነው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 25ቢሊየን ችግኞችን በመትከል ከእቅድ በላይ በመፈጸም ስኬት ማስመዝገቡ ይታወሳል። ይህ ስኬት በአገር ደረጃ በተፈጠረ ንቅናቄና በስራ የተመዘገበ ነው።
መርሀ ግብሩ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች በደን መመናመንና መራቆት እንዲሁም በአፈር መሸርሸር የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል። እንደ አገር የተያዘውን የልማት እቅድ ለማሳካትና እድገትን ለማረጋገጥም ሥነ ምህዳሩ የተስተካከለ አካባቢ መኖር እንዳለበት የዘርፉ ባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ እየሰጡ እንደመሆናቸውም መርሀ ግብሩ ከፍተኛ ፋይዳ አለው።
በመንግስት በግብርናው ዘርፍ ከተያዙ ሰፋፊ ስራዎች ሌላው የስንዴ ልማት መሆኑ ይታወቃል። በዚህም በመኸርና በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከፍተኛ ምርት ማግኘት እየተቻለ ነው። ባለፈው አመት 26 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ በበጋ መስኖ ማግኘት ተችሏል፤ በዚህ የምርት ዘመን ደግሞ 52 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ ነው።
በእንስሳትና እንስሳት ውጤቶች፣ በዶሮና እንቁላል፣ በአሳ፣ ንብ ማነብና በመሳሰሉት ላይ በስፋት ለመስራትም እንዲቻልም መንግስት የሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብር በይፋ እንዲጀመር አድርጓል። በአርባ ምንጭ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ይፋ የተደረገው ይህ መርሃ ግብር፣ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችም በይፋ ተጀምሯል።
አሳን ጨምሮ የእንስሳትና እንስሳት ውጤት ምርትን በማምረት ላይ ባተኮረው በዚህ መርሀ ግብር ኋላቀር የአመራረት ዘይቤዎችን ከመቀየር ጀምሮ ዘመናዊና የተሻሻሉ ዝርያዎችን ወደልማቱ በማስገባት በዘርፎቹ ስኬት ለማስመዝገብ ታቅዶ ነው ወደ ሥራው የተገባው።
ንብ ማነብ በሌማት ቱሩፋት መርሀ ግብሩ ከሚሰራባቸው መካከል አንዱ ነው። ለሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብር ንብ ማነብ ያለውን አበርክቶ በተመለከተ በዓለም አቀፍ ሥነ ነፍሳትና ሣይንስ ሥነ ምህዳር ማዕከል (አይ.ሲ.አይ.ፒ ኤ) የሞይሽ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ወርቅነህ አያሌው እንደገለጹልን፤ በሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብር እንደሚለሙ ከሚጠበቁት አንዱ የንብ ማነብ ስራ ነው፤ ከንብ ማነብ የሚጠበቀው ውጤት ማርና የማር ውጤት የሆነው ሰም ብቻ አይደለም። የአካባቢ ሥነ ምህዳርን ለመጠበቅም መርሀ ግብሩ የላቀ ድርሻ ይኖረዋል።
ንቦች ከቦታ ቦታ ባላቸው የመዘዋወር ባህሪ (ኮሎኔሽን) በተለያዩ ሰብሎች ላይ አስተዋጽኦ አላቸው። መሬት ላይ የረገፈ አበባ በንቦች አማካኝነት ወደ ሌላ ምርትነት ይቀየራል። ለአብነትም ቡና ልማት ላይ እስከ 25 በመቶ የሚሆን ምርት በማስገኘትና በጥራት ላይም ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል። ይህ ጠቀሜታ አቮካዶ ላይ እስከ 27 በመቶ ሐብሐብ(ወተርሜሎን)እስከ 84በመቶ ይደርሳል። ቅባት እህሎች ደግሞ ኑግ፣ ሱፍ፣ ተልባ ይጠቀሳሉ። ቅመማቅመም ላይም ውጤቶች ታይተዋል። ንብ ማነብ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል በማሳተፍ መንግሥት ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት በማገዝ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን በማስገኘት ይጠቀሳል።
በመንግሥት የተያዘው የሌማት ቱሩፋት እቅድ ወደ ትግበራ ከመግባቱ በፊት ዓለም አቀፍ ሥነ ነፍሳትና ሣይንስ ሥነ ምህዳር ማዕከል (አይ.ሲ.አይ.ፒ ኤ) በየሽ ፕሮጀክት በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና ትግራይ ክልሎች የንብ ማነብ ፕሮግራም እየተገበረ መሆኑን ዶክተር ወርቅነህ ይጠቅሳሉ። ፕሮግራሙ በማስተር ካርድፋውንዴሽንና በመንግሥት የጋራ ስምምነት የሚተገበር መሆኑንም ገልጸዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ የንብ ማነብ ሥራው ወጣቶችንና ሴቶችን ማእከል አድርጎ የሚከናወን ነው። በዚሁ መሠረትም አይ.ሲ.አይ.ፒ ኤ በአራቱ ክልሎች በአምስት አመት በየሽ ፕሮጀክት ወደ 10ሺ ወጣቶችን ማር አምርቶ ለገበያ እስከ ማቅረብ ያለውን ሂደት በስልጠና በማብቃት እንዲሁም ለንብ ማነብ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችንና የማምረቻ ቴክኖሎጂዎችን በማሟላት ድጋፍ በማድረግ የሥራ ተነሳሽነት በመፍጠር ለውጤት ማብቃት ችሏል።
ወጣቶቹ ባገኙት ክህሎት ተጠቅመው በጥራት የተመረተና የታሸገ ማር ለገበያ በማቅረብ ባህላዊውን የማር አመራረት ዘዴ በማዘመን፣ ለገበያም ምቹ አድርጎ በማቅረብ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑ የአምስት አመቱ ፕሮግራም ግምገማ ማሳየቱን ይገልጻሉ። ጥራቱን የጠበቀ ማር እንዲመረትና የውጭ ገበያንም ለመሳብ አምራች ወጣቶችን የማር ፌስቲቫል በማዘጋጀት የማበረታታት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
በአሁኑ ጊዜም ማር ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሥራ ላይ የተሰማሩ አንዳንድ ድርጅቶች ወደ አምራቾቹ በመሄድ የገበያ ጥናት በማድረግ፣ በማር ልማት ላይ በሚካሄድ የውይይት መድረክና ፌስቲቫል ላይ በመገኘት አስተያየት በመስጠት እያደረጉ ያለው ተሳትፎ ልማቱ የጋራ እየሆነ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል።
ዶክተር ወርቅነህ እንዳሉት፤ በተለያየ ምክንያት ልማቱ ላይ የማይቀጥሉ ሊኖሩ ስለሚችሉ ወደ ሥራው ሲገባ ሰፋ ያለ እቅድ ነው የሚያዘው። በየሽ ፕሮጀክት ፕሮግራም በእቅድ ከተያዙት 10ሺ ወጣቶች ወደ ስምንት ሺ የሚሆኑት በንብ ማነብ መቀጠል ችለዋል። ቀሪዎቹም ቢሆኑ ወጣ ገባ ማለታቸው እንጂ የማልማት ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል።
በየሽ ፕሮጀክት የተከናወነው ንብ ማነብ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ስራውም ገለልተኛ በሆነ አካል ተገምግሞ ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል። ይህንኑ መሠረት በማድረግም ወደ ሁለተኛው የሞይሽ ፕሮግራም ሰፍቶ ድጋፉ ተጠናክሮ ቀጥሏል። የማልማት ፍላጎትም እየጨመረ ነው። በሞይሽ ፕሮጀክት ፕሮግራም በአማራ ክልል ብቻ ለ30ሺ ወጣቶች ሥልጠና ተስጥቷቸው ወደ ልማቱ እንዲገቡ ተደርጓል። በጦርነት ቀጠና ውስጥ በነበሩት ዋግኽምራ፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ጎንደር አካባቢዎች ባጋጠመው ችግር ለተወሰነ ጊዜ ቢስተጓጎልም፣ አብዛኞቹ በልማቱ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው በክልሉ የማር ልማቱ ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል።
በፕሮጀክቱ እስካሁን በተሰሩት ሥራዎች ወደ 70ሺ ለሚሆኑ ወጣቶች በንብ ማነብ ላይ ሥልጠና ተስጥቷል። አገር ላይ ባጋጠመው ጦርነት ከልማታቸው የተስተጓጎሉና በተለያየ ምክንያት ወጣ ገባ ያለ ሥራ ከሚሰሩ ጥቂቶች በስተቀር ስልጠናውን ያገኙት በማልማት ላይ ይገኛሉ።
ከማር አልሚዎች ጎን ለጎን የንብ ኮለን እንዲሁም ለንብ ማነቢያ ቀፎዎች፣ በንብ ቆረጣ ወቅት ጥቅም ላይ የሚውል አልባሳት፣ የማር ምርት ማሸጊያና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁስን ለሚያቀርቡ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። አምራቾቹ አጣርተውና አሽገው ለገበያ የሚያዘጋጁት የማር ምርትም በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ እንዲሆን ፕሮጀክቱ የማቀነባበሪያ መሣሪያ ድጋፍ አድርጎላቸዋል።
የአካባቢው አስተዳደር በሚያመቻችላቸው ቦታ ላይም ማቀነባበሪያና መሸጫ ቦታ ግንብቶላቸዋል። በአካባቢያቸው በተሰጣቸው የእጽዋት ማልሚያም ቦታም በተመሳሳይ በድጋፍ ልማቱን እንዲያከናውኑ ይደረጋል። በዚህ መንገድ በሚደረግ ድጋፍ ነው ምርታማነታቸው እንዲያድግ የሚደረገው።
የምርት እድገቱ እንደ አልሚዎቹ ትጋት እንዲሁም በመካከል ላይ በሚያጋጥም ያልታሰበ ክስተት የሚወሰን ቢሆንም በእስካሁኑ የተመዘገበው አበረታች ነው። ልማቱ በባህላዊ፣ በሽግግር እና በዘመናዊ ቀፎዎች የሚከናወን ሲሆን፣ የግብዓት አጠቃቀሙን በማሻሻል በባህላዊ አመራረት ዘዴ በአማካይ ስምንት ኪሎና ከዚያ በላይ ማር እንዲገኝ ማድረግ ተችሏል።
አንዳንዶች ወደ 30 ኪሎ አግኝተዋል። በሽግግርና በዘመናዊ ቀፎዎች ግን እስከ 40 ኪሎና ከዚያም በላይ ምርት የሚያገኙ አሉ። ምርታማነቱን አስመልክቶ ዶክተር ወርቅነህ እንዳሉት፤ ብዙ አምርቶ ገበያውን ተደራሽ ከማድረግና ከብዛት ትርፋማ ከመሆን ይልቅ አልሚው በአካባቢ ላይ በሚያገኘው ገበያ ረክቶ በመቅረት በስፋት ለማምረት ባለው ፍላጎት ላይ ክፍተት ይስተዋላል። በስፋት ማምረት ላይ መሥራት እንደሚገባ ግንዛቤ በመያዙ ሁሉም በመኖሪያ ግቢው ጭምር እንዲያለማ መነቃቃት እየተፈጠረ ነው። በዚህ ዘዴም ሴቶች ውጤታማ ሆነው ተገኝተዋል።
የንብ ማነብ ሥራውን ለማጠናከር ለስልጠናና ለልማቱ የሚያስፈልግ ግብዓት በማሟላት በአገር አቀፍ ደረጃ ለተከናወነው ንብ ማነብ ልማት ወደ 25ሚሊየን ዶላር ጥቅም ላይ መዋሉን ዶክተር ወርቅነህ ይገልጻሉ። በአምስት አመታት ጊዜ ውስጥ አንድ መቶ ሺ ወጣቶችን በንብ ማነብ ልማት ለማሳተፍ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም ወደ 55 ሚሊየን ዶላር በጀት መያዙን አመልክተዋል።
በፕሮጀክት ተደግፎ ከሚከናወነው በተጨማሪ ክልሉ ሀብቱ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲያስገኝና በተለይም አሁን የተያዘውን የሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብር ከማሳካት አንጻር እየተሰራ ስላለው ሥራ የአማራ ክልል እንስሳትና አሳ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ነጋ ይስማውን ጠይቀናቸው በሰጡን ምላሽ፤ በእንስሳት ልማት በእቅድ እየተሰሩ ካሉ መካከል ንብ ማነብና የሐር ልማት ትኩረት የተሰጣቸው ዘርፎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ለንብ ማነብ ሥራ ክልሉ ምቹ የሆኑ አካባቢዎች አሉት። የማር ምርታማነትን ለመጨመር ክልሉ የ10 አመት ስትራቴጂ እቅድ አዘጋጅቷል። እቅዱም ሲዘጋጅ ያለውን የንብ መንጋ ብዛት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሲሆን፣ የልማቱ ሥራ የሚመራበት ሥርዓትም ተካትቷል።
‹‹የፌዴራል መንግሥት ካስቀመጠው አቅጣጫም እልፍ ብሎ የተትረፈረፈ የሌማት ቱሩፋት ለማስመዝገብ ከሚል እቅድ አኳያም ከአስር አመቱ መሪ እቅድ የተቀዳ የአምስት ዓመት እቅድ በመቅረጽ የሌማት ቱሩፋቱ በሚፈልገው አቅጣጫ የተለጠጠ እቅድ አዘጋጅተናል። እቅዱንም ኅዳር 18 ቀን 2015ዓ.ም ይፋ አድርገናል›› ብለዋል።
አያይዘውም የንብ ልማት አያያዝና ዘመናዊ አሰራርን ለመከተል የሚያስችል ሥራ ለመሥራትም የእናት ንብ ማባዣ ማዕከሎችን በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ለመገንባት በመንግሥትና በአካባቢው በዘርፉ ላይ ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። ከባህላዊ ቀፎ ወደ ሽግግር፤ ከሽግግር ደግሞ ወደ ዘመናዊ ቀፎ የማሳደግ ሥራ መካተቱንና በአጠቃላይ ለማር ልማት የሚሆኑ እጽዋትን ከማልማት ጀምሮ አስፈላጊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።
እንደ አቶ ነጋ ማብራሪያ በክልሉና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች የተለያየ እገዛ እየተከናወነ ያለው የማር ልማት ውጤታማና ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ክልሉ ካለው የማልማት አቅምና ለአገር ኢኮኖሚ ካለው ፋይዳ አንጻር ብዙ መሥራት ይጠበቃል። ይህን ታሳቢ በማድረግ እየተከናወኑ ካሉት ሥራዎች ክፍተቶችን ለይቶ መፍትሄ ማስቀመጥ ይጠቀሳል።
ከሰብል ልማት ጋር ተያይዞ ከሚከሰቱትና የንብ ልማቱን ከሚጎዱት አንዱ ለሰብል ልማት የሚውሉ የኬሚካል ግብዓቶች መሆናቸውን አቶ ነጋ ጠቅሰው፣ ንቦችን የማይጎዳ የኬሚካል ርጭት እንዲከናወን ሥርዓት ማበጀት ያስፈልጋል ብለዋል። በዚህ ረገድም የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠትና የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንዲሁም ንብ ማነቡና የሰብል ልማቱ ሳይጎዳ ጎን ለጎን የሚሄድበትን የህግ ማእቀፍ ረቂቅ መዘጋጀቱን ይገልጻሉ። የህግ ማእቀፉ በውይይት ዳብሮ ተግባር ላይ ይውላል ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የህግ ማእቀፉ ካካተታቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል በሰብል ልማቱ ላይ ያለውና ኬሚካል የሚያቀርበው ባለድርሻ ምን ግንዛቤ አለው የሚለውን መለየትና ግንዛቤ እንዲፈጠርለት ማድረግ አንዱ ነው። የኬሚካል ርጭት ሲከናወን የሚከለከልበትን ቦታ መለየትና የርጭት ጊዜን ለመለየት አስገዳጅ የሆነ አሰራር ሊኖር ይገባል። ለአብነትም የሰብል ልማት ሲከናወን አረምን ለመከላከል የሚከናወን ርጭት መቼ መከናወን አለበት የሚለውን መለየት ይኖርበታል። በዚህ ሁኔታ ህጉ ከተቀመጠ፣ ህጉን የሚተላለፍ ሰው ሲገኝ በህግ እንዲጠየቅ ይደረጋል።
ስትራቴጂ እቅዱ ከመውጣቱ በፊት የተደረገ የጥናት ሥራ ስለመኖሩ አቶ ነጋ ለቀረበላቸው ጥያቄ በክልሉ ከሚገኙ ሰባት ያህል ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከልና የክልሉ ተቋማት ጋራ በመሆን በክልሉ ያለውን የማር ማልማት አቅምና ሀብት፣ በልማቱ አሁን የተደረሰበት ሁኔታና አገራዊ መረጃዎች ተሰብስበዋል። ለልማቱ የሚያስፈልግ የህብረ ንብ መጠንና ቀፎዎች እንዲሁም የክልሉን የህዝብ ብዛት መሠረት ያደረገ የጥናት ሥራ ተሰርቷል።
በክልሉ በአነስተኛ ደረጃ በሚከናወነው ባህላዊ ቀፎ እና ባለው የሥራ አጥ ኃይል በመጠቀም ልማቱን ማሳደግ የሚቻልበት ዕድል መኖሩ መረጋገጡንም ተናግረዋል። ለማር ልማቱ የሚያግዙ ተፋሰሶችና ተራሮች መኖራቸውም ልማቱን ያግዛል ያሉት ኃላፊው፣ በ2015በጀት አመት ጽህፈት ቤቱ ሽግግር ቀፎዎችንና እንስሳትን ሀብት ልማትን መሠረት በማድረግ 90ሺ ወጣቶች በአዲስ መልክ የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዷል ብለዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2015