ተወዳጁና ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ የአለም ዋንጫ አንድ ክፍለዘመን ሊሞላ ጥቂት አመታት በቀሩት እድሜው ውስጥ ተዘርዝረው የማያልቁ ታሪኮችን አስተናግዷል። እያንዳንዱ የአለም ዋንጫ በአራት አመት አንዴ መጥቶ ሲሄድ ልክ እንደ ትናንት የሚታወሱ የራሱን የሆነ ትውስታን ጥሎ ያልፋል። ከዚህ በፊት የተካሄዱት ሃያ አንድ የአለም ዋንጫዎች እያንዳንዳቸው የራሳቸው ጣእምና ትውስታ፣አዳዲስ ታሪክ፣ አስደሳችና አሳዛኝ ክስተቶችን ጥለው የኳታሩ 2022 የአለም ዋንጫ ላይ ደርሰናል። ካለፉት በርካታ የአለም ዋንጫዎች አሜሪካ ያስተናገደችው የ1994ቱ 15ኛው አለም ዋንጫ ግን በአንድ አሳዛኝና አስደንጋጭ እንዲሁም ለማመን የሚቸግር ክስተት ዛሬም ድረስ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ይታወሳል።
የዘንድሮውን የአለም ዋንጫ ያነሳሉ ተብለው ግምት ከተሰጣቸው አገራት ግንባር ቀደም የሆነችው ብራዚል ቻምፒዮን የነበረችበት የአሜሪካ የአለም ዋንጫ፣ በእግር ኳስ ታሪክ ከአሳዛኝ ክስተቶች አንዱና ሁሌም የማይረሳ የሆነውን የአንድሬስ ኤስኮባር የግፍ ግድያ ሰብዓዊነትንና የአለም እግር ኳስ ቤተሰብን ያስደነገጠ ታሪክ የተፈጸመበት ሆኖ ይበልጥ ይታወሳል። እኛም በስፖርት ማህደር አምዳችን ይህን አሳዛኝ ክስተት መለስ ብለን ልናስታውሰው ነው።
አሳዛኙ ክስተት ዛሬ ታሪክ ሆኖ እንዲታወስ ያደረገው አጋጣሚ እንዲህ ይጀምራል። በአሰልጣኝ ፍራንቺስኮ ማቱራና የሚመራው የኮሎምቢያ ብሔራዊ ቡድን ከጅምሩ ዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ በላቲን አሜሪካ አህጉር በምድባቸው ባደረጉት የማጣሪያ ደርሶ መልስ ጨዋታ አስገራሚ ውጤት አግኝተዋል፤ በአለም ዋንጫውም ቢያንስ ለግማሽ ፍፃሜ እንደሚደርሱ ገምተዋል፡፡
ሰኔ 22/1994 አሜሪካ ከኮሎምቢያ። በአሜሪካ ምዕራብ ጠረፍ ካሊፎርኒያ ግዛት፤ ሎስ አንጀለስ ከተማ ፓሳዲና በሚገኘው ሮዝ ቦውል ስታዲየም ከ93 ሺህ በላይ ተመልካቾች የታደሙበት ወሳኝ ጨዋታ ነው። የኮሎምቢያ ተጫዋቾች ዝቅተኛ ግምት የተሰጣት አስተናጋጇ አሜሪካን እንደሚያሸንፉ ተማምነዋል፤ በጨዋታው 35ኛ ደቂቃ የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ጆን ሀርከስ የፍጹም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ለሚገኘው የቡድን አጋሩ ኢርኒ ስቴዋርት ለማቀበል ያሻገረውን ኳስ፤ የአትሌቲኮ ናሲዮናልና የኮሎምቢያ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ አንድሬስ ኤስኮባር በሸርታቴ ለማጨናገፍ ባደረገው ጥረት ግብ ጠባቂው ኦስካር ኮርዶባ ኳሷን ሊያድናት በሚችልበት አቋቋም ላይ አልነበረምና በስህተት በራሱ ቡድን ላይ ግብ አስቆጠረ።
ወቅቱ በኮሎምቢያ ስርዓት አልበኝነት፣ ቁማር፣ ግድያ፣ ዘረፋ፣ እገታ ፣ አንደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ተንሰራፍቶ የተደራጁ ወሮበሎች ታጥቀው መንግሥትን በሚያዙበት ሁኔታ በተለይ ሜድይን (ሜድሊን) ከተማ የወንጀለኞች መዲና ነበረች፡፡ ውጤቱን ተከትሎም በቁማር ብዙ ሚሊየን የተበሉ የኮሎምቢያ ማፊያ ቡድኖችና አለቆቻቸው አንድሬስ ኤስኮባር ላይ ጥርሳቸውን ነክሰው ቀጣዩን ጨዋታ እየተጠባበቁ ነበር።
ሰኔ 26 ስዊዘርላንድ 0- 2 ኮሎምቢያ ብታሸንፍም በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች የተሸነፈችው ኮሎምቢያ በውድድሩ ለመቆየት የአሜሪካና ሮማንያን ጨዋታ ውጤት መጠበቅ ነበረባት፤ ኮሎምቢያ እንድታልፍ የአሜሪካ ማሸነፍ፤ የሮማንያ ደግሞ መሸነፍ የግድ ነበር፡፡ ሮማንያ አሸነፈች ኮሎምቢያ ከውድድሩ ተሰናበተች፡፡
አንድሬስ ኤስኮባር ወደ ሀገሩ ተመለሰ። ጥንቃቄ እንዲያደርግና ለተወሰነ ጊዜ ከእይታ ሸሸግ እንዲል ከወዳጆቹ የተሰጠውን ምክር ችላ ብሎ፤ ከቀናት በኋላ ምሽቱን ለመዝናናት ከጓደኛው ጋር ሜድይን ወደሚገኘው ‘ኤል ኢንዲዮ’ ባር አቀና፤ ትንሽ ቀማምሶ እየተጨዋወተ ሳለ ከመሀል የተወሰኑ ሰዎች ይሰድቡትና ያንጓጥጡት ጀመሩ። በሁኔታው በመከፋት መጠጥ ቤቱን ለቆም ወደ መኪናው አመራ። ሰዎቹ ተከትለውት መጡ፤ ከሶስቱ መሀል አንዱ ሁምቤርቶ ካስትሮ ሙኞዝ ሽጉጡን አውጥቶ አከታትሎ ስድስት ጥይት ኢስኮባር ላይ አርከፈከፈበት። ከአሜሪካ ጋር በነበረው ጨዋታ በቀጥታ ሲያስተላልፍ የነበረው የላቲን ኮሜንታተር ግቡ ሲቆጠር ይል እንደነበረው ገዳዩም ሲተኩስ በእያንዳንዱ ተኩስ “ጎልልልልል” “ጎልልልል”…. እያለ እንደነበር እማኞች ገልፀዋል፡፡ ከመኪናው ወንበር ሆኖ በደም ጨቅይቶ ለሞት እያጣጣረ የነበረው አንድሬስ በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ከ45 ደቂቃ በላይ ሊቆይ አልቻለም፤ ሐምሌ 2 ህይወቱ አለፈች፡፡
በማግስቱ ፖሊስ አንድሬስ ኤስኮባር ላይ ተኮሰ የተባለውን ሁምቤርቶ በቁጥጥር ስር አዋለው። ተጠርጣሪው ወንጀሉን “ፈፅሜያለሁ” ብሎ ቢያምንም ነገሩ ግን ሌላ ነው፡፡ ግድያው እንደተፈፀመ ተጠርጣሪዎቹ ከአካባቢው ለማምለጥ ከተጠቀሙባቸው መኪና የአንዱን ሰሌዳ ቁጥር እማኞች ለፖሊስ ሰጡ፤ ተሽከርካሪው ንብረትነቱ የተመዘገበው በሁለቱ ዝነኛ የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪ ወንድማማቾች ፔድሮ ጋዮንና ዩዋን ጋዮን ነበር። ሁምቤርቶ ደግሞ የወንድማማቾቹ ሹፌርና ጠባቂ ነው። ስለዚህ ሁምቤርቶ ያለ አለቆቹ እውቅና የዚህ አይነቱን ትልቅ ወንጀል ቢፈፅም ሞቱን የሚያስናፍቅ ቅጣት እንደሚከተለው ጠንቅቆ ስለሚያውቅ አያደርገውም። ግድያውን ተከትሎ ወንድማማቾቹ ፔድሮና ዩዋን ወዲያውኑ 3 ሚሊየን ዶላር ጉቦ በመስጠት አቃቤ ህግ ክሱ ሁምቤርቶ ላይ ብቻ እንዲያተኩርና ከጀርባ ያለውን ሀቅ እንዳይበረብር አፉን አዘጉት፡፡
በ1995 ፍርድ ቤት በቀረበለት ማስረጃ መሠረት ሁምቤርቶን ጥፋተኛ ነህ ሲል የ43 ዓመት እስራት ፈረደበት። በግድያው ወቅት የነበሩ ግብረአበሮችም ሆኑ ወንድማማቾቹ ከየትኛውም ክስ ነፃ ሆኑ፡፡ ሁምቤርቶ በእስር ቤት በሰራው የጉልበት ስራና ባሳየው መልካም ባህሪ በሚል (በቁጥጥር ስር ከዋለበት ጀምሮ) ከ11 ዓመት በኋላ ብቻ በ2005 ከእስር ተለቀቀ፡፡ ገና በ27 ዓመቱ ለተቀጨው አመለሸጋ ወጣት አንድሬስ ኤስኮባር የቀብር ስነ-ስርዓት ከመቶ ሃያ ሺ ህዝብ በላይ ተገኝቷል። በተወለደበትና በተገደለበት ሜድይን ከተማ በ2002 መታሰቢያ ሀውልት ቆሞለታል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2 /2015