በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ሦስት ነገሮችን እናያለን፡፡ የወልወል ግጭት፣ የአምባላጌ ጦርነት እና የዓለም የኖቤል ሽልማት፡፡
ፋሺስት ኢጣሊያ፤ ኢትዮጵያን ለመውረር እንደሰበብ የተጠቀመችበት ታሪካዊው የወልወል ግጭት (Wal-Wal Incident) የተከሰተው ከ88 ዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም ነበር፡፡
ኢጣሊያ በ1888 ዓ.ም ዓድዋ ላይ የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀልና ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ምስራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት አካል ለማድረግ ለ40 ዓመታት ያህል ስትዘጋጅና ጊዜ ስትጠብቅ ቆየች፡፡ በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1922 ወደ ሥልጣን የመጣው ቤኒቶ ሙሶሊኒ፣ ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን የውርደት ማቅ እንደሚበቀልና ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት አካል እንደምትሆን መዛት የጀመረው ገና በጠዋቱ ነበር፡፡
ለዚህም እንዲያመቸው የኢጣሊያ መንግሥት ራስ ተፈሪ መኮንን ኢጣሊያን በጎበኙበት ወቅት ‹‹ቪቫ ኢትዮጵያ›› እያለ ወዳጅ መስሎ ሸነገላቸው፡፡ እስከ አፍንጫው የታጠቀ በርካታ ጦር በኤርትራና በሌሎች የኢጣሊያ ምስራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት አካባቢዎች ላይ ያከማች ጀመር፡፡ የጦሩን ውጤታማነት አስተማማኝ ለማድረግም ሀኪሞችን፣ ሰላዮችንና ሌሎች ሙያተኞችን አብሮ አጓጓዘ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን›› የግዛት ባላባቶችን በጥቅም በመደለል ማስኮብለሉንና መረጃ መመንተፉንም ተያያዘው፤ በጨካኝነታቸው የታወቁትን እነ ኢሚሊዮ ዴ ቦኖ፣ ፒትሮ ባዶሊዮ፣ ሩዶልፎ ግራዚያኒና ሌሎች የጦር አለቆችን ወደ ምስራቅ አፍሪካ ላከ፡፡
ኢጣሊያ ይህንን ዝግጅት ካጠናቀቀች በኋላም ኢትዮጵያን የምትወርበት አጋጣሚ መጠባበቅ ጀመረች፡፡ ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም የኢጣሊያ ወታደሮች በኢትዮጵያ እና በእንግሊዝ ሱማሌላንድ (British Somaliland) መካከል ያለውን ወሰን ለመከለል የተላኩትን ሰዎች ይጠብቁ በነበሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ከፈቱባቸው፡፡ (ኢጣሊያ በአካባቢው ያለው የኢጣሊያ ሱማሌላንድ ግዛቷ ስለሆነ ወታደሮቿ በአካባቢው ነበሩ) ውጊያ ተደረገና በሁለቱም ወገኖች በኩል ሰውነት ቆሰለ፣ አካል ጎደለ፣ የሰው ሕይወት ጠፋ፡፡
ኢትዮጵያም ስሞታዋን ለኢጣሊያ መንግሥት ስታቀርብ፤ የኢጣሊያ መንግሥት ይባስ ብሎ የተበደለ መሆኑን በመግለፅ የሚከተሉትን ‹‹የመደራደሪያ ጥያቄዎች›› አቀረበ፡፡
አንደኛ፤ የወቅቱ የሐረርጌ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ገብረማርያም ወልወል ድረስ ሄደው እዚያ የሚገኘውን የኢጣሊያ የጦር መሪ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም ይቅርታ እንዲጠይቁ፣ አንድ የኢትዮጵያ የጦር ጓድ ለኢጣሊያ ሰንደቅ ዓላማ ሰላምታ እንዲሰጥ፣ በኢትዮጵያ በኩል ለተደረገው የማጥቃት እርምጃ ኃላፊ የሆኑት ባለስልጣኖች ሁሉ ተይዘው የኢጣሊያን ሰንደቅ ዓላማ እጅ ነስተው እንዲሻሩና ተገቢውን ቅጣት በአስቸኳይ እንዲያገኙ፣
ሁለተኛ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለቆሰሉት፣ አካላቸው ለጎደለውና ለሞቱት የኢጣሊያ ወታደሮች ካሣ የሚሆን 200 ሺህ ማርቴሬዛ (ጠገራ ብር) እንዲከፍል እንዲሁም በኢጣሊያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ፈፅመው ከባድ ጥፋት ያደረሱት ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ተይዘው ለኢጣሊያ መንግሥት እንዲሰጡ … በማለት የለየለት የትዕቢት ጥያቄ አቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትም የኢጣሊያን ሃሳብ ሳይቀበል ቀረ፤ ጉዳዩ በእርቅ እንዲያልቅ ለማድረግ ቢጥርም ሳይሳካ ቀረ፡፡ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን መውረሯ እንደማይቀር ሲታወቅ፣ ከዓድዋ ድል በኋላ ራሷን በኢኮኖሚ ሳታበለፅግ ለ40 ዓመታት ያህል ባለችበት የቆየችው ኢትዮጵያ መሳሪያ ለመግዛት እንቅስቃሴ ብታደርግም ቄሳራውያኑ ኃይሎች በመመሳጠር እንዳይሳካላት አደረጉ፡፡
ከዚህ በኋላ ፋሺስት ኢጣሊያ ለ40 ዓመታት ያህል ስትዘጋጅበት የቆየችውን እቅድ እውን ለማድረግ በሁሉም አቅጣጫዎች ኢትዮጵያን ወረረች፡፡ በዓለም አቀፍ ሕግጋት ፈፅሞ የተከለከሉ የጦር መሳሪያዎችን (የጦር አውሮፕላን፣ የመርዝ ጋዝ፣ …) ጭምር በመጠቀም በኢትዮጵያውያን ላይ እጅግ በጣም ከባድ የሆነ የጦር ወንጀል ፈፀመች፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያውያን አርበኞች ትግልና በወዳጅ ሀገራት እገዛ ከኢትዮጵያ ተሸንፎ እስኪወጣ ድረስም ዘመን ተሻጋሪ ውጤት(ተፅዕኖ) ያላቸውን በርካታ ወንጀሎችን በኢትዮጵያውያን ላይ ፈፅሟል፡፡
የወልወል ግጭት ኢጣሊያ ለብዙ ዘመናት ሉዓላዊነቷን ጠብቃ የቆየችውን ኢትዮጵያን ለመውረር የነደፈችውን እቅዷን ለማሳካት እንደሽፋን የተጠቀመችበት ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡
የአምባላጌ ጦርነት
ከዓድዋ ጦርነት ሦስት ወራት ቀደም ብሎ የተከናወነው የአምባላጌ ጦርነት የተካሄደው ከ127 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም ነበር፡፡
የአምባላጌውን ውጊያ የጀመሩት ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራ) እና ራስ አሉላ እንግዳ (አሉላ አባ ነጋ) ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ጦር የበላይ አዛዥ ልዑል ራስ መኮንን ነበሩ፡፡
ጦርነቱም በኢትዮጵያ አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን የወራሪው የኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያ መሸነፉ በመላው አውሮፓ በተለይም በተሸናፊዋ ኢጣሊያ ምድር ከፍተኛ ፍርሃት፣ ብስጭትና ቁጣ ፈጥሮ ነበር፡፡
በጦርነቱ ዕለት ንጉሰ ነገሥቱ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ለዓድዋ ጦርነት ዘመቻ ከአዲስ አበባ ተነስተው እየተጓዙና በመንገዳቸውም ላይ ሕዝቡን እያነጋገሩ ገና ወሎ ውስጥ ነበሩ፡፡ የድሉን ዜና ለዳግማዊ ምኒልክ የላኩላቸው ራስ መንገሻ ነበሩ፡፡
የኖቤል ሽልማት 121ኛ ዓመት
ኖቤል ሲባል አስቀድሞ የሚታሰበን ገናና የሆነው ሽልማቱ ነው። ሽልማቱ በየዓመቱ የሚሰጥ ሲሆን፣ ከተጀመረም እነሆ 121 ዓመታትን አስቆጠረ።
የኖቤል ሽልማት መስጠት የተጀመረው በዚህ ሳምንት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ደሴምበር 10 1901 ወይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ታኅሳስ 1 ቀን 1894 ዓ.ም ነው፡፡
ሽልማቱ የተጀመረው የአልፍሬድ ኖቤል አምስተኛው ሙት አመት በተዘከረበት ነው። የመጀመሪያዎቹ ሽልማቶችም የተሰጡት በስዊድን ስቶክሆልም ሲሆን፣ ሽልማቶቹ የተሰጡባቸው መስኮችም ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ህክምና፣ ስነ ጽሁፍ እና ሰላም ናቸው።
ቆይቶም ምጣኔ ሀብት ተጨምሮበታል። ኖቤል በ1895 ባረቀቀው መመሪያ መሠረት ሽልማቱ እየተሰጠ ይገኛል። በስማድናዊው አልፍሬድ ኖቤል ስም የተዘጋጀው ይህ ሽልማት ለሰው ልጅ ትልቅ ዋጋ ያላቸውን ተግባሮች ላከናወኑ እንዲሰጥ በሚል ኖቤል በተናዘዘው መሰረት የሚሰጥ ነው። ተሸላሚው የወርቅ ሜዳሊያ፣ ዲፕሎማ እና የገንዘብ ሽልማት ይሰጠዋል። ሎሬት በመባልም እንዲጠራ ይደረጋል። ኖቤል በምርምር ያገኛቸው የፈጠራ ስራዎች የሰው ልጅን የሚጎዱ በሚል በማህበረሰቡ ዘንድ ይሰነዘርበት የነበረው ነቀፌታ አሳስቦት ሽልማቱን ማዘጋጀቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ሽልማቱ እጅግ በጣም የተከበረ በሚል የሚታሰብና በዓለም ላይ ትልቅ ስኬታማ ሥራ በመሥራት ውጤታማ ለሆኑ ሰዎች ብቻ ይሰጣል። ኖቤል ከኢንቨስተመንቶቹ ከሚያገኘው ሀብት አብዛኛውም ለዚህ ሽልማት እንዲውልም ተናዟል። በቅድሚያ ለተለያዩ የግንባታ ስራዎች (ለሲቪል ስራ) የሚጠቅመውን ድማሚት የፈጠረው አልፍሬድ ኖቤል፣ ምርምሩ እየሰፋ ሄዶ ለጦር መሳሪያ የሚውሉ የተለያዩ አይነት ፈንጂዎችንና በርካታ የጦር መሳሪያ ተቀጣጣዮችን ፈጥሯል። 355 የፈጠራ ስራዎች የባለቤትነት ባለመብትም ነው። ኖቤል በዚህ ሽልማት ይበልጥ ቢታወቅም፣ ኬሚስት፣ ኢንጂነር፣ የፈጠራ ስራዎች ባለቤትና የንግድ እና ኢንቨስትመንት ሰው እንዲሁም በበጎ አድራጎት ስራውም ይታወቃል።
በእሱ ፈቃድ አራት የተለያዩ ተቋማት ተመስርተውም
ነው ሽልማቱ እየተካሄደ ያለው። በዚህ መሠረት ሦስት ስዊድናውያንና አንድ ኖርዌያዊ ሽልማቱን ይሰጣሉ። ከስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም የስዊድን ዘውዳዊ ሳይንስ አካዳሚ ለፊዚክስ ፣ለኬሚስትሪ እና ምጣኔ ሀብት ሽልማት ለመስጠት ሲወስኑ፤ የካርሎኒስካ ኢንስቲትዩት በፊዚዮሎጂ ወይም በሕክምና ዘርፍ እና የስዊድን አካዳሚ በስነ ጽሑፍ ዘርፍ ሽልማት ለመስጠት ይወስናሉ።
በኦስሎ መቀመጫውን ያደረገው የኖርዌይ ኖቤል ኮሚቴ ደግሞ በሰላም ዘርፍ ለሚሰጠው ሽልማት ይወስናል። የኖቤል ፋውንዴሽን ሕጋዊ ባለመብትና የፈንዶቹ ተግባራዊ አስተዳዳሪ በመሆን በመሥራትና የሽልማት ሰጪው ተቋሞች የጋራ አስተዳደራዊ ሚናው በመወጣት ያገለግላል። በሽልማቱ ዙሪያ መመካከርና መወሰን ግን አይችልም። ሽልማቱ የሚገባቸውን ሰዎች የሚወስኑት አራቱ ተቋማት ናቸው።
አልፍሬድ በርንሀርድ ኖቤል የተወለደው እ.ኤ.አ በ1833 በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም ነው። ኖቤል ከተወለደ ከአራት ዓመት በኋላ ቤተሰቦቹ ወደ ሩሲያ ሄዱ። አባቱ በሴንት ፒተስበርግ ከተማ የሚገኝ ፈንጂዎችን እና ሌሎች የጦር መሣሪዎችን የሚያመርት ስኬታማ ፋብሪካን ያስተዳድር ነበር። ይህም ሁኔታ ለኖቤል መልካም አጋጣሚ ሳይፈጥርለት እንዳልቀረ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ኖቤል ፈጠራዎቹን በየጊዜው እያሻሻለ ያወጣም ነበር። የተሻሻለ ፈንጂን በምርምር ማግኘት ችሏል። ይህም በዘመናዊ መልኩ ከፍተኛ ፍንዳታዎችን ማድረግ የሚያስችል ሆነለት።
ፈጠራው በአንድ ጊዜ በርካታ ሰዎችን የሚጨርስና አካባቢዎችን የሚያወድም ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ ነበር። ይህ የኖቤል ናይትሮግሎሲሪን ፋብሪካ እአአ በ1964 ፍንዳታ ይደርስበትና ታላቅ ወንድሙንና ሌሎች በርካታ ሰዎችን ይገድላል።
አልፍሬድ አሁንም ሌላ የተሻሻለ ፈንጂ ለማምረት ምርምሩን ቀጠለ። በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1867 ለአያያዝና ለአጠቃቀም የማያስቸግር ከፍተኛ ፍንዳታ ማድረስ የሚችል ‹‹ኪሴልጉር›› የተሰኘ ቅይጥ የፍንዳታ ፈጠራን እውን አደረገ። ይህ ለፈጠራ የተፈጠረ ሰው በቃኝ አላለም። በ1875 ትልቅ አቅም ያለው ጌላቲን የተሰኘ ድማሚት ፣ በ1887 ባሊሲታይትን አገኘ። በዚህ ወቅት ሌላ ወንድሙ ፈረንሳይ ውስጥ ይሞታል።
ጋዜጠኞች የሞተው አልፍሬድ ኖቤል ይመስላቸዋል። ጋዜጠኞቹ የኖቤልን ፈጠራ በጥሩ አይመለከቱትም ነበርና ይህን በሚመጥን መልኩም አንድ ጋዜጣ ‹‹ የሞት ነጋዴው ኖቤል ከዚህ አለም በሞት ተለየ›› በሚል ርዕስ ዘገባውን አቀረበ። ኖቤል ግን ይችን አለም የተሰናበተው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1896 ነው።
ዜናውን ያነበበው ሁሉ «የማታ የማታ እውነት ይረታ» እንደሚባለው ዘግይቶ ኖቤል አለመሞቱን ቢረዳውም ዜናውን ያነበበውን ኖቤል ግን ምቾትና ሰላም ነሳው። እውነትም ብሞት እንዲህ ተብሎ ነው የሚፃፍልኝ ብሎ ራሱን ጠየቀ። የኔ ብቸኛ ዝናዬ ሞትን ማከፋፈል ማለት ነው ሲል ተፀፀተ።
ያገኘውን ዝናና ዕውቅና በወንድሙ ሞት ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር ቆረጠ። በስሙ ፋውንዴሽን በመመሥረት በሥራው ከሚያገኘው ገቢ አብዛኛውን ለዚህ ሽልማት ድርጅት በመስጠት ተሸላሚዎች እንዲውል የወሰነውም ከዚህ በኋላ ነው።
ጥቁር አሜሪካዊው የሰብአዊ መብት ዋና ተሟጋችና ሰማዕት ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካው ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ የኖቤል ሰላም ሽልማት ከተቀበሉት መካከል ይገኙበታል። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሜናኽም ቤጊን እና የግብጽ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት የኖቤል የሰላም ሽልማት ተካፋዮች ሽልማቱን ተቀብለዋል።
የፍልስጤም መሪ ያሲር አራፋት እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ይስሐቅ ራቢን እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሺሞን ፔሬዝ በጋራ የተሰጣቸውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ከተቀበሉት መካከል ይገኙበታል።
የናይጄሪያው ወሌ ሶይንካ፣ የግብፁ ናጂብ ማህፉዝ እና የደቡብ አፍሪካው ናዲን ጎርዲመር በስነ ጽሑፍ ሽልማትን ተቀብለዋል። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሦስት ዓመት በፊት የሰላም የኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ሽልማት የበቁት ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በአገራቸው ውስጥ ለውጥ ለማምጣት በወሰዱት እርምጃ በተለይ ከኤርትራ ጋር ሠላም ለማውረድ ባደረጉት ጥረት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል ሰላም ሽልማት 100ኛው አሸናፊ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በወቅቱ በትዊተር ገጻቸው ‹‹ በኖርዌይ ኮሚቴ ውሳኔ ተደስቻለሁ፤ ለሰላም ለሚሰሩ እና ለሚተጉ በሙሉ የከበረ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፤ ይህ ሽልማት የኢትዮጵያና የአፍሪካ ነው›› ሲሉ አስፍረዋል፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2 /2015