አሁን አሁን ከሚገርሙኝ ነገሮች መካከል ሀገራችን ውስጥ በየኤፍ.ኤም ሬዲዮንና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚተላለፉልን ፕሮግራሞችና ፕሮግራሞቹ የሚቀርቡባቸው መንገዶች ዋነኞቹ ናቸው። ሁል ጊዜ ስገረም አንድ ቀን ግን በቁም ነገር ቁጭ ብየ ማስታወሻ ይዤ ሁኔታውን በሥርዓት ለመታዘብ ወሰንኩ። ከዚያም ከብዙዎቹ አንደኛውን የኤፍ.ኤም ሬዲዮ ፕሮግራም መሰራጨ ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ተከታተልኩት።
በዚህ መሰረት ለመከታተል የመረጥኩት ከቀኑ 10፡00 እስከ 11፡00 ሰዓት የሚቀርብ፤ የአንድ ሰዓት የሚቆይ የሬድዮን ፕሮግራም ነበር። አቅራቢዎቹ እንደሚሉት “አድማጮች እየተዝናኑ የሚማሩበት” የመዝናኛና የቁምነገር የሬዲዮ ፕሮግራም ነው። ቀደም ሲል በሌላ ቀን ሲተዋወቅ በሰማሁት መሰረት ፕሮግራሙ የሚጀምረው ልክ ከቀኑ አስር ሰዓት በመሆኑ አስቀድሜ ተዘጋጅቼ ስከታተል አስር ሰዓት ሊጀምር አልቻለም። ከፕሮግራሙ መጀመር በፊት ለአራት ደቂቃ ያህል የጣቢያው ዋና ዋና ዜናዎች ቀረቡ። ዜናዎቹ ተደምጠው እንዳበቁ ፕሮግራሙ ይጀምራል ብዬ ብጠብቅም አልሆነም። ለቀጣዮቹ አራት ደቂቃዎች ያህል ሙዚቃ ነበር የተደመጠው። ከዚያ በኋላ 10፡08 ላይ ፕሮግራሙ ተጀመረ። እንግዲህ ከተያዘለት የሰዓት ምጣኔ ላይ ስምንት ደቂቃዎች ተቀነሰለት ማለት ነው። ከዚያም ከ10፡08 እስከ 10፡16 ለስምንት ደቂቃወች ያህል የፕሮግራሙ አቅራቢ ጋዜጠኞች ፕሮግራሙን አሁንም ፕሮግራሙን ያቀርባሉ ብየ ስጠብቅ የፕሮግራሙን አጋሮች መልዕክት አቀረቡ። ከ10፡16 እስከ 10፡21 ለአምስት ደቂቃ ያህል እንደገና የአጋሮች መልዕክት በድጋሜ ቀረበ። ቀጥለው ከ10፡21 እስከ 10፡25 ባሉት አራት ደቂቃዎች “የሚወዷቸውንና የሚያከብሯቸውን” አድማጮቻቸውን ሙዚቃ ጋበዟቸው።
ከዚያ ከ10፡26 እስከ 10፡36 ለአስር ደቂቃወች ያህል የፕሮግራሙ ይዘት ቀረበ። ከ10፡37 እስከ 10፡41 ለአራት ደቂቃ በሙዚቃ እረፍት ተደረገ። 10፡42 እስከ 10፡45 ለሦስት ደቂቃ ከአድማጮች የመጡ አስተያቶች እና አድናቆቶች ቀረቡ። እንደገና ከ10፡46 እስከ 10፡ 53 የፕሮግራም ይዘት ያለው ጉዳይ ይቀርባል ብዬ ስጠብቅ አሁንም በድጋሜ “የአድማጮችን አስተያቶችና አድናቆቶች” መሰረት ያደረጉ ከዋናው የፕሮግራሙ ይዘት የወጡ ወሬዎች ተሰሙ። 10፡54 እስከ 11፡00 ለሦስተኛ ጊዜ የአጋሮች መልዕክት ተሰማና ፕሮግራሙ አለቀ።
ከዚያ ሰዓቶችን ማስላት ጀመርኩ። ከአንድ ሰዓቱ ፕሮግራም ውስጥ ስምንት ደቂቃ ተቀንሶለት ስለተጀመረ አጠቃላይ የሚኖረውን ሰዓት ስናሰላው 42 ደቂቃ ይሆናል። ከ42ቱ ደቂቃ ውስጥ 21ዱ ደቂቃ ለማስታወቂያ ውሏል። ስምንት ደቂቃ ለሙዚቃ፣ 13 ደቂቃ ከፕሮግራሙ ይዘት ውጭ የሆነ ወሬ የተወራበት ሲሆን የዕለቱን ፕሮግራም ለማስተላለፍ ጥቅም ላይ የዋለው አስር ደቂቃ ብቻ ነው። ይህን የአንድ ሬድዮ ጣቢያ ፕሮግራም ለማሳያነት አነሳሁ እንጂ አብዛኞቹ ማለት በሚቻልበት ደረጃ ተመሳሳይ ናቸው።
ይህም እውን የሬድዮ ጣቢያዎችና አብዛኞቹ ፕሮግራሞቻቸው “አዝናኝና አስተማሪ ፕሮግራም” ነው ለአድማጮች እያቀረቡ የሚገኙት? ማዝናናቱና ማስተማሩ ይቅርና እናቀርባለን የሚሉት ፕሮግራም በራሱ ቀርቧል ማለትስ ይቻላልን? በእንዲህ ዓይነቱ የአቀራረብ ሁኔታ ለሬዲዮ አድማጮችና ለቴሌቪዥን ተመልካቾች ከመገናኛ ብዙሃን እየቀረበ ያለው ፕሮግራም ወይስ ማስታወቂያ? ምናልባት በጋዜጠኝነት(Journalism) እና ማስታወቂያ (Advertisement) መካከል ልዩነት የለም ወይንም “ግብርና መር ኢኮኖሚ” እንደሚባለው “ማስታወቂያ መር ጋዜጠኝነት” አለ የሚል አዲስ ምሁር ካልተነሳ በቀር በጊዜ ሰሌዳው ውስጥ ያለው የሰዓት ምጣኔ በግልጽ እንደሚያሳየው አሁን ላይ በብዙወቹ የሃገራችን መገናኛ ብዙሃን እየቀረበ ያለው ፕሮግራም ሳይሆን ማስታወቂያ ነው። ይህ ደግሞ ከአገር አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ጋርም የተቃረነ ነው።
ይህ ሁኔታ መገናኛ ብዙሃኑ ከተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ማሰራጫ ከመሆን ይልቅ በብዛት የንግድ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎቶች ማሻሻጫ ሆነው ሲሰሩ መታየታቸው የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያወች ወይስ ሻጭና ገዥ የሚገናኙባቸው ገበያዎች ብለን እንድንጠይቅ ያስገድዳል። እናም በመገናኛ ብዙሃኖቻችን በሚቀርቡልን ዕለታዊና ሳምንታዊ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ከሕዝባዊ አጀንዳ መድረክነት ወይንም እንደ ስማቸው የብዙሃን መገናኛ ከመሆን ይልቅ የነጋዴዎች መገበያያ መድረክ እየሆኑ መምጣታቸው፤ “ለመሆኑ የጋዜጠኞችና የጋዜጠኝነት ዓላማ ምንድነው?” ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርግም ነው።
ጋዜጠኝነት ክቡር ሞያ ነው ብለናል። ክቡርነቱም ክቡር ከሆነው ከሰው ልጅ ህይወት ጋር በጥብቅ የተቆራኜ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን አመላክተናል። ጋዜጠኝነት ክቡር ብቻ አይደለም ታላቅም ነው። መነሻውም መድረሻውም ታላቁ የሰውነት ተፈጥሮ ነውና! ዓላማው ሕዝብና የሕዝብ ጥቅምን ማስጠበቅ ነውና። ተልዕኮው ሰውን አስቀድሞ በሰዎች መካከል እኩልነት፣ ፍትህ፣ ሰላም፣ ዲሞክራሲ እንዲኖር፤ የሃገርና ሕዝብ ዕድገትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ መንገድ ማቃናት ነውና። ከዚህ የሚበልጥ ትልቅ ዓላማም የለም።
ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ከማስታወቂያ ውጪ የሚቀርቡ ፕሮግራሞች ራሳቸው ከማስታወቂያ የተለዩ አለመሆናቸው ሲሆን ዜናና የህጻናት ፕሮግራሞች ጭምር በስፖንሰሮች የሚቀርቡበት ሁኔታ በህግ የተከለከለ መሆኑ የተዘነጋ ይመስላል።
ታዲያ አሁን ላይ በሀገራችን መገናኛ ብዙሃን የምናየው ከሕዝብ ይልቅ ጥቅምን መሰረት ያደረገ፣ ከብዙኃን አገልጋይነት ይልቅ የጥቂት ባለሀብቶችና ነጋዴዎች መገልገያ የሆነ፣ መረጃን ለሕዝብ ከመስጠትና ከማድረስ ይልቅ ዓላማው ለንግድ ማስታወቂያዎች ገበያን ማፈላለግ ዓይነት የሆነ ጋዜጠኝነት እንዴት ሊፈጠር ቻለ? እንዲህ ዓይነቱ ሥራ በእርግጥ ጋዜጠኝነት ሊባል ይችላል ወይ? ዋናው ጥያቄ ነው።
በቴሌቪዥን ወይም በኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎቻችን ፕሮግራሞች ላይ ሲተላለፉ የምንሰማቸው ማስታወቂያዎች ብዙውን ጊዜ የሚያልቁት “ለየት ያደርገናል”፣ “ተሸላሚ ሆነናል”፣ “ተመራጭ ሆነናል”፣ “ደንበኞቻችን ኮርተውብናል” …ወዘተ በሚሉ የምረጡኝ ቅስቀሳዎችና መፎክሮች ነው። ይህም የሚያመለክተው ድርጅቶቹ ደንበኛን በብቸኝነት ጠቅልሎ ለመያዝና ኢኮኖሚያዊ የበላይነትን ለማምጣት ከፍተኛ የእርስ በእርስ ፉክክር(ጦርነት ቢባል ይቀላል) ውስጥ መግባታቸውን ነው።
ይህንኑ የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ የተሻለው አማራጭ ደግሞ በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ደንበኛን ማብዛት ነውና ረብጣ ገንዘብ ከፍለው ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን ያስተዋውቃሉ። ረብጣ ገንዘብ የተከፈለው የአንድ ፕሮግራም አዘጋጅም ከሌሎች ፕሮግራሞች በላይ ተወዳጅ እና ተከፋይ ለመሆን የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል። በዚህ መካከል የሰው አለቃው ህሊናው መሆኑ ቀርቶ የሚያገኘው ብር ይሆናል። የሞራል ዋጋ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፣ ምን ይሉኝ ይጠፋል። አቅራቢው ድንገት ጋዜጠኝነቱን ረስቶ አስተዋዋቂ ሆኖ ቁጭ ይላል ማለት ነው።
ይህ አሳሳቢና አንገብጋቢ ጉዳይ በመሆኑ የብሮድካስት ባለስልጣንም ሬድዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ምን ያህል የማስታወቂያ አዋጁን በየፕሮግራሞቻቸው እየተገበሩ እንደሚገኙ በቅርብ በመከታተል አዋጁን ተላልፈው የተገኙት ላይ ሁሉንም ሊያስተምር የሚችል እርምጃ መውሰድ አለበት።
ይበል ከሳ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 1 /2015