ወላጆቿ ስሟን ሲያወጡላት በተለየ ምክንያት ነበር። እነሱ በልጃቸው ስያሜ ህይወታቸውን፣ ኑሯቸውን ማሳየት ይሻሉ ። በስም ማውጣት ውሰጣቸውን መግለጽ ይፈልጋሉ። እናት አባት ፍላጎትን በልጃቸው ሰበብ መግለጽ ፣ መንገር ቢሹ አዲሷን ጨቅላ ‹‹በትራቀች ››ሲሉ ሰየሟት። በትራቀች ማለት በጉራጊኛ ‹‹ባደገች፣በወጣች፤በተመነደገች ›› እንደማለት ነው።
በትራቀች በጉንችሬ አንዲት የገጠር ቀበሌ ልጅነቷን እንደእኩዮቿ አሳለፈች። ወላጆቿ አስቀድመው እንደተመኙት በትራቀች ለእነሱ ህይወትና ኑሮ ስኬት ዕድገታቸው ትሆን ዘንድ እያሰቡ አሳደጓት። ልጅነቷ ግን እንደታሰበው ባመረ መንገድ አልቀጠለም። የህጻንነት ዕድሜዋን በወጉ ሳታጣጥም ወላጅ እናቷ ‹‹እዚህ ነኝ›› ሳይሉ ከቤት ጠፉ፣ ራቁ ።
ይህ አጋጣሚ ለመላው ለቤተሰብ ፈታኝ ሆነ። የእማወራዋ በድንገት መለየት ሁኔታዎችን አከበዱት። ልጆች ያለእናት፣ አባወራውም ያለሚስት ኑሮን ለመምራት ህይወትን ለመቀጠል ተቸገሩ። እናታችን ትመጣለች፣ ትመለሳለች፣ ያሉ ልጆች ጠዋት ማታ ከበር ቆሙ፣ ዓይናቸውን አሻግረውም በናፍቆት ተሳቀቁ ። እናት እንደታሰበው አልመጡም። ልጆች ያለማቋረጥ በተስፋ ጠበቁ። አባወራው የሚስታቸውን መመለስ እያሰቡ ቀን ቆጠሩ ። የታሰበው አልሆነም። ከቤት የወጡት ወይዘሮ ሳይመለሱ ቀናት ወራት ነጉዱ።
አዲሰ ህይወት…
ወራት ያስቆጠረው የወይዘሮዋ መጥፋት ተስፋ አስቆርጧል። ርቀው መሄዳቸውን ያወቁት አባወራው ከእንግዲህ እንደማይመለሱ ያወቁ ይመስላል። እንዲህ ማሰባቸው በቀጣይ ህይወታቸው ላይ እንዲወስኑ አድርጓል። እማወራዋ ‹‹ቤቴን ፣ ልጆቼን›› ብለው ካልተመለሱ ትዳራቸውን እዳልፈለጉት ብዙዎች ገምተዋል።ይህ ግምት የአባወራውን ውስጥ ይበልጥ አነሳስቷል።አዲስ ጎጆ፣ አዲስ ህይወት መቀጠል እንዳለባቸው ካመኑበት ቆይቷል።
የታሰበው አልቀረም። አሁን ሰውየው ሌላ ሚስት አግብተዋል ፣ በአዲስ ትዳር አዲስ ህይወት መስርተው ልጆቻቸውን ማሳደግ ፣ ኑሯቸውን መምራት ይዘዋል።አዲሲቷ ወይዘሮ ለቤት ፣ለትዳሯ መበርታት መጣር ይዛለች። አባወራዋ ቀድሞ ያጣውን ልትሞላ፣ በአዲስ ሀይልና ብርታት እየታየች ነው፡ ሰውዬው በሙሽሪት ቅልጥፍና ሀሳባቸው ሞልቷል። የልባቸው ደርሷል። ይህ ስሜት ግን ከልጆች ልብ የደረሰ አይመስልም። ደስታ ከራቀቸው ቆይቷል። ሁሌም አዲሷን ወይዘሮ ሲያዩ እናታቸውን ያስታውሳሉ። እያስታወሱ ሆድ ይብሳቸዋል። ይተክዛሉ፣ያለቅሳሉ።
በትራቀች እናቷን ካጣች ወዲህ ውስጧ ሰላም የለውም። በየምክንያቱ ታኮርፋለች። ትበሳጫለች። ይህ እውነት ከእንጀራ እናቷ አላስማማትም። ደስተኛ አለመሆኗ፣ ሳቅ ጨዋታን መንፈጓ ወይዘሮዋን አናዷል።ሁሌም የእንጀራ ልጇን ባህርይ በመጥፎ ተርጉማ በጥርጣሬ ታያታለች ።
ውሳኔ…
ከቀናት በአንዱ በትራቀች ስታስብ ስታብሰለስል በቆየችበት ጉዳይ ላይ ወሰነች። ከእንግዲህ በተወለደችበት ቤት ማደግ ፣ መኖር እንደሌላባት ቆርጣለች ። ለውሳኔዋ ተጨማሪ ቀን አልሰጠችም። ቀጣይ ህይወቷ አዲስ አበባ እንዲሆን አስባለች። የዛኑ ቀን በእጇ ከነበራት ጥቂት ገንዘብ ጥቂቱን አንስታ መኪና ተራ ሄደች ።
ለመንገዷ ከአምስት ብር በላይ አልተጠየቀችም። መኪናውን ተሳፍራ መንቀሳቀሱን ጠበቀች ። በእጥፍ የቆየ መሰላት። ተሳፋሪዎች ወንበሩን ሲሞሉ ሞተሩ ተንቀሳቀሰ። በንቃት ራሷን አዘጋጀች። አገሯን ስትለቅ የነገ ህይወቷን አሰበች። ከዛሬ ነገ እንደሚሻል ተሰማት ። ደስ እያላት ስሜቱን አጣጣመችው።መኪናው ጉዞ ሲጀምር የአዲስ አበባን አቅጣጫ ያዘ። ልቧ ደጋግሞ ሲመታ ተሰማት።ቦታ አልሰጠችውም።ዓይኖቿን ተክላ መንገዷን ተከተለች።
አዲስ አበባ…
በትራቀች ዕድሜዋ ከአስራ ሁለት አያልፍም ። አዲስአበባን የምታውቃት በስም ብቻ ነው ። ከመኪናው ወርዳ ካሰበችው ደረሰች። ልደታ አካባቢ ያሉ አክስቶቿ ፊት አልነሷትም። መምጣቷ ሳያስከፋቸው እንግድነቷን ተቀበሉት። ትንሽዋ በትራቀች ለቀረባት ሁሉ ባዳ አልሆነችም። የታዘዘችውን ሰርታ ፣የተሰጣትን ጎርሳ መስላ ማደርን አወቀች። ዕቃ ማጠብና ፣ መላላክ ስራዋ ሆነ ።
ጥቂት ቆይቶ ዘመዶቿ ሌላ አሰቡ ። ከሰው ቤት ተቀጥራ ብትሰራ፣ ገንዘብ እንደምታመጣ መከሩ ። ምክክራቸው ሲጸድቅ በቤት ሰራተኝነት አስቀጠሯት። በትራቀች የእድሜዋ ለጋነት ብዙ አላራቃትም። ጥቂት ቀን ቆይታ ተመልሳ መጣች ። አክስቶች በግምት ምክንያቷን ጠየቁ። ስራው እንደከበዳት ፣ አቅሟን እንደፈተናት ተናገረች። መልሷን ባይወዱትም ‹‹ይሁን›› ብለው ተቀበሏት።
በሌላ ቀን ለበትራቀች ሌላ ስራ ተገኘላት ። ስራው ሞግዚነት ነው ። ጨርቋን ቋጥራ፣ ልትበረታ አስባ ከተባለው ቤት ደረሰች ። የቤቱ እመቤት ሰው በማግኘቷ ተደስታለች። በትራቀችን እንዳየች አልቆየችም። የመጀመሪያ ግዴታዋን ልጇን በማሳዘል አስጀመረቻት። ትንሸዋ ሞግዚት የወፍራሙን ህጻን ክብደት መቋቋም አልቻለችም። ከጀርባዋ ያለው ልጅ ከላይዋ ተመቻችቶ ክፉኛ አንገዳገዳት ። ቀጫጫ እግሮቿ ሸክሙን ሊይዙ ተቸገሩ ። የልጅነት አካሏ ተንቀጠቀጠ። ትከሻ፣ ወገቧ ከዳት፣ መላ ሰውነቷ ተብረከረከ።
በትራቀች አሁንም በአዲሱ ስራ አልዘለቀችም ። ልብሷን ቋጥራ በሄደችበት እግሯ ተመለሰች። አክስቶቿ ከስራዋ መውጣቷን አልፈቀዱም። መግባት ፣ መውጣት ድግግሞሹ ቀጥሏል ፡ይህ እውነት ከአክስቶች ጋር መሰልቸትን አስከትሎ ተያዥ እንድታጣ፣ ከሌላ እንዳትቀጠር ሰበብ ሆኗል።
አሁን በትራቀች ዕድሜዋ ጨምሯል። ከትናንት ዛሬ የተሻለውን እያሰበች ነው። በየጊዜው ስራ ብታገኝም ተያዥ የላትም። የአክስቶቿ ውሳኔ እያስከፋት ነው። ህይወቷ በሰው ቤት ስራ መወሰኑ ጭምር ያሳስባት ይዟል ።እንዲህ መሆኑ የትንሸዋን ልጅ ልብ አሸፈተ ።ደግማ ደጋግማ አሰበች። ከአክስቶቿ ቤት ይሻለኛል ያለችውን መረጠች። በድንገት ከቤት ወጥታ ከጎዳና ዋለች።
ጎዳና ነው ቤቴ
በትራቀች በድንገት ከቤት ወጥታ ከጎዳና መዋሏ አሳሳቢ ሆኗል ። እንደትናንቱ ህጻን ባትሆንም ማንነቷ ከስጋት ላይ ነው። እሷም ሴት መሆኗ፣ የደጁን ዓለም አለማወቋ እንደሚከብድ ታውቃለች። ። ህይወቷ በዚሁ ከቀጠለ የነገውን አታውቅም ።
ኑሮን አስክትለምድ ጥቂት ጊዜን በልመና አሳለፈች። ያገኘችውን እየቀመሰች የጎዳናውን ብርድና ጸሀይ ለመደችው። ጥቂት ቆይታ ግን ልመናውን ትታ በሌላ አማራጭ ተገኘች።ልደታ አካባቢ ውሎዋን በዕጣን ሽያጭ እያሳለፈች አዳሯን ከቤተክርስቲያኗ ግንብ ማድረግ ጀመረች።
ቀኑን ከጎኗ ሆና ቄጤማ የምትሸጠው ሴት እንደሷው መጠጊያ የላትም። አዳራቸውን በአንድ አድርገው ሌሊቱን አብረው ይገፋሉ። ህይወቷ በጎዳና የቀጠለው በትራቀች ውሎ አዳሯ ከዚህ ህይወት አልረቀም። ቀን ጸሀዩ ፣ሌት ብርድና ውርጩ እያንገላታት ሁለት ዓመታትን ቆጠረች።
አንድ ቀን ግን ከዚህ ያልተመቸ ህይወት የሚታደጉ በጎ ዓይኖች አረፉባት ። አንዲት ሴት ድንገት ቀርባ እሷንና ቄጤማ ሻጭዋን ሴት አዋየቻቸው ። እነሱ ውጭ ከሚያድሩ በእሷ ምግቤት አካባቢ ቢጠጉ እንደሚሻል ነገረቻቸው። ሴትዬዋ ለበትራቀች ስሜት አልከበደችም ። ያለችውን ሰምታ ፈጥና ተስማማች ።
የታሰበላቸው ተሳካ። ባለቄጠማዋ ከአንድ ቦታ በትራቀች ከዘበኛው ቤት አጠገብ እንዲያድሩ ተወሰነ። ሁለቱም ሀሳቡን በምስጋና ተቀብለው የጎዳናውን ጥግ ለቀቁ። ከተዘጋጀላቸው ስፍራ እያደሩም የዕጣን ቄጤማ ስራቸውን ቀጠሉ።
አንድቀን ግን ያልታሰበው ሆነ። በድካም የዋለችው በትራቀች ዕንቅልፍ እንደጣላት ያወቀው ዘበኛ ካለችበት ደርሶ ሊደፍራት ታገለ ። ዕንቅልፍ የለሸዋ ሴት በዋዛ እጇን አልሰጠችም ። እየጮኸች ራሷን ከጥቃት ለመከላከል ታገለች። ድምጽዋን የሰማችው ባልንጀራዋ ሮጣ ደረሰችላት ። የእሷን ፈጥኖ መምጣት ያየው ዘበኛ ሮጦ አመለጠ። እስከዛሬ ጎዳና ስትኖር ያልሆነባትን የመደፈር ሙከራ እያሰበች በትራቀች አለቀሰች፣ከልቧ አዘነች።
ይህ አጋጣሚ ግን ሌላ አጋጣሚን አስከተለ። ሁኔታውን የሰማች አንዲት የዕጣን ደንበኛዋ ከእሷ ማዕድ ቤት እንድትጠጋ ፈቀደችላት። ሴትዮዋ እንዳለችው ሆኖ ከቤቷ ወስዳ ከማድቤቱ አሳረፈቻት። እስካሻት ድረስ ብትኖር ፣ ውጭ እንደማትላትና ልጆቿም እንደማይጥሏት ቃል ገባችላት። በትራቀች። ሴትዬዋ እንደቃሏ ሆነች። በትራቀች የልቧ ሀሳብ ሞላ ፈጣሪዋን ደጋግማ አመሰገነች።
ጥቂት ቆይቶ ወይዘሮዋ ሌላ ሀሳብ አመጣች።በብቸኝነት ከምትኖር ልትድራት እንደምትሻ አሳወቀቻት። በትራቀች አልተግደረደረችም ። በሀሳቧ ተስማምታ በይሁንታ ጋብቻውን ተቀበለች ።
ህይወት በጎጆ
አሁን በትራቀች ባለትዳር ወይዘሮ ሆናለች ። ከባለቤቷ ጋር መኖር ከጀመረች ወዲህ ልጆች ወልዳ እያሳደገች ነው ። ትዳሯ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት መልካም የሚባል ነበር ። ጥቂት ቆይቶ ግን በባለቤቷ ላይ የሚታየው ባህሪይ አሳሳቢ ሆነ። እሷ ባታውቅም ባለቤቷ ቀደም ሲል የዓዕምሮ ታማሚ ነበር። ቆይቶ ህመሙ ሲያገረሽ እሷና ልጆቿ ካልታሰበ ፈተና ወደቁ።
ባለቤቷ አማኑኤል ሆስፒታል የህክምና ክትትል አለው። እሱን ከሚፈለገው አድርሶ ወደቤት ለመመለስ ጉልበትና ስልት ይጠይቃል። ይህን ለማድረግ አቅሙ የሌላት ወይዘሮ በታመመ ቁጥር እየታመመች አብራው በእንግልት ቀጥላለች። በትራቀች ቤተሰቧን ለማኖር የዕጣን ንግዷን ትሰራለች። በእሷ ትከሻ ብቻ የወደቀው የቤቱ ኑሮ የተሟላ አይደለም። አልጋ ፍራሽ፣ ብርድልብስና ሌላም ቁሳቁስ በወጉ የለም።
ለዕለት ፍላጎት ተብለው የተቀመጡ አንዳንድ ቁሳቁሶች በዓይምሮ ታማሚው አባወራ ይሰባበራሉ፣ ይወረወራሉ። ወይዘሮዋ እሱን ጨምሮ ልጆቿን ለመመገብ የሚቻላት አልሆነም። ከዕለት ገቢዋ ሰርታ ከምታመጣው በቀን አራት እንጀራ ብትገዛ ለባለቤቷ ሁሉንም ትሰጣለች። እንጀራው የግዢ ነውና ሆዱን አይሞላም። በየጊዜው ‹‹ምግብ አምጣ›› ለሚለው ፍላጎቱ አይበቃም።
ባለቤቷ ጤናማ ሳለ ሮጦ አዳሪ ነበር። ያገኘውን ተሸክሞ ለቤቱ ለመሆን ብርቱ ነው። የዛኔ ቤተሰቡ ለዕለት ጉርስ አያጣም። በእሷና በባለቤቷ የጎደለው ሞልቶ ፣ ልጆች በሰላም ተኝተው ያድራሉ። እሷም ልብስ አጥባ ጉልት ተቀምጣ ከምታገኘው ለቤቷ ስትሆን ኖራለች።
የነ በትራቀች ቤት በላያቸው ከወደቀ ቆይቷል። አሮጌውን አንስቶ በተሻለ ለመጠገን አቅም ይሉት የለም። ለምግብ እንጂ ለስራ ያልደረሱት ልጆች ውለው ሲገቡ የእናታቸውን እጅ ያያሉ። ሁሌም ይርባቸዋል፣ ይበርዳቸዋል። ታማሚው አባወራ የትኛውም ድምጽ ይረብሸዋል። የማሽን ፣ የሙዚቃ፣ የሰዎች ጫጫታ ባወከው ጊዜም ዕቃ እየወረወረ፣ አብዝቶ እየጮኸ ይወራጫል ።
የበትራቀች ልጆች አቅማቸው ደርሶ እናታቸውን የሚያግዙ አይደሉም። የአባታቸውን ጩኸት እንደግዴታ ተቀብለው አብረውት ይኖራሉ። በተሰበረው በርና መስኮት፣ በወደቀው ማገርና ግድግዳ የሚገባው ብርድና ንፋስ ለቤተሰቡ ችግር ሆኖ ዘልቋል ። ቤቱ የቀበሌ ነውና በትራቀች እንዲታደስላት ስትወተውት ኖራለች። አልተሳካም።
አንዳንዴ ቤተሰቡ ከአቅም በላይ የሚባል ችግርን ይጋፈጣል።ወይዘሮዋ ብዙ ችግሮችን አሳልፋለች፣ ችግሯን ለመፍታት ፣ መላ ዘዴውን ለማምጣት ብዙ ደክማለች። ከባለቤቷ ህመም ተያይዞ የሚገጥሟት ፈተናዎች ግን ከሁሉም ይብሳሉ።
በአንድ ወቅት ታማሚው አባወራ ለተለመደው ህክምና ወደሆሰፒታል አቀና ። ሀኪሞቹ ተገቢውን ምርመራ አድርገው መድሀኒት አዘዙለት። መድሀኒቱ ለሶስት ወራት የሚያገለግል ነበር። ታማሚው ግን የተሰጠውን የሶስት ወራት ክኒን በአንድጊዜ ወሰደው ። በወቅቱ ህይወቱን ባያጣም በጤናው ላይ ተጨማረ እክል ተፈጠረ።በቤቱ ሆኖ ህክምናውን እንዲወስድም ምክንያት ሆነ።
ይህ አጋጣሚ ወይዘሮዋን እንደልብ ወጥታ እንዳትሰራ ፣ያገኘችውን ለልጆቿ አቃምሳ እንዳታድር ሰበብ ሆኖ ዛሬን ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል።አሁን የበትራቀችን ባለቤት ሆስፒታል የሚያመላልሰው የለም። ለእሱ ጤና፣ ለራሷና ለልጆቿ ህይወት ማለዳ የምትሮጠው ወይዘሮዋ ብቻ ነች።
ዛሬ…
በትራቀች በላይዋ ሊወድቅ ያዘነበለ ቤቷ የዘወትር ስጋቷ ነው። የልጆቿ አለመድረስና የእሷ የብቻ ድካምም ያሳስባታል። ከሁሉም የባለቤቷ ጤና ማጣት የህይወቷ ጎዶሎ እንደሆነ ይሰማታል። የእሷ የአንድ እጅ ድካም ከወቅቱ የኑሮ ውድነት ተዳምሮ እያንገዳገዳት ነው።
አሁን በቅርቡ በልደታ አካባቢ በተከፈተው የምገባ ማዕከል ተጠቃሚ ሆናለች። ማዕከሉ የእሷን ችግር ከሌሎች በመለየት የሶስት እንጀራ ተጠቃሚ አድርጓታል። የያዘችውን ይዛ፣ ተጨማሪውን አክላ ለህመምተኛው ባለቤቷ ትደርሳለች ። በትራቀች ሁሌም አመስጋኝ ልብ አላት። ጎዶሎዋን ትታ ፣ የሆነባትን ረስታ በተደረገላት ትረካለች። ዛሬም ባልቀናው ኑሮ፣አሁንም ባልሞላው ህይወት ትባዝናለች ። ስለነገው ግን በልጆቿ ተስፋ አትቆርጥም።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 1 /2015