አቶ ተስፋሁነኝ ተሾመ በንግድ ሥራ ላይ ተሠማርተው መሥራት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። በሥራቸው ስኬታማ ቢሆኑም የተሻለ ገንዘብ ፍለጋ ሁልጊዜ ግራና ቀኝ መመልከት ብቻ ሳይሆን ድንጋይ እስከ መፈንቀል የደረሰ ሥራን ያከናውናሉ። ሀብት የማፍራት ፍላጎታቸው እየጨመረ ሲሄድ በሥራ ከመክበር ይልቅ ሕገወጥ መንገድን ምርጫቸው አደረጉ። በዚህም የተለያዩ ሽያጮችን በሕገ ወጥ መንገድ ማስጓዝን ተለማመዱ።
ሕገ ወጥነትን ምርጫቸው ያደረጉት እኚህ ነጋዴ ደረሰኝ ሳይቆርጡ በርካታ ሽያጮችን ሲያከናውኑ ከቆዩ በኋላ የቫት ተመላሽ ገንዘብ ለማግኘት በማሰብ ምንም አይነት ግብይት ሳይኖር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሐሰተኛ ደረሰኝ ቆርጠው ይይዛሉ። ይህንን ተግባር ከማከናወን አልፈው ከሌሎች ግለሰቦች ጋር በመገናኘት ከሕገ ወጥ ደረሰኝ ሻጮች ጋር ሥራውን በስፋት ማከናወን ይቀጥላሉ።
በደላሎቹ አማካኝነት ሕገወጥ ደረሰኝ የሚሸጥበት ቦታ የሄዱት አቶ ተስፋሁነኝ በሐሰተኛ መታወቂያ በአንድ ግለሰብ ስም ከወጣ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ላይ በሚሊዮኖች ግብይት ስለማከናወናቸው የሚገልፅ ደረሰኝን በሕገወጥ መንገድ ገዝተው ሲወጡ እጅ ከፍንጅ ተያዙ።
ሕገወጧ የሽያጭ ሠራተኛ
ወይዘሪት ገነት ኃይሉ የሽያጭ ሠራተኛ በመሆን የተለያዩ ተቋማት ላይ በሽያጭ ማሽን ሥትሰራ ቆይታለች። ይች በሥራዋ ታታሪ የሆነች ግለሰብ በተለያዩ አጋጣሚዎች የምታገኛቸው ባለሃብቶች በሕገወጥ ደረሰኝ የተለያዩ ግብይቶችን ሲያከናውኑ በዚህም ተዝቆ የማያልቅ ገንዘብ ሲያካብቱ ትመለከታለች።
ሕገወጥነት ይዞ የሚመጣውን ጦስ ብታስብም ከእለት ወደ እለት ግን ሰዎቹ በዚህ ሥራቸው ምንም ሳይደርስባቸው ሲቀር፤ ቀስ በቀሰ በሕገወጥ ሥራው ለመሠማራት ልቧ ይነሳሳል። በዚህም በሕገ ወጥ መንገድ የሽያጭ ማሽን እጇ እንዲገባ ታደርጋለች። በመቀጠል በሥራ አጋጣሚ ከተዋወቀቻቸው ነጋዴዎችና ደላሎች ጋር በመሆን በሕገ ወጥ ሥራው ውስጥ ጠልቃ ትሰምጣለች።
ቀናት ቀናትን እየጨመሩ ገቢዋም ከፍ እያለ ሲሄድ በሕግ እጠየቃለሁ የሚለው ስጋት ከውስጧ ሙልጭ ብሎ ጠፋ። በስጋቱና በይሉኝታ ቦታ ድፍረትንና ስግብግብነትን አንግሳ ሀሳቧን በሙሉ ገንዘብና ገንዘብ ላይ ብቻ አደረገችው። ሆኖም ግን ከዕለታት በአንዱ ቀን በልደታ ክፍለ ከተማ ባልቻ ሆስፒታል አካባቢ ከሚገኝ አሕመድ ሕንጻ ውስጥ በሐሰተኛ መታወቂያ ስም ከወጣ ሕጋዊ ማሽን ላይ ግብይት ሳይኖር 12 ሚሊዮን 135 ብር ሐሰተኛ ደረሰኝ በማዘጋጀት ቆርጣ ስትሰጥ እጅ ከፍንጅ ተያዘች።
ደላላው
አብዲ ጃቢር ፈጣን ወጣት ነው። ያንንም ያንንም መሞከር የሚያስደስተው አይነት ቅብጥብጥ ወጣት ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ በተገኘው ሥራ ላይ በመሠማራት ገንዘብ ከማግኘት የተሻለ ምንም ዓይነት ሕልም አልነበረውም። የሚመርጠው ሥራ ሁሉ አየር በአየር የሚባለው ዓይነት ምንም ሳይደክሙ ገንዘብ ማግኘት ዓይነት ነው። በተገኘው አጋጣሚ በሙሉ ገንዘብ የሚያገኝበትን ነገር ይሞክራል። ገንዘብ የሚያስገኝለት ከሆነ ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይልም።
የተለያዩ ሥራዎችን እየሞከረ ቢቆይም ያሰበውንና እሱ ስኬቴ የሚለው ደረጃ ሊደርስ ባለመቻሉ ሌሎች አማራጮችን መመልከት ጀመረ። ያኔ በአካባቢው የድለላ ሥራን የሚሠሩ ወጣቶች የተለያዩ የማሻሻጥ ሥራ ላይ ተሠማርተው ጠቀም ያለ ገንዘብ ሲያገኙ ይመለከታል። እሱም በዛው የሥራ ዘርፍ ተሰማርቶ ቤቱንም መኪናውንም ሲያሻሽጥ ይቆያል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን በአጋጣሚ የሕገወጥ ደረሰኝ የሚሸጡና መግዛት የሚፈልጉ ሰዎችን የማገናኘት ሥራ እንዳለ ይሰማል።
ይህም በቀላል በማመቻቸት መንገድ ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚገኝበትን የሥራ አማራጭ ዓይኑን ሳያሽ ገባበት። ባለሀብቶችንና ሐሰተኛ ደረሰኝ ሻጮችን በማገናኘት የሚያገኘው ገንዘብ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ አኗኗሩም እየተቀየረ ከእግረኝነት ወደ ባለመኪናነት ሲሸጋገር የሚሠራው ሥራ ሕገወጥ መሆኑን እስከመርሳት ደርሶ ነበር። በሀገርና በወገን ላይ ሸፍጥ የሚሠሩ፤ ከሀገር ላይ በመስረቅ ሀብትን ለማካበት የተመኙትን እያገናኘ እሱም ወደ ሀብት ማማ ተመነጠቀ።
ይህ ሁሉ በሕግ ሲደረስበት ሳያስበው የወጣበት ከፍታ መውረጃው እስኪቸግረው ግራ ተገባ። ሕግም የተመለከተውን ሕገወጥ ሥራ አይተውምና ግለሰቡ ለራሱ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ሐሰተኛ ደረሰኝ እንዲቆረጥ ለሽያጭ ያመቻቸ እና ሐሰተኛ ደረሰኞች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያደረገ በመሆኑ በፈፀመው የተጭበረበሩ ወይም ሕገወጥ የሆኑ ደረሰኞች ለሽያጭ ማመቻቸት ወንጀል ተጠያቂ ተደረገ።
የፖሊስ ምርመራ
በዚህ ሕገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩትን ግለሰቦች ለመያዝ ፖለስ ያደረገው እልህ አስጨራሽ ጥረት ዛሬ በድል ተጠናቋል። ነገሩ እንዲህ ነበር፤ አቶ ተስፋሁነኝ ተሾመ ሐምሌ 24 ቀን 2013 ዓ.ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ልዩ ቦታው ቄራ ዳውን ታወን አካባቢ ካለው ንግድ ቤት ውስጥ ዐቃቤ ሕግ ምስክር ግብይት ሳይኖር ደረሰኝ ብቻ እንደምትፈልግ ለደላላው የነገረችው እና በእርሱ አገናኝነት ደረሰኙ ከሚይዘው ገንዘብ የደላላ አንድ በመቶ እና የደረሰኝ ኮሚሽን ሦስት ከመቶ እንደምትከፍል ተስማምተው በደላላው አማካኝነት አቶ ተስፋሁነኝ ተሾመ ከሚገኝበት ንግድ ድርጅት ከገቡ በኋላ በሐሰተኛ መታወቂያ በአንድ ግለሰብ ስም ከወጣ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ላይ ግብይት ሳይኖር 17 ሚሊዮን 940 ሺ ብር ሐሰተኛ ደረሰኝ በማዘጋጀት ቆርጦ ሲሰጣት እጅ ከፍንጅ ልታስይዛቸው ቻለች።
ግለሰቦቹም በፈፀሙት ሐሰተኛ ወይም አሳሳች መግለጫ ማቅረብ ወንጀል የተከሰሱ ሲሆን እንዲሁም ሐሰተኛ ደረሰኞችን ለማዘጋጀትና ለማተም የሚያገለግሉ ማሽኖችን ይዞ በመገኘት በተደራራቢ ወንጀሎች እንዲጠየቁ መደረጉን ፖሊስ አስረድቷል።
በዛው ዕለት የዐቃቤ ሕግ ምስክሯ በተጨማሪ ሌላ ደረሰኝ ከሌላ ማሽን እንደምትፈልግ ለአቶ ተስፋሁነኝ ተሾመ ስትነግረው ተከሳሹ ስልክ በመደወል ደረሰኝ የሚፈልግ ሰው አለ መጣን በማለት በመዝገቡ ላይ 2ኛ ተከሳሽ የሆነችው ገነት ኃይሉ ከምትገኝበት በልደታ ክፍለ ከተማ ባልቻ ሆስፒታል አካባቢ ከሚገኝ አሕመድ ሕንጻ ውስጥ በሐሰተኛ መታወቂያ ስም ከወጣ ሕጋዊ ማሽን ላይ ግብይት ሳይኖር 12 ሚሊዮን 135 ብር ሐሰተኛ ደረሰኝ በማዘጋጀት ቆርጣ ስትሰጣት እጅ ከፍንጅ የተያዘች በመሆኑ በተጨማሪም ተከሳሿ ምንም አይነት የሽያጭ መመዝገቢያ ለመጠቀም የሚያስችል ሕጋዊ ፍቃድ እና ሰነድ ሳይኖራት በሐሰተኛ መታወቂያ ስም የወጣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ይዛ የተገኘች በመሆኑ በፈፀመችው ሐሰተኛ ደረሰኞችን ለማዘጋጀትና ለማተም የሚያገለግሉ ማሽኖችን ይዞ በመገኘት ወንጀል፣ ሐሰተኛ ወይም አሳሳች መግለጫ በማቅረብ፣ ግብይት ሳይፈጸም ደረሰኝ መስጠት እና የተጭበረበሩ ደረሰኞችን ማዘጋጀት፣ መሸጥና ማሰራጨት ወንጀል በተደራራቢ ክሶች ተጠይቃለች።
በሌላ በኩል አብዲ ጃቢር ከላይ በተገለጸው ሁኔታ ለራሱ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ሐሰተኛ ደረሰኝ እንዲቆረጥ ለሽያጭ ያመቻቸ እና ሐሰተኛ ደረሰኞች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያደረገ በመሆኑ በፈፀመው የተጭበረበሩ ወይም ሕገወጥ ደረሰኞች ለሽያጭ ማመቻቸት ወንጀል በቀረበበት ተደራራቢ ክሶች እንዲጠየቅ መደረጉን ፖሊስ አመልክቷል።
ፖሊስ ማስረጃውን በማጠናቀር በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ከፖሊስ ጋር በመሆን ግብይት ሳይኖር ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ ሐሰተኛ ደረሰኝ በማዘጋጀትና በመሸጥ ለግል ጥቅማቸው ባዋሉ ሦስት ግለሰቦች ላይ ምርመራ በማጣራ፤ ዐቃቤ ሕግ ክስ መሥርቷል።
የፍርድ ቤት ክርክር
ክርክሩ በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 11ኛ ወንጀል ችሎት የተደረገ ሲሆን፤ የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው 1ኛ ተከሳሽ ተስፋሁነኝ ተሾመ፣ 2ኛ ተከሳሽ ገነት ኃይሉ፣ 3ኛ ተከሳሽ አብዲ ጃቢር፣ የተባሉት ላይ ዐቃቤ ሕግ 10 የተለያዩ ክሶች አቅርቦ በመከራከር ረትቷል።
ተከሳሽ ተስፋሁነኝ ተሾመ ሐምሌ 24 ቀን 2013 ዓ.ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ልዩ ቦታው ቄራ ዳውን ታወን አካባቢ ካለው ንግድ ቤት ውስጥ ለ1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ግብይት ሳይኖር ደረሰኝ ብቻ እንደምትፈልግ ለ3ኛ ተከሳሽ የነገረችው እና በእርሱ አገናኝነት ደረሰኙ ከሚይዘው ገንዘብ የደላላ አንድ በመቶ እና የደረሰኝ ኮሚሽን ሦስት ከመቶ እንደምትከፍል ተስማምተው በደላላው አማካኝነት 1ኛ ተከሳሽ ከሚገኝበት ንግድ ድርጅት ከገቡ በኋላ በሐሰተኛ መታወቂያ በአንድ ግለሰብ ስም ከወጣ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ላይ ግብይት ሳይኖር 17 ሚሊዮን 940 ሺ ብር ሐሰተኛ ደረሰኝ በማዘጋጀት ቆርጦ ሲሰጣት እጅ ከፍንጅ የተያዘ በመሆኑ በፈፀመው ሐሰተኛ ወይም አሳሳች መግለጫ ማቅረብ ወንጀል የተከሰሰ ሲሆን እንዲሁም ሐሰተኛ ደረሰኞችን ለማዘጋጀትና ለማተም የሚያገለግሉ ማሽኖችን ይዞ በመገኘት ወንጀል በሦስት ተደራራቢ ክሶች ክርክር ሲያደርግ ቆይቷል።
በዛው ዕለት የዐቃቤ ሕግ ምስክሯ በተጨማሪ ሌላ ደረሰኝ ከሌላ ማሽን እንደምትፈልግ ለ1ኛ ተከሳሽ ስትነግረው ተከሳሹ ስልክ በመደወል ደረሰኝ የሚፈልግ ሰው አለ መጣን በማለት በመዝገቡ ላይ 2ኛ ተከሳሽ የሆነችው ገነት ኃይሉ ከምትገኝበት በልደታ ክፍለ ከተማ ባልቻ ሆስፒታል አካባቢ ከሚገኝ አሕመድ ሕንጻ ውስጥ በሐሰተኛ መታወቂያ ስም ከወጣ ሕጋዊ ማሽን ላይ ግብይት ሳይኖር 12 ሚሊዮን 135 ብር ሐሰተኛ ደረሰኝ በማዘጋጀት ቆርጣ ስትሰጣት እጅ ከፍንጅ የተያዘች በመሆኑ በተጨማሪም ተከሳሿ ምንም አይነት የሽያጭ መመዝገቢያ ለመጠቀም የሚያስችል ሕጋዊ ፍቃድ እና ሰነድ ሳይኖራት በሐሰተኛ መታወቂያ ስም የወጣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ፣ ይዛ የተገኘች በመሆኑ በፈፀመችው ሐሰተኛ ደረሰኞችን ለማዘጋጀትና ለማተም የሚያገለግሉ ማሽኖችን ይዞ በመገኘት ወንጀል፣ ሐሰተኛ ወይም አሳሳች መግለጫ ማቅረብ፣ ግብይት ሳይፈጸም ደረሰኝ መስጠት እና የተጭበረበሩ ደረሰኞችን ማዘጋጀት፣ መሸጥና ማሰራጨት ወንጀል በአራት ተደራራቢ ክሶች ክርክር ስታደርግ ቆይታለች።
በሌላ በኩል 3ኛ ተከሳሽ የሆነው አብዲ ጃቢር ከላይ በተገለጸው ሁኔታ ለራሱ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ሐሰተኛ ደረሰኝ እንዲቆረጥ ለሽያጭ ያመቻቸ እና ሐሰተኛ ደረሰኞች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያደረገ በመሆኑ በፈፀመው የተጭበረበሩ ወይም ሕገወጥ ደረሰኞች ለሽያጭ ማመቻቸት ወንጀል በቀረበበት ተደራራቢ ክሶች ክርክር ሲያደርግ ቆይቷል።
ውሳኔ
ዐቃቤ ሕግም ሦስቱ ተከሳሾች የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኝት በማሰብ ሕግን በመተላለፍ ፈጽመውታል ባላቸው 10 የተለያዩ ክሶች ማስረጃ በማቅረብ ክሱን በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑ የዐቃቤ ሕግን እና የተከሳሾችን ክርክር የመራው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 11ኛ ወንጀል ችሎትም 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በተከሰሱባቸው ክሶች በሙሉ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ በማሳለፍ በአጠቃላይ በ1ኛ ተከሳሽ በ 14 ዓመት ጽኑ እስራት ፣ 2ኛ ተከሳሽ በ12 ዓመት ጽኑ እስራት ፣ እንዲሁም በ3ኛ ተከሳሽ እና የማገናኘት ሥራ የሠራው ተከሳሽም በተከሰሰባቸው 4 ክሶች መካከል በአንድ ክስ ብቻ የጥፋተኝነት ውሳኔ በማሳለፍ በ3 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲወስን ከእስራት ቅጣቱ በተጨማሪ 1ኛ ተከሳሽ የ360 ሺ ብር፣ 2ኛ ተከሳሽ የ210 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ሲል ወስኗል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 1 /2015