የተወለዱትና ያደጉት በምዕራብ ወለጋ ነጆ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ነጆ ከተማ በሚገኘው የስዊዲን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ግን ከአካባቢያቸው 76 ኪሎ ሜትር ርቀት በእግርና በበቅሎ እየተጓዙ ነው ጊምቢ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሩት፡፡ በጎንደር ጤና ኮሌጅ በኮሚዩኒቲ ነርስኒግ ዲፕሎማቸውን አግኝተዋል፡፡ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም በቀጥታ ሚዛን ተፈሪ በሚገኘው ጤና ጣቢያ ተመድበው ለጥቂት ጊዜያት አገልግለዋል። ሆኖም በሴትነታቸው የደረሰባቸውን ትንኮሳ በመሸሽ የአገልግሎት ግዳጃቸውን ሳይጨርሱ ቦጂ በሚገኘው የመካነ-ኢየሱስ ክሊኒክ ማገልገላቸውን ቀጠሉ፡፡ እዛው ሳሉ የሕጻናት ሕክምና ስልጠና በስዊድን ልማት ድርጅት አማካኝነት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወሰዱ፡፡
በመከላከያ ኢንዱስትሪም ተቀጥረው ለሰባት ዓመታት ያገለገሉት እኚሁ ሴት በዚህ ተቋም ውስጥ በነበሩ ባለስልጣናትና ካድሬዎች ተመሳሳይ ጾታዊ ትንኮሳ ችግር ስላጋጥማቸው ሥራውን ለመልቀቅ ተገደዱ፡፡ በመቀጠልም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው ሠሩ፡፡ ፈተናው ግን በሥራ ቦታ ብቻ አላበቃም፤ ከትዳር አጋራቸውም ጋር አለመግባባት ተፈጠረ፤ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳታቸውም እየጨመረ መጣ፡፡ በዚህ ግን ተስፋ አልቆረጡም፤ ሁሉንም ችግር በትዕግስትና በፅናት በመጋፈጥ በሥራም ሆነ በእውቀት ራሳቸውን በማጎልበት አጠነከሩ፡፡ ከራሳቸው አልፈውም ኢንተር አፍሪካ ኮሚቴ ኦን ትራዲሽናል ፕራክቲስ ተቀጥረው እየሠሩ ጎን ለጎን የራሳቸውንና ችግረኛ ሴቶችን የሚረዳ የበጎአድራጎት ድርጅት አቋቋሙ፡፡ በዚህም ድርጅት አማካኝነት ለበርካቶች የሥራ እድል መፍጠር የቻሉ ሲሆን በጭቆና ላይ ለነበሩ ሴቶች መልካም ምሳሌ በመሆንም ይታወቃሉ፡፡ ይሁንና ይህ የድጋፍ ሥራዎች አሁንም በወቅቱ በነበሩ የቀበሌ ካድሬዎች ከፍተኛ ችግር ይደርስባቸው ጀመር ፡፡
የድርጅቱን ሕንፃ ግንባታ ከማገድ ጀምሮ በነፃ የሚሠሩበትን የቀበሌ ቦታ ኪራይ ከማስከፈልና በእርዳታ ያገኟቸውን ማሽኖች እስከመውሰድ በመድረስ የሚረዷቸው ሴት ተበተኑ፡፡ የፅናት ተምሳሌት የሆኑት እኚሁ ብርቱ ሴት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲቋቋም ፕሮፖዛል በማዘጋጀት ጭምር ለመንግሥት ሃሳብ በማቅረብ አስተዋፅዖ ማድረጋቸው ይጠቀሳል፡፡
ነፃ የትምህርት እድል አግኝተው አሜሪካ ከከተሙ አሁን 27 ዓመታት አልፏቸዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት አምስት ልጆችን እያሳደጉ ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ መሥራት ችለዋል። በተጨማሪም እንደእርሳቸው በትዳር አጋራቸውና በሌላ አካል ተፅዕኖ የሚደርስባቸው ስደተኛ ሴቶችን ለመርዳት አልቦዘኑም፡፡ በስደት ሃገር የራሳቸውን የበጎአድራጎት ድርጅት ከፍተው ስደተኞችን ይረዳሉ፤ ያስተምራሉ፤ በኢኮኖሚ ያቋቁማሉ፡፡ ከዚህም አልፈው ለስደተኞች እንቅፋት የሆኑ የአሜሪካ ሕጎች እንዲሻሻሉ ብርቱ ተጋድሎ በማድረግ ስኬታማ ሆነዋል፡፡
ሃገራቸውን ከልብ የሚወዱት እንግዳችን በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ወገኖቻቸውን ይደግፋሉ። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የከተማ ግብርና ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ለማድረግና ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ ይህንን የሕይወት ውጣ ውረዳቸውን የሚያሳዩ ሁለት መጽሐፍትን ለንባብ ያበቁ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በኦሮምኛ እና በአማርኛ ቋንቋ በማስተርጎም ላይ ነው የሚገኙት፡፡ በዚህና በሌሎች ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሆልስቲክ ፍሪደም ኢንተርናሽናል መሥራችና ፕሬዚዳንት ከሆኑት ዶክተር አጊቱ ወዳጆ ጋር ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሴትነትዎ ያጋጥምዎት የነበረው ችግር አሁን ለደረሱበት ስኬት ምክንያት እንደነበር በጻፉት መጽሐፍ ላይ አንስተዋል። እስቲ ያሳለፉትን ፈተና እና ያለፉበትን መንገድ ያስታውሱን ?
ዶክተር አጊቱ ፡– በመሠረቱ በዚያ ጊዜ በነበሩት ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ ነበረኝ። ሆኖም በወቅቱ የነበሩት አለቃዬና ካድሬዎች በሴትነቴ እጅግ ያስቸግሩኝ ነበር። በሌላ በኩል አሁን ልገልፀው የማልችለው ነገር ግን በመጽሐፌ ላይ ያሰፈርኩት በትዳሬ ከፍተኛ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። የነበረብኝ ከፍተኛ ተፅዕኖ ቢሆንም እንደአንድ ክርስቲያን ሴት መታገስ እንዳለብኝ በማመኔና ልጆቼ በንፁሕ አዕምሮ እንዲያድጉ በማለት ችግሩን በፀጋ ተቀበልኩት። እነዚያ ፈተናዎች ግን እኔን ቀረፁኝ እንጂ ወደኋላ አላስቀሩኝም። በዚህ ምክንያት እሠራበት ከነበረው የመከላከያ ኢንዱስትሪ ለቅቄ ባሌ ለአንድ ዓመት ሠራሁኝ፤ በመቀጠልም እርሻ መሣሪያዎችና ቴክኒካል አገልግሎት ለአንድ ዓመት ሠራሁ። ኢንተርናሽናል ኮርዲኔቲንግ ኮሚቴ ፎር ዌልተር ኤንድ ዴቨሎፕመንት ፕሮግራምስ በሚባልና ማዘጋጃ ቤት ውስጥ የነበረ ድርጅት ለጥቂት ጊዜ ሠርቻለሁ።
ይሁንና በከፍተኛ ባለስልጣናት የነበረውን ሙስና በመቃወሜ ከሥራ አባረሩኝ። ግን ዝም አላልኩም፤ ከስሼ የአንድ ዓመት ደመወዜን እንዲሰጡኝ አድርጌያለሁ። በአፍሪካ ኢኮኖሚክስ ኮሚሽን ውስጥ ጎጂ ባሕላዊ ልማዶች አስተባባሪ ሆኜ ተቀጠርኩኝ። ይህም ብሔራዊ ኮሚቴውን ነበር የሚመራው። የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ በየክፍለሃገሩ እየዞርን የሃይማኖት መሪዎች፣ የሴቶችና የወጣቶች ተወካዮች፤ የጤና ባለሙያዎች በተገኙበት ወርክሾፕ እናካሂድ ነበር። በዚህም ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ችለናል።
እንዳልኩሽ የነበርኩበት ወጀብ ቀረጸኝና ለድሃ ሴቶች ሕይወታቸውን የሚለውጥ ሥራ እንድሠራ መንገድ ከፈተልኝ። በዚያ መነሻ የሴቶች ራስን መቻል ማኅበር የርዳታ ድርጅት አቋቋምኩኝ።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ድርጅት ምንድን ነበር የሚሠራው?
ዶክተር አጊቱ፡- ይህ የእርዳታ ድርጅት በቆዳ ውጤት፣ ልብስ ስፌት እና በምግብ ፕሮሰሲንግ ሥራ በስፋት ይሠራ የነበረ ነው። ለዚህም ይረዳ ዘንድ የስዊድን የበጎአድራጎት ድርጅት፤ ክርስቲያን ሪሊፍ ዲፕሎፕመንት አሶሴሽን፣ ካናዳ ኤምባሲ ፋኒ ሴፍ ኔዘርላድስና የአሜሪካ ኤምባሲ ድጋፍ አድርገውልናል። በተጨማሪም ሴቶቹ ምንም ገቢ ስለሌላቸው በክርስቲያን ሪሊፍ ዲቨሎፕመንት አማካኝነት ዱቄት፣ዘይት፣ብርድልብስ፣ጫማና ሳሙና እንሰጣቸው ነበር። የሰው እጅ እንዳያዩና ሠርተው ራሳቸውን እንዲለውጡ ከፍተኛ ጥረት አደርጋለሁ። ከዚሁ ጎን ለጎን በራሳቸው እንዲተማመኑና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ሥልጠናዎችም ይሰጣቸው ነበር።
እነዚህ ሴቶች በነገራችን ላይ በወሎ ድርቅ ጊዜ ተፈናቅለው ቀበሌው በሠራላቸው ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የሰፈሩ ነበሩ። እኔ ስደርስላቸው እዚያ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ለ15 ዓመት በከባድ ችግር ውስጥ የኖሩ ናቸው። በወቅቱ ሴቶቹ ራሳቸውን ችለው ቤተሰቦቻቸውን እንዲረዱ የሚያደርግ ከፍተኛ ሥራ በመሥራታችን ደስተኛ ነኝ። ራስን ከመቻል ባለፈ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ በምርታማነት ማሻሻያና በአነስተኛ ጥቃቅን ባለሙያዎች ስልጠና እንዲሰለጥኑ አድርጌያለሁ። በመሠረቱ ምርታቸውም ከፋብሪካ ምርቶች ጋር የሚወዳደር ነበር። ሲመረቁ የተለያዩ ዓለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅቶችን ጋበዝኳቸው፤ እንግዶቹ ባዩት ነገር በጣም ተደሰቱ። ከዚያ ድርጅቴ በከፍተኛ ደረጃ ድጋፍ ያገኝ ጀመር። በየትልልቅ መድረኩ እየተጋበዝኩኝ ድርጅቱና የሴቶችን ሥራ እንዲሁም የወደፊት እቅዳችንን አቀረብኩኝ። ሕንጻ ለመገንባት የሚያስችለንንም ድጋፍ አግኝተን ነበር። ኒጀር ሄጄ ልምድ ከቀሰምኩኝ በኋላ የመንግሥት ለውጥ መጣ።
በኋላ ሁኔታዎች መቀየር ጀመሩ፤ ቀበሌ ውስጥ የነበረውን ድርጅት 350 ብር እንድንከፍል ተደረገ። ግን በወቅቱ የቀበሌ ቤት ከ150 ብር በላይ አይከራይም ነበር። ልክ ተሳክቶልን ሥራችን መጠናከር ሲጀምር የቀበሌው ካድሬዎች አላሠራ አሉን። የቀበሌው ሊቀመንበር ጠርቶኝ ሴቶቹ በምርጫ እነሱ የሚፈልጓቸውን ሰዎች ብቻ እንዲመርጡ ማስገደድ እንዳለብኝ ነገረኝ። እኔ በሁኔታው ስላላመንኩኝ እዚህ ነገር ላይ አልገባም በማለቴ ጠምደው ያዙኝ። ከዚያ ማሳደድ ጀመሩ፤ በኤክስፖ 93 ላይ ምርታችንን ለማቅረብ ነፃ በተሰጠን እድል እንዳንሳተፍ በወታደር ተከለከልን። ደግሞ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተሰጠንን ማሽኖችና መሣሪያዎች ቀሙን።
እያሳደዱኝ ቢሆንም ለሴቶቹ አዲስ ባንክ አካውንት ከፍቼ በኅብረት ሥራ ማኅበር አቋቁሜያቸው ራሳቸውን በራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ፤ ምርታ ቸውን እንዲሸጡ አስተምረን ነው እኔ ወደ አሜሪካ የሄድኩት። ከሄድኩኝ በኋላ ኪራይ አልከፈላችሁም ብለው አባረሯቸው። የነበሩት ወፍጮዎች፤ የስፌት መኪናዎቹንም ወሰዱባ ቸው። በዚህ ምክንያት ሴቶቹም ተበታተኑ።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲቋ ቋም ለመንግሥት ፕሮፖዛል አዘጋጅተው ሰጥተው እንደነበር ሰምቻለሁ። እስቲ ስለዚህ ሁኔታ ያብራሩልን?
ዶክተር አጊቱ፡- በነገራችን ላይ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተቀጥሬ በምሠራበት ጊዜ በርካታ ሃገራትን በመጎብኘት ተሞክሮ ቀስሜያለሁ። ከዚህም መካከል ኒጀር የቀሰምኩት ልምድ ላይ ተሞርኩዤ የሴቶች ጉዳይ ማቋቋም የሚያስችል ፕሮፖዛል ለመጀመሪያ ጊዜ አዘጋጀሁና በወቅቱ ለነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ አቀረብኩኝ። ለካስ እነሱ ‹‹አይሴማን ምን እናድርግ›› ብለው ተጨንቀው ስለነበር ፕሮፖዛሉ ለጭንቀታቸው መፍትሔ ነው የሆነላቸው። ደግሞም ከነመዋቅሩ የሠራሁላቸው በመሆኑ በጣም ተደሰቱ። ሥራም የቀለላቸው በመሆኑ በሦስት ወሩ በሰጠኋቸው ፕሮፖዛል አማካኝነት ሚኒስቴሩ ተቋቋመና ወይዘሮ ታደለች ኃይለሚካኤል እንድትመራው ተደረገ። በተጨማሪም ከ15 ሰዎች ጋር በመሆን ሴቶችን በሚመለከት የወጡ የቀድሞ ሕጎች ላይ ጥናት አደረግን። ለምሳሌ ሴቶች እንዳይወርሱ የሚደነግገውን ሕግ እንዲቀየር ከፍተኛ አስተዋጽዖ ነበረኝ። የሚገርመው በድሮ ሕግ እኔ የሆነ ሰው ቢደበድበኝና ጥርሴ ቢሰበር ካሳ ለባሌ እንጂ ለእኔ አይሰጥም ነበር። እናም እነዚህን የመሳሰሉ ሴቷን ማዕከል ያደረጉ ሕጎች እንዲሻሻሉ ነው የተደረገው።
አዲስ ዘመን፡- ወደ አሜሪካ የሄዱበት አጋጣሚ ምን ነበር?
ዶክተር አጊቱ፡- ነጻ የትምህርት እድል አግኝቼ ነው ወደ አሜሪካ ከእነልጆቼ ሄድኩት። በነገራችን ላይ ሀገሬን በጣም ነው የምወደው። ከዚህ ቀደም በተለያዩ የርዳታ ድርጅት ውስጥ በምሠራበት ጊዜ በርካታ የዓለም ሃገራት የመሄድ እድሉ ገጥሞኛል። ግን እዛ ለመቅረት አስቤ አላውቅም። በኑሮዬም ፈጣሪ ባርኮኝ ስለነበር የማማርርበት ምክንያት አልነበረም፤ መሰደድ አልፈልግም ነበር። የሚገርምሽ አሜሪካ ከሄድኩኝ በኋላ በየዓመቱ ነው ወደ ሃገሬ እመላለስ የነበረው፤ በዚህ ምክንያት ብዙ ጓደኞቼ ‹‹የኢትዮጵያን ባንዲራ ውጠሽ ነው እንዲህ የሚያመላልስሽ›› እያሉ ይተርቡኝ ነበር። ሆኖም መሄዴ ራሱ የፈጣሪ ፈቃድ ስለነበር ከነአምስት ልጆቼ ነው ያለምንም ማንገራገር የተቀበሉኝ። እዛም እንደሄድኩም የማውቃትና የረዳኋት አሜሪካዊት እዛ አገኛኋትና እሷም በተራዋ ሙሉ ቤቷን ለቃ ከነልጆቼ ተቀበለችኝ፤ ልጆቼንም ትምህርት ቤት አስገባችልኝ። በነገራችን ላይ ሜትሮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተመዝግቤ እየተማርኩኝ እዚህ እየተመላለስኩኝ የበጎአድራት ድርጅቴን እከታተል ነበር።
አዲስ ዘመን፡- አሜሪካ ሄደውም የበጎ አድራጎት ድርጅት ከፍተዋል። ለመሆኑ በሰው ሃገር እንዲህ አይነት ድርጅት ማቋቋም ለምን አስፈለገዎት?
ዶክተር አጊቱ፡- አሜሪካ ያቋቁምኩት የበጎ አድራጎት ድርጅት በዋናነት በስደተኞች ላይ የሚያጠነጥንና ለመብታቸው የሚታገል ነው። ስደተኞችን ወክለን አለአግባብ የወጡ ሕጎች እንዲስተካከሉ ከፍተኛ ጥረት አድርጌያለሁ። ለምሳሌ ብጠቅስልሽ ገና በረቂቅ ላይ የነበረና ስደተኞችን የሚጎዳ ሕግ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ሳይፈርሙ በፊት እኔ ለሂላሪ ክሊንተን በቀጥታ ደብዳቤ ፃፍኩኝ። ያ ሕግ ቤጂንግ ዓለምአቀፍ ኮንፍራንስ ላይ ከፈረሙት ጋር የሚጻረር መሆኑን ጠቅሼ ነው የፃፍኩት። ሕጎችና ደንቦች ተግባራዊ ከመሆናቸው በፊት በሕዝቦች ላይ የሚያመጡት ተፅዕኖ መጀመሪያ እንዲጠና ያዛል። ሆኖም ይህ ባለመሆኑ ሕጉ ተግባራዊ ከሆነ ባልና ሚስትን፤ ልጆችን ከወላጅ የሚለያይበትን ሁኔታ እንደሚፈጥር በደብዳቤዬ ለማስረዳት ሞክሬያለሁ። የሚገርመው በዚያ ወቅት እኔ ገና ተማሪ ነበርኩኝ፤ ሊያውም ስደተኛ። ግን ሂላሪ ደብዳቤዬን ሳትንቅ በቀጥታ ለፕሬዚዳንቱ አስተላለፈች። በአጭር ጊዜ ፕሬዚዳንቱ ራሳቸው ምላሻቸውን ያለሁበት ድረስ በደብዳቤ አሳወቁኝ።
ከዚህም ባሻገር ሜኒሶታ ላይ ብቻ አራት ሕጎችን እንዲቀየር አድርጌያለሁ። በእርግጥ ብቻዬን አይደለሁም፤ ሌሎችንም ሰዎች በማስተባበር ጭምር ነው። ለምሳሌ አንዱ ሕግ በእኔ ላይ ከደረሰው ችግር አንጻር ተነስቼ ነው እንዲስተካከል ያደረኩት። ይኸውም እኔ እዚህ የተማርኳቸው ኮርሶችን እዛ ተቀባይነት አያገኝም ነበር። በዚህ ምክንያት ብዙ በስደት ያሉና ከአሜሪካ ውጭ የሰለጠኑ ነርሶች የሥራ ፍቃድ ማግኘት አይችሉም ነበር። በዚህም ከነርስ ረዳትነት ያለፈ ተምረው ከፍተኛ ደረጃ እንዳይደርሱ እንቅፋት ሆኖባቸው ነበር። እናም እኔን ያጋጠመኝ ችግር የነርሶችን ችግር እንዳውቅ ስላደረገኝ በዚህ ላይ ከሚሠራ ቡድን ጋር በመሆን የቀድሞውን ሕግ የሚያሻሽል ረቂቅ ሕግ አዘጋጀን። ረቂቁን ለምክር ቤቱ ከማቅረባችን በፊት ግን ድጋፍ ለማግኘት አስበን የነርሶች ቦርድ አመራር የሆኑትን ሴት በብዛት የሰለጠነ ኃይል እዛው እያለ ፊሊፒንስ ድረስ እየሄዳችሁ ለምን ነርሶች ትቀጥራላችሁ ብለን አነጋገርናቸው። በተለይ እኔ ይህንን ሕግ ቢያሻሽሉ በአንድ በኩል የባለሙያ እጥረታቸውን እንደሚቀርፉ፤ በሌላ በኩል ባሕላዊ የውድድር መንፈስ ትፈጥራላችሁ ብዬ ተሟገትኳቸው። በዚያ መሠረት የእኛም ጥያቄ አብሮ ለምክር ቤት እንዲቀርብ ተደረገ። እናም ሕጉ በምክር ቤቱ ተቀባይነት አግኝቶ 44 የሚሆኑ የአሜሪካ ግዛቶች ይህንን ሕግ ተግባራዊ አድርገውታል።
በቀጣይ ደግሞ የፀጉር ሹሩባ እየሠሩ በሚተዳደሩ ስደተኞች ላይ የነበረውና አላሠራ ያለ ሕግ እንዲሻሻል ነው የሠራነው። በአሜሪካ ሁሉም የፀጉር ባለሙያዎች ‹‹ኮስሞቶሎጂ›› የተባለ ፍቃድ ማግኘት አለባቸው። እኔ ደግሞ ለስደተኞች ሴቶች አንድ የሙያ ማዕከል ከፍቼላቸው ስለነበር ሹሩባ ይሠሩ ነበር። ይሁንና ፈቃዱ ስለሌላቸውና ሕገወጥ ነው ስለሚባል ተረጋግተው አይሠሩም ነበር። ሕጉ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ሹሩባ የሚሠሩትን አይመለከትም ነበር። ስለዚህ ይህም ሕግና የተቀመጡ መስፈርት ተገቢ አለመሆኑን በማስረዳት ሕጉ እንዲሻሻል በራሴ ተነሳሽነት ጥያቄ አቅርቤ በብዙ ሂደት ተቀባይነት አግኝቷል። በነገራችን ላይ አሜሪካ በሠራኋቸው ሥራዎች ምክንያት ‹‹ቡሽ ሊደርሽፕ›› በተባለ ተቋም ነጻ የትምህርት እድል አግኝቼ ኤግዚኪዩቲቭ ፓፕሊክ አፌርስ ዘርፍ ማስተርሴን መሥራት ችያለሁ። በተመሳሳይ የዶክትሬት ዲግሪዬን ደግሞ በክርስቲያን ሊደርሺፕ የሠራሁትም ነፃ የትምህርት ከነሙሉ ወጭዬ አግኝቼ ነው።
እኔም ብሆን የማገኘው የገንዘብ ድጋፍና ከመጽሐፍቶቼ የሚገኘውን ገቢ ለችግረኛና ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ድጋፍ የሚውል ይሆናል። በቀጣይ ስደተኛ ሴቶች በባሎቻቸውና በሌላ አካል ጥቃት ሲደርስባቸው የአደጋ ጥሪ በማድረግ ወዲያውኑ የሕግ አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በመተባበር ለማቋቋም ነው እቅድ ያለኝ። ለዚህም እንዲረዳ ሌላ‹‹ ሆልስቲክ ፍሪደም ኢንተርናሽናል›› የተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት እዛው አሜሪካ አቋቁሜያለሁ። ከመጽሐፌም ከሚገኘው ገንዘብ በየግዛቱ ነው የምናቋቁመው።
በመሠረቱ እዚህ ከፍቼው የነበረው ድርጅት ቢዘጋም አቅመ ደካሞችን መርዳት አላቆምኩም። በየጊዜው እየተመላለስኩኝ የበኩሌን ድጋፍ አደርግላቸዋለሁ። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በከተማ ግብርና እና የጓሮ አትክልት ዓሳ እርባታ ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ዝግጅት እያደረኩኝ ነው የምገኘው። ከዚህ ቀደምም አርጆ ጉደቱ መሬት ተመርተን ግን ተዘርፌ መጉላላት ደርሶብኛል። በአዲሱ ፕሮጀክቴ ገበሬውንም ሆነ ከተሜውን ገቢ በሚያስገኝ ሙያ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ነው እቅዴ። አሁን ላይ ደግሞ ገላን አካባቢ መሬት ተመርቻለሁ። እንዳልኩሽ ግን ከኢንቨስትመንቱም፤ ከእርዳታ ድርጅትም ሆነ ከመጽሐፍ ሽያጭ የሚገኘው የሃገሬን ሕዝብ ለመርዳት ነው የማውለው።
አዲስ ዘመን፡- በሴትነትዎ በቤትም ሆነ በውጭ ያጋጠሞትን ተግዳሮት በጽናት በማለፍ ለስኬት ደርሰዋል። ሌሎች ሴቶች ከእርስዎ የሕይወት ተሞክሮ ምን ሊማሩ ይገባል?
ዶክተር አጊቱ፡– እኔን እዚህ ያደረሰኝ አንደኛ አማኝ ከሆነ ቤተሰብ ውስጥ ማደጌ ነው። እንደአንድ አማኝ ደግሞ እምነት፣ ተስፋ፣ ሁልጊዜ መልካም ማሰብ እና የመጣብኝን ፈተና ለበጎ ነው ብዬ መቀበል ነው ብዬ አምናለሁ። ሌሎች እህቶቼም ከዚህ ፈተና ውስጥ ምንድን ነው የምማረው? ብለው ማሰብ ይገባቸዋል። አስቀድሜ እንዳልኩሽ እኔ በደረሰብኝ መከራ ምክንያት ነው ለሴቶቹ ድርጅት እስከማቋቋም የደረስኩት። በተለይ ሌሎች እንደእኔ በፈተና ውስጥ ያሉና እያለፉ ያሉ ሴቶችን መምከር የምፈልገው መከራውን እያሰቡ ማማረር ሳይሆን፤ ከዚያ መከራ ወይም ችግር ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ማየትና መፈለግ እንዳለባቸው ነው። ምክንያቱም በሚመጣብሽ መከራ አልቅሰሽ የምታተርፊው ምንም ነገር የለም። ታግለሽ ግን ብዙ ታተርፊያለሽ። ቀና ቀናውን በማሰብ መልካም ነገር ማምጣት ትቺያለሽ። በአጠቃላይ በእኔ በኩል አንደኛ የመጣብንን ነገር ማጉረምረሚያ ማድረግ ሳይሆን ማድረግ የሚገባን ከእሱ ውስጥ ምንድን ነው የማገኘው ብሎ መፈለግ ነው። በመሠረቱ በመጣብን መከራ ያለንን ነገር ጭምር ሊያሳጣን ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- የሕዝቡ ታቻችሎ የመኖር እሴት አሁን አሁን እየተሸረሸረ መጥቷል፤ በእርስዎ እምነት ይህንን እሴት እንዴት መመለስ ይቻላል?
ዶክተር አጊቱ፡- በእኔ እምነት ይህ ችግር ብዙ ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው። ነገሥታት በሕዝብ መካከል ልዩነት በመፍጠር ጥቂቱን ማኅበረሰብ ብቻ ተጠቃሚ በማድረግ ሌላውን በገዛ ሃገሩ ባይተዋር እንዲሆን እድሉን በመፍጠራቸው ነው። ይሄ አሁን ላይ ተባብሶ በመሄዱ ቀድሞ የጋራ የምንላቸውና የምንግባባቸውን ማንነቶች እያሳጡን ነው የሚገኙት። በአንድ ብሔር ስም ጥቂቶች የሃገሪቱን ስልጣንና ሃብት በመቆጣጠር ሌላውንም የሚጨቁን ሥርዓት በመዘርጋቱ አሁን ላይ ያለው ትውልድ በልዩነት ብቻ እንዲያምን አድርጓል። ለዚህም እኮ ነው በየአካባቢው አንጃ ኃይሎችና ለነፃነት እታገላለሁ የሚል አካል እየተፈጠረ ያለው። እኔ በመጽሐፌ ላይ እንዳሰፈርኩት ብቸኛ መፍትሔ ያለውን ችግሩን ፍርጥ አድርጎ አቅርቦ፤ ፈጣሪንም ሆነ ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ ነው የሚገባው። ከሁለት ዓመት በፊት ብሔራዊ የንስሐ የእርቅ ቀን እንዲዘጋጅ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ሀሳብ አቅርቤ ነበር።
መጀመሪያ ሕዝቡ ይቅርታ መደራረግ አለበት። ልቡ መፅዳት አለበት። የቂምና በቀል አመለካከት ማስወገድ ይገባዋል። ያ ባለመሆኑ ነው በየዘመኑ እርስበርስ መገዳደልና መጠፋፋት እያደገ የመጣው። አብሮ ለመኖር የማያስችሉ ሕጎችን በመቀየር ረገድ ቅን የሆነ አመራር ያስፈልጋል ባይ ነኝ። ለምሳሌ የአሜሪካ ሥርዓት ውስጥ ቅንነት አለ። እዚህ ሃገር ሕግ እንዲሻሻል የሚጠይቅ ሰው ሕገ-መንግሥቱን ተቋወሙ ተብሎ በክፋት ነው የሚታየው። በመሆኑም ከአመራር ጀምሮ እስከ ሕዝቡ ድረስ ቅንነትን ማስተማር ይገባል። ልክ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ሕዝቡን በማስተማር መቀነስ እንደተቻለው ሁሉ፤ እርስበርስ የመጠፋፋቱና የመመቃኛቱን ክፉ ባሕል ለማስወገድ ከላይ እስከታች ማስተማር ያስፈልጋል። አንድ የማንክደው ነገር የእያንዳንዱ የኢትዮጵያ መሪዎች ችግር ሙስና ሳይሆን ስልጣናቸውን ያለልክ መውደዳቸው ነው። ሕጉ ስልጣንን የሚነካ ከሆነ ማሻሻልም አይፈልጉም። አሁን ግን ከራሳቸው በላይ ለሕዝብ ሊያስቡ ይገባል። አብሮ ለመኖር እንቅፋት የሆነ ህግም ሆነ አሠራር ካለ ለማስወገድ ፈቃደኝነቱና ተነሳሽነቱ ሊኖራቸው ግድ ይላል።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ካነሱት ሃሳብ ጋር በተያያዘ መንግሥት ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁሟል፤ ይሄ ኮሚሽን ምን ፋይዳ ይኖረዋል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር አጊቱ፡– በእኔ እምነት የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ መቋቋም ትልቅ ፋይዳ አለው። ከዚህ ቀደም የለመድነው እርቅ ያለፈው ሳይነሳ ዝም ብሎ ይቅርታ ተባባሉ የሚል ነው። ይሄ ግን ፈፅሞ የሚሆን አይደለም። ምክንያቱም ችግሩ ተፍረጥርጦ ባለመወራቱና በዳይ ጥፋቱን አውቆ ይቅርታ ባለመጠየቁ ቁስሉ ዳግም ሲያገረሽ አይተናል። እንደእኔ እምነት አሁን ላይ ሁሉም ችግሩን የሚያነሳበት መድረክ ከተመቻቸ፤ አጥፊውም ተለይቶ ይቅር እንዲባባል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብዬ አምናለሁ። በተለይ የቅሬታና የልዩነት ምንጭ የሆኑ ነገሮችን ወደፊት ለፊት በማምጣት መነጋገርና መተራረም አለብን። ችግሩን የምንፈታበትንም መንገድ ሕዝቡ ራሱ ነው ሊያመጣ የሚገባው። በነገራችን ላይ እኔ ተማሪ ሆኜም በየአካባቢው ማጉረምረሞች ነበሩ። ግን በተለይ ንጉሡ በጥበብ ቅሬታዎችን ለመፍታት ጥረት ያደርጉ ነበር። በመሠረቱ አሁንም ቢሆን የማይፈታ ችግር አለመኖሩን ሕዝቡን ማስተማር አለብን።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ባለው ግጭት በተለይ ሴቶችና ሕፃናት ናቸው ተጎጂዎች። ይሄ ግጭት በምን መልኩ ነው ሊፈታ የሚገባው?
ዶክተር አጊቱ፡- እኔ ይህንን ችግር ለመፍታት ከሴንትራል አሜሪካ ተሞክሮ መቅሰም አለብን ብዬ አምናለሁ። እነሱ ያደረጉት በመጀመሪያ የፖለቲካ አንጃዎች እርቅ ነው የፈፀሙት። ከዚያ በኋላ እርዳታ አሰባስበው ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋም ሥራ ነው የሠሩት። እኛም ሃገር ይህ ነው መሠራት ያለበት። ከሁሉም ጦርነት በኋላ ትልቁና ከባዱ ችግር ተፈናቃዮችን ወይም በግጭቱ ተጎጂ የነበሩ ሰዎችን መልሶ ማቋቋም ነው። በእኔ እምነት አሁን ላይ በዋናነት መሠራት ያለበት እዚህ ላይ ነው። ለእነዚህ ሰዎች ከመሬት ጀምሮ ፤ የፋይናንስ አቅርቦትና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ መልሰው ራሳቸውን እንዲያቋቁሙና ከተረጂነት እንዲላቀቁ ማድረግ ይጠበቃል። በነገራችን በዚህ ሥራ ላይ እኔ ራሴ መሳተፍ እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ልምዱም አለኝ፤ ከመንግሥት ጋር ሆኜ ድጋፍ ለማድረግ ነው እቅዴ። ይህንንም ከሦስት ዓመት በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ አቅርቤያለሁ። ስለዚህ ይህ ሥራ ሲጀመር እኔም ሆንኩ ሌላው ኅብረተሰብ የበኩሉን ጥረት ሊያደርግ ነው የሚገባው።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ በውጭ የሚኖሩ ጽንፈኛ ብሔረተኞች ሀገር ውስጥ ያለውን ማኅበረሰብ እርስበርስ በማጋጨት ላይ ተጠምደዋል። ለእነዚህ ዲያስፖራዎች ምን መልዕክት ያስተላልፋሉ?
ዶክተር አጊቱ፡- በጣም ትክክለኛ ሃሳብ ነው፤ ይህንን በሚመለከት መጽሐፌም ላይ አስፍሬያለሁ። እኔ በምኖርበት ሜኔሶታ ግዛት በርካታ ዲያስፖራዎች ለሃገር እድገት ገንዘብ ከመላክ ይልቅ በሐሰት ትርክት እርስ በርስ ሕዝብን ለማጫረስ በገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አውቃለሁ። የሚገርምሽ በኢትዮጵያ ምድር ሁሉ ተመቻችቶለት የኖረ፤ የተማረና ልጆቹን አስተምሮ ለወግ ማዕረግ ያበቃ ሳይቀር እዛ ሄዶ መልሶ ሃገርን ለመውጋት የሚያሴርበት ሁኔታ አለ። እኔ በበኩሌ በዚህ ሁኔታ እጅግ አዝናለሁ፤ በኢትዮጵያዊነቴም የምኮራ በመሆኔ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን በገሃድ ነው የምቃወማቸው። በተለይ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ኦሮሚያን ነፃ እናውጣ እያሉ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አልደግፍም። ምክንያቱም የኦሮም ሕዝብ በአፄ ምኒልክ ጊዜም ለሃገሩ ደሙን አፍስሷል፤ እስካሁንም ድረስ ለሃገሩ አንድነት እየተዋደቀ ያለ ሕዝብ ነው። የኦሮሞም ሆነ ሌላው ሕዝብ በባህልም ሆነ በደም የተሳሰረ ነው። ስለዚህ ይህንን በፍቅር የተጋመደ ሕዝብ በምን አይነት ሊያለያዩ አይችሉም። ለምሳሌ እኔ ጎንደር ለትምህርት ስሄድ ብዙ መጥፎ ነገሮች ተነግሮኝ ነበር፤ ሆኖም እዛ ከሄድኩኝ በኋላ የተነገረኝን ነገር ሕዝቡን ሆኖ ያገኘሁት የሰማይና የምድር ያህል ርቀት ያለው ሆኖ ነው። እንዳውም እንግዳ ተቀባይና የፍቅር ሰዎች ነበሩ። አሁንም ሕዝቡ ዘንድ ያለው ይህ አይነቱ ፍቅር ነው። በመሆኑም እነዚህ ሕዝቡን የሚያባሉ ሰዎች ይህንን አውቀው ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ነው መልዕክት ማስተላለፍ የሚፈልገው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር አጊቱ፡- እኔም ሃሳቤን እንድገልፅ ዕድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 1 /2015