በዓለማችን ከ50 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በሚጥል በሽታ ይጠቃሉ። ከእነሱ ውስጥ ደግሞ 80 በመቶ ያህሉ በአፍሪካ ውስጥ ናቸው። የሚጥል በሽታ (epilepsy) የአዕምሯችንን ሕዋሳት ከትክክለኛው ሥርዓት በተለየና በበዛ መልኩ ሲነቃቃ የሚከሰት በሽታ ሲሆን፤ አንድ ሰው የሚጥል በሽታ አለበት ለማለት ምልክቶቹ ቢያንስ ሁለት ጊዜ መከሰት ይኖርባቸዋል። በሽታው መታከም የሚችል በመሆኑም ታማሚውን ወደ ሕክምና ቦታ ማምጣት እጅግ አስፈላጊ ነው።
አብዛኛውን ጊዜ የሚጥል በሽታ ተጠቂዎች የበሽታውን መነሻ ለማወቅ ይቸግራሉ። ነገር ግን የሚከተሉት ነገሮች ለበሽታው መከሰት የራሳቸውን አስተዋፅዖ ያበረክታሉ ተብሎ ይታመናል። ለምሳሌ፣ በቅርብ የቤተሰብ አባላት ላይ ተመሳሳይ በሽታ ካለ፣ ጭንቀት፣ ከመጠን በላይ ትኩሳት፣ በእናት የእርግዝና ወራት የተከሰቱ ችግሮች፣ በጭንቅላት ላይ የደረሰ ጉዳት ወይም አደጋ፣ወደ ጭንቅላት የተሰራጨ ካንሰር፣የደም ውስጥ ስኳር መጠን ማነስ፣ የአደንዛዥ ዕፆች ተጠቃሚነት፣የማጅራት ገትር በሽታ፣ ተደራቢ በሽታዎችና ሌሎችም ለሚጥል በሽታ ምልክቶች ናቸው።
በሌላ በኩልም በሽታው በብዛት ሰውነትን የሚያንዘፈዝፍ ሲሆን በዚህ ጊዜ ታማሚዎች ራሳቸውን ይስታሉ። ዓይናቸውን ወደ ላይ ይሰቅላሉና አረፋ ይደፍቃሉ። በአንዳንድ የበሽታው ዓይነቶች ላይ ምልክቱ ከመታየቱ በፊት ራስ ምታት፣ ልብ የመምታት ስሜት፣ የእይታ ብዥታ ሊታዩት ይችላሉ። ይህም ከአንድ እስከ ሁለት ደቂቃ ሊቆይ ይችላል። ታማሚዎቹ ከነቁ በኋላ የሆነውን ነገር ለማወቅ እና ለማስታወስ ይሳናቸዋል። ለተከታይ ደቂቃዎችም ሽንትና ዓይነምድራቸውን መቆጣጠር ያስቸግራቸዋል ።
በሌላ በኩልም የሚጥል በሽታ በአንድ ሰው ላይ ተደጋግሞ ሲከሰት ከ30 ደቂቃ በላይ የሚቆይ ማንቀጥቀጥ፣ መገለልና መድሎ፣ የግጭት አደጋዎች፣ የአዕምሮ ዘገምተኝነት፣ ድንገተኛ ሞት አስከትሎ ይመጣል። እነዚህን አስከፊ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ለመቆጣጠር ምልክቶቹ በታዩበት ጊዜ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ሕክምና ማግኘት ያስፈልጋል።
ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሕዝብ ቁጥር ውስጥ 1 ነጥብ 10 ሚሊዮኑ የሚጥል በሽታ ያለባቸው መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ። ከእነዚህ ታማሚዎች መካከል ደግሞ ስለ ችግራቸው ቀድመው ተረድተው የሕክምና ክትትል የሚያደርጉት ከ5 በመቶ አይበልጡም፤ ቀሪዎቹ 95 በመቶ የሚሆኑት ታማሚዎች ወደ ሕክምና ተቋም ሄደው አያውቁም ።
በኢትዮጵያ የሚጥል በሽታ በሰዎች ላይ ከፍ ያለ ችግርን እያስከተለ ያለ ቢሆንም ችግሩን የሚመጥን ሥራ ግን እየተሠራ አይደለም። ይህ መሆኑ ደግሞ በታማሚዎች ላይ ከፍ ያለ የጤና፣የማኅበራዊ ግንኙነት አልፎ ተርፎም ኢኮኖሚያዊ ችግርን እያስከተለ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በመሆኑም፣”ኬር ኤፕሊፕሲ ኢትዮጵያ”ም በአገራችን ሕመሙ ያለባቸው ሰዎች ተገቢው ትኩረት ሳይሰጣቸው ለዘመናት እየተሰቃዩ የሚኖሩ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የችግሩ ተጠቂ በሆኑት ወይዘሮ እናት የውነቱ የተቋቋመ፤ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተመዝግቦ በ2008 ዓመተ ምሕረትም ወደ ሥራ ገባ።
መንግሥታዊም፣ ሃይማኖታዊም ያልሆነው ኬር ኤፕሊፕሲ ኢትዮጵያ በሕመሙ ላይ በብቸኝነት የሚሠራ በጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን፤ ሲመሠረት ይዞት የተነሳው ዓላማ በሚጥል ሕመም ምክንያት ለተሸነፉ ማንቂያ በመሆን ተስፋን እንዲሰንቁ ማድረግ፣ ከሕመሙ ጋር ሕልማቸውን እውን አድርገው ስኬታማ ሕይወት መኖር እንዲችሉ ማስገንዘብ፤ እንዲሁም ታማሚዎቹ በራሳቸው እንዲተማመኑ ማስተማር ነው። በሌላ በኩልም ድርጅቱ የመጀመሪያና ብቸኛ እንደመሆኑ ከጤና ሚኒስቴር ጀምሮ በተዋረድ ካሉ የጤና ኬላዎች፣ የክልል ጤና ቢሮዎችና ተዛማጅ ተቋማት ጋር አብሮ በመሥራት በሕመሙ ዙሪያ የተወሰነ ግንዛቤን በመፍጠር፤ ሕሙማኑ ስለ እኛ የሚመለከተው አካል አለ ብለው እንዲያስቡና በተቻለ መጠንም በራሳቸው ለመቆም የሚያስችላቸውን የሕይወት ጥበብ እንዲቀስሙ ሲያደርግ ቆይቷል፤ እያደረገም ይገኛል።
በኬር ኤፕሊፕሲ ኢትዮጵያ ውስጥ በሄልዝ ኦፊሰርነት የሚሠሩት ሲስተር ሃይማኖት አልታሰብ ወደ እነሱ ተቋም ስለሚመጡት የሚጥል ሕመም ተጠቂዎች እንደሚናገሩት ከሆነ፣ የሚጥል ሕመምን በተመለከተ በአገራችን ያለው ግንዛቤ ገና እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ ታማሚዎቹም ገና ትምህርት ቤት እንኳን በቅጡ የሚሄዱበት ሁኔታ የለም፣ይሄዳሉ የተባሉትም ቢሆኑ ለእነሱ በሚሆንና ችግሩ ሲያጋጥማቸውም እንክብካቤ በሚደረግላቸው መጠን እየተማሩ አይደለም። በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ አልፈው ተምረው ሥራ ላይ ሲሆኑም የሚያጋጥማቸው ነገር በትምህርት ቤት ካሳለፉት ሁኔታ የሚለይ አይደለም።
እንደ ሲስተር ሃይማኖት ሙያዊ ማብራሪያ የሚጥል ሕመም ታማሚዎች እንደ ማንኛውም የስኳር አልያም የደም ግፊት ሕመም ታማሚዎች ተገቢውን የሕክምና ክትትል እያገኙ መኖር የሚችሉ ቢሆኑም እንኳን ኅብረተሰቡ ሕመሙን ከእምነትና አጉል ልማድ ጋር የሚያያይዘው በመሆኑ እንደ ማንኛውም ሰው በማኅበራዊ ሕይወት ለመሳተፍ፣ትዳር ለመመሥረት፣ ልጆች ለመውለድ ከፍ ያለ ችግር ያጋጥማቸዋል።
እነዚህ ነገሮች ሲያጋጥማቸው ደግሞ ተቋቁመው ማለፍ ስለሚሳናቸው ከፍ ወዳለ አዕምሯዊ ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ሊሆናቸው ይችላል። ይህንን ሁኔታ ለማገዝና ሕመሙ ያለባቸው ሰዎች እንደማንኛውም የሕመም ዓይነት ሕክምናቸውን እየተከታተሉ፤ መድኃኒታቸውን እየወሰዱ መኖር እንደሚችሉ ለማስገንዘብ ኬር ኤፕሊፕሲ ኢትዮጵያ ከፍ ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ነው።
ሲስተር ሃይማኖት እንደሚሉት ሕመሙ ያለባቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን በብቸኝነትና ድብርት ውስጥ ነው የሚያሳልፉት። ይህ ለመሆኑ ዋናው ምክንያት ደግሞ ሰዎች እኛን ሊቀርቡን፣ ጓደኛ ሊያደርጉን፣ ችግራችንንም ሊረዱልን አይችሉም የሚል፤ ከፍ ያለ ስነልቦናዊ ጫና ነው። በዚህ ምክንያትም ራሳቸውን ከማኅበረሰቡ ነጥለው ብቻቸውን ለመቀመጥ ነው የሚፈልጉት፤ እነዚህን ሰዎች ማገዝና መርዳት ስለሚያስፈልግ ድርጅቱ በሚችለው አቅም ሁሉ የምክር አገልግሎት ፕሮግራም በማውጣት ሥራዎችን ይሠራል።
ሌላው ማንኛውም ሰው እስከ ክልል ድረስ ማለት ነው፣ ችግሩ አለብኝ ብሎ ወደ ኬር ኤፕሊፕሲ ኢትዮጵያ ሲደውል ምን ማድረግ እንዳለበት፤ ወዴት መሄድ እንደሚያስፈልገው መረጃ እንዲያገኝ ይደረጋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ችግራቸውን ለይተው መድኃኒት እየወሰዱ ያሉ፤ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ መድኃኒቶች ከገበያው ላይ ሲጠፉ መድኃኒት ሊገኝ የሚችልበትን ቦታ በመጠቆም፤ ችግሩ ከዛም በላይ ከሆነ መድኃኒቱን በመስጠት የማገዝ ሥራን ይሠራል።
የሚጥል ሕመም በሰዎች ላይ ሲከሰት፣በተለይም ሲጥላቸው ለአጭር ደቂቃ የሆነ የአእዕምሯቸው ክፍል ሥራውን አቁሟል ማለት ነው። በዚህን ጊዜ ራስን ስቶ መውደቅ፣ መንቀጥቀጥ፤ አልያም የአፍ መጣመም፣ የሰውነት ቀጥ ብሎ መቅረትም ሊኖር ይችላል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በሽታው ራሱ ዓይነቱ ብዙ ስለሆነ ነው። እኛ በተለምዶ የምናውቀው ”ሰው ራሱን ስቶ ይወድቃል፤ ከዛ አረፋ ይደፍቃል” ነው፤ ግን መገለጫው ይህ ብቻ አይደለም። እነዚህ ሰዎች ከክስተቱ በኋላ ወደ ነበሩበት አዕምሯዊ ይዞታ የመመለስ ሁኔታ አላቸው። በመሆኑም ኅብረተሰቡም ይህንን በቅጡ ሊረዳ፤ ተገቢውን ትኩረትም ሊሰጥ ይገባል።
ሲስተር ሃይማኖት እንደሚሉት የሚጥል ሕመም በየትኛውም የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን ሊያጠቃ ይችላል። ነገር ግን፣ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ አብዛኛውን ጊዜ ሕመሙ በወጣቶች ላይ ይበዛል።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሰዎች ደም ግፊት፣ስትሮክ ገጥሟቸው በጭንቅላታቸው ውስጥ ደም ከፈሰሰ በዚህን ጊዜ የሚጥል ሕመም ሊከሰትባቸው ይችላል። ይህ የሚያመለክተን በተለያዩ አደጋዎች ምክንያትም የሚመጣበት አጋጣሚ መኖሩን ነው።
“አሁን ላይ በአገራችን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚያሳየን ከሆነ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከማዳበር አኳያ ብዙ መሠራት ያለበት መሆኑን ነው። ኬር ኤፕሊፕሲ ከተቋቋመ ስምንተኛ ዓመቱን ይዟል። በዋናነትም ትኩረቱን ግንዛቤ ላይ አድርጎ እየሠራ ነው። ነገር ግን ትንሽ የግንዛቤው ሁኔታ እያደገ የመጣ ቢመስልም ለውጡ ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሻለ ግንዛቤ ላይ ደርሷል ለማለት ይከብዳል። ምክንያቱም አዲስ አበባ ውስጥ ተቀምጠው ይህ ሕመም እንዳለ ሰምተው የማያውቁ፣ችግሩ ሲመጣም ምን መደረግ እንዳለበት የማያውቁ ብዙ ሰዎች አሉ። በዚህ ምክንያትም የሚጥል ሕመም የተከሰተባቸውን ሰዎች ከቡዳ፣ከእርኩስ መንፈስ ወዘተ ጋር የማገናኘት ነገር እንጂ ወደ ሕክምን ተቋም ሄዶ ከማማከር አኳያ ገና ብዙ ይቀረናል” እንደ ሲስተር ሃይማኖት ገለጻ።
የኬር ኤፕሊፕሲ ኢትዮጵያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዐቢይ አሥራት በበኩላቸው ድርጅቱ ሲመሠረት ዋና ዓላማው የሚጥል ሕመም ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሻለ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ነው። በተጓዳኝም፣ በበሽታው ዙሪያ የኅብረተሰቡን አመለካከት ቀይሮ ሕሙማኑ እንደማንኛውም ሰው የሚኖሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው።
ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት ሕመሙ ላለባቸው ሰዎች የሕክምና እርዳታን ይሰጥ የነበረው አማኑኤል ሆስፒታል ብቻ ነበር። ነገር ግን ድርጅቱ ከተከፈተ በኋላ የጤና ባለሙያዎች ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ፤ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀትና ግንዛቤ በመፍጠር ለሕመሙ ትኩረት ከመስጠትም በላይ በመድኃኒትና በሌሎች ነገሮችም በኩል የተሻለ ነገር እንዲመጣ ሰፊ ሥራ ሠርቷል።
ዛሬ ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ ሕሙማኑ ነጻ የሕክምና አገልግሎትን እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው። በዚህም ማዕከሉ ወርሐዊ ነጻ የሕክምና አገልግሎት በስፔሻሊስት ሐኪሞች በመስጠት ላይ ይገኛል። በአሁኑ ሰዓትም የዕድሉ ተጠቃሚ የሆኑ ከ8 መቶ በላይ ታማሚዎችም አሉ።
እነዚህ ታማሚዎች የተሻለ የሕክምና አገልግሎት ከማግኘታቸውም በላይ ድርጅቱ የጤና መድህን ስለሚገባላቸው አቅም የለንም ብለው ከሕክምና አገልግሎቱ እንዳይገለሉ ሆኗል። መድኃኒቱ ሲጠፋም ድርጅቱ አፈላልጎ በመስጠት እንዳይቋረጥባቸው እያደረገ ይገኛል።
አቶ ዐቢይ እንደሚሉት አብዛኞቹ ታማሚዎች እንደ ኤምአርአይ እና አይጂን የመሳሰሉ ምርመራዎች አይደረጉላቸውም። ምክንያቱ ደግሞ ሰዎቹ የአቅም ውስንነት ስላለባቸው፤ እንዲሁም መሣሪያው እንደልብ ስለማይገኝ ነው። አሁን ድርጅቱ ኤይጂ ማሽን በእርዳታ በማግኘቱ ታማሚዎችን በመሣሪያው ታግዘን የመመርመር፤ ከዛ ባለፈም ተጨማሪ ምርመራዎች ሲያስፈልጉ በከተማው ካሉ ዲያግኖስቲክ ማዕከላት ጋር በመነጋገር በነጻ አገልግሎቱን የሚያገኙበትን ሁኔታ የማመቻቸት ሥራን በመሥራት ላይ ይገኛል። ይህ ምናልባትም ለታማሚዎች ከፍ ያለ እገዛ ነው።
“የሚጥል በሽታ ሀገራችን ላይ በመንግሥትም ደረጃ እንዲሁም ኅብረተሰቡ ውስጥ ባለው ሁኔታ ትኩረት አግኝቷል ማለት ይከብዳል። በሌላ በኩል ደግሞ ሕክምናው ከአዕምሮ ጤና ችግር ጋር የተያያዘ ተደርጎ ተወስዷል። ነገር ግን መሆን የለበትም። ይህ ደግሞ ሰዎች በዚህ ሕመም ተቸግረው ሲመጡ የሚላኩት አማኑኤል ሆስፒታል ስለሚሆን የሚፈጥርባቸው መደናገጥ ከፍ ያለ ነው። በመሆኑም ይህንን ሁኔታ ተረድቶ ማስተካከል ያስፈልጋል። እኛም ላለፉት ስምንት ዓመታት ሁኔታው ይሻሻል ዘንድ ብዙ ጥረት እያደረግን ነው” ይላሉ ምክትል ሥራ አስኪያጁ።
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት የመንግሥትን ሸክም እየተጋራ ያለ ቢሆንም በአንዳንድ በጎ አድራጊዎች፣ እንዲሁም በመሥራቿ ወይዘሮ እናት የውነቱ ጥረት እዚህ ይድረስ እንጂ ብዙ ችግሮች አሉበት። በተለይም ታማሚዎች መጥተው ሲመረመሩ ብዙ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ይኖራሉ። እነዛን ሁሉ ነገሮች ለማሟላት፣በዚህ በሽታ የተያዙ ሕጻናት ያላቸውን ወላጆች በማገዝ በኩል ከፍ ያለ የአቅም ውስንነት አለበት። በመሆኑም ይህንን ብቸኛ ድርጅት ማገዝ ዜጎችን ማገዝ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
የሚጥል በሽታ በሕክምና ቁጥጥር ስር እስካልዋለ ድረስ ምን ጊዜና የት ቦታ ሕመምተኛውን እንደሚጥለው ማወቅ አይቻልም። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። የእሳት፣ የመብራት ወይንም የቴሌቪዥን ማንፀባረቅና ማብለጭለጭ በሽታውን ሊቀሰቅሰው እንደሚችል አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በሽታው ድንገት የሚቀሰቀስና ታማሚውን እጅግ ለከፋ አደጋ የሚዳርግ በመሆኑ የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎች መኪና ከማሽከርከር፣ ሳይክል ከመንዳት፣ ከዋና፣ ፈረስና በቅሎ ከመጋለብ፣ ከፍታ ቦታዎች ላይ ከመሥራትና እንደ አልኮልና ጫት ካሉ ሱሶች በእጅጉ መቆጠብ እንዳለባቸው ባለሙያዎች ይመክራሉ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 1 /2015