መቸም ጀግናና ጀግንነት ሲነሱ የሚያስነሱት ርእስና ርእሰ ጉዳይ የዋዛ አይደለም። የቱን ጥዬ፣ የቱን ይዤ … እስኪባል ድረስ ነው የሚያስጨንቁት። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ጀግንነትም ሆነ ጀግናነት (ጀግና መሆን) በቀላሉ ፊጥ የሚባልበት ባለመሆኑና እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ የሚዘልቅ ተግባር መፈፀምን ስለሚጠይቅ ነው። ይህ ሁሉ የሚሆነው፣ የሚወደሰውና ከባለ ውለታነት ተርታ የሚያሰልፈው የጀግንነት ውሎውና ተግባሩ ለአገርና ለሕዝብ እስከሆነ ድረስ ነውና የዛሬውን ባለውለታችንን ከዚሁ አኳያ የምናነሳቸው ይሆናል።
ሊየተናል፡ጄኔራል፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ ይባላሉ፤ በሌላኛው (በጀግንነት) ስማቸው ደግሞ አባ፡ ይባስ።
ሊየተናል፡ ጄኔራል፡ ነጋ፡ ተጽፎም ሆነ ተነግሮ የማያልቅ ታሪክ ባለቤት ናቸው። ያልወጡት ዳገት፤ ያልወረዱት ቁልቁለት የለም። ይሁን እንጂ በዚህ አንድ ገፅ ጋዜጣ ሁሉንም ቀርቶ የሰናፍጭ ቅንጣት ያህሏን ታሪካቸውን እንኳን ልናወራላቸው አንችልም። በመሆኑም፣ ያለን አማራጭ አንባቢ ስለ ባለታሪኩ ሰነዶችን በማገላበጥ ገድላቸውን መገንዘብ ያለበት መሆኑን መጠቆም ነው።
ትውልድና፡ እድገት
ሊየተናል. ጄኔራል፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ ካባታቸው፡ ከልጅ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ሞላ ከናታቸው፡ ከወይዘሮ፡ ደስታ፡ አባዬ የይፋት፡ አውራጃና፡ የመንዝ፡ አውራጃ፡ አዋሳኝ፡ በሆነው ጎራት፡ አካባቢ ሚያዝያ፡ 30፡ ቀን፡ 1910 ዓ.ም.፡ ተወለዱ።
ልጅ፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ አብዛኛውን፡ የሕፃንነትና፡ የልጅነት፡ ዘመናቸውን፡ ይፋት፡ (መንግሥት፣ ጎራት፣ ዐማች፡ ዐምባ፣ ቍጫጭ፡ ዐምባ፣ ቆቦ)፡ አሳለፉ።
ትምህርት
በጥንታዊው፡ የኢትዮጵያ፡ ልማድ፣ አራት፡ ዓመት፡ ካራት፡ ቀን፡ ሲሞላቸው፣ ደብተራ፡ ገብረ፡ ክርስቶስ፡ ዘንድ፣ ቀጥሎም፡ አጎታቸው፡ አለቃ፡ ገብረ፡ ክርስቶስ፡ ዘንድ፣ እንዲሁም፡ መምህር፡ ተቀጥሮላቸው፣ ከፊደል፡ መቍጠር፡ እስከ፡ ዳዊት፡ መድገም፡ ያለውን፡ ባህላዊ፡ የቀለም፡ ትምህርት፡ ባስደናቂ፡ ፍጥነት፡ አጠናቀቁ። በጊዜው፡ ለጨዋ፡ ልጅ፡ ኹሉ፡ ይሰጥ፡ የነበረውንም፡ የሥርዐት፣ የጠመንጃ፡ ተኩስ፣ የውሃ፡ ዋና፣ የፈረስ፡ ግልቢያና፡ የመሳሰለውን፡ ትምህርት፡ አገኙ።
በ1917 ዓ.ም፣ ልጅ፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ ከወንድሞቻቸው፡ ከልጅ፡ አሰፋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴና፡ ከልጅ፡ ለማ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ጋራ፣ እናታቸውን፡ ወይዘሮ፡ ደስታ፡ አባዬን፡ ተከትለው፣ በሕይወት የሌሉትን ያባታቸው (ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ሞላ)ን የወግ፡ ዕቃ፡ ለመንግሥት፡ ለማግባት፣ አዲስ፡ አበባ፣ ራስ፡ ተፈሪ፡ መኰንን፡ ዘንድ፡ ቀረቡ። ልጅ፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ ራስ፡ ተፈሪ፡ መኰንን፡ በዚህ፡ ዕለት፡ ለመጀመሪያ፡ ጊዜ፡ አዩአቸው፤ ስላባታቸውም፡ ማረፍ፡ የገለጹላቸው፡ የሐዘን፡ ስሜትና፡ የማጽናናት፡ ቃል፡ በልጅነት፡ አእምሯቸው፡ ለመቼውም፡ ተቀርጾ፡ ኖረ።
ራስ፡ ተፈሪ፡ መኰንን፣ የልጅ፡ ኀይለ፡ ሥላሴን፡ ልጆች፡ ማስተማር፡ የኛ፡ ተግባር፡ ነው፡ ቢሉም፣ የልጆቹ፡ ዕድሜ፡ ማነስ፡ ከቤተሰብ፡ ርቆ፡ ለመኖር፡ ስላልፈቀደ፣ ከሁለት፡ ዓመት፡ በኋላ፡ ከይፋት፡ ይዘዋቸው፡ እንዲመጡ፡ ወይዘሮ፡ ደስታን፡ ዐደራ፡ አሉ።
ይፋት፡ ተመልሰው፣ ሁለት፡ ዓመት፡ እንደ፡ ሞላም፣ በ1919፡ ዓ.ም.፣ የልጅ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ማኅበርተኞች፣ እነደጃዝማች፡ አበበ፡ አውራሪስ፣ ልጅ፡ (ዃላ፣ ቢትወደድ)፡ መኰንን፡ እንዳልካቸው፣ ልጅ፡ መኵሪያ፡ ይገባሻል፣ ባላምባራስ፡ (ዃላ፣ ራስ)፡ አበበ፡ አረጋይ፣ ነጋድራስ፡ አበበ፡ ድረስ፣ ልጅ፡ ኀይለ፡ ማርያም፡ ገዝሙ፡ አንድጋ፡ ኾነው፣ “ዐልጋ፡ ወራሽ፡ ራስ፡ ተፈሪ፡ መኰንን፡ ባዘዙት፡ መሠረት፣ ልጆችዎ፡ ትምህርት፡ ቤት፡ እንዲገቡ፡ ወዳ አዲስ፡ አበባ፡ ይላኳቸው”፡ የሚል፡ ማስታወሻ፡ ደብዳቤ፡ ለወይዘሮ፡ ደስታ፡ ጻፉላቸው። ከጥቂት፡ ወራት፡ በዃላ፣ ሦስቱ፡ ወንድማማቾች፡ (ልጅ፡ ነጋ፣ ልጅ፡ አሰፋ፣ ልጅ፡ ለማ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ) አዲስ፡ አበባ፡ እንደ፡ መጡ፥ ካባታቸው፡ ማደሪያ፡ በደጃዝማች፡ ይገዙ፡ በሀብቴ፡ በኩል፡ እየተሰበሰበ፥ በወር፡ 30፡ ብር፡ እንዲከፈልላቸው፡ ሆኖ፣ እተፈሪ፡ መኰንን፡ ትምህርት፡ ቤት፡ ባአዳሪነት፡ ተመዝግበው፣ ዘመናዊ፡ ትምህርታቸውን፡ በፈረንሳይኛ፡ ቋንቋ፡ ለሰባት፡ ዓመት፡ ተከታተሉ።
ሦስቱም፡ ወንድማማቾች፡ እጅግ፡ ብሩህ፡ አእምሮ፡ ነበራቸውና፣ በመጀመሪያው፡ ዓመት፣ ያንደኛ፡ ደረጃ፡ ትምህርታቸውን፡ ባስደናቂ፡ ውጤት፡ አጠናቀው፣ ባምስተኛው፡ ዓመት፡ ልጅ፡ አሰፋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ በሰባተኛው፡ ዓመት፡ ደግሞ፣ ልጅ፡ ለማና፡ ልጅ፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ የሁለተኛ፡ ደረጃ፡ መፈጸሚያና፡ የዩኒቨርሲቲ፡ መግቢያ፡ “ባካሎሬያ፡ ሲያንቲፊክ”፡ ፈተናቸውን፣ በ1924ና፡ በ1926 ዓ.ም. መጨረሻ፣ በ”ፍጹም፡ ጥሩ”፡ (“ኤክሰለንት”)ና፡ በ”እጅግ፡ ጥሩ”፡ (“ትሬ፡ ቢየን”)፡ ማዕርግ፡ አልፈዋል። ይኸውም፡ የባካሎሬያ፡ ፈተና፡ በኢትዮጵያ፡ ለመጃመሪያ፡ ጊዜ፡ መካሄዱ፡ ነበር። በዚሁ፡ ብልህነታቸው፣ እንዲሁም፡ በትሕትናቸውና፣ በግብረ፡ ገብነታቸው፣ አስተማሪዎቻቸውም፡ ሆኑ፡ የተማሪ፡ ቤት፡ ጓደኞቻቸው፡ በተለይ፡ ወደዷቸው፣ አከበሯቸው፣ ተመኩባቸውም፤ “የተፈሪ፡ መኰንን፡ ኮከቦች”፡ የሚል፡ ማቈላመጫ፡ ስምም፡ አወጡላቸው። ልጅ፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ በሒሳብ፣ በሳይንስ፣ በሥዕልና፡ በሙዚቃ፡ የተለየ፡ ስጦታ፡ ነበራቸው። ባአዲስ፡ አበባ፡ ትምህርት፡ ቤቶች፡ መካከል፡ በተደረጉ፡ የሙዚቃም፡ የሥዕልም፡ ውድድሮች፣ አንደኛ፡ እየወጡ፣ ከንግሥተ፡ ነገሥታት፡ ዘውዲቱ፡ እጅ፡ ሽልማትን፡ ተቀብለዋል።
ባካሎሬያቸውን፡ አግኝተው፣ ለከፍተኛ፡ ትምህርት፡ ወደ፡ አውሮፓ፡ እንዲሄዱ፡ መወሰኑ፡ ሲነገራቸው፣ “ፋሺስት፡ ኢጣሊያ፡ ኢትዮጵያን፡ ለመውረር፡ እየተሰናዳች፣ አገሬን፡ ጥዬ፡ አልሄድም”፡ ብለው፣ ወደ ጦር፡ ትምህርት፡ ቤት፡ ለመግባት፡ ያላቸውን፡ ፍላጎት፡ ገለጹ። ጦር፡ ትምህርት፡ ለመግባት፡ የዕድሜያቸው፡ ማነስ፡ እንደማይፈቅድላቸው፡ ቢነገራቸውም፣ ለግርማዊነታቸው፡ አመልክተው፣ ከስድስት፡ ወር፡ ጥበቃ፡ በኃላ፣ በልዩ፡ ፈቃድ፣ በጥር፡ ወር፡ 1927፡ ዓ.ም እገነት፡ ሆሎታ፡ ቀዳማዊ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ጦር፡ ትምህርት፡ ቤት፡ ገብተው፣ ከትምህርቱ፡ ተሳተፉ።
በስዊድን፡ ወታደራዊ፡ ተልእኮ፡ በፈረንሳዊ፡ ቋንቋ፡ የተሰጠው፡ የጦር፡ ትምህርት፡ ሙሉ፡ በሙሉ፡ የፈረንሳይ፡ ጦር፡ አካዳሚ፡ ትምህርት፡ መርሐ፡ ግብር፡ ነው። ወቅቱ፡ አስቸኳይ፡ ስለ፡ ሆነ፣ የሦስቱን፡ ዓመት፡ የጦር፡ ትምህርት፡ መርሐ፡ ግብር፣ ዓመት፡ ተመንፈቅ፡ ባልሞላ፡ ጊዜ፣ አንደኛ፡ በመውጣት፡ አጠናቀው፣ በመድፈኛ፡ ደንብ፡ ውስጥ፣
•ኅዳር፡ 14፡ ቀን፡ 1928፡ ዓ.ም.፣ የመቶ፡ አለቃ፤
•ታኅሣሥ፡ 14፡ ቀን፡ 1928፡ ዓ.ም፣ የሻምበል፤
•ጥር፡ 21፡ ቀን፡ 1928፡ ዓ.ም.፣ የሻለቃ፡ (የ5፡ ሻምበል፡ አዛዥ)፤
•በመጨረሻም፣ የካቲት፡ 21፡ ቀን፡ 1928፡ ዓ.ም.፣ በሊየተና፡ ኮሎኔልነት፡ ማዕርግ፣ አዲስ፡ ለተቋቋመው፡ ብሪጌድ፡ ዋና፡ ኤታ፡ ማዦር፡ ሹም፡ ሆነው፡ በንጉሠ፡ ነገሥቱ፡ ተሠየሙ።
አገልግሎት
ወዲያው፣ ሚያዝያ፡ 13፡ ቀን፡ 1928፡ ዓ.ም.፣ አዲሱን፡ ጦር፡ በኤታ፡ ማዦር፡ ሹምነት፡ በጣርማ፡ በር፡ ግንባር፡ አዘመቱ። የኢትዮጵያ፡ ጦር፡ ከተፈታ፡ በኋላ፣ ጥቂት፡ የገነት፡ መኰንኖችንና፡ ሰራዊቱን፡ ይዘው፣ ሚያዝያ፡ 24፡ ቀን፡ 1928፡ ዓ.ም.፡ አርበኝነት፡ ወጡ። እስካ 1930፡ ዓ.ም.፡ ፍጻሜ፡ ድረስ፣ ለሁለት፡ ዓመት፡ ተኩል፣
• ሸዋ፡ (አዲስ፡ አበባ፡ ዙሪያ፣ ሙሎ፣ ሰላሌ፣ ተጕለት፣ መርሐቤቴ፣ ግንደበረት፣ ጊዳ፣ ሜጫ፣ ሜታ፣ …)፤
• ወለጋ፡ (አሞሩ፣ ኤበንቱ፣ ጨልያ፣ ሆሮ፣ ጉድሩ፣ …)፣
• ጎጃም፡ (አለፋ፡ ጣቁሳ፣ ቡሬ፣ አሰዋ፡ ጉደራ፣ አገው፡ ምድር፣ ማቻከል፣ …)
ከደጃዝማች፡ ዘውዴ፡ አስፋው፡ ዳርጌ፣ ከራስ፡ አበበ፡ አረጋይና፣ ከታላላቅ፣ ያርበኝነት መሪዎች፡ ጋራ፡ በጦር፡ መሪነት፣ እዚህ፡ ሊዘረዘሩ፡ በማይችሉ፡ ልዩ፡ ልዩ፡ ውጊያዎች፡ በታላቅ፡ ጀግንነት፡ ተዋግተውና፡ አዋግተው፣ ባርበኞች፡ ዘንድ፡ የላቀ፡ ዝናን፣ የተለየ፡ አድናቆትን፡ አትርፈዋል።
በወቅቱ፣ ሱዳንን፡ በቅኝ፡ ግዛትነት፡ ይገዛ፡ የነበረው፡ የብሪታንያ፡ መንግሥት፣ ኢትዮጵያን፡ ለኢጣሊያ፡ አፅድቆ፡ ኖሮ፣ መስከረም፡ 19፡ ቀን፡ 1931፡ ዓ.ም.፣ ሊ.፡ ኮሎኔል፡ ነጋ፡ ኀይል፡ ሥላሴ፡ ከተከተሏቸው፡ ዐርበኞች፡ ጋራ፣ የሱዳንን፡ ጠረፍ፡ እንዳለፉ፣ ጠረፉን፡ የሚጠብቀው፡ የብሪታንያ፡ ጦር፡ ይይዛቸዋል። ጥቂት፡ ወራት፡ በጦር፡ እስረኝነት፡ ገዳሬፍና፡ ካርቱም፡ እንደ፡ ቈዩ፣ ኢጣልያ፡ በታላቋ፡ ብሪታንያ፡ ላይ፡ ጦርነት፡ በማወጇ፣ የታሰሩት፡ ዐርበኞች፡ ተፈቱ።
ሊ.፡ ኮሎኔል፡ ነጋ፡ ኀይል፡ ሥላሴም፣ ከሰራዊቱ የተላኩትን፡ መልክት፡ (ያርበኝነት፡ ተጋድሎው፡ የደረሰበትን፡ ደረጃ፣ ያስገኛቸውንም፡ ውጤቶች፡ አስታውቆና፣ ከንጉሠ ነገሥቱ፡ ጋራ፡ ግንኙነትን፡ መሥርቶ፣ የጦር፡ መሣሪያና፡ የሥንቅ፡ ርዳታ፡ በቶሎ፡ ላርበኛው፡ እንዲደርስ እንዲያደርጉ የሚጠይቀውን ደብዳቤ) በብሪታንያ፡ ባለሥልጣኖች፡ በኩል፡ ለንጉሠ፡ ነገሥቱ፡ አስተላልፈው፣ ወደ፡ ኢትዮጵያ፡ ለመመለስ፣ ዐብረዋቸው፡ የሚዘምቱ፡ ሁለት ሺህ፡ የሚኾኑ፡ ስደተኞችን፡ ላርበኝነት፡ አሰባስበው፡ በሚያደራጁበት፡ ጊዜ፣ የታላቋ፡ ብሪታንያ፡ መንግሥት፡ በጎ፡ ፈቃድና፡ ወታደራዊ፡ ድጋፍ፡ ደረሰላቸው።
ሰኔ፡ 27፡ ቀን፡ 1932፡ ዓ.ም.፡ ንጉሠ፡ ነገሥቱ፡ ከብሪታንያ፡ ወደ፡ ካርቱም፡ እንደ፡ ተመለሱ፣ ሊ.፡ ኮሎኔል፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴን፡ አስጠርተው፣ ሶባ፡ እተባለው፡ የሱዳን፡ ቀበሌ፣ አዲስ፡ የሚቋቋመውን፡ ቅዱስ፡ ጊዮርጊስ፡ የጦር፡ ትምህርት፡ ቤት፡ ከብሪታንያ፡ ጦር፡ መኰንኖች፡ ጋራ፡ በጣምራ፡ እንዲመሩ፡ አዘዟቸው።
በወቅቱ፡ የመርድ፡ አዝማች፡ አስፋ፡ ወሰን፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ወታደራዊ፡ ማዕረግ፡ የሻለቃ፡ ስለ፡ ነበር፣ ከርሳቸው፡ ማዕርግ፡ በልጦ፡ እንዳይገኝ፣ ሊ.፡ ኮሎኔል፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ ማዕርጋቸው፡ አንድ፡ ደረጃ፡ ዝቅ፡ ብሎ፣ በሻለቅነት፡ ማዕርግ፡ ሥራቸውን፡ እንዲቀጥሉ፡ ከንጉሠ፡ ነገሥቱ፡ ታዘዙ። ኮሎኔሉም፣ ጃንሆይ፤ ጉዳዬ፡ ከሥራው፡ እንጂ፡ ከማዕረጉ፡ አይደለም፤ ብለው፡ ተቀበሉ።
የካቲት፡ 1933፡ ዓ.ም.፡ ኢትዮጵያ፡ ገብተው፣ ከ3፡ ወር፡ ዘመቻ፡ በኃላ፣ ደብረ፡ ማርቆስ፡ ከኢጣሊያ፡ ጦር፡ እጅ፡ ነጻ፡ ወጣች። ሻለቃ፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ በጦሩ፡ በኩል፡ ለሚኖረው፡ ጉዳይ፡ ኹሉ፡ ኀላፊ፡ ኾነው፣ የንጉሠ፡ ነገሥቱንም፡ ወታደራዊ፡ መመሪያ፡ ይዘው፣ ከምክትሎቻቸው፡ ከሻለቃ፡ ዐቢይ፡ አበበና፡ ከሻለቃ፡ ሙሉጌታ፡ ቡሊ፡ ጋራ፣ የንጉሠ፡ ነገሥቱን፡ ባለሙሉ፡ ሥልጣን፡ እንደራሴ፡ ቢትወደድ፡ መኰንን፡ እንዳልካቸውን፡ ዐጅበው፣ ሚያዝያ፡ 5፡ ቀን፡ 1933፡ ዓ.ም.፡ በማለዳ፡ ከደብረ፡ ማርቆስ፡ ባየርዠበብ፡ (አይሮፕላን)፡ ተጉዘው፣ የኢትዮጵያ፡ መናገሻ፡ ከተማ፣ አዲስ፡ አበባ፣ ጧቱኑ፡ ገቡ። ሻለቃ፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴን፡ ካርበኝነት፡ ዘመን፡ አንሥቶ፡ ያውቋቸውና፡ ያደንቋቸው፡ የነበሩት፣ ዝነኛዋ፡ ባለቅኔ፡ ንጋቷ፡ ከልካይ፣ የምሥራቹን፡ እንደ፡ ሰሙ፣
ጠቅል፡ ባንዲራውን፡ ጠረፍ፡ ቢዘረጋ፣
አዲስ፡ አበባ፡ ላይ፡ አስቀድሞ፡ ነጋ።
ሲሉ፡ ገጠሙላቸው።
አዲስ፡ አበባ፡ እንደ፡ ገቡም፣ ጽሕፈት፡ ቤታቸውን፡ በጃንሆይ፡ ዐፄ፡ ምኒልክ፡ ቤተ፡ መንግሥት፡ ግቢ፡ ውስጥ፡ አድርገው፣ ያርበኛውን፡ ጦር፡ በከተማዋ፡ ዙሪያ፡ አዋቅሮ፡ በማሰምራትና፣ ከብሪታንያ፡ ጦር፡ ኀላፊዎች፡ ጋራ፡ ዐብሮ፡ በመሥራት፣ የከተማውን፡ ጠቅላላ፡ ጸጥታ፡ አረጋግጠው፣ ወታደራዊ፡ አስተዳደሩን፡ አደራጅተው፣ ንጉሠ፡ ነገሥታቸውን፡ በመናገሻ፡ ከተማዋ፡ ለመቀበል፡ አስፈላጊውን፡ ዝግጅትና፡ መስተንግዶ፡ አከናወኑ። በዚህ፡ ሥራቸው፣ ከብሪታንያ፡ ጦር፡ አመራር፡ ጋራ፣ አልፎ፡ አልፎ፣ አለመግባባትና፡ ግጭት፡ ቢፈጠርም፡ ቅሉ፣ ሻለቃ፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ አንዳችም፡ ጊዜ፡ ቢኾን፡ የኢትዮጵያን፡ እግዚእና (ሉአላዊነት)፡ ሳያስደፍሩ፣ ክብሯንም፡ ሳያስነኩ፣ ተልእኳቸውን፡ ጠንቅቀው፡ ፈጽመዋል።
ሰኔ፡ 7፡ ቀን፡ 1954፡ ዓ.ም፣ የሊዬተና፡ ዤኔራልነት፡ (ታኅሣሥ፡ 11፡ ቀን፡ 1951፡ ዓ.ም.፣ የሜጀር፡ ዤኔራልነት፡ ማዕረግ) ተሰጥቷቸው ወደ ጎንደር፡ ሄዱ። ጎንደር እንደ፡ ገቡም፤
“አህያ፡ መጣች፡ ተጭና፡ ሞፈር፤
በነጋ፡ ጊዜ፣ እኽል፡ እንዳፈር።”
በሚል፡ ትንቢታዊ፡ ቃል፡ ሕዝቡ፡ ተቀበላቸው።
ወደ ሲዳሞ ተሹመው በሄዱበትም ጊዜ ልክ እንደ ጎንደሩ ሁሉ፤
በባሌ፡ ዑጋዴ፣ በጎንደር፡ አስመራ፣
እየነጋ፡ ሲኼድ፣ ሥራው፡ እያበራ፣
በየደረሰበት፡ ሀገሩን፡ ሲያኰራ፣
ዕድል፡ ሲያጋጥመው፡ እንዲሁ፡ በተራ፣
ብቅ፡ አለ፡ በደቡብ፡ ለሲዳሞ፡ ጮራ።
ሲሉ፡ ተቀኝተውላቸዋል።
ሊ.፡ ዤኔራል፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ በ1953፡ ዓ.ም.፡ በመከላከያ፡ ሚኒስቴር፡ ሚኒስትር፡ ዴታ፡ በነበሩበት፡ ወቅት፣ ስላርበኝነት፡ የአምስት፡ ዓመት፡ ታሪክ፡ ለቀረበላቸው፡ ጥያቄ፣ ያሰናዱትናቀ ከ50 አመት በኋላ ለ70ኛው የድል በአል መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ፣”የ1928—1933፡ ዓ.ም.፡ ዐርበኝነት፤ እንዴት፡ እንደተወጠነና፡ እንደተስፋፋ፡ የሚገልጥ።” በሚል ርእስ ለህትመት የበቃውን ባለ 12 ገጽ ጽሑፋቸውን መመልከት እጅግ ጠቃሚ ይሆናል። (ለተጨማሪ በወሌ፡ ነጋ የተዘጋጀውና የ1928-1933፡ ዓ.ም፡ ዐርበኝነት፤ እንዴት፡ እንደተወጠነና፡ እንደተስፋፋ፡ የሚገልጥ። (ሚያዝያ፡ 27፡ ቀን፣ 2003፡ ዓ.ም)” በሚል ርእስ ”የሚያዝያ፡ 27፡ ድል፡ በዓል፡ መታሰቢያ” ይሆን ዘንድ ለንባብ የበቃው ስራቸውን ማየት ተገቢ ነው።)
የድርስት ሕይወታቸው
ከስራዎቻቸው እጅግ፡ ጥቂቶቹ፡ ብቻ፡ ለህትመት የበቁላቸው ሲሆን፣ ስለ፡ ታሪክም፡ ኾነ፡ ስለግዛት፡ ፍልስፍና፣ ስለ፡ ቀለምም፡ ኾነ፡ ስለ፡ ቋንቋ፣ ዐያሌ፡ ጽሑፎችን፡ ደርሰዋል። ተጽፈው፡ የተዘጋጁና ያለቀላቸው፤ ነገር፡ ግን፡ ገና፡ ያልታተሙ፡ ሌሎች፡ በርካታ መጽሐፎችም፡ አሏቸው። ያገር፡ ፍቅር፡ መዝሙሮችም የስራዎቻቸው አካል ነበሩ።
ማህበራትን ከማቋቋም እስከ መምራት
አገር አቀፍና የልማት ማኅበራትን፣ ድርጅቶችን፡ … አቋቁመዋል፤ ብዙዎቹንም፡ በሊቀ፡ መንበርነት፡ መርተዋል። ጥቂቶቹም፤
ጥንታዊት፡ ኢትዮጵያ፡ ሀገራዊ፡ የዠግኖች፡ ማኅበር፡ (ሚያዝያ፡ 1956፡ ዓ.ም.)፣ ሊቀ፡ መንበር፤ የይፋት፡ ልማት፡ ሕዝባዊ፡ ኅብረት፡ (ግንቦት፡ 10፡ 1960፡ ዓ.ም.)፣ ሊቀ፡ መንበር፤ የኢትዮጵያዊያን፡ ሀገራዊ፡ ሥልጡንሕዝባዊ፡ አንድነት፣ ሐምሌ፡ 1፡ ቀን፡ 1967፡ ዓ.ም.፣ ሊቀ፡ መንበር፤ (ሚያዝያ፡ 10፡ 1982፡ ዓ.ም.)፡ የጊዜያዊ፡ ከዋኝ፡ ምክር፡ ሊቀ፡ መንበር፤ የኢትዮጵያ፡ ዐውደ፡ ቀለም፡ (መስከረም፡ 24፡ ቀን፡ 1990፡ ዓ.ም.)፣ ሊቀ፡ መንበር። በ1954፡ ዓ.ም.፣ የኢትዮጵያ፡ እግር፡ ኳስ፡ ፌደሬሽን፡ ሊቀ፡ መንበር፡ በነበሩበት፡ ወቅት፣ ኢትዮጵያ፡ የአፍርካ፡ ዋንጫን፡ ለመጃመሪያ፡ ጊዜ፡ አሸንፋለች። በብፁዕ፡ ወቅዱስ፡ አቡነ፡ ባስልዮስ፡ ርእሰ፡ ሊቃነ፡ ጳጳሳት፡ ወፓትረያርክ፡ ዘኢትዮጵያ፡ ሠያሚነት፣ የኢትዮጵያ፡ ኦርቶዶክስ፡ ተዋሕዶ፡ ቤተ፡ ክርስቲያን፡ ሥጋዊ፡ አስተዳደር፡ ጉባኤ፡ አባል፡ ኾነው፡ ለጥቂት፡ ዓመት፡ አገልግለዋል። በሌሎች በርካቶችም እንዲሁ። አምባሳደርም ነበሩ።
ሽልማቶች
ከኢትዮጵያ፡ ንጉሠ፡ ነገሥት፡ መንግሥት፤
•ያርበኝነት፡ ሜዳይ፣ ጥር፡ 12፡ ቀን፡ 1937፡ ዓ.ም፤
•የቅዱስ፡ ጊዮርጊስ፡ የጦር፡ ሜዳ፡ ሜዳይ፣ ጥር፡ 12፡ ቀን፡ 1937፡ ዓ.ም፤
•የዳግማዊ፡ ምኒልክ፡ የመኰንን፡ ደረጃ፡ ሊሻን፣ መጋቢት፡ 12፡ ቀን፡ 1943፡ ዓ.ም፤
•የኢትዮጵያ፡ የክብር፡ ኮከብ፡ ታላቅ፡ መኰንን፣ ሚያዝያ፡ 27፡ ቀን፡ 1943፡ ዓ.ም፤
•የድል፡ ኮከብ፡ ሜዳይ፣ ሚያዝያ፡ 16፡ ቀን፡ 1948፡ ዓ.ም፤
•የዳግማዊ፡ ምኒልክ፡ ኮርዶን፡ ኒሻን፣ ሚያዝያ፡ 27፡ ቀን፡ 1958፡ ዓ.ም።
የውጭ፡ መንግሥታት፡ ከሸለሟቸው፡ ውስጥ፤
•ከስዊድን፡ መንግሥት፣ Kömmendor med stora av Kungl. Svärdsorden፥
የካቲት፡ 1952፡ ዓ.ም፤
•ከታላቋ፡ ብሪታንያ፡ መንግሥት፣ Knight Commander of the Victoria Order፤ 1957፡ ዓ.ም.፤ ይገኙባቸዋል።
ከባለቤታቸው፡ ከክብርት፡ ወይዘሮ፡ ከፈይ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ሰባት፡ ልጆች፡ ወልደዋል፤ ሦስት፡ የልጅ፡ ልጆችንም፡ አይተዋል።
ሊ.ጄኔራል፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ እንግሊዝ፡ አገር፡ 32፡ ዓመት፡ በስደት፡ ከቈዩ፡ በዃላ፣ ሚያዝያ፡ 8፡ ቀን፡ 1999፡ ዓ.ም.፡ ከባለቤታቸው፡ ጋራ፡ ወደ፡ ውድ፡ አገራቸው፡ ኢትዮጵያ፡ ተመልሰው፣ ዓመት፡ ከሦስት፡ ወር፡ አዲስ አበባ ተቀምጠዋል። ሐምሌ፡ 15፡ ለ16፡ አጥቢያ፡ 2000፡ ዓ.ም.፡ ዐርፈዋል።
የክቡር፡ ሊ.፡ ዤኔራል፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ቀብር፡ ሥርዐት፥ ሐምሌ፡ 19፡ ቀን፡ 2000፡ ዓ.ም፣ ዐዲሰ፡ አበባ፡ እመንበረ፡ ጸባኦት፡ ቅድስት፡ ሥላሴ፡ ቤተ፡ ክርስቲያን፣ ቤተ፡ ሰብ፡ ቤተ፡ ዘመድ፣ ወዳጅ፡ ወገን፣ ብዙ፡ ሕዝብ፡ በተገኘበት፣ ባርበኞች፡ ዐጀብ፣ በተዋሕዶ፡ ክርስቲያን፡ ሥርዐት፡ ተፈጽሟል።
ስም ከመቃብር በላይ ነው።
አዲስ ዘመን ኅዳር 28/ 2015 ዓ.ም