ቆፍጣናዋ የሠብዓዊ መብት ተሟጋች

የዘንድሮ የሴቶች ታላቁ ሩጫ ላይ ለመሳተፍ በተገኘሁበት ወቅት ነበር ክራንች የያዘች የመሮጫውን ቲሸርት ለብሳ ለመሮጥ የተዘጋጀች ሴት የተመለከትኩት። አካል ጉዳተኛ ናት ፊቷ ላይ ልበ ሙሉነት ይታያል። ማንም ሰው ፊቷን አይቶ ውስጧ የተሞላውን ጥንካሬ መመልከት ይችላል። ለሰው የሚጋባ አይነት የመንፈስ ጥንካሬን የተሞላች ናት። በአጋጣሚ አብራት የቆመችው ማርታ ደጀኔ የተባለች የሙያ አጋሬ ነበረችና ቀርብ ብዬ ተዋወኳት። የሆነ ጥንካሬ ከውስጧ ሞልቶ ፈሶ ፊቷ ላይ ይነበባል።

ይህችን ልበ ሙሉ ሴት አግኝቼ ማናገር ለእኔም ብርታት እንደሆነ ተሰማኝ። እውነትም ልበ ሙሉ ናት። የጠንካሮች ማሳያ የሆነችው ተጫዋችና ተግባቢ ሴት፤ ወይዘሮ ርግበ ገበረሐዋሪያ ትባላለች። የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ናት። ይህችን ለብዙዎች ተምሳሌት ትሆናለች ያልኳትን ሴት የሕይወት ተሞክሮ በዚህ መልኩ አዘጋጅቼዋለሁ።

ልጅነት

የተወለደችው በትግራይ ክልል እዳጋ ሀሙስ በተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ በ 1976 ዓ.ም ነበር። ከወይዘሮ ለምለም ገብረ እግዝአብሄርና ከአቶ ገበረሐዋሪያ ሐጎስ ሰባት ልጆች መካከል ሶስተኛዋ ልጅ ናት። ቤታቸው ውስጥ አራት ሴቶችና ሶሰት ወንዶች ልጆች ሲኖሩ ቤተሰቡ በፍቅርና በምግባር እንዲያድግ የወላጆቻቸው ከፍተኛ ጥረት እንደነበር ትናገራለች።

ሶስተኛዋ ሴት ልጅ ርግበ የሁለት ዓመት ህፃን በነበረችበት ወቅት በፖሊዮ ወረርሽኝ ምክንያት አካል ጉዳት ገጠማት። የአካል ጉዳቱም በቀኝ እግሯ ላይ ነበር። አሁን ላይ ስትንቀሳቀስ ድጋፍ ( ክራንች) እና የእግር ድጋፍ ትጠቀማለች።

የአራት ዓመት ህፃን እያለች መላ ቤተሰቡ ርግበ ለገጠማት የአካል ጉዳት ህክምናና የተሻለ እድልን ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ መጡ። የህክምና ሙከራዎች ከተደረጉላት በኋላ በቼሻየር ሆም የአካል ድጋፍ ተሰርቶላት እንደ ልቧ መንቀሳቀስ ስትችል ትምህርት ቤት ገባች።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በካቶሊክ ካቴድራል የሴቶች ትምህርት ቤት ውስጥ የተከታተለች ሲሆን ሁለተኛ ደረጃንም በዛው በካቴድራል ትምህርት ቤት ግን ከወንዶች ጋር ተቀላቅላ በመማር አጠናቀቀች።

የርግበ አባት በትምህርት የሚያምኑ በተለይም ርግበ ተምራ ትልቅ ደረጃ እንድትደርስ የበኩላቸውን ጥረት የሚያደርጉ ነበሩ። በወቅቱ ሁኔታዎች ለአካል ጉዳተኞች ብዙም ምቹ ስላልነበሩና እነሱን ማሳተፍ የሚችል ትምህርት ቤት ስላልነበር ባሉት ትምህርት ቤቶች ጉዳት አልባ ከሆኑ ተማሪዎች ጋር ታግሎ ለማስተማር የራሳቸውን ጥረት በሙሉ ማድረጋቸውን ትናገራለች።

እናቷ ለልጆቻቸው የኖሩ ለልጆቻቸው በሙሉ ድጋፍ የሆኑ ሲሆን ወንድም እህቶቿ ደግሞ ለሕይወቷ ማገር ሆነው አጠንክረው እንዳቆሟት ትናገራለች። አባትና እናቷ በመደበኛ ትምህርት ያለፉ አይደሉም፤ አባቷ በአግባቡ ለማንበብና ለመፃፍ የሚያስችል ጥቂት የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት አግኝተዋል ።

የርግበ አባት በትምህርት የገፉ ባይሆኑም እንኳን ልጆቻቸውን በማስተማር ረገድ አቻ የሌላቸው ናቸው። አባትየው በንግድ ሥራ ተሠማርተው የተሳካላቸው ሰው ስለነበሩ ለልጆቻቸው አስፈላጊውን ነገር በሙሉ እያሟሉ አኑረዋቸዋል።

ከአስራ ሶስት ዓመታት በፊት አባቷ እንደተለዩ የምትናገርው ርግበ ትልቅ ሰው ለመሆን፤ ስኬት ላይ ለመድረስ ግን አርአያ የሆኗት የጥንካሬ መለኪያዋ የእሷ ጀግና አባቷ እንደ ነበሩ ታስረዳለች።

ህፃናት ማግለልን መለየትን ባለማወቃቸው የተነሳ በትምህርት ቤት በነበረችበት ወቅት በተለይም በልጅነቷ ቦርቃ እንደ ልጅ ማደጓን ትናገራለች። እያደገች ስትሄድ ሰው የምታሳዝን ልጅ አይነት አድርጎ መመለክቱ ያስቸግራት የነበረ መሆኑን ታስረዳለች። አሁን ላይ ሰዎች የሚያሳዩትን ፊት በመረዳት የምታልፈው ይህች ሴት አካል ጉዳት ሕይወቷ ላይ ለውጥ የማያመጣ እስኪሆን ድረስ ግን ረጅም ርቀትን ተጉዛለች።

በራስ መተማመኗ አድጎ ሰዎች ትኩረታቸውን እሷ ላይ አደረጉ አላደረጉ የማይገዳት እስኪሆንበት ጊዜ ድረስ ማህበረሰቡ ለአካል ጉዳተኞች የሚያሳየው ፊት ይረብሻት እንደነበረም ትናገራለች።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች አዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብታ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች። በመቀጠለም በሶሻል ወርክ በማስተርስ ዲግሪ ለመመረቅ በቅታለች።

የሥራ ልምድና ሌላው የሕይወት ተሞክሮ

ለርግበ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አጠናቃ ወደ ሥራ ዓለም መግባት አልጋ በአልጋ እንዳልነበረ ትናገራለች። አካል ጉዳተኛ ሆኖ ሥራ ማግኘት እጅግ ፈታኝ ነበር የምትለው ርግበ ሰዎች ገና አቋሜን እንዳዩ ነበር እንደማልችል ያስቡ የነበሩት ብላለች። ከዛ በኋላ ግን ኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲስኤብሊቲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት የሚባል አካል ጉዳተኞችን ማካትት ላይ የሚሠራ እና ብቁ የሆኑ አካል ጉዳተኞችን መቅጠር የሚፈልግ ድርጅት ውስጥ ነበር የገባችው። በተቋሙም ሥሰራ በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ ጠለቅ ያለ እውቀት እንዲኖረኝ ሆነ የምትለው ኮምሽነር ርግበ ከዛ በፊት አካል ጉዳተኛ ነኝ እንጂ ስለ አካል ጉዳተኝነት በቂ እውቀት አልነበረኝም ትላለች።

በድርጅቱ የተለያዩ አካል ጉዳተኞችን ስታገኝ፤ የተለያዩ አይነት የአካል ጉዳት አይነቶች መኖራቸውን ስታውቅ ቀድሞ ከነበራት በላይ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የመስራት ፍላጎት እንዳደረባት ትናገራለች። በዚህም ምክንያት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብታ በሶሻል ወርከር ማስተርስ ትምህርት የመማር ፍላጎት ያደረባት።

ከዛ በኋላ አካል ጉዳተኞችን በማካተት ላይ የተለያዩ የማማከር ሥራዎችን በሯሷ ቢሮ መሥራቷን ትናገራለች። በመቀጠል አሜሪካን ኤምባሲ ውስጥ ለአራት ዓመታት በአካል ጉዳተኝነት አማካሪና የሰው ሀብት ሥራ ላይ መሥራቷን ታስታውሳለች። ከዚህም በተጨማሪ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ በቦርድ አባልነትና በሌሎች ሁኔታዎች አገልግላለች። በተለያዩ ጊዜያት በአካል ጉዳተኞች፣ በወጣቶች እና በሴቶች እንቅስቃሴ ላይ በንቃት በመሳተፍ ትታወቃለች።

አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር በመሆን እያገለግለች ትገኛለች።

ልበሙሉነት በርግበ አንደበት

እርሳስ ሲቀረፅ እየተቆረሰ ስል እንደሚሆነው ሁሉ አካል ጉዳተኝነት ይዞት የሚመጣው ተግዳሮት በራሱ ባለ ጉዳቱን ጠንካራ እንዲሆን ያደርገዋል፤ የምትለው ርግበ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ አካል ጉዳተኛ ሆኖ መኖር በጣም ከባድ ነው። እኔ በቤተሰብ በቂ ድጋፍ ተደርጎልኝ በጥሩ አስተዳደግና ትምህርት ታግዤ ማደጌ እድለኛ እድርጎኛል ብላ ታስባለች። ምንም እንኳን እሷ እድለኛ ብትሆንም ሁሉም አካል ጉዳተኛ በእሷ ሁኔታ አለማደጉ በርካታ ተግዳሮቶች እንዲኖሩት ማድረጉን ትናገራለች።

አካል ጉዳተኛ ሲኮን ሰዎች አትችልም ወይም አትቺይም ይላሉ። ለዛ ነው መቻልን ለሰዎች ለማሳየት የሚኬድበት ሂደት ቀረፆ አጠንክሮ ስል አድርጎ የሚያወጣው። ብቁ ለመሆን ልበ ሙሉነትን ለመረጋገጥ ተግዳሮቶችን መጋፈጥ ችሎ ማሳየት ትልቁ መሳሪያው ነው ትለናለች።

እንደ ርግበ ገለፃ ሴቶች ከወንድ እኩል መወዳደር ስላለባቸው ወንድ የተሻለ ይሠራል ስለሚባልም መቻላቸውን ለማሳየት የበለጠ አቅም ፈጥረው እጥፍ ሲሠሩ ነው ጎልተው የሚታዩት። የተሰጣቸው ቦታ ትንሽ ሲሆን ከፍ ብሎ ለመታየት እጥፍ መሄድ የግድ ይላል። አካል ጉዳተኛ ሴት ሲኮን ደግሞ ሶስት አጥፍም መጓዝ ሊጠይቅ ይችላል።

በዚህ ሂደት ውስጥ የምታደርገው ትግል ጠንካራ ሠራተኛ እንድትሆን ማደረጉን ትናገራለች። ሰዎች ያላቸውን አመለካከት ለማስቀየር በሚደረግ ጥረት ውስጥ ነው ጠንካራ ሠራተኛ መሆን የቻልኩት ትላለች።

“አሜሪካን ኤምባሲ ሥሰራ በነበረበት ወቅት፤ የነበረኝ አለቃ ስጠራሸ እሳቀቃለሁ የሚል አስተያየት ሰጥቶኝ ነበር። ነጮች የተሰማቸውን መናገራቸው ጥሩ መገለጫቸው ነውና ቢጠራኝ ቢያዘኝ ምንም ችግር እንደሌለ ተናገሬ እሱም የሚሰማው ነገር እንዲቀረፍለት ሆኗል ” የምትለው ርግበ ሰዎች እስኪያናግሯት የሚሰማቸው ስሜትና አናግረዋትና ሥራዋን ተመልክተው በአንዴ የሚቀየሩት ነገር ያስገርመኛል ትላለች።

የፍቅር ግንኙነት እስከ ትዳር

ከልጅነት ወደ ጉርምስና በሚኬድበት እድሜ፤ ሁሉም ልጆች ስለ ቁንጅናና ስለ ፍቅር ግንኙነት በሚያሰላስሉበት ጊዜ እሷ ይህ ጉዳይ አይመለከተኝም ብላ ትታው እንደቆየች ትናገራለች። ለዚህ ምክንያት ነው የምትለው ማህበረሰቡ ስለ ቁንጅና ያስቀመጣቸው መስፈርቶች ውስጥ እሷን የሚመስል ሰው ባለመኖሩ ነበር። በዚህም ለግንኙነት ያልተፈቀደላት አድርጋ አስባለች።

በየመጽሄቱ፤ በየፊልሙ፤ በየሙዚቃው ያሉ ቆንጆዎች ውስጥ እንደሷ አይነት አካል ጉዳተኛ ሰው ባለመኖሩ የልጀነት ትንሸ ልቧን ለፍቅር ግንኙነት ቦታ እንዳይኖራት ስትዘጋ ቆይታለች።

ከዛ በኋላ ግን ወጣት ወንዶች በእሷ መሳብ ሲጀምሩ ይሄ ነገር ይመለከተኝ ይሆን እንዴ? ብላ መጠየቅ ጀመረች። በይበልጥ ዩኒቨርሲቲ ስትገባ ቆንጆ እንደሆነች የሚነግሯት ሰዎች መብዛት ጀመሩ። በዛ

ላይ በባህሪዋ ሳቂታ፥ ተጫዋች፥ ብዙ ጓደኞች የነበሯት (ያሏት)፥ መልካም፤ ቆንጆ፤ ደግሞ ጎበዝ ተማሪ ነበረች። ርግበ ማህበረሰቡ ሲሰጣት ከነበረው የአስተሳሰብ ቅርፊት ውስጥ ራስዋን ፈለቅቃ ስታወጣ ነው የፈጣሪ ድንቅ ጥበብ መገለጫ መሆኗን ያመነችው።

የፈጣሪ ድንቅ ሥራ የሆነች ወብ ሴት እንደሆነች ማሰብ መጠንከር ከጀመረች በኋላ በመልካም የፍቅር ግንኙነት ውስጥ መግባቷን ትናገራለች። ከዛም እንደ ማንኛውም ሰው ጥሩ የፍቅር ጊዜን አሳለፋ ወደ ትዳር ገብታለቸ። ከትዳሯም ሁለት ልጆችን ያገኘች ሲሆን በዚህም በጣም መልካም ቤተሰብ ለመመስረት የቻለች እናት መሆኗን ትናገራለች።

ማህበረሰቡ አካል ጉዳተኞች ትዳር መመሥረት፣ ልጆችን መውለድና ቤተሰብ ማፍራት አይችሉም ብለው ማሰብ እንዳይኖርባቸው ለመናገር የሚሞክሩ፤ አካል ጉዳተኞችም ይህ ነገር ለእነሱ የተፈቀደ ስለማይመሰላቸው የሚተውት ጉዳይ መሆኑን መመልከት ይቻላል።

ማህበረሰቡ በተለይ ጉዳት አልባ ከአካል ጉዳተኛ ጋር ትዳር ሲመሠረት በፍቅር ግንኙነት የተጀመረው ለመርዳት እንደሆነ ማሰቡ ያስገርማል። አካል ጉዳተኛው ሠርቶ ቤቱን ማስተዳደር ተዋዶ ተፋቅሮ መጋባት የማይችል እንደሆነ መታሰቡ ይገርመኛል ትላለች።

በአብዘኛው ከቤትም ከውጭም ድጋፍ ያጣ ሰው በቀላሉ እንዲሰበር የሚያደርገው ይህን አመለካከት መሻገር የቻለችው አባቷ በኩራት ስለ ልጆቻቸው ማውራታቸው፤ የትም መድረስ የምትችል መሆኗን እየነገሩ ማሳደጋቸው የትኛውም እንቅፋት ከመንገዷ እንዳላቆሟት ትናገራለች።

በየመንገዱ፤ በተለያዩ ትላልቅ መድረኮች ላይ ሰዎች በትኩረት ይመለከቱኛል የምትለው ርግበ ሰው ካላየኝ ራሱ ምን ተፈጠረ ቢዬ እስከመገረም እደርሳለሁ ፤ ሲያየኝ የምሸማቀቅበት ምክንያት የለም።

ትዳርና እናትነት

ለኛ ለኢትዮጵያውያን ቤተሰብ ከመመስረት ከማግባት ከመውለድ የበለጠ እንደ ትልቅ ስኬት የሚጠቀስ ነገር አለመኖሩ የሚታወቅ ነው፤ ርግበም አካል ጉዳት መልካም እናት ጥሩ ሚስት ከመሆን አላገዳትም። ከባቢያዊ ሁኔታው በራሱ ከሚያመጣው ተፅእኖ በስተቀር በእናትነት ሂደት ውስጥ ይህ ነው የሚባል የከፋ ገጠመኝ እንደሌላት ትናገራለች።

በትዳራችን ውስጥ ማንኛውም አይነት ትዳር ሊገጥመው የሚችል ፈተና እየገጠመን ነው ትዳራችን የምንመራው የምትለው ርግበ በትዳሬ ከአካል ጉዳተኝነቴ ጋር በተያያዘ እንዲሰማኝ አንድም ቀን ሆኖ አያውቅም ትላለች። እንደ መታደል ሆኖ ቤተሰቦቼም የትዳር አጋሬም ወደ ፊት እንዳልፍ እንድሻገር የሚደገፉኝ በመሆናቸው ይህ ገጠመኝ የምለው ነገር ባይኖርም አካል ጉዳትና እናትነት በራሱ የሚፈጥረው ጫና ግን አለ ትላለች።

በሥራ ቦታ ያሉ ሰዎች መልካም ድጋፍ የቤት ውስጡንም ድጋፍ ጨምሮ እርግዝና ብዙም አስቸጋሪ ሳይሆንባት የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ይህች እናት ለወላጆቿ ጠንካራና የምታኮራ ልጅ፤ ለባለቤቷ መልካምና አቅም ያላት ሚስት፤ ለልጆቿ ደግሞ የምትሳሳ የምትመራ መልካም እረኛ የሆነች እናት ለመሆን በቅታለች።

በኮምሽነርነት ጊዜ

ርግበ በኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆነችው በኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደረገ ሹመት ነው ። በሠብዓዊ መብቶች ላይ ለመሥራት ከየትኛውም የፖለቲካ ተፅእኖ ነፃ የወጣ ሰው መሆን አለበት፤ የምትለው ርግበ በተቋሙ የሚሠሩ ሥራዎች ከአድሏዊነት የፀዱ ነፃ አእምሮን የያዙ ሰዎች ሊሠሯቸው የሚችሉ መሆናቸውን ታስረዳለች።

የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ለመሆን መጀመሪያ የሕዝብ ጥቆማ ይሰጣል፤ ከዛ በምልመላ ኮሚቴ ተቋቁሞ በሂደት አልፎ ሹመት ይሰጣል። በዚህ መሠረትም ርግበ በሹመት የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የዘርፍ ኮሚሽነር ከሆነች ሁለት ዓመት ተኩል ሆኗታል።

በሥራዋ ደስተኛ መሆኗን የምትናገረው ርግበ የምትወደውንና የምትፈልገው የሥራ ዘርፍ ላይ መሠማሯቷ አጅግ በጣም ደስተኛ እንዳደረጋትም ትናገራለች። መልካም የሥራ ባልደረቦች፤ ልትሠራው የምትፈለገውን ሥራ ለመስራት የሚያስችል ምቹ የሥራ አካባቢ ውስጥ መሥራቷ ለውጥ ያለው ሥራ እንደትሠራ ያደረጋት መሆኑን ትናገራለች።

የሠብዓዊ መብቶች መጠበቅ መከበርና መስፋፋት ላይ የሚሠራው ተቋሙ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ነው። በተቋሙ የተለያዩ የሠብዓዊ መብት ዘርፎች ይዞ የሚሠራ በመሆኑ የሠብዓዊ መብት ክትትልና ምርመራዎች፤ ውትወታዎችና ጉትጎታዎች በየዘርፉ የሚሠሩ መሆኑን ታብራራለች። በአጠቃላይ ለሰው ልጆች መሰረታዊ የሆነውን ሠብዓዊ መብት የማስጠበቅ ሥራ በሚሠራበት ተቋም የሯሷን ጡብ የምታስቀምጥ ጠንካራ ሴት መሆናን ታብራራለች።

አካል ጉዳተኛ ሴት ሆኖ አመራር ላይ መገኘት ብዙም ያልተለመደ ጉዳይ በመሆኑ ከፍ ያለው ቦታ ለአካል ጉዳተኞችም ለሴቶችም የተፈቀደ መሆኑን ማሳያ እንደሆነች ትናገራለቸ። አንዳንዴ የራስ ጥረትና ፍላጎት ያለበት፤ አንዳንዴ እንዲያውም የሆነን ቦታ በግድ ፈልፍሎ የመግባት ያህል ትግልን በሚጠይቅ ሥራ ሴት አካል ጉዳተኛን አመራር ቦታ ለማስቀመጥ።

የሴቶች የመብት ጉዳይ እየተነሳ የሴት አካል ጉዳተኞች ጉዳይ የሚዘነጋበት ሁኔታ መኖሩ እንደሚያስገርማት የምትናገረው ርግበ እሷ በሴቶች መብት ላይ በሰራቻቸው ሥራዎች ስለዚህ ጉዳይ ስታነሷ መኖርዋን ትናገራለች።

አካል ጉዳተኛ የሚታወቀው በልመና በችግር ይሆንና የመገረም መደነቅ ብሎም በጣም የማሞካሸት ወይም በተቃራኒው የማየት ነገሮች መኖራቸው እንደሚያስገርማት ታብራራለች። በሠራችበት ሁኔታ ሁሉ ችላ ማሳየትን ከፍ ማለትን መሞከርን መመሪያዋ አደርጋ ትኖራለች። ከዚህ ሁሉ ጀርባ ግን እዚህ ለመድረሷ የበርካታ ሰዎች ትከሻ መኖሩን ለእሱም የላቀ ክብር እንዳላት ትናገራለች።

የነገ ህልም

ለርግበ የእድሜ ዘመን ህልሟ ሰዎችን ማገልግል ብቻ ነው። ነገ ይሄን እሠራለሁ ይሄን አደርጋለው ብሎ ማውራት ሳይሆን በተገኘችበት ቦታ ሁሉ የሚጠበቀውን አገልግሎት መስጠት ነው። ሕዝብን ማገልገል በአገልግሎት ውስጥ መኖር ትፈልጋለች። የምትወክላቸውን ሴት አካል ጉዳተኞች ተምሳሌት መሆን ሌላው ህልሟ ነው።

ለርግበ እዚህ መድረስ የሌሎች ድጋፍ መሰላሉን እንዳወጣት ሁሉ እሷም ሌሎችንም የምትጎትት ሌሎችን ወደ ከፍታው ለማምጣት የምትጥር ሴት መሆን ህልሟ ነው። ለርግበ መኖር ትግል ነው ባይባልም፤ ታግሎ ማሸነፍ ከትግል በኋላ ወደ ከፍታ መራመድ ግን የሕይወት መስመሯ ነው፤ ሕይወት ለእሷ በበርካታ መልካም ሰዎች እጅ ወደ ከፍታ መውጣት፤ ይህ ሲባል ግን የሷ ብረቱ ጥረት ታክሎበት ሲሆን ህልሟ ያለችው ነገር ድምፃቸው ለታፈነና ድምጽ ለሌላቸው መሰሎቿ የስኬትን መንገድ መጥረግ ነው።

ያለማቋረጥ ባላት ችሎታ ለሁሉም አቅም መፍጠርን፤ የሌሎችን ድምፅ ከፍ ብሎ እንዲሰማ ማደረግ በየእለቱ የሚነሱትን ችግሮች እስኪቀረፉ ድረስና እድሜ እስከሰጣት ድረስ መታገል ህልሟ ነው። ብዙ ነገር ውስጥ መግባት በመሞከር ለእያንዳንዱ ጥያቄ ትርጉም ያለው መልስ ለመስጠት በመታገል ላይ መሆኗን ታብራራለች።

በመጨረሻም

“ብዝሀነት የሚለውን ሃሳብ ደምቆ እንዲታይ እፈለጋለሁ፤ ሁልጊዜ በሴቶች የመብት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገለሉ አሉ። በአካል ጉዳተኞች የመብት እንቅስቃሴ ውስጥ ተመሳሳይ ነው። ሁሉንም ፍላጎት አንድ አይነት እንደሆነ የማሰብ ነገርም ይታያል። ሁሉም በአንድነት ውስጥ ያለን መለያየት ማለትም በተለያየ ፍላጎትና ማንንት ያለው ሰው መሆን ተረድቶ የሁሉም ድምፅ እንዲሰማ ማድረግ ያስፈልጋል።

በእያዳንዱ የመብት እንቅስቃሴ ውስጥ አሳታፊ መሆን የግድ ነው። ይሄ አውቅልሃለውና የአውቅልሻለሁ አሠራር መቅረት አለበት። ለአካል ጉዳተኞች ራሳቸው ያውቃሉ፤ በዛ ውስጥ አካል ጉዳተኛ ሴቶች አሉ በየጉዳት አይነታቸው የተለያዩ ፍላጎቶች ያሏቸው ሰዎች አሉ ያንን መረዳት ያስፈልጋል።

ስንሰባሰብ የተለያዩ ልዩነቶችን መመልከት ያስፈለጋል። ሁሉም ስለ ራሱ መናገር የሚችልበት አቅም መፍጠር፤ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖር ማድረግ ግድ ነው። መንግሥት፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ ሚዲያ፤ ማህበረሰቡ በሙሉ አሳታፊ መሆንና አለመሆኑን ራሱን በመገምገም ማየት ይገባዋል ” ብላለች።

“የአሳታፊነት ጉዳይ ሲነሳ አንዱ ሰጪ አንዱ ተቀባይ የሆነ ማስመሰል፤ የችሮታ አይነት አስተሳሰብ መታየት የለበትም። መንግሥት አካል ጉዳተኞችን፤ ሴቶችን ማሳተፍ፤ ለአረጋውያን ሥራ መሥራትን እንደ ችሮታ ማሰብን ወደ ጎን በመተው መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማድረግ ተገቢ ነው ” ትለናለች።

የፅናት ተምሳሌት የአልበገርም ባይ እናት የሆነችው ይች ሴት በቀጣይም የአካል ጉዳተኞችን ችግር የተገነዘበ ማህበረሰብ እንዲፈጠር ጠንክራ የምትሠራ መሆኑን ትናገራለች። እድሜዋን ሙሉ አካል ጉዳተኞችን ማገለገል ስለነሱ መኖር ህልሟ ነው። ሴትነት ፤ አካል ጉዳተኝነት ከዓላማዋ ሳያናጥባት ትልቅ ደረጃ የደረሰች ሴት በቤተሰባዊ ሕይወትም ሆነ በስራ እንቅስቃሴ የተሳካላት ይችን አይነት የጥንካሬ ተምሳሌት አሁን ባለችበት የሠብዓዊ መብት የማስጠበቅ ሥራዋ ላይ የተሳካ ቁም ነገርና ለውጥ የሚያመጣ ስራ እንደ ምኞቷ እንድትሠራ ያድርግልን ብለን ተሰናበትን።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You