አስቸጋሪ ሰዎችን እንዴት መቀየር ይቻላል?

ብዙዎቻችሁ በዙሪያችሁ ባሉ ሰዎች ምክንያት ከምትፈልጉት መንገድ እየቀራችሁ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ሰዎች እየተነጫነጩባችሁ፣ እየተጨቃጨቋሁ፣ ሰበበኛ ሆነውባችሁ ሕይወታችሁን እየተቆጣጠሩት ሊሆን ችሏል። ምን አድርጌ ይህን ሰውዬ ልገላገለው የምትሉት ሰው ሊኖር ይችላል። ደግሞ ልትገላገሉት የማትችሉት ዓይነት ሰውም አለ። በጣም ረጅም ዓመት የፈጀው የዓለማችን ስለደስታ የተደረገ ጥናት ነው። እናም ጥናቱ የሰው ልጅን ደስተኛም፤ ስኬታማም የሚያደርገው የሚል ነው። ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ነው ይህን ጥናት ያደረገው። ከሰባና ሰማኒያ ዓመት በላይ የቆየ ጥናት ነው። አሁንም ጥናቱ እየተካሄደ ነው። የጥናቱ ውጤቶች ግን በየጊዜው ይፋ ይደርጋሉ።

የጥናቱ ውጤት ቁጥር አንድ የእኛን ደስታና መድረሻችንን የሚወስነው በዙሪያችን ካሉ ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ነው ይላል። በተለይ በትዳር ወይም በፍቅር ግንኙነት ያለን ሁኔታ የእኛን ደስታ ይወስነዋል ይላል ጥናቱ። ስለዚህ በዚህ ጥናት መነሻነት አስቸጋሪ ሰዎች በጣም ሲያልፉ መርዛማ ሊሆኑ ይችላሉ። ወይም ደግሞ ልናስተካክላቸውና ልንቀይራቸው እንችላለን። አስቸጋሪ ሰዎች ስንል ተጨቃጫቂዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በትንሽ ትልቁ ነገር የሚፈልጉ ሊሆኑ ይችላሉ። ወይ ደግሞ ሰበበኛ ሊሆኑ ይችላሉ። አልያ ደግሞ በማንኛውም ጉዳይ ላይ የእናንተ እንከን የሚታያቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። እንድታዝኑላቸው፣ እናንተ ፀፀት እንዲሰማችሁ የሚያደርጉ ሊሆኑም ይችላሉ። ብቻ አይምሯችሁ ውስጥ ትልቅ ቦታ ይዘዋል። ትንንሽ ሃሳቦች ሊሆኑ እኮ ይችላሉ። ግን ይቆጣጠሯችኋል።

አዘርግ የተባለ ደራሲ ‹‹ትንንሽ ሃሳቦች ሁሌም ትንንሽ ናቸው ግን ትልቁን ሃሳብ ይይዛሉ›› ይላል። እነዚህ ጨቅጫቃ ሰዎች ለደቂቃ ይሆናል የምታገኟቸው። ከእነዚህ አስቸጋሪ ሰዎች ጋር ከስንት አንዴ ይሆናል የምትደዋወሉት ወይም የምትገናኙት። ግን አዕምሯችሁን የሚቆሰቁስ ነገር ነግረዋችሁ ዞር ይላሉ። የሥራ ባልደረባ፣ ጓደኛ፣ የፍቅር ጓደኛ፣ ትዳር ውስጥ ሊሆን ይችላል ብቻ በሥራ፣ በትምህርት፣ በፍቅር ግንኙነት በማንኛውም ቦታ ላይ ልታገኟቸው ትችላላችሁ። ትልቁ ጥያቄ እነርሱን ይዘን እንዴት ወደ ዓላማችን እንጓዛለን?፣ ብንችል እንዴት አድርገን እንቀይር?፣ ካልቻልን እንኳን ከእነርሱ ተፅእኖ እንዴት እንውጣ?፣ እነርሱን በአስተሳሰብ በልጠን እንዴት እንዳይጫወቱብን እንዳርጋቸው? የሚለው ነው።

1ኛ. መጀመሪያ ራስህ ተቀየር

ለውጥ የሚጀምረው ካንተ ነው። ሰዎችን ለመለወጥ ስትነሳ በደንብ ማወቅ ያለብህ ነገር ሰዎችን የምትቀይራቸው አንተ ስትለወጥ ነው። አንተ ከእነርሱ በአስተሳሰብም፣ በስሜት ብስለትም በማንኛውም ጉዳይ መብለጥ አለብህ። የምትበልጣቸው ደግሞ ራስህ ላይ ከሰራህ ነው። ያለበለዚያ ነግረሃቸው፤ መክረሃቸው አይቀየሩም። ሰዎች ምክር አይሰሙም። ሰዎችን የሚቀይራቸው ተግባር ነው። አንተ ከተለወጥክ እያዩሁ ይለወጣሉ። ምን አግኝቶ ነው የተለወጥከው ፤ እንዴት እንደዚህ ሆነ ይላሉ።

ሕፃናት እንኳን የሚያስቸግሩትን ሰው ይሮጣሉ። ሁሉንም ሰው እኮ አያስቸግሩም። የሚሞላቀቁበት ሰው አለ። በሥርዓት የሚያስተናግዱት ሰው አለ። አስቸጋሪ ሰዎች እንደ ሕፃናት ናቸው። ማንን እንደሚያስቸግሩ ይመርጣሉ። አንተ ለማስቸገር የማይመች፤ ከፍ ያለ ማንነት ያለህ ሰው ከሆን አያስቸግሩህም። እንደውም እርሱ እንዴት ተለወጠ፤ እኔም ራሴን ልለውጥ ብለው ወደራሳቸው ማየት ይጀምራሉ። ከንግግርህ ይልቅ ተግባርህ ይገዛቸዋል። ታዲያ እንዴት አድርጌ ራሴን ልቀይር ካልክ መጀመሪያ ስሜታዊ መሆን አቁም። ምክንያታዊ ሁን።

ለምን እንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ሰዎች እንደሆነ ለማወቅ ሞክር። ሰዎች በተለያየ ምክንያት ፀባያቸው መጥፎ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በፊት የገጠማቸው መጥፎ አጋጣሚና ቁስል ሊኖርባቸው ይችላል። ከዚህ በፊት የገጠማቸው ችግር በሕይወታቸው አሁንም ደግሞ የሚፈጠር ሊመስላቸው ይችላል። ስለዚህ ሁልጊዜ ነገሮችን ይቃወማሉ። ሁሉንም ሰው ይገፋሉ። ለምን? እንደድሮው ላለመበደል። ራሳቸውን ለመከላከል ሲሉ መጥፎ ሊሆኑ ይችላሉ። ለሰዎች ጥሩ አመለካከት ላይኖራቸው ይችላል። ፍርሃት አለባቸው። ለራሳቸው የሚሰጡት ግምት በጣም ዝቅ ያለ ሊሆን ይችላል።

እነርሱ ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ወይም ከፍ የሚሉ የሚመስላቸው ሌሎችን አብረው ዝቅ ካደረጉ ነው። አንተ የፈለከውን ያህል ጥሩ ሥራ ልትሠራ ትችላለህ። አለቃህ ወይ የፍቅር ጓደኛህ በዙሪያህ ያሉ ሰዎች አይዋጥላቸውም። እንደውም ትንሿን እንከንህን አጉልተው ሊወቅሱህ ይፈልጋሉ። እነዚህ ሰዎች ውስጣቸው ሞልቶ የፈሰሰውን የበታችነት ስሜት የሚያረኩት አንተን በመተቸት ነው። አንተን በመስደብ ነው። ዝቅ በማድረግ ነው። ስለዚህ ልትረዳቸው ይገባል። እኔን ስለሚጠሉኝ ነው ብለህ አታስብ። ከእነርሱ አንፃር ነገሩን የምትረዳው ከሆነ ጥሩ ነህ ማለት ነው። በልጠሃቸዋል ማለት ነው።

ሌላው ደግሞ ‹‹ፐርሰናሊቲ ዲስኦርደር›› ሊሆን ይችላል አስቸጋሪ ሰው ያደረጋቸው። ይህ በሳይኮ ቴራፒ ወይም በሳይካትሪ ባለሞያዎች የሚፈታ ችግር ነው። ስለዚህ አንተ ምንም ልታደርገው አትችልም። ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ችግር ኖሮባቸውም ልትረዳቸው ይገባል። አንድን ነገር በጥሩ ጥራት ልታየው የምትችለው ከፍ ብለህ ነው። በአስተሳሰብ የምትበልጣቸው እነርሱ ለምን እንደዚህ እንደሆኑ ማሰብ ስትጀምር ነው። ከዛ ግን ራስህን የምትለውጥባቸው መንገዶች አሉ።

2ኛ. አድማጭ መሆን

ከመናገር ይልቅ ማዳመጥ ኃያል ያደርጋል። ስትናገር የምታውቀውን ነው የምታወራው። ስታደምጥ ግን ብዙ አዲስ ነገር ወደ አዕምሮህ ታስገባለህ። እነርሱን ለመረዳት ሞክር። ከቻልክ መጨረሻ ላይ ተናገር። አንዳንዴ ከሰዎች ጋር ስናወራ እነርሱ እያወሩ እኛ የምናስበው ለእነርሱ ምን እንደምንመልስላቸው ነው። ልክ እንደጨረሱ እንዲህ እለዋለሁ ብለን ነው የምናስበው። ግን መልስ ማሰቡን ትተነው ምን እያለኝ ነው ብለን ለመስማት ብቻ ሳይሆን ለማድመጥ መሞከር አለብን። ‹‹እኔ በእርሱ ጫማ ብሆን ለካ እንዲህ ነው የማስበው›› ብለን ለመረዳት መሞከር አለብን።

የእውነት ጊዜ ሰጥታችሁ ስታደምጧቸው እነርሱ ምን ያስባሉ ‹‹እንዴ እንደዚህ ተረጋግቶ ያደመጠኝ ከሆነ እኔም አደምጠዋለሁ›› ይላሉ። አየህ! ሰዎች የምትፈልገውን የሚሰጡህ አንተ ቀድመህ የሚፈልጉትን ከሰጠሃቸው ነው። ሁሉም ነገር ጨዋታው ሰጥቶ በመቀበል ነው። ዝም በልህ የምትቀበለው ነገር የለም መስጠት አለብህ። ስለዚህ እነርሱ ትልቁ ረሃባቸው መደመጥ ነው። መከበር ነው። ስለዚህ ታደምጣቸዋለህ፤ ታከብራቸዋለህ።

እንደውም ከተናገሩት ውስጥ አንተ የምታደንቅላቸው ወይም የምትስማማበት ክፍል ካለ ቀድመህ ትነግራቸዋለህ። ‹‹በነገራችን ላይ ይህን ያልከውን ጉዳይ በደንብ እስማማበታለሁ፣ ጥሩ ሃሳብ ነው፣ አድንቄሃለሁ›› ልትላቸው ትችላለህ። ወይም በጣም እያደመጥካቸው እንደሆነ እንዲያስቡ ጥያቄ ልትጠይቃቸው ትችላለህ። ‹‹በነገራችን ላይ እዚህ ጋር ምን ማለት ፈለግህ ነው፤ ስለገረመኝ ነው የጠየኩህ›› ስትላቸው ‹‹ኦ! አክብሮኝ እያደመጠኝ ነው፤ ቦታ ሰጥቶኝ ነው›› ይላሉ።

በመጨረሻ አንተ ተናግረው ሲጨርሱ ካስጨረስካቸው በተራህ አንተ ስታወራ ትልቅ ቦታ ይሰጡሃል። ለምን? አድምጠሃቸዋል፤ ሰምተህ ጥያቄ ጠይቀሃቸዋል፤ ከዛ ውስጥ ደግሞ የምትስማማበትን እያደነክ ነግረሃቸዋል። ስለዚህ ረሃባቸውን አስታግሰኸል። ትጥቁን ይፈታል ያ ሰው። ሊከላከል፣ ሊሰድብና ሊያጠቃህ የነበረው ሰው ትጥቁን ይፈታና ለመስማት ክፍት ይሆናል። ያኔ አንተ የምታምንበትን ነገር ብትነግረው እንኳን የመቀበል እድሉ ሰፊ ነው። በዚህ መንገድ ነው የምትቀይራቸው። እስኪናገሩ የማታስጨርሳቸው ከሆነ፣ አንተ ለመመለስ ብቻ የምታወራ ከሆነ የቃላት ጦርነት ውስጥ ትገባለህ። ከዛ መሰዳደብ ትጀምራለህ። ቀንህን ሙሉ ያበላሹታል። እነርሱ ይቆጣጠሩሃል። ስለዚህ አድማጭ ሁን።

3ኛ. የሚፈልጉትን ነገር እውቅ

በማርኬቲንግ ‹‹መብሻውን አይደለም መሸጥ ያለብህ፤ ቀዳዳውን ነው›› ይባላል። ምክንያቱም ሰዎች አንተ ጋር መጥተው ነጋዴ ከሆንክ የሚገዙህ መብሻውን ወደውት አይደለም። ቀዳዳውን ፈልገው ነው። ስለዚህ ከሰዎች ጋር ስታወራ የሚፈልጉትን ነገር አስቀድመህ እወቅ። አየህ! አንዳንድ ሰው መደነቅ ሊወድ ይችላል። አንዳንዱ ደግሞ ስትስቅለት የሚወድ ሰው አለ። ሌላው ደግሞ በጣም መደመጥ የሚወድ ሰው አለ። አለቃህ ካዘዘህ ሥራ በተጨማሪ ሰርተህ እንድታመጣ ሊፈልግ ይችላል። ቤተሰብ ደግሞ ትእዛዙን እንደምታከብርለት ሊያይና ሊፈልግ ይችላል።

ስለዚህ አስቸጋሪ የምትላቸው ሰዎች ምን እንደሚፈልጉ ማወቅ ይኖርብሃል። ያኔ ነው የምትገበያየው። ያ ሰው የሚፈልገውን ነገር ከሰጠኸው አንተም የምትፈልገውን ነገር ከሰውዬው ትወስዳለህ። እነርሱ የሚፈልጉትን አውቀህ ስትሰጣቸው በእነርሱ አዕምሮ ውስጥ ያንተ ተፈላጊነት ይጨምራል። እርሱ እኮ ይረዳኛል፤ እኔ የምፈልገውን ነገር ያውቃል ለዚህ ሰው ያለኝን አመለካከት መቀየር አለብኝ ብለው ከራሳቸው ጋር መነጋገር ይጀምራሉ። ይህ የሚሆነው አንተ ከበሰልክና ራስህ ላይ ከሰራህ ነው። የሚፈልጉትን ነገር እንዴት ማወቅ እችላለሁ ካልክ አድማጭ ሁን። ስታደምጣቸው ንግግራቸውን ብቻ አይደለም። ሁኔታቸውን፣ የደረሰባቸውን ነገር፣ የሚያስጨንቃቸውን፣ ስቃያቸውን፣ የሚያሳስባቸውን ወይም ደግሞ በጣም የሚያስደስታቸውን ነገር ሁሉ ነው።

4ኛ. አንዳንዴ ተሸነፍላቸው

ከነዚህ አስቸጋሪ ከሚባሉ ሰዎች ጋር ያለህ ግንኙነት ቀጣይነት ካለው፣ ሁሌ በሕይወትህ በዙሪያ ያሉ ከሆኑ ሁልጊዜ ስለማሸነፍ አታስብ። ሁሌ ለማሸነፍ አትታገል። ተራ የሆኑና ቀላል ጉዳዮች ላይ ያንተ ሕይወት ላይ ብዙ ተፅእኖ የማይፈጥሩ ነገሮች ላይ ተሸነፍላቸሁ። ‹‹እሺ! ልክ ነህ በቃ፣ ሳስበው ያልከው ነገር ሳያስማማኝ አይቀርም›› እያልክ ተሸነፍላቸው። ለምን መሰለህ አስቀድመህ ነጥብ እያስቆጠርክ ነው። ‹‹ሊረዳኝ ይፈልጋል ማለት ነው፣ እኔ የምለውን ነገር ቦታ ይሰጠዋል ማለት ነው›› ብለው ያስባሉ።

እነርሱ አዕምሮ ውስጥ ያንተ ይህንን እሺ የማለት ነገር በበጎ ነው የሚታየው። ከዛ ነገ አንተ ወሳኝ ነገሮች ላይ ሃሳብህን ስትሰጥ ወይም ደግሞ አይ ይሄ ነገር ቢስተካከል ስትል ያደምጡሃል። ለምን? በትናንሽ ጉዳዮች ላይ ትናንት ተሸንፈህላቸዋል። በትልቁ ግን አሁን ታሸንፋቸዋለህ። ስለዚህ የረጅም ጊዜ ተፅእኖ ያላቸውን ነገሮች በጥበብ ለማሸነፍ ሞክር። ከሰዎች ጋር የሚኖርህን እያንዳንዱን ግንኙነት በስሌት አድርገው።

5ኛ. ድምበር ማስቀመጥ

አንዳንድ ሰዎች ድምበርህን ጥሰው ሊመጡ ይችላሉ። አስቸጋሪ ከመሆን ያልፋሉ። ከመጨቃጨቅ፣ ነገረኛ ከመሆን፣ ከሰበበኛነት ያልፉና መርዛማ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንዴ እጅ የሚቆረጠው ስለማይፈለግ አይደለም። በእጅ ላይ የወጣው ደዌ ወደሌላው የሰውነት ክፍል ተሰራጭቶ ጉዳት እንዳያስከትል ነው። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ከድምበር ሊያልፉ ሲሉ ማስቆም አለብህ። ድምበርህን ማወቅ አለብህ። እንዳትሰዳደብ፣ የቃላት ጦርነት ውስጥ እንዳትገባ፣ ስሜትህን እንዳያበላሹት ድምበርህን አስምረው።

እስከ ተወሰነ ደረጃ ልነጋገርና ላወራ እችላለሁ፤ ከዛ የሚያልፉ ከሆነ ግን ንግግሩን እቆርጠዋለሁ ማለት አለብህ። ከሕይወትህም ቆርጠህ ልታወጣው ትችላለህ። ምክንያቱም ለጤናህም ጭምር መርዛማ ሊሆኑ ይችላሉ። በየቀኑ ከእነርሱ ጋር በተጨቃጨክ ቁጥር ደምህ ከፍ፤ ስኳርህም ሊጨምር ይችላል። ብዙ ነገሮች ውስጥ ልትገባ ትችላለህ። ስለዚህ ከሆነ ነጥብ በኋላ ከእነርሱ ጋር ሙግትህን አቁም። በእነርሱ ሜዳ አትጫወት። መሰዳደብ አያዋጣህም። እነርሱ ሊረሱት ይችላሉ። አንተ ግን ልታብሰለስለው ትችላለህ። ስለዚህ ድምበር አስቀምጥ። ያለበለዚያ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን መቀየር ላንተ ከባድ ሊሆን ይችላል።

አስናቀ ፀጋዬ

 

አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You