አንድ ጋዜጠኛ ከዓመታት በፊት በማህበራዊ ገጹ የጻፈው ትዝብት ትዝ አለኝ።ሚዲያ ውስጥ ከመግባቱ በፊት በኢህአዴግ ዘመን በነበረው የመንግሥት ጉዳዮች ኮምኒኬሽን ይሰራ ነበር።እዚያ ሲሰራ ያጋጠመውን ነው የጻፈው፡፡
ወደ አርባ ምንጭ ለሥራ ይሄዳሉ።የሄዱት የመንግሥት ኮምኒኬሽን ለሚሰራው ጥናት ነው።በጥናቱ ማወቅ የተፈለገው መንግሥት በሚሰጠው የመሰረተ ልማት አገልግሎት የሕዝቡን ትክክለኛ የልብ ትርታ ማወቅ ነው፡፡
በየቴሌቭዥኑ እና ሬዲዮው የሚታየውና የሚሰማው ሕዝቡ በመሰረተ ልማት ያገኘውን አገልግሎት ሲያደንቅና ሲያመሰግን ነው።እዚህ ላይ ታዲያ አንድ ሀሜት አለ፤ ጋዜጠኛው ቀድሞ ‹‹እንዲህ ነው ማለት ያለባችሁ›› ብሎ ይነግራቸዋል የሚል ወቀሳ በየጊዜው የምንሰማው ነው።
ይህን ሀሜት የሚያውቀው የመንግሥት ኮምኒኬሽን ሰራተኛ (ጋዜጠኛ መባል ይችላል) ጋዜጠኛ መሆኑን ሳያሳውቅ እንደማንኛውም መንገደኛ ሆኖ ያገኘውን ሁሉ ይጠያይቃል።የተጠቀመውን ዘዴ ተጠቅሞ ስለመሰረተ ልማት ይጠይቃቸዋል።የሚነግሩት ሁሉ መንግሥትን ወቀሳ ነው።መንግሥት የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ እንዳላደረጋቸው ነው፡፡
በኋላ ጋዜጠኛ መሆኑን አሳውቆ ‹‹አሁን የነገራችሁኝን ምንም ሳትቀንሱ ንገሩኝ›› ብሎ ካሜራውን ደቀነ።የነገሩት ግን በተቃራኒው ነበር።መሰረተ ልማት እንደተሟላላቸው፣ መንግሥት ልማት ላይ ጠንክሮ እየሠራ እንደሆነ ነው የተናገሩት።ጋዜጠኛው እንደዚያ በሉ አላላቸውም፤ እንዲያውም እሱ የፈለገው ትክክለኛው ችግር እንድነገር ነበር፡፡
ሰዎቹ ካሜራ ፊት በተቃራኒው ለማውራታቸው ብዙ ነገር ሊባል ይችላል።የመንግሥትን ችግር የተናገረ ይታሰራል፣ የሆነ ጥቅም አያገኝም… ስለሚባል ፈርተው ነው ሊባል ይችላል። ወይም በየቴሌቭዥኑና ሬዲዮው የሚሰሙት አድናቆት ብቻ ስለሆነ በካሜራና መቅረጸ ድምጽ ፊት የሚወራው ምስጋና ብቻ ነው ስለሚመስላቸው ይሆናል፡፡
በነገራችን ላይ ይሄ ነገር በተደጋጋሚ ያስተዋልኩትና የታዘብኩት ነው።በሆነ ጉዳይ ላይ አስተያየት ስጠይቅ የሚነግሩኝ ያንን የተማረሩበትን ነገር አይደለም፤ በአብዛኛው መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚሰሙትን ነው። እንደዚያ በሉልኝ ስላላልኳቸው ‹‹ለምንድነው ያንን የተማረሩበትን ያልነገሩኝ›› ብየ ተገርሜ አውቃለሁ። ምናልባት መንግሥትን የወቀሰ እንዲህ ይደረጋል ሲባል ስለሚሰሙ ፈርተው ይሆናል።
ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ግን በግልጽ የመናገር ልማዳችን ደካማ ነው። ይህን ሁሉ ያስታወሰኝ ከትናንት በስቲያ (ሰኞ) በመንግሥት ሰራተኞች ማመላለሻ አውቶብስ (ፐብሊክ ሰርቪስ) ውስጥ የሰማሁት ሀሜት ነው።
ሁለት ሰዎች አንዲትን የመስሪያ ቤታቸው የበላይ አመራር ያብጠለጥላሉ።በወቀሳቸው ውስጥ፤ ተቋሙን የግል ካምፓኒዋ እንዳደረገችው፣ በማን አለብኝነት ‹‹አባርርሃለሁ!›› እያለች እንደምትናገር፣ በአጠቃላይ ፈላጭ ቆራጭነቷን ነው የሚያወሩት።
ሀሜቱን ስሰማ በውስጤ የመጡ ጥያቄዎች ‹‹እነዚህ ሰዎች ይህን ችግሯን ፊት ለፊት ነግረዋት ያውቁ ይሆን?›› የሚል ነው።በፍፁም አይመስለኝም።ምክንያቱም እንዲህ አይነት ሀሜት ከቅርቤ ጀምሮ ስለማውቅ ነው።ፊት ለፊት የመናገር ልማድ የለንም።በየካፌውና በመስኮቱ የምንንሾካሾከውን በባለቤቱ ፊት ግን በተቃራኒው አድንቀን ነው የምንናገር። ይሄ የአድርባይነት ባህሪ ነው። እወደድባይነት ነው። በተለይም የበላይ አመራር ከሆነ የተለየ ተወዳጅነትንና ተደናቂነትን ለማግኘት ነው፤ በዚህ ደግሞ የሆነ ጥቅም ያስገኝልኛል ተብሎ ይታሰባል ማለት ነው፡፡
በእርግጥ ይሄ የሀሜተኞች ችግር ብቻ አይደለም። የባለቤቶችም ችግር ነው፤ በግልጽ ሲነገረው ራሱን የሚያዞረው ብዙ ነው።እውነታው በግልጽ ከሚነገረው ይልቅ የድለላ አድናቆት ያሞቀዋል። በሽንግላ ሙገሳ የሚኮራ ብዙ ነው።
አንዳንድ አመራር ወይም ሰራተኛ እውነተኛ ነገር ሲነገረው የምርም ያኮርፍ ይሆናል፤ ሥልጣን ያለው ከሆነ ደግሞ ምናልባትም ተናጋሪውን ለመጉዳት ያስብ ይሆናል። እንዲህ አይነት ነገር ሀሜትን ማበረታታት ነው። ጠቃሚው ግን ፊት ለፊት የሚነገር አስተያየት ነው። ምክንያቱም ያ ባለሥልጣን ሲወደስና ሲሞካሽ ኖሮ ከሥልጣን የወረደ ዕለት የሚያበሻቅጠው ይበዛል፤ በዚያው ሞራሉ ይነካል።ትችትንና ወቀሳን የተላመደ ቢሆን ግን ምንም አይመስለውም።ስለዚህ ሀሜተኞችን በወቀስነው ልክ ግልጽ አስተያየትን የሚጠሉትንም ልንወቅስ ይገባል።
ሀሜት ልማዳችን ነው። የተማረው ክፍል ሊያስቀረውና ሊያሻሽለው ሲገባ እንዳለ እያስቀጠለው ነው። በቡና ላይ ወሬ ሀሜት የተለመደ ነው። በዚህ ልማድ በታዳሚዎች ውስጥ የሌለ ሰው ነው የሚታማ፤ አብሮ ያለ ሰው አይታማም። እንዲያውም በዚሁ ምክንያት ‹‹ጓደኛህ ሲታማ ለኔ ብለህ ስማ›› የሚባል አባባል ሁሉ አለን።‹‹ጆሮ ለባለቤቱ ባዕዳ ነው›› የሚባል ሌላ አባባልም አለ፤ የዚህ አባባል ትርጉም ደግሞ ሀሜት ስንታማ ጆሯችን የማይሰማ መሆኑን ለመግለጽ ነው። የሁለቱም አባባሎች መልዕክት ሀሜት ሰውየው በሌለበት የሚደረግ መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡
እንግዲህ ይህ በድሮው ዘመን የነበረ፣ዘመናዊ ትምህርት ያልነበረበትና በልማድ ብቻ የሚኖርበት ነው እንበል! አሁን በዚህ ዘመን ግን ስለግልጸኝነት፣ ስለሒስ እና ግለ ሂስ በትምህርትም በመድረክም እየተማርን እዚህ ደርሰን አሁንም ሀሜተኞች ነን።‹ ‹የተማረ›› ተብሎ ሀሜተኛ መሆን ደግሞ የበለጠ ነውር ነው።
በስነ ጽሑፍ ሙያ ውስጥ ‹‹ሂስ›› የሚባል ነገር አለ።በፖለቲካ ዘርፍ ደግሞ ግምገማ የሚባል ነገር አለ። በስነ ጽሑፍ ዘርፍ ሂስ ማለት ባለሙያም ሆነ ሌላ ታዳሚ የሚሰጠው አስተያየት ነው። የሰውየውን ስህተቶች መንገር ነው። ዳግም ሌላ ስህተት እንዳይሰራ ማስተማሪያ ማለት ነው፡፡
በፖለቲካም ግምገማ የሚባለው እንደዚሁ ነው። የሰውየውን ደካማ ጎኖች በግልጽ ከፊት ለፊቱ መናገር ማለት ነው። የሚነገረው እነዚያን ስህተቶች እንዳይደግም ነው፡፡
የታደሉት ሂስ ሲነገራቸው ደስ ይላቸዋል።በግልጽ የሚናገራቸውን ሰው ይወዳሉ። ያ በግልጽ የተናገረ ሰው ውስጥ ለውስጥ የሚያንሾካሹከው አይኖረውም። በውስጡ የሚያስበው አይኖረውም፡፡
ሀሜተኛ ግን ግልጽ አይደለምና ሌላ ተጨማሪ ሴራ ሁሉ ሊያስብ ይችላል። ለዚያ ለሚያማው ሰው ወጥመድ ሊያጠምድ ሁሉ ይችላል።እንዳለመታደል ሆኖ ግን በግልጽ ከሚነግረን ሰው ይልቅ እየሸነገለ የሚያሞካሸንን እንወዳለን። ይህ ሰው አይጠቅመንም፤ ወደ ወጥመድ ነው የሚወስደን፡፡
በተለይ ትንሽ ታዋቂነት ወይም ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ላይ ደግሞ ሀሜት ይበዛል። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ አድርባዮች የምንሆን። ታዋቂ ሰው የሆነ ነገር ቢጽፍ አብዛኛው ሰው የሚሰጠው አስተያየት ‹‹የኛ ጀግና›› የሚል ነው። ከልባቸው ለሚሉት ችግር የለውም፤ ዳሩ ግን እነዚሁ ሰዎች ሰውየን የሚወቅስ ሰው ሲያገኙ አብረው ነው የሚያብጠለጥሉት።
አንዳንዶች ላይ ደግሞ የምታዘበው አንድን ታዋቂ ሰው ወይም ባለሥልጣን አላገኘውም በሚል ይወቅ ሱታል፣ ይሰድቡታል። ሰውየውን የማግኘት ዕድል ሲያጋጥማቸው ግን ከማንም በላይ አድናቂው መሆናቸውን የሚናገሩ እነርሱ ናቸው።ሥራዎቹ ሁሉ እንከን የማይወጣላቸው አድርገው ነው የሚነግሩት።ይሄ አድርባይነት ነው። ይሄ ልማድ ቢያንስ በተማረው ክፍል ዘንድ ሊቀረፍ ይገባል፡፡
ታዋቂ ሰዎችና ባለሥልጣናትም በሽንገላ ከሚያቆለጳጵሳችሁ ይልቅ እውነተኛ ስሜቱን በግልጽ የሚነግራችሁን አመስግኑ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 28/ 2015 ዓ.ም