በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገነቡ ህንፃዎች ጥራትና ደህንነታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ምን እየተሰራ ነው? ግንባታቸውስ በምን መልኩ ክትትልና ቁጥጥር ይደረግበታል? ህንፃው ተጠናቆ የአገልግሎት ፈቃድን ካገኘ በኋላስ ለተገቢው ግልጋሎት እየዋለ ነወይ? የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ይዘን የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ስጦታው አካለ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ተግባርና ኃላፊነቱ ምንድነው ?
ኢንጂነር ስጦታው፦ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን በከተማዋ ውስጥ እንደማንኛውም አስፈፃሚ ተቋም ግንባታና ግንባታ ነክ የሆኑ ጉዳዮችን እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ የሚሰሩ አጠቃላይ መሰረተ ልማቶችን የሚያቀናጅ የሚቆጣጠር እና ከግንባታ ፈቃድ ጋር የሚገናኙ አምስት ዋና ዋና እና 29 ዝርዝር አገልግሎቶችን የሚሰጥ ተቋም ነው።
ተቋሙ በየጊዜው በአዳዲስ አደረጃጀትና መዋቅር እየተሻሻለ እየሰፋ የመጣ ነው። በ2014 በጀት አመት በአዋጅ 74/2014 ተግባርና ኃላፊነቱ ተሻሽሎ ለበርካታ ተገልጋዮች አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው።
አዲስ ዘመን፦ ተቋሙ በከተማዋ የሚገነቡ ህንፃዎችን ፈቃድ የሚሰጥ እንደመሆኑ የፍቃድ አሰጣጥ ሂደቱ ምን ይመስላል የሚለውን ቢያብራሩልን?
ኢንጂነር ስጦታው፦ የግንባታ ፈቃድ ለመስጠት የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። የግንባታ ፈቃድ የሚፈልግ አንድ ተገልጋይ ከመሬት ተቋም የተሰጠው ህጋዊ የሆነ የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ይዞ ይመጣል ። በተጨማሪም ሌሎች የእዳና እገዳ ሰርተፍኬት ከዛው ተቋም ያቀርባል። እነዚህ ከተሟሉና የተገልጋዩ ማመልከቻ አስካለ ድረስ የግንባታ ፈቃድ ይሰጣል። ፍቃዱ ከተጠየቀ በኋላ በቅድሚያ የማጣራት ስራ ይሰራል። ይህ ሲባል ቦታው ለምን አገልግሎት እንደተፈቀደ፤ የአካባቢው ፕላን ምን እንደሚመስል፤ የህንፃው ከፍታ እና ሌሎች ዲዛይንና ፕላንን በሚያጣጥም መልኩ ታይቶ የግንባታ ፈቃድ ይሰጣል።
ፍቃድ ከተሰጠ በኋላ የተሰጠውን ጊዜ እንዲያጠናቅቅ የጊዜ ገደብ ይቀመጣል። የጊዜ ገደቡ እንደየ ግንባታው አይነት ሊረዝምና ሊያጥር ይችላል። በተሰጠው የጊዜ ገደብ ግንባታው መከናወኑ የግንባታ ክትትል ይደረጋል። ክትትሉ ግንባታው በጥራት እየተካሄደ መሆኑን፤ በምህንድስናው ዘርፍ ባሉ ባለሙያዎች ሙያዊ ምዘና እየተደረገ በየደረጃው ይከናወናል።
የሲሚንቶ ሬሾ፤ የብሎኬት ጥራት፤ የስራ አካሄድ ሂደት፤ የባለሙያዎች ብቃትን በተቀመጠበት ቀን ልክ በፍጥነት እየሰራ መሆኑን በመከታተል ግንባታው እስኪያልቅ ይሰራል። በዚህ የክትትል ሂደት ውስጥ በተለይም የጥራት ችግር ሲያጋጥም ስራውን በማስቆም እርማት እንዲወሰድ ይደረጋል። ከዚህም ባለፈ ቅጣት የሚጣልበት ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ እገዳ ይደረጋል። በስህተት ጥራቱን ሳይጠብቅ ሾልኮ የተሰራ ግንባታ ከተገኘ በተለያዩ የላብራቶሪ ምርመራዎች ታይቶ ህንፃው እንዲፈርስ ይደረጋል።
መፍረስ ላይ ከመድረሱ በፊት የቅደመ ክትትል ስራ ይሰራል። አንድ መሀንዲስ ክትትል ሲያደርግ እለት እለት የሚሰራውን የግንባታ ደረጃ በማዘዝ ክትትል ስለሚያደርግ የግድ ካልሆነ በቀር የማስፈረስ ስራ አይሰራም። ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ ውስጥ ያሉ ያረጁ አደጋ ያስከትላሉ ተብለው የሚታሰቡ ህንፃዎች የማፍረስ ስራ ይሰራል። በዚህ መልኩ ነው እንግዲህ የግንባታ ቁጥጥርና ፍቃድ ተቀናጅተው የሚሰሩት።
አዲስ ዘመን ፦ ተቋሙ ይሄን ያህል የቁጥጥር ስራ ላይ ትኩረት አድርጎ በኃላፊነት ስሜት የሚሰራ ከሆነ በተለያዩ ጊዜ ፈረሱ፣ ተናዱ ጉዳት አስከተሉ ሲባል የምንሰማቸው ህንፃዎች በምን ምክንያት ነው?
ኢንጂነር ስጦታው፦ የትኞቹ ህንፃዎች ናቸው የተናዱት? መረጃው አለሽ? እኔ አንድ ያረጀ ህንፃ በመርካቶ ከመናዱ በስተቀር የማውቃቸው ቦታዎች የሉም። የመርካቶውም ቅርስ ነው ተብሎ እየተጠበቀ የቆየ ሲሆን ሌሎቹም ህንፃዎች በተገቢው መልኩ ካልተያዙ አደጋው የከፋ ሊሆን እንደሚችል ያስጠነቀቀ ነው። ይህ ህንፃ በተገቢው ላለመታየቱ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሊመለከተው ይገባ ነበር። ከእኛ ጋር የተያያዘ ግን የማውቀው የፈረሰ ህንፃ የለም።
አዲስ ዘመን፦ ይህ ህንፃ ፈርሷል አልፈረሰም በማለት ለመከራከር ሳይሆን ውዱን የሰው ህይወት የሚያስከፍለን አደጋ እንዳይከሰት በተባለው ልክ ትኩረት ስለመሰጠቱ እንዲያረጋግጡልን ጭምር ነው ይሄን ጉዳይ ያነሳሁት፤ ምናልባትም ህንፃውን በሚከታተሉት ባለሙያዎችና ሌሎች ላይ የሚታይ የስነምግባር ጉድለት ሊኖር ቢችልስ?
ኢንጂነር ስጦታው፤ የስነምግባር ጉዳይ ተቋሙም ትኩረት አድርጎ የሚሰራበት ጉዳይ ነው። ከአመራር እስከታች ሰራተኛ የሆነ ሰው ስለ ህንፃው ደህንነት የማይጨነቅ ሰራተኛ፤ ስለ ግንባታ የኮንክሪት ሬሾ የኮንክሪት ጥንካሬ የማይጨነቅ ከሆነ ህንፃው አደጋ ላይ ነው የሚሆነው። በተለይ ደግሞ ግንባታውን የሚያከናውነው ኮንትራክተርና አማካሪ ስለሚሆን ባለቤት ስለማይሆን እንደ ባለቤት ያለመጨነቅ ሁኔታ አለ። ይህንን እንደባለቤት የማይጨነቅ ኮንትራክተርና አማካሪ ተቋሙ ጠበቅ ብሎ በንፅህና ተከታትሎ አስፈላጊውን እርማት ካልሰጠ ለህንፃው አደገኛ ነው የሚሆነው። ስለዚህ የቁጥጥር ጉዳይ ምንም ድርድር ውስጥ አይገባም።
ይህ ሲባል ግን የስነምግባር ጉድለት የለም ማለት አይደለም። አልፎ አልፎ ይታያል። ይህ ግን በተደረሰበት ልክ እርምጃ የሚወሰድበት አካሄድ እየተሰራ ነው። አመራርም ቢሆን፤ ባለሙያም ቢሆን ይጠይቃል። በበጀት አመቱ ሩብ አመት ማለትም ባለፈው ሶስት ወር ከስራ የታገዱ የታሰሩ የተለያዩ የቅጣት እርምጃዎች የተወሰደባቸው አሉ።
በአዲሱ አዋጅ ላይ ክትትሉንም ቅጣቱንም ጠበቅ ያደረገ መመሪያ በመኖሩ ለብልሹ አሰራር የሚጋለጥበት እድል እየጠበበ ነው። ይህ ቢሆንም ግን ሾልኮ የተገኘ ጥፋት ተቆጠጣሪ ባለሙያው ላይ ብቻ ሳይሆን ኮንትራክተሩም ፍቃዱን እስከመንጠቅ የሚደርስ ቅጣት እየተወሰደ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ከስራው ስፋትና ስራውም ከሚያስከተለው የከፋ ጉዳት አንፃር ክትትሉ በቂ ነው ብለው ያምናሉ? ለቀጣይስ ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ምን ምን ተግባሮች መከናወን አለባቸው?
ኢንጂነር ስጦታው፦ ከላይ በበጀት ዓመቱ ሩብ አመት እርምጃ ተወሰደባቸው ያልናቸው ሰራተኞችና አመራሮች 39 ናቸው። እነዚህም ይህን የስነ ምግባር ጥሰት ሲፈፅሙ የተደረሰባቸው ናቸው። በሶስት ወራት ውስጥ ይሄን ያህል ቁጥር ያለው ሰው ካገኘን የሚቀጥለው ሩብ አመት ቁጥሩ ሊጨምርም ሊቀንስም ይችላል። ሰው እንዲጠየቅ ዋና አላማ አድርጎ ከመስራት ይልቅ ችግሩ እንዳይፈፀም በተለያዩ አይነት መንገዶች በመጠቀም ለመከላከል ጥረት ይደረጋል።
የተያዙት ግን ባልተገባ መንገድ ሌሎችን ለመጥቀም የሞከሩ ናቸው። ይሄ እንዳይኖር ብዙ የህግ ማእቀፎችን አሻሽለናል። ብዙ የሙስና ምንጮችን አድርቀናል። ብዙ ለብልሹ አሰራር የሚያጋለጡ አሰራሮችን ፈተናል፤ አርመናል እንዲሁም አዲስ መመሪያ አዘጋጅተናል። ደንብ አፅድቀናል። አዋጅ ተስተካክሏል። የተለያዩ የህንፃ እስታንዳርድ፤ የውጭ ማስታወቂያ እስታንዳርድ የህንፃ ቀለም እስታንዳርድ አዘጋጅተናል።
አዲሱ የህንፃ ወይም የግንባታ መመሪያን አስተካክለነዋል ፤አሻሽለናል። እነዚህ ሁሉ ለሙስና ምንጭ ነበሩ። አብዛኛው ሰው ይቸገር ነበር።አሁን ቀለል ተደርገዋል፤ ተገልጋይ በቀላሉ ገንዘብ ሳልሰጥ መስተናገድ አልችልም እንዳይል አድርገነዋል፤ አሁን ተገልጋይ ለሙስና ለመክፈል አይገደድም። ሲስተሙ አሁን ቀሏል ፤አብዛኛው ነገር በኦላይን ነው የሚስተናገደው፤ እዚህ ቢሮ ውስጥ ያለ አገልጋይ ከማንም ባለጉዳይ ጋር ሳይገናኝ ብቻውን ስራውን ሰርቶ መጨረስ ይችላል። ከዚህ ውጪ ኦላይን ሲስተም መጠቀም የማይችሉ ሰዎች አሉ፤ እንደገና ደግሞ ያልተገባ አገልግሎት ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ በዚህ መንገድ የተገኘ ግድፈት ሊሆን ስለሚችል ቁጥሩ ያነሰ መስሏል።
እነዚህን የህግ ማእቀፎች ከማዘጋጀታችን በፊት ከላይ ተቀጡ ያልናቸው ሙያተኞች በቀን ውስጥ ሊያዙ የሚችሉ ሊሆን ይችል ነበር። አሁን ግን ሰፊ ርብርብ በማድረግ አሰራሩን በዘመናዊ መልኩ ለመቀየር በመቻሉ መሻሻሎች ታይተዋል።
አንቺ ከመምጣትሽ በፊት የገባው ባለጉዳይ ይዟቸው ከመጣቸው ማስረጃዎች መካከል አንድ ፎርጅድ ሰነድ በማቅረቡ እጅ ከፍንጅ ተይዞ ፖሊስ ይዞት ሲሄድ ተመልክተሻል። ምንም አይነት ስህተት የማይሰራበት መንገድ ተፈጥሯል።
አዲስ ዘመን፦ተቋሙ ግንባታዎች ሲከናወኑ ምን ያህል ደህንነቱን የጠበቀ የግንባታ ሂደት እየተከናወነ ስለመሆኑስ ይከታተላል?
ኢንጂነር ስጦታው፦ የእኛ ተቋም የግንባታ ፈቃድ ሲፈልግ የሚረጋገጠውን አረጋግጦ ፍቃድ መስጠት፤ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ ደግሞ ሄዶ የግንባታ ጥራት፤ ማለትም በዲዛይኑ መሰረት እየተሰራ መሆኑ የቴክኒክ ስህተት እንዳይኖርበት እስከመጨረሻው ድረስ በመከታተል ህንፃው ሲጠናቀቅ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷል በማለት የመጨረሻውን የመጠቀሚያ ፍቃድ የመስጠት ኃላፊነት ነው ያለው።
ከዛ ውጭ ያሉ ደንብ መተላለፎች ሲኖሩ አይመለከትንም በማለት ከመተው ይልቅ ከደንብ ማስከበሮች ጋር በመሆን እርምጃ የሚወሰድበትን መንገድ እንፈልጋለን። እኛ ፍቃድ የሰጠነው ገንቢ መንገድ ላይ የግንባታ እቃውን አስቀምጦ የመንገድ ደህንነት ሰርአቱን ካስተጓጎለ ሊቀጣ ይገባል። ከደንብ ማስከበር ከአቅም በላይ ከሆነ የግንባታ ማስቆሚያ ይሰጠዋል፤ ስለዚህ ይህንን ለማድረግ የሚሞክሩ አይመስለኝም ግን ከአጠፉ ግንባታ እስከ ማስቆም እርምጃ ይወሰድባቸዋል።
ሌላው የግንባታ ደህንነት ጋር የተነሳው ለመመለስ ይህ የህንፃ ላይ ደህንነት በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ወደኛ ሀገር ስንመጣ አለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በሙሉ ለመጠቀም ሙከራ ይደረጋል። ክሬንና ሊፍትን ጨምሮ የተለያዩ ለደህንነት የሚጠቅሙ ቁሶችን መጠቀም ይችላሉ።
ይህ ቢሆንም ግን አደጋ አይከሰትም ማለት አይቻልም። አንዳንዴ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ሌላ ጊዜ ደግሞ በቸልተኝነትም ሊመጣ ይችላል። በኛ በኩል ግን የደህንነት መጠበቂያ ቁሶች ላይ ምንም አይነት ክፍተት እንዳይፈጠር ቁጥጥር ይደረጋል። ለምሳሌ ማንኛውም ሰው ሄልሜት ሳያደርግ፤ ሴፍቲ ሹዝና አንፀባራቂ ልብስ ሳያደርግ ወደ ግንባታው ቦታ እንዳይገባ ይደረጋል። ይህም አደጋ ቢደርስ የአደጋውን መጠን ለመቀነስ ይረዳል።
የህንፃ ደህንነት ግንባታው ውስጥ በሚሰሩ ሰራተኞች ብቻ ሳይሆን ግንባታው ያለበት አካባቢ ያሉ ቤቶች ላይ አደጋ እንዳያደርስ መከለያ የሚባል ግንባታው በመከለያ ተሸፍኖ እንዲሰራ ይደረጋል። ብዙ ጊዜ ብሎኬትና ሌሎች የግንባታ ቁሶች ወድቀው ሰው ላይና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ የሚደረግ ሲሆን ይህንን ሳያደርጉ የሚገነቡ አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፦ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ህንፃዎች ላይ እንደምንመለከተው ለአካል ጉዳተኞች መወጣጫ ተብለው የሚሰሩ የውልቸር መውጫዎች ተደርጓል ለማለት በሚመስል መልኩ ዲግሪያቸው ከፍ ያሉ ይሆናሉ፤ ሊፍቶችም ቢሆኑ አይነስውራን ሊጠቀሙባቸው የሚችሏቸው አይነት ድምፅ ያላቸው ሲሆኑ አይታዩም፤ የህብረተሰቡ ግማሽ ክፍል የሆኑ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ ህንፃ ከማስገንባት አንፃርስ ተቋሙ ምን ይሰራል?
ኢንጂነር ስጦታው፦ ህንፃዎች የህንፃ መጠቀሚያ ፈቃድ ሲሰጣቸው አንዱ ባፀደቀው ፕላን መሰረት ተጠናቀቀ ወይ? የሚለው ነው የሚታየው። የቀረበው ዲዛይንና ፕላን የሚፀድቀው ደግሞ አካል ጉዳተኛን ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑ እናረጋግጣለን። ለዚህም አንዱ ሊፍት ነው፤ ሁለተኛው የውልቸር መውጫ ከሊፍት ውጭ ያለ ደረጃ ነው። የዚህ ድግሪ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ በምን ያህል ድግሪ መሰራት አለበት የሚለው ተቀምጧል። የህንፃ መጠቀሚያ ፈቃዱ የሚሰጠውም ይሄው ተረጋገጦ ነው።
ሁለተኛው ከባለአራት ፎቅ በላይ ለሆኑ ህንፃዎች ጠቅላላ ሊፍት እንዲኖራቸው እናስገድዳለን። ሊፍት ሳይኖረውም የመጠቀሚያ ፈቃድ አይሰጠውም ማለት ነው። ሊፍቶቹ በህንፃው ስፋት መሰረት የሊፍት እስታንዳርድ ወጥቶለት ይሰራል። አካል ጉዳተኞችን ያማከለ ህንፃ እንዳይኖር ለማድረግ መመሪያው ላይ በጉልህ ተቀምጧል። አዲሱ መመሪያም ከዚህ በፊት የነበሩ አይነት ችግሮች እንዳይከሰት ምንም ክፍተት የሌለባቸው እንዲሆኑ እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፦ ካስፈለገ የውልቸር መወጣጫዎቹ የቆሙ ተራሮች የሚመስሉበት ህንፃዎችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፤ እነዚህ ያልናቸው ህንፃዎችስ በምን መስፈርት ነው ታዲያ የህንፃ መጠቀሚያ ፈቃድ የተሰጣቸው?
ኢንጂነር ስጦታው፦ እንደዚህ አይነት ህንፃዎች አሉ ከተባለ ያንን ህንፃ ሲቆጣጠር የነበረ ባለሞያ ፍቃድ የሰጠበት የራሱ ምክንያት ይኖረዋል። ወይ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ውስጥ ያለበት ይሆናል፤ ወይ ሌላ አማራጭ አስቀምጧል፤ ይህ ሲባል ምናልባትም በቤዝመንቱ በኩል ሊፍት ለአካል ጉዳተኛው ተዘጋጅቶ ሊሆን ይችላል፤ ምናልባትም አንቺ ያየሽው ለእቃ ማጓጓዣ የተሰራ ይሆናል። ለአካሉ ጉዳተኛ የሚሆን የውልቸር መወጣጫ ካልሆነም ፍቃድ አይሰጥም።
ይህን የምለው ሙሉ ለሙሉ ከችግር የፀዱ ህንፃዎች አሉ ላይባል ቢችልም ይህ ህንፃ በተገቢው መልኩ ሁሉንም ማህበረሰብ ያማከለ አገልግሎት ሳይሰጥ ለአገልግሎት ክፍት ያደረገው ባለሞያ መቼም ቢሆን ከተጠያቂነት አያመለጥም። ምንም ያህል ጊዜ ቢፈጅ ህንፃው ሳይገባው ከተፈቀደለት ከሀያና ሰላሳ አመታት በኋላም ሊጠየቅ ይችላል። የተባለው ሆኖ ቢገኝ ህንፃው ባለቤት አፍርሶ እንዲያያስተካክል ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- አንድ ህንፃ የአገልግሎት ፍቃድ ካገኘ በኋላ በትከክል ህንፃውን ለተፈለገው አገልግሎት እያዋለ ነው የሚለውን ትቆጣጠራላችሁ? ይህ ሲባል የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች አንዳንዴ ላልተሰሩበት አላማ ሲውሉ ይታያሉና ቁጥጥሩ እስከምን ድረስ ነው?
ኢንጂነር ስጦታው፡- ህንፃዎች ለተሰሩበት አገልግሎት ብቻ እንዲውሉ የመቆጣጠር ሀላፊነት የተሰጠው ለተቋሙ ነው። አንዱና ከሁሉ በላይ ትኩረት የሚሻው የህንፃ ቤዝመንቶች ለተፈቀደላቸው ለፓርኪንግ አገልግሎት ብቻ እንዲውሉ የማድረግ ቁጥጥር ይደረጋል። ነገር ግን የህንፃ መጠቀሚያ ፍቃድን ካገኙ በኋላ የተፈቀደለትን አገልግሎት በመተው ለጭፈራ ቤቶች፤ ለመጋዘኖች ሊውል ይችላል።
ህንፃዎች ሲለሙ ህንፃው ውስጥ አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ ተገልጋዮች መኪናቸውን መንገድ ዳር በማቆም ከተማይቱን ማጨናነቅ እንዳይኖር ያደርጋል። ፍቃዱም የፓርኪንግ መሰረተ ልማትን ላሟላ ህንፃ የሚሰጥ ነው። ፍቃዱን ከወሰደ በኋላ ግን መቀየር እንዳይችል በየስድስት ወሩ ህንፃው ኦዲት ይደረጋል። የቀየረ ካለ አጠቃላይ የህንፃው ባለቤት የንግድ ፍቃዱ ተነጥቆ ህንፃው ይታሸጋል።
ይህ ደግሞ ለንግድ ቢሮም በሚላክ ደብዳቤ የንግድ ፍቃዱም እንዲሰረዝ ይደረጋል። አሁን በተሻሻለው መመሪያ መሰረት ቅጣቱ ከፍ ተደርጓል። ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮች እንዳይደገሙ ቅጣትና ቁጥጥር እየተደረገ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፦ ፍቃድ አሰጣጡም ላይ ቀጣይ ቁጥጥሩም ላይ በብልሹ አሰራር የተነሳም የህንፃ ፓርኪንጎች ላልተገባ አገልግሎት ሊውሉ ይችላሉ። ከላይ እርምጃ እንደተወሰደ ቢነገርም አሁንም የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ከመኪና ማቆሚያነት ውጪ ለሆነ አገልግሎት የሚውልበት ሁኔታ ይታያል፤ ስለዚህስ ጉዳይ ምን ይላሉ?
ኢንጂነር ስጦታው፦ የብልሹ አሰራር ጉዳይ በአንድ ጊዜ ይስተካከላል ፤ይጸዳል የሚባል ጉዳይ አይደለም። ነገር ግን አሁን በሰራናቸው ሪፎርሞች ያሉ ችግሮችን ቀንሰናል፤ በዚህኛው አመትም ዜሮ ለማድረግ እየሰራን እንገኛለን። በዚህ ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙት የማያዳግም እርምጃ ይወሰድባቸዋል። የአሰራር ክፍተት ያለባቸውን የአሰራር ማሻሻያዎች እያደረግን እናስተካክለዋለን። ከአሁን በፊት የነበረው ፍቃድ አሰጣጥ ህግ ራሱ ለሌባ ምቹ ነበር። አሁን ያለው ግን ለባለሙያውም ጥሩ ነው።
በህገ ወጥ መንገድ ለሚሰሩት ምቹ የነበረበት ጊዜ አሁን ቀሎ ተገልጋዩ ቀላሉን መንገድ እንደጠቀም መብቱን እንዲያስከብር ህጉን እንዲያውቅ ይሰራል። ከዚህ ያለፈው ቅጣት ይጣላል። አሁን የአሰራር ስርአቱን በማዘመን ባለጉዳይና አገልጋይ ሳይገናኙ አገልግሎቶች የሚያገኙበት መንገድ እየተመቻቸ ነው።
ይህ ሲደረግ ባለጉዳይ መንገድ ላይ የሚያጠፋውን ጊዜ ይቀንሳል። ተሽከርካሪውን ይዞ መንገድ ሲያጨናንቅ አይታይም። ባለሙያ ጋር መጥቶ ደጅ አይፀናም። ዛሬ ነገ ከነገ ወዲያ በመባል የሚደረግ መመላለስ አይኖርም ። ኦላይኑ ላይም ስህተት እንዳይፈጠር የበላይ አመራሮች ይቆጣጠሩታል። አንድ ማመልከቻ መች እንደገባ ፤ በስንት ጊዜ ጉዳዩ መጠናቀቅ እንደሚኖርበት ይታያል፤ ተገልጋዩ ካልተስተናገደ ሲስተሙ ስለሚያመለክት በምን ምክንያት ሙያተኛው እንዳላስተናገደ በመጠየቅ ብቻ ስራው እንዲቀላጠፍ ያደርገዋል።
ፕላን ስምምነት፣ የግንባታ ፈቃድ፣ ክትትል እና መሰል አገልግሎቶችን በዚህ እየሄድን ነው። በተቻለ መጠን ካሉ 20 በላይ ዝርዝር አገልግሎቶች አብዛኞቹ በኦን ላይን ሲስተም አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፤ ህንፃዎች ሲገነቡ ቤዝመንቱ ለፓርኪንግ፤ የተወሰነው የህንፃ ክፍል ለቢሮና ለተለያዩ አገልግሎቶች፦ የተቀረው ደግሞ ለመኖሪያ ቤት እንዲሆን ቅይጥ አገልግሎትን የሚሰጡ ህንፃዎችን ለመገንባት መመሪያ ወጥቶ እንደነበር ይታወሳል።አሁን በዛ ልክ እየተሰራ ነው?
ኢንጂነር ስጦታው፦ አጠቃላይ በከተማዋ የሚገነቡ ትላልቅ ህንፃዎች ላይ የቅይጥ አገልግሎት የሚሰጡ ህንፃዎችን ለማድረግ ፕላን ህጉ ይፈቅዳል። በፕላን ህጉ መሰረት ማስፈፀም ደግሞ የተቋሙ ኃላፊነት ነው። በተለይም መሀል ከተማ የሚባሉ አካባቢዎች ላይ ቅይጥ የተባሉት አይነት ህንፃዎች እየተገነቡ ነው።
ቤቶቹ መኖራቸው የከተማዋን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል። ህንፃዎቹ በሙሉ ልክ እንደመኖሪያ አፓርትመንት በመሆን በራሳቸው የንግድ ውድድር መሰረት ተወዳድሮ መከራየት ለቻለ በሙሉ በማቅረብ ይሰራል።
አዲስ ዘመን፦ የከተማይቱን ውበት ለመጠበቅ በሚል የህንፃ ቀለም ቅብ እስታንዳርድን ከማስጠበቅ አንፃር ተቋሙ ምን እየሰራ ነው?
ኢንጂነር ስጦታው፦ የህንፃ ቀለም እስታንዳርድ ከባለፈው አመት ጀምረን ጥሩ ውጤት መጥቶበታል፤ እስታንዳርድም ተዘጋጅቷል። ከተማዋን ከመዘበራረቅ ቆንጆ እይታን ለመፍጠር፤ ለደህንነትም፤ለውበትም ችግር ሆኖ የነበረውን የህንፃ ቀለም መዘበራረቅ እና ሌሎች ስሜትን የሚጎዱ ቀለማት ለማስቀረት እየተሰራ ነው።
በዚህ መሰረት ሞዴል የሆነ አካባቢን፤ ቀጥሎ ክፍለ ከተማን፤ቀጥሎ እንደ ከተማ ወደ አንድ በመምጣት ከተማዋ የራሷ ብራንድ እንዲኖራት፤ ከተማዋ በአለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅበት የራሷ አንድ ቀለም እንዲኖራት ነው እሳቤው። የሚረብሹ ጤናን የሚጎዱ በፀሀይ ጊዜ ለማየት የሚያስቸግሩ የመስተዋት ህንፃዎች እንዳይኖሩ ያደርጋል።
በእስታንዳርዱ የተመረጡለት ቀለሞች አንድ ሁለት ሶስት አይደሉም በርካታ ናቸው። ከእነዛ ውጪ ሰው እንዳይጠቀም እየተደረገ ነው። ለምሳሌ ግራጫ ቀለም ውስጥ ራሱ እንደ ክሬም ከለር፤ ላይት ግሬይና ከ20 በላይ የሆኑ አማራጮች ይኖሩታል።
እንደ ገንቢ ግንባታ ፍቃድ ሲጠይቅ መጨረሻ ላይ ህንፃው ምን መምሰል እንዳለበት ቀድሞ ይታወቃል። ግንባታ ፍቃድ ሲጠይቅ የወሰደው የፕላን ስምምነት ላይ የህንፃውን ከፍታ፤ በሩን፣ የመስታወት አይነቱን፣ቀለሙ ምን እንደሚመስል ቀድሞ ያስቀምጣል። የሚመርጠው ቀለም ለአካባቢው የተፈቀደው ቀለም ሲሆን ከአጎራባች ቀለም ኮዶች ጋር የሚጣጣመው ታይቶ የተጣጣመ ቀለም ይመረጣል። በአሁኑ ሰአት በርካታ የቀለም እስታንዳርዶች እየተሰሩ ነው ያሉት። ሞዴል አካባቢ የሆነው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ውስጥ ያለ አካባቢ ተጀምሯል ያም በጣም በጥሩ ሂደት ላይ ነው ያለው።
የከተማዋ ቀለም እስታንዳርድ ሲመረጥ ከስነልቦና ባለሙያዎች ጋር በመመካከር፤ የቀለም ባለሙያዎች፤ የኪነ ህንፃ ምሁራንን በማካተት ቀለሞቹ ነዋሪው ህዝብ ላይ ምንም ጫና እንደማይፈጥሩ ተረጋግጧል። አንዲት ከመቶ አመታት በላይ እድሜ ያላትን ከተማ በአንዴ መቀየር የማይቻል መሆኑ አሳቤ ውስጥ በማስገባት ከተማዋ ያላት ቀለም አይነት ሊለይ ተሞክሯል። በከተማዋ ያሉት ህንፃዎች ከስልሳ እስከ ሰባ በመቶ ድረስ በግራጫ የቀለም ክልል ውስጥ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
የህንፃ ቀለም እስታንዳርድ ሲቀመጥ የከተማዋ የአየር ሁኔታ፤ የአካባቢው የአፈር አይነት፤ የሙቀት መጠኑ ይታያል፤ መልከአ ምድሩ ምን እንደሚመስለ ታይቶ ቀለም ምርጫ ይወሰናል። በአጠቃላይ በብዛት በከተማዋ ያሉት ቀለማት ግራጫ ቀለም ውስጥ ያሉ ናቸው።
ለውጥ ሲመጣ ካሉ አሉባልታዎች የሚነሱት ለውጥን ከማይቀበሉ ሰዎች ነው እንጂ ከሙያተኞች ጋር የተወሰነ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ስለውበት ካነሳን የውጭ ማስታወቂያዎችስ በምን መልኩ ይመራሉ፤ አንዳንዴ ያለፈባቸው ማስታወቂያዎች ተለጥፈው ይታያሉ፤ ከከተማዋ ውበት አንፃር ያለው የውጪ ማስታወቂያ እስታንዳርድ እንዴት ይታያል?
ኢንጂነር ስጦታው፦ አንዱ የከተማዋን ውበት ከመጠበቅ አንፃር የተሰራው ነገር የውጭ ማስታወቂያን በህግ የመምራት ስራ ነው። ከዚህ ቀደም የውጭ ማስታወቂያ መመሪያ ተዘጋጀቶ በዚያ መሰረት የት አካባቢ በምን አይነት ደረጃ ያሉ ማስታወቂያዎች መሰቀል አለባቸው የሚል እስታንዳርድ ተቀምጧል። ከዚህ ቀደም የተሰቀሉ ሁሉም ማስታወቂያዎች በክፍለ ከተሞችም በወረዳም ደረጃ በርብርብ እየተነሳ ይገኛል።
አሁን ወጥ በሆነ መንገድ ተቋሙ እየፈቀደ ዘመናዊ በሆነ መልኩ እንዲሰቀል እየተደረገ ነው። በከተማዋ ዲጂታል እስክሪኖች እንዲበዙ ተደርገዋል። ቢልቦርዶችም ቢሆኑም ደረጃቸውን የጠበቁ ቢል ቦርዶች እንዲኖሩ ተደርጎ ከዛ ውጭ ያሉት በሙሉ ግን ይነሳሉ።
አዲስ ዘመን፦ ተቋሙ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያለበትን ተግዳሮች ቢገለፁልን?
ኢንጂነር ስጦታው፦ አገልግሎቱ ላይ ከአቅም በላይ የሆነው ችግር ህገ ወጥነት ነው። ይህን ከተማ በፕላን መምራት አለብን፤ በፕላን የማይመራ ከተማ ለነዋሪዎቹ ምቹ አይሆንም፤ ስለዚህ ህገወጥ ግንባታ ህገወጥ ያልተፈቀዱ የውጭ ማስታወቂያ ፍቃዶች ሌሎች ህገወጥ ተግባሮችንም ለመከላከል ህብረተሰቡም መረባረብ አለበት።
ከተማዋ የጋራችን እንደመሆኗ ሁሉም አካላት በጋራ የሚሰሩባት፣ በጋራ የሚኖሩባትና በጋራ የሚንከባከቧት ከተማ እንድትሆን መሰራት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፦ ውድ ጊዜዎን ሰውተው ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍላችን ስም አመሰግናለሁ።
ኢንጂነር ስጦታው፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ኅዳር 28/ 2015 ዓ.ም