ፋን ኢትዮጵያ ሕዳር 25 ቀን 2015 ዓ.ም በጂንካ ከተማ ባካሄደው የ8 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በክብር እንግድነት የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ፣ የደቡብ ኦሞ ዞን ከፍተኛ የሆነ እምቅ የአትሌቲክስ አቅም ያለው መሆኑን እንደተገነዘቡ ገልጸዋል፡፡
የደቡብ ኦሞ ዞን በተፈጥሮና በባህል የታደለና ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ ያለበት ከመሆኑም ባሻገር ከሃገር አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ሊያስጠሩ የሚችሉ ተተኪ አትሌቶችን ለማግኘት የሚያስችል የአትሌቲክስ እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ ይህን አቅም አውጥቶ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በመሆኑም መንግሥት በዞኑ ላለው የስፖርት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚከታተለውና አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ሚኒስትሩ የጠቆሙ ሲሆን፣ የዞኑ ነዋሪዎችም የተጀመረውን የማሕበረሰብ ስፖርት አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በበኩላቸው፤ ዞኑ በቱሪዝም ብሎም በአካባቢው ያሉትን ግዙፍ የስኳር ፋብሪካዎች ጨምሮ በግብርና ምርትም ከክልሉ አልፎ ለኢትዮጵያ ዋልታና ማገር የሚሆን ግዙፍ ሃብት ያለበት መሆኑን ጠቁመው በስፖርት በተለይም በአትሌቲክሱ ትልቅ ደረጃ ሊደርስ የሚችል እምቅ ሃብት መኖሩን ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ኦሞ ዞን በምስራቅ አፍሪካ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ርቀቶች በርካታ ስመ ጥር ተወዳዳሪዎች መፍለቂያ ከሆነው ሰሜን ኬኒያ ጋር የቅርብ ጎረቤት በመሆኑ “ትኩረት ሰጥተን ከሠራንበት በእኛም ሃገር በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ አያሌ አትሌቶችን ለማፍራት የሚያስችል ዕድል አለ” ብለዋል፡፡ ዞኑ በተለይም የሰሜን ኬኒያ አጎራባች ከሆኑት በእኛንጋቶም፣ ከዳሰነች፣ ከሐመር፣ ከቦዲ፣ ከሙርሲ በአጭርና በመካከለኛ ርቀት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊያስጠሩ የሚችሉ በርካታ አትሌቶችን ለማፍራት ትልቅ አቅም ያለው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በሩጫም ብቻ ሳይሆን በጦር ውርወራ፣ በውሃ ዋና፣ በእርምጃና በሌሎችም የስፖርት ዓይነቶች ጭምር ከፍተኛ እምቅ ሃብት የሚገኝበት መሆኑንም ዋና አስተዳዳሪው አመላክተዋል፡፡ በመሆኑም ከፋን ኢትዮጵያ ጋር ከተካሄደው ከዚህ ውድድር ጀምሮ የዞኑን ብሎም የሃገርን እምቅ የአትሌቲክስ ሃብት ለመጠቀም የሚያስችል ወርቃማ በር መከፈቱን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ከፍተኛ እምቅ ሃብት ባለበት የአትሌቲክስ ዘርፍም ሆነ በሌሎችም አትራፊ የሆኑ የዞኑ ሃብቶች ሁሉ ኢንቨስት ማድረግና ሃገርን መጥቀም የሚፈልግ ሃገር ወዳድ ባለ ሃብት ሁሉ ወደዞኑ በመምጣት ኢንቨስት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ለዚህም ዞኑ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግና ኢንቨስት ማድረግ ከሚፈልጉ ባለሃብቶች በሙሉ ትብብር ለመሥራት በቁርጠኝነት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋለል፡፡
በይበል ካሳ