የበርካታ ኮከብ አትሌቶች ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያን በርካቶች በዓለም አትሌቲክስ ውስጥ ባላት ግዙፍ ስም ብቻ ሊመለከቷት ይሻሉ። አትሌቶቿን ውጤታማና ስመጥር ካደረገው ምቹ የአየር ንብረቷ እና መልከዓ ምድሯ ጥቂት ሊቋደሱ የሚፈልጉ ጥቂት አይደሉም። ኢትዮጵያ ዓለም እና አህጉር አቀፍ ውድድሮችን በስፋት ብታዘጋጅ የብዙዎች መዳረሻ እንደምትሆን አስተያየት የሚሰጡም ቁጥራቸው ብዙ ነው። ነገር ግን ይህን ለማድረግ በኢትዮጵያ ያለው ምቹ ሁኔታ እጅግ አናሳ የሚባል ነው። ምክንያቱ ደግሞ እንደ ሀገርም ሆነ ስፖርቱ በሚመለከታቸው አካላት እየተደረገ ያለው ጥረት አናሳ በመሆኑ ነው።
የስፖርትን ያለማዘውተሪያ ስፍራዎች ማሰብ አይቻልም። ለስፖርት እድገት አስፈላጊ የሆነው ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል። እንደየደረጃው ከትንንሽ ሜዳዎች አንስቶ እስከ ኦሊምፒክ መንደሮች ለመገንባት ዓለም አቀፍ መስፈርትን ማሟላት ደግሞ መሰረታዊ ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ በርካታ ስታዲየሞች መገንባት ከጀመሩ ዓመታትን ያስቆጥሩ እንጂ እስካሁን ሊጠናቀቁ ግን አለመቻላቸው ይታወቃል። ባሉበት ሁኔታ ውድድሮችን እንዳያሰናዱም አስገዳጅ የሆኑ መስፈርቶችን ባለማሟላታቸው ለእገዳ ተዳርገዋል። በዚህም ምክንያት የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድኑ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን በሰው ሀገር ለማድረግ መገደዱ ይታወቃል። ከእግር ኳስ ባሻገር ባሉ ስፖርቶችም በተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟሉ ማዘውተሪያ ስፍራዎች ባለመኖራቸው ኢትዮጵያ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ እድል አላገኘችም።
በኢትዮጵያ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ከምትገኘው አፋር የተሰማው ዜና በዚህ ረገድ ኢትዮጵያን አንድ ርምጃ እንደሚወስድ ታምኖበታል። በአፋር ክልል እየተገነባ በሚገኘው የሰመራ ስታዲየም የመሮጫ መም የዓለም አትሌቲክስን መስፈርት በማሟላት ዕውቅና ማግኘቱ ተጠቁሟል። በክልሉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡመር ኢብራሂም የሰመራ ስታዲየም ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲኖረው እየተሰራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ የመሮጫ መሙ ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ መገንባቱን ተናግረዋል። የአትሌቲክስ ስፖርት የሚያካትታቸውን የሩጫ፣ ዝላይና ውርወራ ስፖርቶችን ማካሄድ የሚችል ዘመናዊ መም በስቴድየሙ መነጠፉን የቢሮው ሃላፊው ገልጸዋል። ይህንንም ከዓለም አቀፉ አትሌቲክስ በመጡ ባለሙያዎች በማስገምገም ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል። መሙ ሲነጠፍ ተሳታፊ የነበረው ባለሙያ ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ምስክር ወረቀት የተሰጠው ባለሙያ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የብሄር ብሄረሰቦች በዓል መከበር እውን እንዲሆኑ ካደረጋቸው ስታዲየሞች መካከል አንዱ የሰመራ ስታዲየም ነው። በ2009 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ስታዲየሙ በሶስት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ነበር የታቀደው። በ178 ሺህ 736 ስኩየር ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ስታዲየሙ፤ ግንባታው በተጀመረበት ወቅት 727 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ ነበር የተገለጸው። ከ30 ሺህ በላይ ተመልካቾችን እንደሚይዝ የሚጠበቀው ስታዲየሙ፤ የተለያዩ የስፖርት ዓይነቶችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀም ነው።የግንባታ ስራው በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ የሚከናወን ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ የተመልካች መቀመጫ፣ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ፣ የመሮጫ መም እንዲሁም ዋና ዋና የስታዲየም ስራዎችን ያጠቃልላል። በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የአሌክትሮ መካኒካል እና የፍሳሽ ማስወገጃ ስራዎችን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ የማጠቃለያ ስራዎችን ለማካተትም ነው ታቅዶ የነበረው። የስታዲየሙ ግንባታ ሲጠናቀቅም ለንግድና ለቢሮ አገልግሎቶች የሚውሉ የተለያዩ ክፍሎች ይኖሩታል።
ከተጀመረ ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረው የስታዲየሙ ግንባታ አሁን ከ80 ከመቶ በላይ መድረሱ ተጠቁሟል። በዚህም ተጨማሪ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የወጣ ሲሆን፤ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅም ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚጠይቅ ታውቋል። ይሁን እንጂ ስቴድየሙ አሁን ባለበት ቁመና ውድድሮችን ማከናወን ይችላል ተብሏል። የመሮጫ መሙ በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት መገንባቱ ደግሞ ከስታዲየሙ ስኬቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ተጠቁሟል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም