አካባቢው ነፋሻማና ቅዝቃዜውም አጥንት ሰብሮ የሚገባ የሚባለው አይነት ነው። በሰፋፊ ማሳዎች ላይ የለማ አዝመራ ይታያል። አዝመራው ቀልብን በእጅጉ ይስባል፤ ከስንዴ ማሳው ከፊሉ ቢጫ ሆኖ ይታያል፤ ይሄ ሊታጨድ የደረሰው ነው። የተቀረው ደግሞ አረንጓዴ ሆኖ በማሳው ላይ እየተዘናፈለ ይገኛል።
ሰፊውን ማሳ የተመለከተ በአይኑ የሚጠግብ ቢሆንም፣ የስንዴ ዘለላውን ጠጋ ብሎ የተመለከተ ደግሞ ይበልጥ ይጠግባል፤ ከዚህም ጥሩ ምርት እንደሚሰበሰብ መገመት ይችላል፤ በኢሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ጨፌዶንሳ ጉምቢቹ ወረዳ የሚገኝ የዱረም ስንዴ ልማትን በጎበኝንበት ወቅት የተመለከትነው የሰብል አዝመራ።
አካባቢው በዳቦ ስንዴ ልማት የታወቀ ስለመሆኑ በማሳዎቹ የሚታየው የስንዴ አዝመራ ምስክር ነው።
አርሶ አደሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ዱረም የተባለውን የፓስታና ማካሮኒ ስንዴ ዝርያ ማምረቱን ተያይዞታል። በወረዳው በ2014-2015 የምርት ዘመን ወደ 12ሺ500 ሄክታር መሬት ገበያ ተኮር ለፓስታና ማካሮኒ ግብአት በሚውል ዱረም የተባለ የስንዴ ዝርያ እንዲለማ ተደርጓል። ልማቱም የተሳካ መሆኑን በጉብኝታችን ካገኘነው መረጃ መረዳት ችለናል። በአርሶ አደሩ እየለማ ያለው ገበያ ተኮር ዱረም ስንዴ ማንጉዶ በሚል ይጠራል።
በኦሮሚያ ግብርና ምርምር የተለቀቀውን ይህን ዝርያ፣ አሊያንስ ባዮቨርስቲና ሲያት ጥምረት (CIAT) የተባለ ድርጅት ዝርያውን በማስተዋወቅና በማስገምገም ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ እገዛ ያደርጋል።
በድርጅቱ የሚደገፈው የስንዴ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪና ተመራማሪ ዶክተር ደጀኔ ካሳሁን እንደሚሉት፤ ድርጅታቸው ሀገር በቀል ዝርያዎችን ወደማሳ አውጥቶ ልማት ላይ እንዲውል በማድረግ ሲሰራ ቆይቷል፤ የተለያዩ አዳዲስ ዝርያዎች ዛሬ ጥቅማቸው በሚገባ ባይታወቅም በጊዜ ሂደት ግን ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ ግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የግብርና ሥራውን እያገዘ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ጨፌዶንሳ ጉምቢቹ ወረዳ ሀርቡ ሴፍቱ ቀበሌ ገበሬ ማህበር መተግበር ከጀመረ ሰባት ዓመት ሆኖታል። የልማቱ ሥራም አርሶ አደሩን ማዕክል ባደረገ መልኩ እንዲከናወን እየተደረገ ነው። አርሶ አደሩ ዝርያዎችን ወስዶ አይቶ የተሻለውን ዝርያ እንዲመርጥ ከተደረገ በኋላ በብዙዎች የተመረጠው ልማት ላይ እንዲውል ይደረጋል።
በዚሁ መሠረትም የማስመረጡ ሥራ እኤአ ከ2016 አስከ 2018 ድረስ የተከናወነ ሲሆን፣ እኤአ በ2019 ደግሞ መረጃውን የመተንተን ሥራ ተከናውኗል። ከዚህ ሂደት በኋላ ነው አሸናፊ የሆነው ዝርያ ተለይቶ ልማት ላይ እንዲውል የተደረገው። ዝርያውን የማስፋፋት ሥራ ደግሞ እኤአ ከ2020 ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል። በዚህ መልኩ ለፓስታና ማካሮኒ ግብአት የሚውል የስንዴ ልማት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፣ ጨፌዶንሳ ላይ እየተከናወነ ይገኛል።
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ጨፌዶንሳ ጉምቢቹ ወረዳ በአርሶ አደሮች ተመርቶ እየለማ ያለው ማንጉዶ የተባለው የፓስታና የማካሮኒ ግብት ስንዴ በክላስተር ደረጃ እየለማ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ደጀኔ፤ ልማቱ ሲጀመር ኩታገጠም (ክላስተር) ደረጃ ይደርሳል የሚል ግምት እንዳልነበርም አስታውሰዋል። የዘር ስርጭቱም ከአስር ኪሎ የበለጠ እንዳልነበርና በወቅቱም በዘር አቅራቢዎች አማካኝነት ለአንድ ሺ 500 አርሶ አደሮች ዝርያዎችን ማድረስ የሚል ዓላማ ተይዞ ነው ወደ ሥራ የገባው።
ዝርያውን የወሰዱት አርሶ አደሮችም ያመረቱትን ለሌሎች ለማስተላለፍ፣ በተጨማሪም በድርጅቱ የተማሩትን የአመራረት ዘዴ እንዲሁም ስለዘሩ ባህሪ ያገኙትን ሥልጠና ለሌሎች እንዲያካፍሉ ግዴታ መግባታቸውንም ዶክተር ደጀኔ ይናገራሉ። ከፓስታና ማካሮኒ የስንዴ ዝርያ በተጨማሪ በበሽታና በተለያየ ምክንያት ከምርት ውጭ ሆኖ የቆየውን የሽምብራ፣ የባቄላና ዳጉሳ ሰብል ልማቱ መልሶ እንዲለማ በፕሮጀክቱ ተካትቶ መከናወኑን ገልጸዋል።
በዚህ መልኩ ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው ሶስት ክልሎች 180ሺ አርሶ አደሮችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው፣ እቅዱ እስከ 203ሺ አርሶ አደሮችን ተደራሽ ማድረግ እንደሆነና ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚሳካ ገልጸዋል። አርሶ አደሮቹ ዘሩን ለሌሎች በማዳረስና በማሳቸው ላይም በስፋት በማምረት ልማቱን በማሳደግ ላይ እንደሆኑ አስረድተዋል።
የፓስታና የማካሮኒ ስንዴ ልማቱ ገበያ ተኮር ስለሆነ አርሶ አደሩ ለምግብ ፍጆታ ማዋል የሌለበት ስለመሆኑ ጎን ለጎን በሚሰጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለውጥ መምጣቱንም አመልክተዋል። በዚህ መልኩ ታግዞ ልማቱን ሲያከናውን ግን በሚመለከተው አካል የገበያ ትስስር ሊፈጠርለት ይገባል ብለዋል። ድርጅታቸው ገበያ ማፈላለግ ተልእኮው እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ በተቻለ መጠን አርሶ አደሩ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር እንዲገናኝ ለማመቻቸት ጥረት እንደሚያደርግም ነው የገለጹት።
እንደ ዶክተር ደጀኔ ገለጻ፤ በፕሮጀክቱ ከተሸፈኑት ኦሮሚያ፣አማራና ትግራይ ክልሎች መካከል የትግራይ ክልል በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የልማቱ ሥራ ተቋርጧል። ፕሮጀክቱን በማራዘም ሥራውን ለመቀጠል ታስቧል። በፕሮጀክቱ በተከናወነው የዱረም ስንዴ ልማት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ወደ 560 ሄክታር መሬት በዱረም ስንዴ ተሸፍኗል። ምርታማነቱ ላይም በተደረገ የናሙና ጥናት በሄክታር ከ60 ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።
ይህን የስንዴ ዝርያ በስፋት በማሳቸው እያለሙ የሚገኙት አርሶ አደር አበራ ገብሬ ፤የስንዴ ዝርያው በአካባቢያቸው የፓስታና ማካሮኒ ስንዴ የሚያለሙ አሉ የሚል ወሬ ከመስማታቸው በስተቀር በአካባቢው የተለመደ አይደለም። እርሳቸውም ሆኑ ሌሎች በስፋት ለዳቦ የሚሆን ስንዴ ነው የሚያለሙት። ከዛሬ ሶስት ዓመት ጀምሮ ግን ስለልማቱ ጥቅም ለአካባቢው አርሶ አደሮች ትምህርት መሰጠቱን ያስታውሳሉ።
እርሳቸውም ዝርያው ለፓስታና ማካሮኒ ግብዓት እንደሚሆን፣ ስለአመራረቱ፣ስለሚደረግላቸው ድጋፍና ክትትል ቢሾፍቱ ከተማ ላይ ሥልጠና አግኝተዋል። ምርታማነታቸው ከጨመረ ተጠቃሚነታቸውም በዚያው ልክ ከፍተኛ እንደሚሆን በሥልጠናው ወቅት ከተሰጣቸው ትምህርት መገንዘባቸውን ጠቅሰው፣ ከእርሳቸው ቀድመው ወደ ልማቱ የገቡ የአካባቢያቸው አርሶ አድሮች ያለሙትን ማየት መቻላቸው ፍላጎታቸው እንዲጨምር እንዳስቻላቸው ይናገራሉ።
አርሶ አደር አበራ ከማሳቸው የተወሰነውን ለዱረም ስንዴ ልማቱ ለሙከራ ሲያዘጋጁ ዘር በነጻ ተሰጥቷቸዋል። የባለሙያ ድጋፍና ክትትልም ተደርጎላቸዋል። ማርታማነቱም ጥሩ ሆኖ ስላገኙት በ2014-2015 የምርት ዘመን ከማሳቸው አንድ ሄክታር ተኩል በሚሆነው ላይ ዘርተው ምርቱን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ጥሩ ምርት እንደሚሰበስቡና ምርታቸው ለታለመለት ዓላማ ውሎ እርሳቸውም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አርሶ አደሩ ተስፋ አድርገዋል።
አርሶ አደር አበራ ዘር ለሚፈልጉም ዘሩን በመሸጥ በሚያገኙት ገቢም እየተጠቀሙ ነው። ቀደም ሲል ያመረቱትን ገበያ አውጥተው ሸጠው መጠቀማቸውን እንጂ ለትክክለኛው ዓላማ ስለመዋሉ እርግጠኛ እንዳልነበሩ ይናገራሉ። አንዳንድ ነጋዴዎችም ለዳቦ ግብዓት ከሚውል ስንዴ ጋር ቀላቅለው እየሸጡ መሆኑንም ማየታቸውን ገልጸዋል። ምርታቸው ለትክክለኛው ዓላማ እንዲውልና እርሳቸውም በተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፓስታና ማካሮኒ ከሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች (ፋብሪካዎች) ጋር ትስስር እንዲፈጠርላቸውም ጠይቀዋል።
አርሶ አደር ዘርፌ ጌታቸውም በፓስታና ማካሮኒ ስንዴ ልማት ተሳታፊ ናቸው። አርሶ አደሯ አንደነገሩን የአካባቢያቸውን አርሶ አደር በማየት በ2014-2015 የምርት ዘመን ነው ወደ ልማቱ የገቡት። ወደ ልማቱ ሲገቡም 10 ኪሎ ዘር በነፃ ተሰጥቷቸዋል። እሳቸው እንደሚሉት፤ ሰብሉ እስካሁን በበሽታ አልተጠቃም። ቁመናውና ይዞታው ጥሩ ሆኖ ነው ያገኙት። ወደ አራት ኩንታል ምርት እንደሚሰበስቡም ይጠብቃሉ።
አራት ልጆች ያለ አባወራ እያሳደጉ እንዲህ ባለው ልማት መሳተፋቸውን እንደ አንድ ስኬት የሚያዩት እማወራዋ አርሶ አደር የአሁኑን ውጤት ካዩ በኋላ በሰፊው ለማልማት አቅደዋል። ምርታቸውን ቀጥታ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች (ፋብሪካዎች) በመሸጥ ልማቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በግላቸው ጥረት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
የጉምቢቹ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አቡሽ አራጌ እንደሚሉት፤ አካባቢያቸው ለዳቦ በሚሆን ስንዴ አምራችነቱ ይታወቃል። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን ገበያ ተኮር የሆነ ለፓስታና ማካሮኒ የሚውል ዱረም ስንዴ ለማምረት የአርሶ አደሩ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ የአካባቢው ምርታማነት ከፍ እያለ መጥቷል።
በ2014-2015 የምርት ዘመን በአካባቢው ለተለያየ ሰብል ልማት ዝግጁ ከሆነው 48ሺ889 ሄክታር መሬት ውስጥ ወደ 12ሺ500 ሄክታር የሚሆነው መሬት ማንጉዶ በሚባለው የተሻሻለ ዝርያ ባለው ዱረም ስንዴ ተሸፍኗል የሚሉት ሃላፊው፣ የዱረም ስንዴን ማምረት በኩል የአርሶ አደሩ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ይገልጻሉ። በዘር የሚሸፈነውም መሬት እየሰፋ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አቡሽ፣ ለአርሶ አደሩ የማምረት ፍላጎትና የምርታማነት መጨመር ምክንያቱ አርሶ አደሩ ለመለወጥ ካለው ፍላጎት የመነጨ መሆኑን ያብራራሉ። ወደ ልማቱ ከመግባቱ በፊትም ያገኘው ሥልጠና ተነሳሽነቱን እንደጨመረው አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ማንጉዶ የተባለው የስንዴ ዝርያ በአካባቢው ላይ በስፋት ይታወቃል። ለእያንዳንዱ አርሶ አደር 10 ኪሎ ዘር በመስጠት የማዳረስ ሥራ እየተሰራ ነው። ዝርያውን በማባዛት መንግሥት ሳይጠበቅ በራስ አቅም ለመንቀሳቀስ ጥረት እየተደረገ ነው።
ወደፊት የዘር አቅርቦት ችግር እንዳያጋጥም ወረዳው የተለያዩ ሰብሎችን ነባር ዝርያዎች ለመጠበቅ የዘር ማቆያ (ሲድ ባንክ) በወረዳው ላይ አቋቁሟል ያሉት አቶ አቡሽ፣ ከነባር ዝርያዎች የፓስታና ማካሮኒ ግብዓት የሚውሉ የስንዴ ዝርያዎችም ይገኙበታል ይላሉ። ወረዳው እንዲህ ያለ ጥረት ቢያደርግም ጥበቃ የተደረገላቸው ዝርያዎች በህጋዊነት ባለመመዝገባቸው ከተለያዩ ሀገራት የሚገቡ ዝርያዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ከዚህ ቀደም ለሙከራ በአካባቢው የተመረተው ጌጃ የሚባል ነባር የስንዴ ዝርያ ናሙና ጣሊያን ሀገር ተልኮ ዝርያው ለፓስታና ማካሮኒ ግብአት ተፈላጊ እንደሆነ በጥናት ተረጋግጦ ወደሀገር መላኩን ያስታወሱት አቶ አቡሽ፣ ዝርያው ተበረታትቶ ምርቱ እንዲጨምር በማድረግ ተጠቃሚ መሆን እየተቻለ ትኩረት ባለመሰጠቱ እየተመረተ እንዳልሆነ ነው ያስረዱት። ነባር ዝርያዎችን ይዞ ከመቀመጥ ጥቅም ላይ የሚውሉበት መንገድ በመንግሥትና በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በኩል መመቻቸት እንዳለበትም አስገንዝበዋል። ለፓስታና ማካሮኒ ግብዓት ተብሎ እየለማ ያለው ስንዴ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ካልተደረገ ምርቱ ለምግብነት ፍጆታ መዋሉ የማይቀር እንደሆነ ገልጸዋል።
ላለፉት ሶስት ዓመታት በበጋ መስኖ የተጀመረው የስንዴ ልማት ለዳቦ ግብዓት የሚውለውን ስንዴ በሀገር ውስጥ በመተካት ዜጎችን ተጠቃሚ ከማድረግ በተጨማሪ ለግዥ የሚወጣውንም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማዳን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ይታወቃል። ለፓስታና ማካሮኒ ግብዓት የሚውለውን የዱረም ስንዴ ልማት ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልገውን የስንዴ ግብዓት ለማግኘት ፋይዳው ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር እንደ ሀገር ለተያዘው የስንዴ ልማት ፋይዳው ከፍተኛ ነው። በመሆኑም የዱረም ስንዴ ልማቱም ከመኸር ወቅት በተጨማሪ በበጋ ስንዴ መስኖ ልማትም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ከገበያ ጋር ተያይዞ የተነሳው ችግርን ለመፍታትም በትኩረት መሰራት ይኖርበታል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2015