የንግድ ሥራን ከተቀላቀሉ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል። ለሥራው ያላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አቋርጠው ንግዱን እንዲቀላቀሉ አድርጓቸዋል። ‹‹ወጣትነት ትኩስ ኃይል ነው›› እንደሚባለው በድፍረትና በይቻላል ስሜት የ9ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አቋርጠው የንግድ ሥራቸውን በሸንኮራ አገዳ አሀዱ ብለው ጀመሩ።
አፍላው የወጣትነት እድሜያቸው ከልብ ከመነጨው የንግድ ሥራ ፍላጎታቸው ጋር ተደምሮ የንግድን ጣዕም ለመለየት ጊዜ አልወሰደባቸውም። ሥራው በባህሪው ፈታኝና ውስብስብ ቢሆንም፣ የሸንኮራ አገዳ ንግዳቸው እንደ ሸንኮራው ጣዕም ጣፋጭ ሆነላቸው። በሸንኮራ አገዳ ንግድ ጀምረው በንግዱ ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን የበቁት የዛሬው የስኬት አምድ እንግዳችን አቶ ዲና ገዛኸኝ፣ የዲና ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት መስራችና ባለቤት ናቸው።
አቶ ዲና፤ ተማሪ እያሉ ጀምሮ ለንግድ ሥራ ልዩ ምልከታ እንደነበራቸው ያስታውሳሉ። በሸንኮራ አገዳ የጀመሩትን የንግድ ሥራ በወጉ መምራትና ማጣጣም በመቻላቸው ዛሬ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች በመሰማራት ስኬታማ መሆን ችለዋል። የሸንኮራ አገዳ ንግዱ የወለዳቸው የንግድ ስራዎች አንዱ ሌላውን እየወለደ የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን በቀላሉ ማቀላጠፍ እንዲችሉ በር እንደከፈተላቸውም ይናገራሉ።
በኦሮሚያ ክልል በቀድሞ አጠራሩ ባሌ ክፍለ ሀገር ጋሰራ ወረዳ ሸለል በምትባል ቀበሌ ገበሬ ማህበር ተወልደው ያደጉት አቶ ዲና፤ በአካባቢያቸው ከሚዘወተሩ ትናንሽና ትላልቅ የንግድ አይነቶች መካከል የሰንጋ ንግድ አንዱ እንደነበር ያስታውሳሉ። በወቅቱም በርካታ የጋሰራ ወረዳ ሰዎች በሰንጋ ንግድ ይታወቁ ነበር። ይህ ብቻ አይደለም፤ በሰንጋ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦች በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው፤ አንቱ የተባሉና በትክክለኛው የሕይወት መስመር ውስጥ ያሉ ስለመሆናቸውም ይታመን ነበር። እንደ አብዛኞቹ የአካባቢው ማህበረሰብ አባላት አመለካከት እርሳቸውም ለሰንጋ ነጋዴዎች ልዩ ምልከታ ነበራቸውና ልባቸው ሰንጋ ነጋዴ መሆንን አጥብቆ ተመኘ።
ምኞታቸውን እውን ለማድረግ ጊዜ ያልፈጁት አቶ ዲና፤ በሸንኮራ አገዳ ያጣጣሙትን ንግድ በአካባቢው ትልቅ ቦታ በሚሰጠው የሰንጋ ንግድ ሊደግሙት አሁንም አሀዱ ብለው ተነሱ። ይሁንና ሸንኮራ አገዳ ቸርችረው ያጠራቀሟት ትርፍ ሰንጋ መግዛት አልቻለችም፤ በዚህ ተስፋ አልቆረጡም፤ ወደ ሰንጋ ንግድ ሊያሸጋግረኝ ይችላል ያሉትን የበግና ፍየል ንግድ ጀመሩ። ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› እንዲሉ ሆነና ይህ የበግና ፍየል ንግዳቸው ውጤታማ ሆነና በሕይወታቸው ትልቅ ቦታ የሰጡትን የሰንጋ ንግድ መጀመር አስቻላቸው። በወቅቱ እርሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው ማህበረሰብ በሙሉ ትልቅ ግምት በሰጠው የሰንጋ ንግድ ሲሰማሩ የተሰማቸው ደስታ ጥልቅ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ወደ ሰንጋ ንግድ ያደሉት አቶ ዲና፤ ጥቂት የማይባሉ ውጣ ውረዶችን አልፈው እንዳሰቡት ሁሉ በሰንጋ ንግድም ውጤታማ መሆን ችለዋል። በአንድ ሺ 520 ብር መነሻ ካፒታል የተጀመረው የሰንጋ ንግድ በብዙ ትጋት፣ ጥረትና ቁርጠኝነት የስንዴ ዱቄት ንግድን ጨምሮ ወጪ ገቢ ንግድንም ማዋለድ አስቻላቸው።
አቶ ዲና፤ የመጀመሪያውን የቁም እንስሳት ንግዳቸውን የጀመሩት በአካባቢያቸው እጅግ የተጎዱ ከብቶችን ከአርሶ አደሮች በመግዛት ነበር። በወቅቱ የገዟቸውን ሰባት ከብቶች ጥሩ ጥሩ መኖ በማቅረብ ነብስ ዘሩባቸውና የሰንጋ ንግዱን ተያያዙት። በወቅቱም ያ ጅምራቸው ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ይታያቸው ነበር። ሰባቱን የደለቡ ከብቶች ይዘው ከሰላሌ ወደ አዳማ እጅግ አድካሚና አሰልቺ ጉዞ አድርገዋል።
ያኔ ሰንጋ የሚሸጠው አዳማ እንደነበር በማስታወስ ከብቶቹን እየነዱ ከሰኞ እስከ ሰኞ ይጓዙ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዲና፤ ጉዞው በእግርም በመኪናም እንደነበርም አጫውተውናል። ከሰላሌ አዳማ በትንሹ 330 ኪሎ ሜትር የሚያህለውን መንገድ በብዙ ትጋትና ጥልቅ ፍላጎት ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ተመላልሰው ነግደዋል። እጅጉን የሚመኙትንና የታላላቅ ሰዎች መለኪያ ነው ብለው ያመኑትን የቁም እንስሳት ንግድ መጀመር በመቻላቸው እጅግ ደስተኛ የነበሩት አቶ ዲና፤ ያሳልፉት ውጣ ውረድ ይበልጥ ብርታት ሆኗቸዋል።
ጥልቅ በሆነ ጉጉትና በከፍተኛ ድካም ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ተመላልሰው የነገዱት አቶ ዲና፤ ከአንድ አመት አጋማሽ በኋላ ለእንስሳት ንግዱ ምቹ በሆነችው አዳማ ከተሙ። ለሥራው በነበራቸው ከፍተኛ ጉጉት ተግተው መሥራት በመቻላቸው በወቅቱ ጥሩ ከብት አድላቢ ከሚባሉት ተርታ መሰለፍ ችለዋል። የእንስሳት ቁጥሩንም ከጊዜ ወደ ጊዜ በማበራከት 20፣ 30፣ 40 እያሉ ጥሩና ቀዳሚ የቁም እንስሳት ነጋዴ መሆን ችለዋል።
ንግድ ማለት ምን እንደሆነ የተረዱት አቶ ዲና፤ የሥራ ዘርፋቸውን በማስፋት ከቁም እንስሳት ንግድ ጎን ለጎን የእንስሳት መኖ አቅራቢ ሆኑ። ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ከብት አድላቢዎች የእንስሳት መኖ በማቅረብም ቀዳሚ የእንስሳት መኖ አቅራቢ ሆነዋል። በወቅቱ የቁም እንስሳት ንግዳቸው ጠንካራ መሰረት የጣለ በመሆኑ ለላኪዎች ያቀርቡ የነበረውን የቁም እንስሳት እርሳቸው በቀጥታ ወደ ውጭ ገበያ ማቅረብ ጀመሩ። በወቅቱም በአገሪቱ አሉ ከሚባሉ የቁም እንስሳት ላኪዎች መካከል አንዱ እርሳቸው እንደነበሩም ያስታውሳሉ።
የቁም እንስሳት ንግዱን አጠናክረው በመቀጠልም የውጭ ገበያውን በስፋት የመተዋወቅ ዕድል አገኙ። የተለያዩ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት የገቢ ንግዱንም መተዋወቅ ቻሉ። ወደ አገር ውስጥ ያስመጧቸው ከነበሩ ምርቶች መካከልም መኪና፣ የመኪና መለዋወጫና ሌሎችም ይገኙበታል። የወጪና ገቢ ንግዱን መስመር ማስያዝና ማጠናከር የቻሉት አቶ ዲና፣ ሌላ የንግድ ዘርፍ ማማተርን ደሞ ተያይዙት። የንግድ ዘርፉን በማጥናት ትኩረታቸውን ወደ ማኑፋክቸሪንግ በማድረግ ዲና የምግብ ማቀነባበሪያ ድርጅትን አቋቋሙ። ድርጅቱ የተቋቋመው የስንዴ ዱቄትን ጨምሮ ፓስታ፣ ማካሮኒና ብስኩቶችን ለማምረት ቢሆንም፣ ለጊዜው ዱቄት ብቻ እያመረተ ይገኛል።
ዲና የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በአዋሽ መልካሳ በ70 ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ አራት የተለያዩ ዘመናዊ ማሽኖችንም ይዟል። ከአራቱ ማሽኖች መካከልም ሁለቱ ስንዴ የሚፈጩ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በቆሎና ጤፍ መፍጨት የሚችሉ ናቸው።
‹‹ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማራሁት የቁም እንስሳት የወጪ ንግዱ እጅግ ፈታኝና ለኮንትሮባንድ የተጋለጠ በመሆኑ ነው›› የሚሉት አቶ ዲና፤ ለእንስሳት ልዩ ክብር ያላቸው በመሆናቸው ብቻ በርካታ ውጣ ውረዶችን እየታገሉ ላለፉት አስር ዓመታት ቀዳሚ ከሆኑት የቁም እንስሳት ላኪዎች መካከል አንዱ ሆነው ቆይተዋል።
ዘርፉ አሁንም ድረስ እጅግ ፈታኝ ችግሮች እንዳሉበት በመጥቀስ፣ የአገሪቱን የቁም እንስሳት ከአረብ አገራት ባለፈ ለአውሮፓ ገበያ ማቅረብ እንዳልተቻለ ይጠቁማሉ። አውሮፓውያኑ በሚፈልጉት ደረጃ እንስሳቱን ማቅረብ ባለመቻሉ ገበያው በአረብ አገራት ብቻ ተወስኗል የሚሉት አቶ ዲና፣ በአረብ አገራት ያለው የገበያ ሁኔታም በኮንትሮባንድ የተዋጠ መሆኑን ይገልጻሉ። የአረብ ሀገሮች እንስሳቱ በህጋዊ መንገድም ሆነ በኮንትሮባንድ መቅረባቸው ግድ የማይሰጣቸውና ሚዛን ውስጥ የማያስገቡ መሆናቸውን ይናገራሉ። የኮንትሮባንድ ንግዱ በህጋዊ መንገድ የሚነግደውን ነጋዴ ከማዳከም አልፎ እያሸነፈው መሆኑን ጠቅሰው፣ እሳቸው ሌሎች አማራጮችን ማሰብ እንዳስፈለጋቸው ነው ያጫወቱን።
አቶ ዲና የቁም እንስሳት ንግዱ እጅጉን የፈተናቸው ቢሆንም፣ ከእንስሳቱ መለየት አልፈቀዱም። ስለእንስሳት ንግዱና እንስሳት በቂ ግንዛቤ ያላቸው በመሆናቸው ዘርፉን በማስፋት ስጋ ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ እየተዘጋጁ ስለመሆናቸው ይጠቁማሉ። እንስሳት እያረቡ፣ እያደለቡ እሴት ጨምረው ስጋ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ናቸው፤ በአሁኑ ወቅትም ቄራ እየገነቡ መሆናቸውን ይገልፃሉ።
የእንስሳት መኖ አቅራቢ እንደመሆናቸውም ቃሊቲ ላይ በቀን 120 ቶን ወይም አንድ ሺ 200 ኩንታል የማምረት አቅም ያለው የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ገንብተዋል። ከእርሳቸው ባለፈም የእንስሳት መኖን ለሌሎች ያቀርባሉ።
እንደ አገር በቁም እንስሳት ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ይቻላል የሚሉት አቶ ዲና፤ መንግሥት በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት በተለያየ ጊዜ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር ያስታውሳሉ። ህገወጥ ንግዱ መቶ በመቶ ገበያውን ተቆጣጥሮት መቆየቱ ጠቅሰው፣ ችግሩን ለመፍታት ቀላል አልሆነም ይላሉ። አሁን ባለው የገበያ ሁኔታም እንስሳቱን በቁሙ ለውጭ ገበያ ከመላክ ይልቅ ስጋውን መላክ የተሻለ እንደሆነ በማመን ነው ቄራ ወደ ማቋቋም የገቡት።
የቁም እንስሳት ንግድ በአግባቡ መመራት ከቻለ ለአገሪቱ ከፍተኛ የዶላር ምንጭ መሆን እንደሚችል ጠቅሰው፣ መንግሥት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ያስገነዝባሉ። በተለይም ህገወጥ የቁም እንስሳት ንግድን ለመቆጣጠር መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን መከተል እንዳለበት ይጠቁማሉ።
እንደ አቶ ዲና ገለጻ፤ በቁጥጥሩ ሂደት አንደኛ ህገወጥ ንግድ አገርን የሚጎዳ ስለመሆኑ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፤ ሁለተኛ የእንስሳቱን እንቅስቃሴ መገደብና መከታተል፤ ሶስተኛ የቁጥጥርና የክትትል ስርዓቱን ዘመናዊ በማድረግ ህገወጦችን ከመስመር ማስወጣት ይገባል። ይህን ማድረግ ሲቻል አገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ያስችላል።
በቀን 2000 ኩንታል የስንዴ ዱቄት በሚያመርተው ዲና የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ፣ በእንስሳት እርባታና ማደለብ እንዲሁም በእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያው በድምሩ ለ333 ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩት አቶ ዲና፤ በቀጣይም ይህን ቁጥር ለማሳደግ እየሠሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት በአሁኑ ወቅት በአዋሽ መልካሳ አካባቢ ደረጃውን የጠበቀ ትልቅ ትምህርት ቤት እያስገነቡ ይገኛሉ። ከዚህ ባለፈም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ቁሳዊና የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉት አቶ ዲና፤ በተለይም መንግሥት ለሚያቀርባቸው ማንኛውም ጥሪዎች ምላሽ ለመስጠት ወደኋላ የማይሉ መሆናቸውን ይናገራሉ። በዚህም የተለያዩ የምስክር ወረቀቶችን አግኝተዋል።
በቀጣይም የተጀማመሩ ሥራዎችን ከፍጻሜ ለማድረስ እተጋለሁ የሚሉት አቶ ዲና፤ በተለይም ከብቶችን ከማርባትና ከማደለብ ከፍ በማለት ስጋ ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ እንዲሁም ስንዴን ከዱቄት ባለፈ ወደ ፓስታ፣ ማካሮኒና ብስኩት ማሳደግ እና የጤፍና የበቆሎ ዱቄትንም እንዲሁ እሴት በመጨመር ለማምረት አቅደው እየሰሩ ይገኛሉ። በሆቴል ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ፍላጎትና ዝግጁነት እንዳላቸውም ይናገራሉ።
‹‹በንግድ ሥራ ውስጥ እጅግ ፈታኝ የነበሩ ወቅቶችን በመቋቋም ዓላማዬን ማሳካት ችያለሁ›› የሚሉት አቶ ዲና፤ ማንም ሰው ጠንካራ፣ ታታሪና ትጉህ ከሆነ ምንም ነገር ቢጎረብጠው የተነሳበትን ዓላማ ማሳካት ይችላል በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ኅዳር 24/ 2015 ዓ.ም