የሸቀጥ ሱቅ ውስጥ እናትና ልጅ ይገኛሉ። በጠባቦ የሸቀጥ ሱቅ ውስጥ ብዙ ነገር አለ። መርፌ፣ ክብሪት፣ ሻማ፣ ሳሙና፣ እርሳስ፣ ከረሜላ፣ ዘይት ወዘተ በትንሿ ሱቅ ውስጥ ከሚገኙት መካከል ናቸው። የተከፈተው ሬዲዮ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን እየዘገበ ነው። እንደ ጨዋታው ሁኔታ የጨዋታው አስተላላፊ ጋዜጠኛ ድምጹን ከፍ ዝቅ እያደረገ አየሩን ተቆጣጥሯል። እናት በሱቁ ውስጥ ያሉትን እቃዎች የት እንደተቀመጡ ያውቃሉ። ታዳጊው ልጃቸው ደግሞ በእቃዎቹ ላይ የተጻፈበትን አንብቦ በመረዳት ከእርሳቸው የተሻለ ነው።
የበዙት እቃዎች መነሻቸው ቻይና መሆኑን ታዳጊው ልጃቸው ያውቃል። አልፎ አልፎ ደግሞ የሌሎች አገራት እቃዎችም አሉ። ጋዜጠኛው የሚጠራውን አገር ስም ልጃቸው የሚረዳው ከአገራቸው በሚመጣው እቃ ነው። ቻይና በዓለም እግር ኳስ መድረክ ላይ ስሟ ከፍ ብሎ አለመጠራቱን ልጃቸው እያሰበ ንግድና ስፖርት ሁለቱም ውድድር እንደሆነ ያብሰለስላል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሆነው ልጅ እናቱን፤ እማዬ ስፖርት እና ንግድ አንድ መሆኑን ታውቂያለሽ ብሎ ይጠይቃቸዋል። እናትም እንዴት አልክ ልጄ ሲሉ ይመልሳሉ። ልጅም እግር ኳስ ላይ ከምድባቸው አልፈው ወደ ቀጣይ ደረጃ ለመግባት እና በመጨረሻም ዋንጫው ላይ ለመድረስ ነው ይህን ያክል የሚለፉት፤ በንግድም እኮ ያመረቱት ምርት ገበያ እንዲያገኝ ድንበር ተሻግሮ ውጤታማ እንዲያደርጋቸው ነው የሚሰሩት። ለምሳሌ እኛ ሱቅ ውስጥ ባለው እቃ አሸናፊው ቢለይ ቻይና እንደ አገር አሸናፊ ናት ምክንያቱም የቻይና እቃ ሱቃችንን የሞላው ስለሆነ። ኳስም ወደ ዋንጫው ለመድረስ የሚደረግ ፉክክር ነው ንግድ ደግሞ ገበያውን ለመቆጣጠር የሚደረግ ፉክክር ነው። ሲል ማብራሪያውን ሰጠ። እናትም የልጃቸውን ማብራሪያ በጥሞና ካዳመጡ በኋላ እርሱስ ልክ ነህ ልጄ ሕይወት በጥቅሉ በፉክክር ውስጥ የተቃኘች ናት። እኛም በአቅማችን አጠገባችን ካለው ሱቅ ጋር ተፎካክረን ገበያ ለማግኘት ፈልገን አይደል የምንደክመው። ሁሉም የሚለፈው ተፎካክሮ ወደ ውጤት ለመድረስ ነው። ፉክክሩ ግን የራስን ጥቅም ለማስከበር በሚል በሌላው ላይ ወንጀል በመስራት የሌላውን መብት በመደፍጠጥ አይደለም። እግር ኳስ ሜዳው ውስጥ ዳኛው ባይኖር ምን ሊፈጠር እንደሚችል እስኪ አስበው። ተጫዋቾች ሊደባደቡ ሁሉ ይችላሉ። ፉክክር መኖሩ እንዳለ ሆኖ ረጅሙ መንገድ ፍሬያማ እንዲሆን ከመነሻው እስከ መድረሻው ፍትሐዊ የሆነ አሰራር አስፈላጊ ነው። ወደ ዓለም ዋንጫ መጥቶ ለመወዳደር በየደረጃው የሚደረገው ውድድር ፍትሃዊ ባይሆን፤ ዳኞች ጨዋታውን በፍትሃዊነት እንደሚዳኙ ተስፋ ባይደረግ፤ ወዘተ ውድድሩ ሊደረግ አይችልም። በማለት ልጃቸው በጀመረው መስመር ገብተው መልእክታቸውን አስተላለፉ።
ልጃቸው የእናቱን ሃሳብ በማድመጥ ላይ እያለ በምናቡ ከአንድ የዓለም ዋንጫ እስከ ቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ድረስ ያሉትን አራት አመታት አሰባቸው። በአራት አመት ውስጥ ዛሬ ከምድባቸው የወደቁ በቀጣይ ወደ ውድድር መድረኩ ተመልሰው ፍሬያማ ስራ የሚሰሩበት፤ ዛሬ ዋንጫ የበላ በሚቀጥለውም ለመድገም ጥረት የሚያደርግበት፤ በዓለም ዋንጫው መሳተፍ የሚፈልጉ ነገር ግን እድሉን ያላገኙ በቀጣይ ወደ መድረኩ ለመምጣት የሚሰሩበት ወዘተ አራት አመታት ናቸው። ተጫዋቾች ደግሞ በየክለቦቻቸው በሚያደርጉት ተሳትፎ ውጤታማነት ለብሄራዊ ቡድን ለመጠራት ብዙ የሚሰሩበት ነው። ከአንድ የዓለም ዋንጫ እስከ ቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ውስጥ እጅግ ብዙ ስራዎች ይሰራሉ። ተረኛው የዓለም ዋንጫ ደጋሽ አገር የሚነሳበትን ማናቸውም ጥያቄዎች እየመለሰ ድግሱን አከናውኖ በድል ለመጨረስ ጥረት ያደርጋል። ታላቅ ድግስ ነውና።
ድግስን ባሰብን ጊዜ፤-
1. ዝግጁ መሆን
አንዳንዱ ነገር በእቅድና በስራ የሚመጣ ነው። አንዳንዱ ነገር ሳይታቀድ ድንገት የሚሆን እና መሰረታዊ በሚባል ደረጃ የሕይወታችንን አቅጣጫም የሚቀየርም ነው። በሕይወት ላይ ያልተጠበቀ ሊሆን እንደሚችል በማሰብ አስቀድሞ ዝግጅት የሚያደርግ ሰው ምን ያህሉ ይሆን? ሰዎች በሰዎች የሚጎዱበት ዋናው ምክንያት የማይጠብቁ በመሆናቸው ነው። የሚጠብቁ ቢሆኑ አይጎዱም፤ ያልጠበቁት በሚሆንበት ሁኔታ ግን ለጉዳት ይዳረጋሉ። በኮቪድ ወቅት የነበረው አስቸጋሪ ነገር በሽታው ብቻ አልነበረም፤ በሽታውን ተከትሎ የመጡ ያልተጠበቁ ነገሮችም ይገኙበታል።
አርሶ አደሩ ወደ እርሻው ስፍራ ሲሄድ ግብ የሚያደርገው ያቀደውን ምርት ከማሳው ላይ መሰብሰብ ነው። ተማሪው ከትምህርት ቤት ሲሄድ ወደቤቱም ሲመለስ፤ ከመጽሐፍት ጋር ጊዜን ሲያሳልፍ ያለመውን ውጤት የራሱ ለማድረግ ነው። ነገር ግን በተጨባጭ የታሰበው ሳይሆን ሲቀር ሕይወት ላይ ጥሎ የሚያልፈው ጠባሳ ከባድ ይሆናል። አንዳንዴም በመነሻችን ላይ እንዳገኘነው ታሪክ እስከ ወዲያኛው የሕይወትን በር መዝጋት ይሆናል።
በመሆኑም በሌሎች ሰዎች ላይ የደረሰው አንድ ቀን በእኔ ሕይወት ውስጥ ቢደርስ ምን አደርጋለሁ ብሎ ራስን እየጠየቁ መኖር እጅግ ማትረፍ ነው። ዛሬ መልካሙን ለመያዝ ፍጠን፤ ነገር ግን ሕይወት ባልተጠበቀው አቅጣጫ መንገድን ሰርታ ብትጠብቀህ ወደ መልካሙ አቅጣጫ ሕይወትን ለመውሰድ አንድ እርምጃ ወደ መፍትሔው ለመቅረብ እንድትችል ያልተጠበቀው ቢሆን የሚል ዝግጁነት ይኑርህ።
መልካሙን ወይንም ምርጡን መጠበቅ እንዳለ ሆኖ ነገር ግን በተቃራኒው አስከፊው ሊመጣ እንደሚችል በማሰብ ዝግጁ መሆን ይገባሃል። ‘የምበላው አጣ ይሆን?’ ብለህ አስበህ በማታውቅበት ወቅት ወይንም ጓዳህ ተትረፍርፎ ባለበት ወቅት ሕይወት በተቃራኒው አቅጣጫ ሄዳ የምትገኝበት ጊዜ መጎዳት እንዳይሆን ሁሌም ለማንኛውም ነገር ዝግጁ መሆን አትራፊነት ነው።
መነሻው አንድ ነው
የጊዜ ቀለበት መነሻው ሁለት አይደለም፤ አንድ ነው። መነሻው አመታት አይደለም ሽርፍራፊ ሰከንድ ነው። አንድ ብለን መቁጠር ጀመርን። አንድ ብለን መቁጠር ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ወደኋላ በምናብ ብንሄድ ወራቱና ቀናቱ ትዝታ ሆነው ከኋላችን ናቸው። የዘመናችንን ታሪክ ለመስራት የተገለጡ አዳዲስ ቀናት ደግሞ ከፊታችን። በውስጣዊ ሰውነት በአዲስነት ለሚቀበለው ትርጉም የሚሰጥ። የለውጥ መንገድን የራሱ ላደረገ ሰው ትርጉም የሚሰጥ የጊዜ ቀለበት።
በዘመን መለወጫ ወቅቶች በአመቱ ውስጥ ሽልማት የተገባቸውን ለይቶ እውቅና የመስጠት ባህል እየተለመደ ያለ ባህል ሆኗል። በዘርፉ ላይ ጎላ ብለው የወጡና አስተዋጽኦ ያደረጉትን መርጦ የመሸለም ተግባር በአገራችንም በመላው ዓለምም የተለመደ ተግባር ነው። ሰዎች በአደባባይ የሚሸልሟቸው ወደ ደረጃው ከመውጣታቸው በፊት ራሳቸውን የሸለሙ መሆናቸውን አስበን እናውቅ ይሆን? ለራሳችን ከራሳችን በላይ የሚቀርብ ስለሌለ ራሳችንን ለመሸለም ማንም ሊቀድመን አይገባንም ብሎ የሚያምን ሰው የሚያደርገው። ለራስ ትርጉም በመስጠት የሕይወት ቅኝት ውስጥ የሚመዘዝ ሰበዝ።
አዲስ አመትን ለማብሰር የሰፈሩ ልጃገረዶች አበባይሆሽ ይላሉ። በየቤቱ ደጃፍ ሄደው እየቆሙ ዜማቸውን አሰምተው የሚሰጣቸውን እየተቀበሉ ከአንድ ቤት ወደ ሌላ ቤት የሚደረግ፤ ሁሌ የማይደረግ በልጅነት ወራት በጊዜ ቀለበት ውስጥ የሚሆን። ለልጃገረዶቹ ቤት ያፈራው ሲቀርብ እነርሱም በዜማ ምስጋናቸውን ያቀርባሉ። በጊዜ ቀለበት ውስጥ ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላኛው ምዕራፍ ለመሸጋገር ቆሞ ማመስገን የተገባ ነው።
በምን አወቅናቸው?
በዓለማችን ውስጥ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርገው ያለፉ ሰዎችን በምን አወቅናቸው ብለን እንጠይቅ። እከሌን በእዚህ አወቅኩት፤ እከሊትን በእዚህ አወቅናት ስንል የምናነሳው ተጨባጭ ውጤት አለ። ጋንዲን በሰብዓዊ መብት አወቅነው ለዊንስተን ቸርችልን ስለ ነጻነት በሄዱበት ርቀት፤ ማርቲን ሉተር ኪንግ ስለ እኩልነት በጉልህ የፊት ለፊት ሰው ሆኖ በከፈለው ታላቅ መስዋእትነት፤ ቢልጌት በቴክኖሎጂ አብዮተኛነቱ አወቅነው። እንዲህ እያልን ሌሎችንም መጥቀስ እንችላለን። እኒህ ግለሰቦች አንድ ግለሰብ ሆነው ሳለ ለዓለም ባበረከቱት አስተዋጽኦ የታወቁ ሆነው አገኘናቸው። እይታቸው ይዟቸው ከወጣበት ከፍታ ላይ ቆመው ዓለም አያቸው፤ ወደ ከፍታው ለመድረስ ያለፉበት መንገድ ትልልቅ መጽሐፍ ይወጣዋል።
ዛሬ ሰዎች እንዲያውቁን ከመድከም የጠራ እይታ ኖሮን፤ ተፈጽሞ ልናይ የምንወደው ሆኖ እንድናይ እንመላለስ። ዛሬ በማህበራዊ ሚዲያ ዘመን የሚከተሏቸውን ሰዎች ለማብዛት ትኩረት ሳቢ በሆነ እንቅስቃሴ የተጠመዱ ሰዎችን እናገኛለን። እኛም ከእነርሱ አንዱ ሆነን እንደሆነ በፍጹም አንድከም፤ ስራችን ስለ እኛ መናገር ሲጀምር ሰዎች እንዲከተሉን ሳንጠይቃቸው የሚከተሉን ሆነው እናገኛቸዋለን።
የጠራ እይታ በያዝን፤ በያዝነው እይታ መሰረት በግለት ለመልካም ስራ በተጋን ቁጥር ለውጥ እናመጣለን። የምናመጣው ለውጥ ውስጣችን በተቀጣጠለው እሳት ልክ በተሰማራንበት ዘርፍ ውስጥ ወደፊት ለፊት ይዞን ይወጣል። የተቀጣጠለው እሳትም ነዳጅ ሆኖን ልንሆን ያሰብነው ጋር እንድንደርስ ያግዘናል። ወደ ውስጣችን ብንመለከት በአንዳች ጎልቶ በወጣ ነገር ውስጣችን ሲቀጣጠል ልናገኘውም እንችላለን።
በታሪክ መዝገብ ውስጥ ስለ ሰው ልጆች መልካም ይሆን ዘንድ በብዙ የተጋደሉ ሰዎች መደበኛ ሕይወት ኖረው ካለፉ ሰዎች በተጨባጭ የሚለዩ ናቸው። ይህ በሁሉም ዘርፍ ተመሳሳይ ነው። ጠንካራ የውስጥ ፍላጎት የጠራ እይታን ሰጥቷቸው በጠራ እይታ ወደ ተራራው የደረሱ። ደካማ ፍላጎት ደካማ ውጤት ነው የሚያመጣው። ትንሽ እሳት ትንሽ ሙቀት እንደሚፈጥር ማለት ነው። ትልቁ የውስጥ እሳት ግን አንዳንዴ በትንሽ ነገር እንዳይጋረድ ጥንቃቄን በሚሻ አካሄድ።
ትንሿ ሳንቲምና የተራራው ምሳሌ
ወደ ትልቁ ተራራ የሚደረገውን ጉዞ መገዳደር በተመለከተ የትንሿ ሳንቲምና የተራራው ምሳሌ በአስተውሎት እንመልከት። ተራራው ገዝፎ የሚታይ እሩቅ ሆኖ እይታ ውስጥ መገባት የሚችል ነው። ከእርቀት የሚታየውን ተራራ ግን ትንሿ ሳንቲም ወደ አይናችን ባስጠጋን ቁጥር እየጋረደችው ትመጣለች። ሳንቲሙ ወደ አይናችን አብዝቶ ከተጠጋ አብዝቶ የተራራው ምስል እየደበዘዘ ይመጣል።
እይታ በትንሽ ነገር ከተጋረደ ትልቁን ምስል ማየት የማንችልበት ደረጃ ላይ እንደርሳለን። ትልቁ ምስል ከተጋረደ እለታዊ እንቅስቃሴያችን ትንሽ ይሆናል፤ አይናችንን በቀረበው ነገር ልክ ይያዛል። ዛሬ ከእይታ ውስንነት የተነሳ እንቅስቃሴያችን በሰፊው የተገደበ እንደሆነ እናስተውላለን። የፖለቲካ ስሪታችን እንዲሁም አጠቃላይ ማህበረሰባዊ ጉዟችን የሚገነባ ሳይሆን የሚያፈርስ ሆኖ ይታያል። በመቀራረብ አቅምን አሰባስቡ ድምር ውጤቱ ሁሉንም አሸናፊ ከሚያደርግ ጉዞ ይልቅ ሁሉም በጋራ ተሸናፊ የሚሆንበት መንገድን የመረጥን ይመስላል። ተቃርኖው መቆሚያው የት እንደሆነ እርግጠኛ ባንሆንም የእይታ ልክ ግን የሚሰራው ስራ ስለመኖሩ አንዳች ጥርጥር የለንም። ትንሿን ሳንቲም ከአይን ላይ አንስቶ የሚሆን እይታ።
የአይን ህክምና ሰዎች የአይንን የማየት አቅምን ተመልክተው የእይታ ደረጃችን ላይ አስተያየት እንደሚሰጡ በአገራችን እየተገበርናቸው ባሉት ፖሊሲዎችና መሰል ተግባራት እይታችንን በመመርመር ወደ መፍትሔ መራመድ አለብን። ትንሿ ሳንቲም የገራደችውን ተራራ ተመልክቶ ወደ ተራራው የሚደረገውን ጉዞ ከማደናቀፍ በተራራው ስር ያለውን ሃብት አውጥቶ መጠቀም ተገቢነት እንዳለው አምኖ እይታን ማስተካከል።
በትንሿ ሳንቲም የሚወከል እይታችንን የጋረዱትን ነገሮች ለማንሳት ብንሞክር የምናገኘቸው እውነታዎች በዙሪያችን ያለውን ሁኔታ አግዝፈን በማየት አልችልም ማለታችን፤ በዙሪያችን ያሉ ተስፋ አስቆራጭ ድምጾችን አድምጠን መቆማችን፤ ትላንት ሞክረው ያልተሳካለቸው ሰዎችን ምክር ሰምተን ከጉዞ መታቀባችን፤ ደጋግመን አንኳኩተን ያልተከፈተውን በር አጥብቀን ከማንኳኳት መመለሳችን፤ ከእለት ወደ እለት እየደቀቀ ያለ ኢኮኖሚ የሚፈጥረው ተስፋቢስነት ህልማችንን እንደ ቅዠት መቁጠራችን ወዘተ ናቸው።
አንባቢው እንዲረዳው የሚያስፈልገው ነገር በመነሳሳት ወይንም በተቀጣጠለ ልብ ውስጥ አንዳች ነገር ለማሳካት የሚነሱ ሰዎች ተቀምጠው ተግዳሮትን ከሚያወሩ በየትኛውም መንገድ የተሻሉ መሆናቸው ነው። ዛሬ በልባችን ውስጥ ያለውን ድምጽ በሚገባ አድምጠን መሄድ ወደምንፈልገው አቅጣጫ መራመድ እንድንችል ከልብ መነሳሳት ያስፈልገናል። ከሁኔታው በላይ መራመድ የሚያስችልን አቅም ከውስጣችን ፈልገን ከፈጣሪ ጋር ለመነሳት የእይታ ምልከታችን ወሳኝነት አለው።
በእይታችን ልክ የምንወርሰውን ተራራ እንመልከት። ተራራው ግዙፍ ነው፤ ተራራው በመካከል ካለው የትኛውም ተግዳሮት በላይ ልናየው የተገባም ነው፤ ተራራው ላይ ደርሰን ከፍታውን በተቆጣጠርን ጊዜ አካባቢውን በሚገባ መቃኘት የምንችልበትም ስፍራ ነው።
ከተራራው ማዶስ
እይታውን ተራራው ላይ አድርጎ ጉዞን የጀመረ ሰው ከተራራው ጋር ሲደርስ ስኬቱን ያከብራል። በጉዞው የገጠሙትን ተግዳሮቶች እንዴት በድል እያሸነፈ እንደ ዘለቀ ከትዝታው ማህደር እያወጣ ደስታውን ያጣጥማል። ተራራው ጫፍ ጋር ደርሶ መቆም አንድ አመራጭ ሲሆን ሌላው አማራጭ ከተራራው ጫፍ ተነስቶ ሌላኛውን ተራራ ጫፍ መመልከት ነው። ወደ አዲስ ተራራ፤ ወደ በለጠው ከፍታ። ሁኔታ በተግባር ሕይወት ውስጥ ቀላል አይደለም፤ ነገር ግን የእይታ ሰዎች መገለጫ ነው።
በኢኮኖሚክሱ የሰው ልጅ ፍላጎት በቀላሉ የማይረካ መሆኑን እንረዳለን። በምድር ላይ ያለው ሃብት ውስን ቢሆንም የሰው ልጅ ፍላጎት ግን የሚቀጥል ነው። አንድ ሰው በሕይወት ጉዞ ውስጥ ራሱን ሲያገኝ ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ ደረጃ በሚያደርገው ጉዞ ውስጥ እሴትን መያዝ አለበት። ከአንድ ተራራ ወደ ሌላ ተራራ በጽናት የመጓዝ በስተመጨረሻም በአሸናፊነት ማማ ላይ ለመድረስ።
ከተራራው ማዶ ሌላኛውን ተራራ መመልከት ውስጥ ጽናት አለ። እይታን አጥርቶ የመጓዝ ጽናት። ልጆች ማሳደግ ምን ያህል አስቸጋሪ መሆኑን ልጆችን በማሳደግ ሕይወት ውስጥ ያለፉ ያውቁታል። ሰዎችን መምራት ምን ያህል አስቸጋሪ መሆኑን በመሪነት ውስጥ ያለፉ ሰዎች ይናገራሉ። አንዳንዱ ወደ ግራ እንሂድ ሲል ሌላው ወደ ቀኝ ሲል በመካከል በሚፈጠረው መሳሳብ አማካኝነት የሚሆን አስቸጋሪነት። ከተራራው ማዶ የሚያዩ ሰዎች የተግዳሮቱ ምንጭ ምንም ይሁን እያንዳንዱን ቀን በእሴት የተሞላን ኑሮን በመኖር ወደ ውጤት ይደርሳሉ።
በሕይወት ጉዞ ውስጥ ከአራቱም አቅጣጫ የሚመጣውን ተግዳሮት ተቋቁሞ ወደ ውጤት መድረስ እንዲቻል የእይታ ልክ ወሳኝነት አለው። ነገሮችን በልካቸው ማየት፤ ያየነውን ትልቁን ምስል ጠብቀን መራመድ፤ በብርቱ መነሳሳት።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 24/ 2015 ዓ.ም