ወይዘሮ አምሳለ ተገኑ ወልዶ የመሳም ፀጋን ለመጎናፀፍ ቀናትን እየቆጠረች ነው። እርግዝናዋን ካወቀችበት ቀን አንስቶ የመጨረሻው ቀን ልጇን የምትታቀፍበት ቀን እስኪደርስ ያሉትን ቀናት እያንዳንዱን የስሜቷን ልክ እየለየች በፍፁም የእናትነት ስሜት በጉጉትና በስጋት መካከል ሆና እዚህ ደርሳለች። ጠዋት ከመኝታዋ ስትነሳ ጀምሮ ባልተለመደ መልኩ ቁርጠት እያጣደፋት ነው። ግራ ሲገባት ጎረቤት ሄዳ ስታማክር ምጥ እንደሆነ ነግራው በአቅራቢያዋ ወደሚገኝ የጤና ተቋም ወሰዷት።
ብዙም ምጥ ያልጠናባት ወይዘሮ አጋጊ ወንድ ልጇን ለመታቀፍ ከግማሽ ቀን በላይ ማማጥ አልተጠበቀባትም ነበር። ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ታቀፈች። በስስት የምታየው የበኩር ልጇ ፍፁም ጤነኛና ደስተኛ ነበር። አንድ ቀን ግን ህፃኑ ከባድ ትኩሳት አጋጠመው። ቀዝቃዛ ውሃ በፎጣ ብታደርግ፤ የትኩሳት መድሃኒት ብትሰጠው ለውጥ ማግኘት አልቻለችም። የስስት ልጇ ህመምን ማየት የከበዳት እናት ልጇ ፈጥኖ መፍትሄ ያገኝ ዘንድ ወደ ጤና ተቋም ይዛው በረረች።
ያልታሰበው ክስተት
በአዊ ብሔረሰብ ዞን የጃዊ ሆስፒታል ልጇን ይዛ የሄደችው እናት እርዳታን ጠይቃ ሊሰጣት ልጇን የተቀበላትን ሀኪም በተማፅኖ አይን እየተመለከተች “ ዶክተር እባክህ በፈጣሪ ይዤሀለሁ ልጄን አድንልኝ …..” እያለች በመማፀን ተከትላው ወደ ህክምና መስጫው ክፍል ገባች።
‹‹ዶክተር›› የተባለው ሰውም ልጁን በማዳመጫና በእጁ ሲነካካ ቆይቶ ‹‹ጉንፋን ነው ምንም አይለውም›› በማለት የትኩሳትና ለጉንፋን የሚሰጥ ሽሮፕ ሰጥቶ ወደ ቤቱ መለሰው። የሰባት ወሩ ህፃን ግን ከህመሙ ከመፈወስ ይልቅ እየደከመ ሄደ። መልሰው ወደ ጤና ተቋሙ ሲወስዱት የሳንባ ምች እንደሆነና ወደ የከፋ ደረጃ እንደተቀየረ ነግራው አልጋ አስያዙት። ቀድሞ የመረመረው ሀኪም ባለመኖሩ ተደውሎለት እንዲመጣ ተደረገ። ልጁ ተዳክሞ ሲያየው በድንጋጤ ይሆናል ያለውን መርፌ ለህፃኑ ይሰጠዋል። ተወዳጁ የአምሳለ ልጅ በዚህ አይነት ሁኔታ ህይወቱ አለፈ።
የስስት ልጇን ያለአግባብ የተነጠቀችው ሴትም ጉዳዩን ይዛ ህግ ዘንድ ቀረበች፡፡ ያን ጊዜ ዶክተር ነው የተባለው ጌትነት ወንድአወቅ ምርመራ እንዲደረግበት ታዞ ጉዳዩን ፖሊስ ያዘው። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ‹‹ዶክተሩ›› ከስራ ገበታው አልታገደም ነበር።
ሌላኛው አሳዛኝ ክስተት
የግሌ ያለው በአዲስ ተስፋ ህይወትን ለመጀመር አንድ ብላ ስትነሳ ነገን በተስፋና በጉጉት የምትመለከት ፍልቅልቅ ወጣት ነች። የ25 ዓመት ወጣት የሆነችው የግሌ ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቀች ዓመት አልሞላትም፡፡ በምርቃቷ ማግስት ስራ ማግኘቷ ሁሉንም አስደስቷል፡ ፡ ስራ አጥታ ባለመቀመጧ እንደ እድለኛ እየታየች ኑሮን ማጣጣሟን ቀጠለች። አልፎ አልፎ ከሚያስቸግራት የጨጓራ ህመም ውጪ ፍፁም ጤነኛ ነበረች።
አንድ ቀን ‹‹ጨጓራዬን አመመኝ›› ብላ ከስራ ቀረች፡፡ ብታርፍም ምንም አልተሻላትም፡፡ ለውጥ አለመምጣቱን የተመለከቱት ወላጆቿ በአቅራቢያዋ ወደ ሚገኘው በአዊ ብሔረሰብ ዞን የጃዊ ሆስፒታል ይዘዋት ጎራ አሉ። ሰአቱ መሽቶ ስለነበር የምሽት ተረኛ የሆነውን ‹‹ዶክተር›› አነጋግረው እርዳታ ሊያደርግላት ይዟት ገባ። ወደ ህክምና ተቋሙ የገባችው ወጣት የግሌ ግን በእግሯ ከመጣችበት ሆስፒታል በሬሳ ሳጥን መመለስ እጣዋ ሆነ።
ለክፉ ይሰጣል ያልተባለው በሽታ ምን ትሁን ምን ሳይታወቅ ለዘላለም አንድታሸልብ አደረጋት። ህመሟ ለሞት ያለማድረሱ ነገር አልዋጥ ያላቸው ቤተሰቦቿ ጉዳዩን ወደ ህግ ይዘውት ሄዱ። ያን ጊዜ ምርመራ ሊያደርግ የመጣው የፖሊስ ቡድን ከዚህ ቀደም ክስ የነበረበት የሆስፒታሉ ሰራተኛ ጌትነት ወንድአወቅ ህክምናውን እንደሰጣት ሲታወቅ የአስክሬን ምርመራ እንዲደረግ ታዘዘ።
ልጅቷም በተሳሳተ መድሃኒት የተነሳ ህይወቷ ማለፉን ፖሊስ ደረሰበት። ጉዳዩ ጊዜ እንደማይሰጥና ‹‹ዶክተር›› ተብዬው ስራ ላይ ቢቆይ የባሰ ጥፋት እንደሚያደርስ የተገነዘበው ፖሊስም ‹‹ዶክተር›› ነው የተባለውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራውን አጠናክሮ ቀጠለ።
‹‹ አስመሳዩ ዶክተር››
ግለሰቡ ጌትነት ወንድአወቅ ይባላል። ከልጅነት ጀምሮ ህልሙ የህከምና ሰው መሆን ነበር። በልጅነቱ ‹‹ዶክተር መሆን እፈልጋለሁ›› እያለ ቢያድግም ‹‹ዶክተር›› እንዲሆን ሊያደርገው የሚችል ምንም አይነት ጥረት ሲያደርግ አይታይም ነበር። በትምህርቱ ሰነፍ ከሚባሉት ተማሪዎች ተርታ የተሰለፈ ለመምህራኑ የማይታዘዝ አስቸጋሪ ልጅ ነበር።
እየወደቀና እየተነሳ አስረኛ ክፍል የደረሰው ይህ ሰው እንደ ምንም የቴክኒክና ሞያ ትምህርት ሊያገኝ የሚችልበትን ነጥብ አግኝቶ በአንድ የሙያ ትምህርት ቤት 12+4 ወረቀት ይዟል። ምንም እንኳን የትምህርት ደረጃው እዚህ ላይ ቢሆንም የህክምና ፍቅርና ምኞቱ ከውስጡ አልወጣለት ብሏል።
በህልሙም በእውኑም የሚታየው ሀኪም መሆን ብቻ ነበር። ይህን ህልሙን ለማሳካት በአንድ የግል አነስተኛ ክሊኒክ ውስጥ የካርድ ክፍል ባለሙያ ሆኖ ተቀጠረ። ያኔ ነጩን ገዋን ለብሶ ሰዎችን ሲያስተናግድ ‹‹ዶክተር›› የመሆን ህልሙን ሊያሳካ የሚችል ቦታ ላይ መቆሙን አሰበ። ከዛ ቀስ በማለት በመለሳለስ ከነርሶቹም ከሀኪሞቹም ጋር ጠጋ በማለት ጨዋታቸውንም ስራቸውንም ይሸመድድ ገባ።
ከዕለታት አንድ ቀን እሱና የምሽት ተረኛው ሀኪም ብቻ በጤና ተቋሙ ውስጥ ያድራሉ። ሌሊት አካባቢ አንድ የታመመ ሰው ይመጣል፤ ተረኛውን ሀኪም ሊጠራው ሲሄድ በር ዘግቶ በመተኛቱ የተነሳ ሊያዳምጠው አልቻለም።
ይሄኔ የዘላለም ምኞቱ የሆነውን ህክምና የሚለማመድበት ሰአት እንደደረሰ በማመን በመመርመሪያ ክፍል ውስጥ ገብቶ እንደ ዶክተር በመሆን መዘጋግቦ መረመርኩ ብሎ ሲያበቃ ማስታገሻ በማዘዝ በሽተኛውን ይሸኛል። እንደዚህ ብሎ የጀመረውን ስራ በየአጋጣሚው በመደጋገም ውሸቱን ተላምዶት እውነተኛ ዶክተር የሆነ መስሎት ቆየ። ዶክተር የመሆን ህልሙንም ማንም ሰው የማያውቀው ቦታ በመሄድ በህክምና ለመቀጠር የሀሰት የትምህርት ማስረጃ አዘጋጀ።
ግለሰቡ ካዘጋጀው የሀሰተኛ ትምህርት ማስረጃ በተጨማሪ በአብክመ ጤና ቢሮ ከ4/2/2014 – 4/2/2019 የሚያገለግል የሚል የሀሰት የሙያ ፈቃድ በመያዝ በአብክመ ጤና ቢሮ ሥር ባሉት ሆስፒታሎች በማችንግ ፈንድ ፕሮግራም የቋሚ ቅጥር ማስታወቂያ ተወዳድሮ 50 በመቶ በማምጣት በደረጃ 14 ብር 9056 እየተከፈለው እንዲሰራ ይደረጋል።
በዚህ ሂደት ነው አንግዲህ ያለምንም እውቀት በድፍረት የሰዎች ህይወትን የሚያስከፍል ሞያ ላይ ተሰማርቶ ከተጠየቀባቸው ሰዎች በተጨማሪ በሱ ስህተት የተበላሹና ህይወታቸውን ያጡ ሰዎችን ሐኪም መስሎ አታለለ። ይህ የቅጥፈት ተግባሩን ሲያከናውን የነበረው ግለሰብ የሰዎች ህይወት በመጥፋቱ የተነሳ በቁጥጥር ስር ሆኖ ምርመራ ይደረግበት ጀመር።
የፖሊስ ምርመራ
ግለሰቡ እድሜው 35 መሆኑና የትምህርት ደረጃውም 12+4 መሆኑ ታወቀ። የጃዊ ሆስፒታል ቅጥር ሰራተኛ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ጌትነት ወንድአወቅ የተባለ ተከሳሽ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሳይማር በሜዲስን የዶክትሬት ዲግሪ እንደተማረ በማስመሰል በሀሰት በተዘጋጀ የዶክትሬት ሰርተፊኬት የትምህርት ማስረጃ ያቀረበ መሆኑም ታወቀ።
ከዚህም በተጨማሪ ግለሰቡ በአብክመ ጤና ቢሮ ከ4/2/2014 – 4/2/2019 የሚያገለግል የሚል የሀሰት የሙያ ፈቃድ በመያዝ በአብክመ ጤና ቢሮ ሥር ባሉት ሆስፒታሎች በማችንግ ፈንድ ፕሮግራም የቋሚ ቅጥር ማስታወቂያ ተወዳድሮ 50 በመቶ በማምጣት በደረጃ 14 ብር 9056 እየተከፈለው ሲሰራ እንደነበር ተደረሰበት።
ፖሊሶችም ግለሰቡ እድሜው 35 መሆኑና የትምህርት ደረጃውም 12+4 መሆኑን፤ እንዴት ግለሰቡ ” ዶክተር ” ተብሎ ሊጠራ ቻለ? እንዴት ፈተናውን አለፈ? ግለሰቡ ይሄን ያህል ርቀት ሲጓዝ ከጀርባው ማን ነበር? የሚሉ ጥያቄዎችን አስነሳ። እዚህ ጋር በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ‹‹ዶክተር ነኝ›› ያለው ግለሰብ እንዴት የተሰጠውን ፈተና 50 በመቶ ሊያልፍ እንደቻለ የተገኘ ማስረጃ የለም።
የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ተጨማሪ ምርመራዎች እያደረገ ቢሆንም በዚህ ልክ በድፍረት በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ያደረሰው ሰው ግን በህክምና የእውቀት ችግር ምክንያት በተፈጠረ ስህተት አንድ የ7 ወር ህፃን እና አንዲት የ25 ዓመት ወጣት ለሞት መዳረጉ ተረጋገጠ።
ፖሊስ ሲመረመር ቆይቶ፤ አንድ በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ‹‹ዶክተር ነኝ›› ብሎ ሲሰራ የነበረ ግለሠብ ለፍረድ እንዲቀርብ ስራውን ቀጠለ። ፖሊስ የምስክሮችን ቃል የታክቲክና የቴክኒክ ማስረጃዎችን በማጠናከር ተጠርጣሪውን ለአዊ ዞን ብሄረሰብ ዞን ፍትህ መምሪያ አቃቤ ህግ በማድረስ ጉዳዩ ለፍርድ እንዲቀርብ አመቻቸ።
አቃቤ ህግም የምርመራውን ውጤት በመያዝ ክስ የመሰረተ ሲሆን፤ በፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪው ቀርቦ የእምነት ክህደት ቃሉን በመስጠት ጉዳዩ ሲታይ ቆይቶ የሚከተለውን ውሳኔ አስተላልፏል።
ውሳኔ
አቃቤ ህግ ከአይን እማኞችና ከተለያዩ ምርመራዎች የተገኙ ማስረጃዎችና መረጃዎች ተጠናክሮ የቀረበለትን ማስረጃ በመያዝ ለአዊ ዞን ብሄረሰብ ፍትህ መምሪያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል። ተከሳሹም የመከራከር መብቱን ተጠቅሞ የተለያዩ ክስ ማቅለያዎችን ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በመጨረሻም ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን አይቶ ያለውን መረጃና ማስረጃ መርምሮ ተከሳሹ ላይ ውሳኔ ተላልፎበታል።
ግለሰቡ በፈፀመው በሀሰተኛ ሰነድ መገልገልና በሰው ህይወት የማጥፋት ወንጀል በአስራ አንድ ዓመት ጽኑ እስራትና በብር 5 ሺህ እንዲቀጣ ተወስኗል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ኅዳር 24/ 2015 ዓ.ም