ዛሬ ጠጣር ጉዳዮችን ለጊዜው ተወት አድርገን ቀላል የሚመስሉ ግን ዋጋቸው ትልቅ የሆኑ የሕይወት ክፍሎቻችን እያነሳሳን እረፍት እናደርጋለን። በእርግጥ የሥነ አዕምሮና ሥነ ልቦና ሊቃውንት እንደሚመክሩን እንደጭንቀት፣ ድብርትና ከመሳሰሉ ሌሎችም የአዕምሮ በሽታዎች ለመዳን ተመራጩ መንገድ ሁልጊዜ ራሳችንን ሥራ ውስጥ መደበቅ ነው። ይሁን እንጂ “ሰውም ገደብ(ሊሚት) አለው” እንዳለው ጓድ መንግስቱ ኃይለማርያም ድካም የተፈጥሮ ባህሪያችን ነውና እረፍት ማድረግም ከሥራ እኩል ለጤና አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ምክንያቱም ሁሌም ያለምንም ሥራ ሁሌም በእረፍት ላይ መኖር ለጭንቀትና ድብርት መንስኤ እንደሚሆነው ሁሉ ያለእረፍት መሥራትም ከሰው ተፈጥሯዊ ባህሪ ተቃራኒ በመሆኑ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናልና።
ታዲያ እውነታው ይህ ከሆነ እርስዎ ሳምንቱን ሙሉ በሥራ ተጠምደው ሰንብተው ቅዳሜና እሁድ ሲመጣ በሥራ የዛለ አካልዎትን ዘና ለማድረግ ወደ የት ነው የሚሄዱት? ለምሳሌ ከጓደኞችዎ ጋር ሰብሰብ ብለው ሻይ ቡና እያሉ ጥሩ ጊዜ ሊያሳልፉ ወደሚችሉባቸው መናፈሻ ቦታዎች ሊያመሩ ይችላሉ። አልያም ከከተማ ወጣ ብለው ነፋሻማውን አየር ተመግበው፤ ጋራ ሸንተረሩን ቃኝተው፣ የዛፎቹ ጥላ ሥር አርፈው የወፎቹን ዜማ አዳምጠው፣ በአበቦች መዓዛ ረክተው ተፈጥሮን በማድነቅ ራስዎን አዝናንተው ሊመለሱ ይችላሉ።
ምናልባትም እርስዎ መጠጣት ላያስደስትዎት ይችላል(መጠጣት ሲባል ውሃ አለመሆኑ ልብ ይባልልኝ፤ ያችን ሞቅ የምታደርገንንና የሆድ የሆዳችንን የምታስወራንን የመጠጥ ቤቷን ውሃ ማለቴ ነው)። መጠጣት የሚያዝናናቸው ግን ብዙ ሰዎች አሉ። ብቻ መዝናናት ወይም መዝናኛ እንደየሰው ፍላጎትና ስሜት ይለያያል። እርስዎን የሚያዝናናዎ ሌላውን ላያዝናናው ይቻላል። እናም መዝናናት ልክ እንደ ውበት ነው። ውበት እንደ ተመልካቹ፤ መዝናኛም እንደ ተዝናኙ ነው።
በዚህም ሆነ በዚያ መዝናናት ሲባል ብዙውን ጊዜ ቀድሞ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው ግን በሥራ የደከመ አካላችንን ዘና የሚያደርግልን ነገር ነው። ይሁን እንጂ በዕውቀት ወይንም በሳይንስ የተደገፈ ሳይሆን በዘልማድ የምናደርገው፣ አግባብነትም የሌለው ልማዳዊ አመለካከት ነው። ምክንያቱም በሥራ የሚደክመው አካላችን ብቻ አይደለም። ያለምንም እረፍት በርካታ ጊዜያትን በሥራ ተወጥረን በምናሳልፍበት ጊዜ አካላችን ብቻ ሳይሆን አዕምሯችንም ድካም ይሰማዋል፤ የምንሠራቸው ሥራዎች ሁሉ የሚሠሩት በአካል ብቻ ሳይሆን በአዕምሮም ጭምር ነውና።
ጉዳዩን በአንክሮ ከመረመርነው እንዲያውም ከአካላችን በላይ አዕምሯችን ነው ብዙ የሚደክመው፣ ብዙ የሚሠራውም እርሱ ነውና። ከዚህም ባሻገር በዘርፉ ሳይንስ እንደሚታወቀው አዕምሯችን ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንደኛው፤ “በከፊል ያልነቃው” ወይንም በእንግሊዝኛው “Subconscious Mind” በመባል የሚታወቀውና እጅግ አስፈላጊው የአዕምሯችን ክፍል ሃያ አራት ሰዓት ነው የሚሠራው። ቀን ስንሠራ ውለን በተፈጥሮ ሕግ ምክንያት ሌሊት ስንተኛ አካላችን ሲያርፍ እንኳን ይሔኛው የአዕምሯችን ክፍል አያርፍም፤ ሁልጊዜ ያለእረፍት ነው የሚሠራው።
ስለሆነም ከሥራ ተመልሰን በእረፍት ቀናችን እረፍት ስናደርግ ማረፍ ያለበት አካላችን ብቻ ሳይሆን አዕምሯችንም ጭምር መሆን አለበት። በእረፍታችን ሰዓት ስንዝናናም መዝናናት ያለበት አካላችን ብቻ ሳይሆን አዕምሯችንም ጭምር መሆን አለበት። ምክንያቱም ሰው አካላዊም አዕምሯዊም ፍጡር ነውና። ለምሳሌ እርስዎ በሥራ ብዛት የደከሙ ጡንጫዎችዎችን ዘና ለማድረግና እንደገና በአዲስ ኃይል ለመሙላት በእረፍት ቀንዎ ወደማሳጅ ቤት ሄደው ማሳጅ ሊያደርጉ(ሰውነትዎን ሊታሹ) ይችላሉ። አቅም ካልገደብዎት ይህንን ማድረጉ መልካም ነው፣ ጠቃሚም ነው። በእርግጥም በሥራ ብዛት የደከመ አካልዎን ያክማልና።
በሥራ ብዛት፣ የደከመ(የተሰላቸ)፣ በኑሮ ውጣ ወረድ በውጥረት የተጨነቀ አዕምሮዎን ዘና ለማድረግ ቢፈልጉስ ምንድነው የሚያደርጉት? ወዴትስ ነው የሚሄዱት? እንዴትስ ነው ይህንን ማድረግ የሚችሉት? እርስዎ የራስዎ ብልሐት ይኖርዎታል። እኔ በበኩሌ የአካልዎ ብቻ ሳይሆን የአዕምሮ ማሳጅ ቤት ያስፈልግዎታል እልዎታለሁ። አዕምሮ ከድካሙ የሚታደሰውና እንደገና አዲስ ኃይል የሚያገኘው ከመሰልቸትና ከተስፋ መቁረጥ ስሜት ተላቅቆ ስለ ስኬትንና ድል አድራጊነትን ማሰብ ሲጀምር ነው።
አዕምሮን ከድካሙ ለማሳረፍና በኃይል እንዲታደስ ለማድረግ በሕይወት ጉዞ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በፅናት ታግሎ አሸንፎ፣ መሰናክሎችን በብቃት አልፎ ከተራራው ጀርባ ከሚገኘው ብሩሃማ ቦታ መድረስ እንደሚቻል ማወቅና ማመን ይህንንም ለአዕምሯችን መንገር ያስፈልጋል። ይህ ነው የአዕምሮ ማሳጅ የሚባለው። ደጉ ነገር ደግሞ የአዕምሮ ማሳጅ ለማግኘት እንደ አካላዊው ማሳጅ ብዙም ከባድ አለመሆኑ ነው። በእርግጥ አካላዊ ማሳጅ ለማድረግ የሚከፈለው ክፍያም ያን ያህል ውድ ሆኖ አይደለም(ለእኔና የእኔ ቢጤ ጓደኞቼ ግን ለማሳጅ የሚከፈለው የወር አስቤዛችን ሊሆን ስለሚችል ነው ከአካላዊው ይልቅ የአዕምሮ ማሳጅ ቤት ይቀላል ያልኩት)።
ጭብጤን በደንብ ለማስረዳት ወይም ለማለት የፈለግኩት የአዕምሮ ማሳጅ ለማድረግ በእርግጥም ብዙ የሚያስወጣ አይደለም ነው። በተለይ መረጃ እጅግ እየቀረበን መጥቶ በሁላችንም እጅ መዳፍ ላይ በሆነበት በአሁኑ ዘመን አዕምሮዎን ለማዝናናትና በአንዳች ደስ የሚል የአሸናፊነት ስሜት ለመሙላት “አነቃቂዎች” ጋር መሄድ አይጠበቅብዎትም።
ይህን ለማድረግ ጥቂት ሳንቲሞችን ብቻ አውጥተው ስለስኬት የተጻፉ መጽሃፎችን ማንበብ(በተመሳሳይ እጅዎ ላይ የሚገኘውን ተንቀሳቃሽ ስልክዎንም ለዚህ ተግባር ሊጠቀሙበት ይችላሉ)። አለያም ጥቂት ሳንቲሞችን ብቻ ከፍለው እጅዎ ላይ ባለው ሞባይል ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ሙያዊና ሳይንሳዊ ንግግሮችንና ቪዲዮዎችን ከበይነ መረብ አውርደው ሊያዳምጡና ሊመለከቱ ይችላሉ።
ከእርስዎ የሚጠበቀው ፍላጎት ብቻ ነው። ለዚህም እረፍትና መዝናናት የሚያስፈልገው ለአካላችን ብቻ ነው ከሚለው ልማዳዊ የተሳሳተ አስተሳሰብ ባሻገር ማሰብ፣ አዕምሮም እረፍት እንደሚያስፈልገው ማወቅ ፍቱን መፍትሔ ይሆንልዎታል። መልካም እረፍት ይሁንልዎ!
ይበል ከሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 24/ 2015 ዓ.ም