የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዳማ አፄ ገላውዲዮስ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ጎን ለጎንም ደብረሊባኖስ በአብነት ትምህርት ሲከታተሉም ቆይተዋል። አስተዳደጋቸው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋር በእጅጉ የተቆራኘው እንግዳችን በተለይም ወላጅ አባታቸውም የቤተክርስቲያን አገልጋይ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ መንፈሳዊውን ዓለም የበለጠ ለማወቅ ልባቸው ወደ መንፈሳዊው ትምህርት አዘነበለ። እናም በስነ-መለኮት በአገር ውስጥና በግሪክ ተምረው ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ዶክትሬት ዲግሪያቸውን አገኝተዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያ ውስጥ በተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ላይ የቆዩት እኚሁ ሰው በተለያዩ አገራት በሚገኙ አብያተ ቤተክርስቲያናት በመዘዋወር መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን በትጋት መወጣታቸው ይነገራል። እንግዳችን በውጭ በነበሩበት ጊዜ ከበርካታ ፖለቲከኞች ጋር የመገናኘቱ እድል ስለነበራቸው በማህበራዊ፤ በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ስለፖለቲካውም ያላቸውን እውቀት አጎልብተዋል። በተለይም በስደት ላይ ይገኙ ከነበሩ የኢህአፓ አባላት ጋር ይበልጥ በመቀራረባቸው በፖለቲካ እሳቤያቸው ተማረኩ። ቀድሞውንም ደግሞ የ‹‹ሶሻል ዲሞክራሲ›› ርዕዮተ ዓለም ደጋፊ በመሆናቸው ልባቸው ወደ ኢህአፓ አዘነበለ።
ለውጡ ሲመጣም በውጭ ላሉ ፖለቲከኞች ጥሪ ሲቀርብ እሳቸውም ድርጅቱ ውስጥ ተቀላቀሉ። በድርጅቱ ውስጥ በተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊነቶች ላይ ሲሰሩ ቆይተው በአሁኑ ወቅት የኢህአፓ ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲሁም ዋናው የጋራ ምክር ቤት አቅም ግንባታ ሰብሳቢ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ። አዲስ ዘመን ጋዜጣ የኢህአፓን ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት መጋቢ ህሩይ አብርሃም ሃይማኖትን የዘመን እንግዳ›› አድርጓቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- የመንፈሳዊ አገልጋይ ሆነው ሳለ ወደ ፖለቲካ ሊገቡበት የቻሉበትን ምክንያት ያብራሩልና ውይይታችንን እንጀምር?
መጋቢብሉይ አብርሃም፡– በነገራችን ላይ ‹‹ፖለቲካ›› የሚለው የግሪክ ቃል የመፍትሔ ሃሳብ ማለት ነው። ደግሞም የመፍትሔ ሃሳብ የሌለው ፍጡር የለም። እኔም የራሴን አስተዋፅኦ በአገሬ ላይ ለማበርከት አስቤ ነው የገባሁት። ስለዚህ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ወደ ፖለቲካው ስገባ ብዙ አልከበደኝም። በእርግጥ የመንፈሳዊው ዓለም ብዙ መልካም ትምህርቶችና መልካም በጎ ጎኖች አሉት። በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የብዙ እውቀቶችና ፀጋዎች ባለቤት እንደመሆንዋ ከቤተክርስቲያኒቷ የቀስምኩት እውቀት ቀላል የሚባል አይደለም። ያንን እውቀት በመጠቀም የራሴን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደምችል ስለተሰማኝ እንዲሁም ኢህአፓ ታሪካዊ ድርጅት በመሆኑ፤ በዚህ ድርጅት ውስጥ ደግሞ ብዙ አቅም የነበራቸው ሰዎች ያሉበት በመሆኑ በጋራ መስራት እንደምችል አምኜ ነው ድርጅቱን የተቀላቀልኩት። እንዳሰብኩትም ፓርቲው ውስጥ በመግባቴ የተሻለ ግንዛቤና እውቀት እንዲኖረኝ አድርጎኛል።
አዲስ ዘመን፡- ፓርቲውም ሆነ አባላቶቹ አንጋፋ እንደመሆናቸው እንደእርሶ ላለ ወጣት ፖለቲከኛ ተግባብቶ መስራት ያስቸግራል የሚል ስጋት አላደረቦትም?
መጋቢብሉይ አብርሃም፡- እንዳልሽው ፓርቲው አንጋፋ ድርጅት ነው፤ በተለይ በዚያ ጊዜ የነበሩትና የ60ዎቹ ትውልድ የሚባሉት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብዙ በጎ ነገሮችን አበርክተዋል። የዚያኑ ያህል ብዙ ክፉ ነገሮች አሉት ይሄ ደግሞ አጠያያቂ አይደለም። በመሰረቱ እኔ ያ ትውልድ ፍፁም ነው ብዬ የማምን ሰው አይደለሁም። ነገር ግን ከዚያ ትውልድ ጋር ተያይዞ ሁሉንም ነገር አጣጥሎ መሄድ የለበትም። መልካሙን ነገር ከትውልድ ትውልድ መሸጋገር ይገባዋል ብዬ ስለማምን ነው ፓርቲው ውስጥ ገብቼ የራሴን በጎ አሻራ ለማሳረፍ እየሰራሁ ያለሁት። በነገራችን ላይ ነሃሴ ወር ላይ የፓርቲውን 50ኛ ዓመት ስናከበር በርካታ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና የፖለቲካ መሪዎች በተገኙበት የዚያ ትውልድ አባላት በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።
እኔ እንደአዲስ የፓርቲው መሪ ያ ትውልድ ክፉውን ነገር በይቅርታ በማለፍ፤ በጎውን ነገር ደግሞ ማስቀጠል ይቻላል ብዬ አምናለሁ። በነገራችን ላይ የዚያ ትውልድ አካል የሆነው አክራሪ ብሔርተኛ በመሆን እርስ በርስ ሲያባላን እንደቆየ የማንክደው ሃቅ ነው። ይህ አካል ከአንድነት ኃይሉ ጋር ለመተባበሩና በጥበብ አለመጓዙ ከዚያም በላይ ደግሞ የደርግ አምባገነንት ሕብረ- ብሔራዊ አንድነት የሚያቀነቅነውን ኃይል እንዲጠፋ አድርጎታል። እርስበርስ በጥላቻ የፖለቲካ ምህዳር ያለመስፋቱ ክፉው ኃይል እንዲበረታ አድርጎታል። በተለይ ደግሞ የፅንፈኛ አካል በውጭ ኃይሉ ይደገፍ ስለነበር፤ እርስበርስ በማፋጀት በተለያዩ ቦታ ላይ የእነሱን አጀንዳ የሚያስፈፁሙ አካላትን ሲያደራጁና ሲደግፉ ነው የኖሩት።
በመሆኑም የውጭ ጠላቶቻችን ያንን ትውልድ ታሪካዊ ምድር የሆነችውን ሃገራችንን ለመበጥበጥ እንደመሳሪያ ተጥቀመውበታል። አሁን ያለው ትውልድም ቢሆን ታሪኩን እንዲረሳና ማንነቱን እንዲጠላ በማድረግ የእጅ አዙር ቀኝ ግዛት ዓላማቸውን ሲያስፈፅሙ ነው የኖሩት። ያም ቢሆን ግን በጎ ነገሩን ከማንሳት ይልቅ ክፉውን ነገር ብቻ ይዞ ያንን ትውልድ በደፈናው የማይረባ አድርጎ መቁጠሩ ትክክል አይደለም። በተለይ ኢህአፓን ካነሳሽ ኢትዮጵያን ለማዳን የተከፈለውን መስዋዕትነት መዘንጋት አይቻልም፤ ስለሆነም ከዚያ ትውልድ በጎ ነገሩን ይዘን እኛ ደግሞ መቀጠል አለብን የሚል እምነት ስላለኝ ነው ኢህአፓ ውስጥ በድፍረትም በደስታም የገባሁት።
አዲስ ዘመን፡- አገሪቱ ከሁለት ዓመት ላላነሰ ጊዜ በጦርነት ቆይታ በቅርቡ የሰላም ስምምነት መፈፀሙ በግሎት ምን አይነት ስሜት ፈጠረቦት?
መጋቢብሉይ አብርሃም፡- በነገራችን ላይ ቀደም ሲል ጦርነቱ እንዲያበቃና የትግራይ ህዝብ ነፃ እንዲወጣ ደጋግመን ስናሳስብ ቆይተናል። ከነበረው ሁኔታ አንፃር ስምምነቱ እውን ይሆናል ብሎ ማሰብ ከባድ ነበር። የፖለቲካ ኃይሎቹ ፅንፍ የያዘ አቋም ለድርድር የማይመች ስለነበር እንደማኛውም ዜጋ አሳስቦኝ ነበር። የሚሆንም አልመሰለኝም ነበር። ነገር ግን የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ለመንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ስናደርግ ቆይተናል። በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዲሞክራሲያዊ የሆነ የፖለቲካ ጅምር እንዳለ ማሳያ ከምርጫው ጊዜ ጀምሮ አኩሪ ተግባር መፈጸማቸው ሳላደንቅ አላልፍም። ደግሞም ሌላው የፖለቲካ ኃይል ተጨምሮ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ እንደአገር ትፈተንና አደጋ ውስጥ ትውድቅ እንደነበር ግልፅ ነው። ሆኖም እኛ የበለጠ በሰለጠነ የፖለቲካ አካሄድ በመመራትና አገርን በማስቀደም፤ በአገር ጉዳይ ላይ ባለመደራደር፤ ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት የሚል እምነትን በማሳደር መረባረባችን ጠቅሞናል የሚል እምነት አለኝ።
በመሰረቱ የጋራ አገራችንን ኢትዮጵያ ለገዢው ብልፅግና ፓርቲ ብቻ የምንተዋት አይደለችም፤ በዚህ መንፈስ ሁሉም ፓርቲዎች በጋራ መደጋገፍ አለብን የሚለውን ቁርጠኝነት ይዘን ህዝቡን በጋራ በማስተባበር ስንሰራ ቆይተናል። ፓርቲያችን ደግሞ እንደሚታወቀው በስደት የሚኖሩ በርካታ አባላት ያሉት በመሆኑ በ ‹‹No more›› እንቅስቃሴው ከፍተኛ ሚናቸውን እንዲወጡ ፓርቲው አስፈላጊውን ነገር አድርጓል። ከዚያም በተጨማሪ ደግሞ እንደአገር የገጠመንን ችግር በጋራ የሰው ኃይልንም ጭምር በማቅረብ ሚናችንን ተወጥተናል። ለምሳሌ የቀድሞ የኢህአፓ ሰራዊት ተዋጊ የነበሩትን ጭምር ተሳትፈው የተሰውም አሉ።
በዚህ ልክ በአገራዊ ጉዳይ መተባበራችን የውጭ ኃይሎችን አስጨንቋል፤ ጠላቶቻችንንም አሳፍሯል። እንደአገር ደግሞ አኩሪ ተግባር ተፈፅሟል ባይ ነኝ። የኢትዮጵያ መንግስትም ለሰላም ቅድሚያ በመስጠቱ የሃሳብ ልዩነትን በጥላቻ ሳይሆን በመቀራረብ እንዲፈታ ጥረት አድርጓል። ስለዚህ ይሄ ሁሉ ተደማምሮ ኃይል ሆኗል። በዚህ ምክንያት ችግር ፈጣሪዎችም ሆነ የውጭ ኃይሉ የሚገቡበትና የህዝቡን አንድነት የሚሸረሽሩበት እድል ጠፍቷል። ስምምነቱ የውጪ ኃይሎች ጭምር እጃቸውን እንዲሰበስቡ ምክንያት ሆኗል። በነገራችን ላይ በውጪ ጣልቃ ገብነት የፈረሱ ሊቢያንም ሆነ ኢራቅን አብነት አድርገን መጥቀስ እንችላለን። በአህጉራችንም ሴንትራል አፍሪካ ዛሬ ምንላይ እንዳለች ማየት በቂ ነው።
በዚህ ሁሉ ሴራና ውስብስብ ችግር ውስጥ ሆኖ ለሰላም መቀመጡ በራሱ ትልቅ ድል ነው። የመላው ኢትዮጵያዊ አንድነትና የጥምር ኃይሉ እንዲሁም የአገር መከላከያ ቆራጥነት ለሠላም መሠረት እንደሆነ ግልፅ ነው። ያም ቢሆን ግን ለሰላም አማራጭ ተስማምተው መሄዳቸው ለእኛ ድርብ ድል ነው ብለን ነው የምናምነው። በአጠቃላይ ለሰላም እድል መሰጠቱን እናደንቃለን። በተጨማሪም ለዚህ ሰላም ስምምነት እውን መሆን የትግራይ ህዝብ ቆራጥነትም ሊዘነጋ አይገባም። አሁን ላይ እንደምንሰማውም በተለይ የአገር መከላከያ ሰራዊት በተቆጣጠረባቸው አካባቢዎች የትግራይ ህዝብ ከፍተኛ ድጋፍ እየሰጠ ነው ያለው። ይህ ደግሞ ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት ማሳያ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስምምነቱ በተጨባጭ ወደ መሬት እንዲወርድ በመንግስት በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዴት አዩት? ምንስ ይቀራል?
መጋቢብሉይ አብርሃም፡- መንግስት በተለይ ለተጎዳው የትግራይ ህዝብና ከፍተኛ ጦርነት ማረፊያ የሰሜኑ አካባቢ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲዳረስ እያደረገ ያለው ጅምር ጥረት የሚበረታታ ነው። ይሄ ጦርነት እንደሚታወቀው መላውን ህዝብ ጠባቂ ያደረገ፤ የአገራችንንም ኢኮኖሚ ለከፋ ጉዳት ያጋለጠ ሆኗል። እንደመንግስት እየወሰዳቸው ያላቸውን አማራጮችን ስንመለከት በእውነት ለመናገር የሚደነቅ ነው። ትላንትና ብዙ ሲሉ የነበሩ የውጭ ኃይሎችም አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርጉ አልታዩም። በዚህ አጋጣሚ መንግስት ግን ያለውን አቅም በመጠቀምና ከጥቂት በጎ አድራጊ ወዳጅ አገራት ጋር በመሆን እየሰራቸው ያላቸው ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው። የበለጠ ተደራሽ እንዲሆኑ መስራት ያስፈልጋል። እኛም ብንሆን ይሄ የመንግስት ስራ ብቻ አይደለም ብለን ፓርቲዎች ሰፊ ስራ እየሰራን ነው የምንገኘው። አሁን አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተናል።
ለዚህ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ያለምንም ማመንታት ከሰላም ስምምነቱ የሚያፈነግጠውን አካል መቃወምና ማጋለጥ ይገባዋል። በህዝብና በመንግስት መሃል ጥርጣሬ እንዲፈጠር የሚያደርጉትንም መከላከል አለበት። አንዳንድ ጊዜ እንደምንሰማው በድርድሩ ያልተነሱ ኃሳቦችን ጭምር በማንሳት ህዝብ ከህዝብ ጋር ለማጋጨትና ሌላ ቀውስ ለመፍጠር እየተደረጉ ያሉ ሴራዎች አሉ። እንዲሁም የሰላም ስምምነቱን በተለያየ መንገድ በመተርጎም መፈፀም ከሚገባው ጊዜ በላይ እንዳይወስድ መንግስት ሚናውን ሊወጣ ይገባል። አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል። እኛም ፓርቲዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ድጋፍ ልናደርግ ይገባል። በአጠቃላይ ይህ የሰላም ስምምነት ለትግራይም ሆነ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን ስምምነት አለመደገፍ አንችልም።
በግሌ ኢትዮጵያ ከዚህ ሰላም ስምምነት ብዙ ነገር ታተርፋለች የሚል እምነት አለኝ። ተገደን የገባንበትን የህልውና ዘመቻ ደግሞ አሁን ወደኋላ እንዲመለስ መፍቀድ የለብንም።
አዲስ ዘመን፡- የምክክር ኮሚሽኑ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ምን ይጠበቅበታል ብለው ያምናሉ?
መጋቢ ብሉይ አብርሃም፡- ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ሊኖራት የሚችለው አገር አቀፍ ምክክሩ ሲሳካ ነው ብዬ አምናለሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ የተለያዩ ጥያቄዎች አሉት እንዲሁም እንደአገር ደግሞ የምንጠይቀው አለ። በእርግጥ ጥያቄዎች እንደየአካባቢው ይለያያሉ። በዚህ ረገድ የኮሚሽኑ መቋቋሙም ሆነ ተቋሙን የሚመሩ አካላት ምርጫ ላይ እንደ ኢህአፓ ቅሬታ የለንም። የተመረጡት ሰዎች ይህንን አገራዊ ኃላፊነት በብቃት ሊወጡ እንደሚችሉ እምነት አለን። ይሁንና ህዝቡ የኮሚሽነሮቹን ሚና በቅጡ ተረድቷል ብዬ አላምንም። የእነሱ ዋነኛ ሚና አጀንዳ መሰብሰብ ነው። ለምሳሌ የህገ-መንግስት ጥያቄ አለ፤ የሰንደቅ አላማ ጥያቄ አለ፣ የፌዴራሊዝሙ ጉዳይ አለ። አጀንዳ ከታች ነው የሚነሳው። ስለዚህ ሁሉም በእኩልነት የሚስተናገድበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል።
እንደሚታወቀው የህዝቡ ጥያቄ እንደአገር ያልተግባባንባቸው፤ ልዩነት የፈጠርንባቸው፤ ኢትዮጵያ የታመመችባቸው ችግሮች አሉ። ይህንን መንግስት አልፈፅምም እንኳን ቢል በአደባባይ ይጋለጣል። አለመፈፀም ራሱ አይችልም። ባይፈፅመው ህዝብ ይታገለዋል። ሆኖም ጊዜ እንደሚፈጅ ይታወቃል። ስጋቴ ግን አጀንዳ የመሰብሰቡን ሂደት የፖለቲካ ካድሬዎች ብቻ እንደልባቸው የሚፈነጩበት እንዳይሆን ነው። ስለዚህ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆነ ሁሉም አካል ሊሳተፍበት ይገባል። በአጠቃላይ አጀንዳዎቹ ሲሰበሰቡ በእኩልነት የሚቀርብ ሃሳብ ወይም አናሳ ተብሎ እንዳይኖር ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም የሁሉም ሃሳብ ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል። የሁሉንም ጥያቄ ስትመልስ ነው ኢትዮጵያ የሁላችንም የምትሆነው። ሁሉንም ጥያቄ ደግሞ በፍቅር ማየት አለብን።
በመሰረቱ በርካታ የአለም አገራት ወደ ሰላም የመጡት በአገራዊ ምክክር ነው። ጀርመኖች ከሂትለር አስከፊ ጭፍጨፋ በኋላ ልዩነቶቻቸውን የፈቱት አስቀድመን የጠቀስናቸው የህግ ተጠያቂነትን በማስፈንና ህዝባዊ ውይይት በማድረግ ነው። በተመሳሳይ ደቡብ አፍሪካ ላይም ከዚያ ሁሉ የአፓርታይድ ጭፍጨፋ በኋላ ነጩም ሆነ ጥቁሩ በፍቅርና በሰላም መኖር የጀመረው አገር አቀፍ ምክክር በመደረጉ ነው። እርግጥ ነው አካታችነት ከሌለ ልክ እንደደቡብ ሱዳን ምክክሩ የከሸፈ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የእኛም አገር አቀፍ ምክክር እንዲከሽፍ አንፈልግም። ነገር ግን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የሚከሽፍ ነገር እንደሌለ እርግጠኛ ነኝ።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚቻለው መጠን መሰባሰባችን አስፈላጊ ነው ብለን ስለወሰድን ትልቅ ስራ ጀምረናል። ሰብሰብ ብለን ኃይል ፈጥረን አገራችንን ማዳን አለብን ወደሚል ድምዳሜ ላይ መጥተናል። እንደአገር ደግሞ የእኛን አስተዋፅኦ ኢትዮጵያ ትፈልጋለች፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የአንድ ግለሰብ ወይም የጥቂት ሰዎች ስብስብ ብቻ አይደለችም። የእኔ፣ የአንቺ፣ የሁላችንም ናት። ስለዚህ እንደህዝብ በአገር ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን ያስፈልጋል። የምንችለውን አስተዋፅኦ ማድረግ መቻል አለብን። ሃሳቦቻችንን ያለከልካይ ልናቀርብ ይገባል። ይህንን ካደረግን የማይሳካ ነገር የለም። በግሌ በዚህ በአገር አቀፍ ምክክሩ ተስፈኛ ነኝ። በተለይ ህገ-መንግስቱ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች ቀርበው መፍትሔ ይሰጣቸዋል ብዬ አምናለሁ። በነገራችን ላይ ኢህአፓ ሃገርአቀፍ ውይይት እንዲደረግ 40 ዓመት ጮኋል። ግን ሰሚ ሳያገኝ ነው የቆየሁ። አሁን ደግሞ ያለው መንግስት የምክክርን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ምህዳሩን ማመቻቸቱ በራሱ ልናመሰግነው እንወዳለን። በቀጣይም ምክክሩ ሁሉንም እንዲያሳትፍ፤ ሃሳቦች ያለገደብ እንዲንሸራሸሩ የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ህዝብን በከፍተኛ ደረጃ እያማረረ ያለው ሙስናን ለመከላከል በመንግስት የተጀመረውን ጥረት እንዴት ያዩታል? ከችግሩ ስፋት አንፃር ምን ሊሰራ ይገባል ይላሉ?
መጋቢብሉይ አብርሃም፡- ሙስና እንደአገር ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ያለ ጉዳይ ነው። አሁን ላይ እጅግ በሚገርም ሁኔታ ተስፋፍቶና አቅሙን አደራጅቶ የአገሪቱን ሁሉ ነገር አንቆ የያዘበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በአጠቃላይ ሌብነት በሁሉም ተቋማት ተንሰራፍቶ ይገኛል። በእምነት ተቋማት ሳይቀር ሰንሰለቱ ረዝሞ ሲታይ ያስደነግጣል። ህዝቡም ደግሞ ሙስና ካልሰጠ የሚፈለገው ነገር የሚፈፀምለት ወደማይመስለው ደረጃ ላይ ደርሷል። በእኔ እምነት ይህንን የፈጠረው ራሱ ማህበረሰቡ ነው። በነገራችን ላይ የማይገባውን ሰው ስፍራ መስጠት ለራስም ሆነ ለአገር አደጋ አለው። የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚታወቀው ‹‹ከሰው መርጦ ለሹመት፤ ከእንጨት መርጦ ለታቦት›› እንደሚባለው ከዚህ ቀደም ስንት ህዝብ ሲያስነቡ የነበሩ ሰዎች ዳግሞ ተሹመው የህዝብ ብሶት ምንጭ ሆነዋል።
እኔ በበኩሌ ለሌብነቱ መስፋፋት ህዝቡም ተጠያቂ ነው ባይ ነኝ። እኛ መርጠን የሾምነው መልካም አስተዳደር ካላሰፈነና በሚገባ ካላገለገለን መልሰን የማውረድ መብታችንን ተግባራዊ ልናደርገው ይገባል። መንግስት ርምጃ እስከሚወስድ መጠበቅ የለብንም፤ ህዝቡ ራሱ ሌቦቹን በቃ ሊላቸው ይገባል። ያ ማለት አመፅ መቀስቀስ ማለት አይደለም። ሁሉም በአካባቢው ያለውን የመንግስት ሌባንም ሆነ ግብረአበሮቹን ማጋለጥ አለበት። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ መንግስት ብቻውን ሚናውን ሊወጣ አይችልም። ሙስናን ማፅዳት የምንችለው የህብረተሰቡ ተሳትፎ ሲኖር ነው። የኢትዮጵያ ህልውና የሚረጋገጠው ሰላም በማስከበር ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚዋን ከሌቦች ስንታደግ ነው። እስካሁን ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ ሁላችንም በአገር ህልውና ጉዳይ ላይ ተጠምደን ስንቆይ ሌቦቹ ደግሞ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያ ገጸ-በረከቶች በመዝረፍ ላይ ተጠምደው ነበር። ስለዚህ አሁን ላይ አንጻራዊ የሚባል ሰላም በመስፈኑ ትኩረታችን እነዚህን ሌቦች በማጋለጥና በህግ ተጠያቂ ማድረጉ ላይ ሊሆን ይገባል።
በአጠቃላይ ሙስና እንደፓርቲም የምንታገለው ጉዳይ ነው። መንግስት ሌቦቹን ለህግ አጋልጦ የመስጠቱን ኃላፊነት አጠናክሮ እንዲሄድ እንፈልጋለን። እስካሁን ከታች ያሉትን ሌቦች የማጋለጥ ነገር አይተናል፤ ግን ደግሞ በከፍተኛ የመንግስታዊ ኃላፊነት ላይ ተቀመጠው ሰንሰለት ዘርግተው አገር እየመዘበሩ ያሉትንም ላይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። ይህንን ማድረግ ከቻለ ህዝቡ ራሱ ከእሱ ጎን ይሰለፋል፤ ያለፍርሃትም ያጋልጣል። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን ራሱ መንግስትንም አደጋ ውስጥ ነው የሚጥሉት። ከኢህአዴግ ጊዜ ጀምሮ አሁንም ጃኬታቸውን ቀይረው የመጡ ሌቦች አሉ። እነዚህ ደግሞ ተራ ሙሰኞች አይደሉም፤ አሁን ኢትዮጵያ ላለችበት የኢኮኖሚ ቀውስ የዳረጉ ናቸው።
አሁንም ሰንሰለታቸው አልተበጠሰም፤ እንደልባቸው እየፈነጩ ነው ያሉት። ኢትዮጵያ እንዲህ በውጭ ምንዛሬ እጥረት እየተፈተነች ባለችበት ጊዜ እነሱ ግን ምንዛሬውን እንዳሻቸው እያንቀሳቀሱነው ያሉት። በህሊናቢስነት ኢኮኖሚውን የሚዘውሩ ኃይሎች አሉ። ከላይ ጀምሮ በደህንነት መዋቅር ውስጥ ሁሉ ገብተው በሰፊው እየሰሩ ያሉ ሌቦችንም ያለአንዳች መከላከል ለህግ አሳልፈን ልንሰጣቸው ይገባል። መፍትሔው ህዝቡና መንግስት እጅ ላይ ነው ያለው። እኛም ካለስስት ለማገዝ ዝግጁ ነን።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በአንባቢዎችና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
መጋቢብሉይ አብርሃም፡– እኔም እድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ኅዳር 24/ 2015 ዓ.ም