‹‹…አስናቀች አለሙ እባላለሁ። የመጣሁት ከሚዛን ቴፒ ነው። ሕመሜ የደም ካንሰር ነው። ሕክምናው በአንድ ወይንም በሁለት ቀን የሚቋጭ አይደለም። ሁልጊዜም ክትትል ይፈልጋል። ስለዚህ እኔ አልጋ መያዝ የማልችል አቅመ ደካማ ስለሆንኩ እዚያው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አግዳሚ ወንበሮች ላይ ተኝቼ አድር ነበር። የብርዱ ነገር አይወራም። በዚህ ሁኔታ ከበሽታው በላይ በሁኔታው ስሰቃይ ቆየሁ። … በፊት በፊት መድሀኒቱ ለሶስት ወር ስለሚሰጠኝ የሶስት ወሩን ይዤ ወደ አገሬ እሄድ ነበር። አሁን ግን እጥረት አለ ተብሎ መድሀኒት የሚሰጠኝ የአስራ አምስት ቀን ነው። የትራንስፖርቱ አልጋና ምግብ ሳይጨምር አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ነው። ደርሶ መልሱ ሶስት ሺህ ብር ይፈልጋል። በየአስራ አምስት ቀኑ ይህ ገንዘብ ከየት ይመጣል? ይህ ሕመም ከጀመረኝ አስር ዓመት ሆነው።
በፊት ልጆቼንም ቤቴንም የምደግፈው ጠጅ እየነገድኩ ነበር። አሁን ካንሰር ከያዘኝ ጀምሮ ይሄው አስር ዓመት ሆነኝ፤ ምንም ሰርቼ አላውቅም። ልጆቼን እንደእናትነቴ ከዳር ለማድረስ አልቻልኩም። አባታቸው ብቻውን እየተንገላታ ነው። እኔ እስከአሁን እየታመምኩ ነው። በእርግጥ አብረውኝ የሚታከሙ እየሞቱ ነው…… የእኔን መጨረሻ አላውቅም….›› ይላሉ በአንድ ወቅት ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ በህክምና አገልግሎቱ ምክንያት እየደረሰባቸው ያለውን እንግልት የተናገሩ እናት ።
የወይዘሮዋ ታሪክ በህክምናው ዘርፍ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ የደረሰበትን አስከፊነት የሚያሳይ ነው። በአገልግሎቱ ውስንነት የተነሳ ፈውስን ፈልገው የሚመጡ ህሙማን ግን በሚፈልጉት ልክ አገልግሎቱን አግኝተው አይሄዱም። ምክንያቱም የሕዝብ ቁጥሩና መሰረተ ልማቱ እንዲሁም የአገልግሎት አይነቱና መድሀኒቱ ብዙ ችግር አለበት።
አብዛኞቹ ሪፈራል ተብለው የሚጠሩት የመንግስት ትልልቅ ሆስፒታሎችም ሲታዩ ብዙ ነገር የሚጎላቸው ናቸው። ለምሳሌ በቂ ባለሙያም ላይኖራቸው ይችላል። በተለይ አሁን እየጨመረ ያለውን የሕዝብ ቁጥር የሚመጥን ቦታና ባለሙያ ማግኘት ፈተና ነው። በዚህም ሰዎች በሄዱበት ፍጥነት አገልግሎትን ሳያገኙ ቀርተው ይሞታሉ፤ አለያም የአካል ጉዳተኛ ይሆናሉ። የአገልግሎት አሰጣጥና የህብረተሰብ አለመመጣጠንም ተኝተው መታከም ያለባቸውን ሰዎች በየኮሪደሩ እንዲወድቁ ያደርጋቸዋል። ለዚህም እንደአገር የተለያዩ መፍትሄዎች በመስጠት ላይ ነው። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ሆስፒታሎችን ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት ማድረግ ሲሆን፤ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ይህንን መሰረት አድርገው ከተቋቋሙት መካከል ይጠቀሳል።
አመሰራረቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በነፃ እንዲሁም በዝቅተኛ ዋጋ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ነው። በዚህም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የአሁኑ የአውቶብስ ተራ (መናኸሪያ) ቅጥር ግቢ ውስጥ በ1939 ዓ.ም ተጀምሮ ይህንን አገልግሎቱን ለ24 ዓመታት ሲሰጥ ቆይቷል። ከዚያም አገልግሎቱ ዘመናዊ እንዲሆን በመወሰኑ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ማለትም አሁን ባለበት ቦታ ላይ ባለ አራት ወለል ሕንፃ ተገንብቶለት በ1963 ዓ.ም ሥራውን እንዲጀምር ሆነ።
በአሁኑ ወቅትም ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በሚል ስሙን ቀይሮ ከአንገት በላይ ህክምና ጨምሮ የውስጥ ደዌ ፣ የማህጸንና ጽነስ፣ የህጻናት ህክምና፣ የአስክሬን ምርመራ ህክምና፣ የህብለ ሰረሰር ቀዶ ህክምና፣ የቃጠሎ አደጋ ህክምና፣ የኩላሊት ህክምና፣ የፊኛና የሽንት ትቦ መስመር ህክምና እና ያለ ቀዶ ህክምና ጠጠሮችን የሚያስወግዱ ህክምናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የጀመረው የፈርቲሊቲና የስነ ተዋልዶ ህክምና ማዕከል ሆስፒታሉን አንድ እርምጃ ከፍ ካደረጉለት ተግባራት የሚጠቀሱ ናቸው።
በሌላ በኩልም የህክምና ኮሌጁ በ104 ሚሊዮን ብር ወጪ የአፍንጫ፣ የጆሮ፣ የጉሮሮ እና ተመሳሳይ ከአንገት በላይ ህክምናዎች ዘመኑ በደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ መስጠት የሚያስችሉ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ከውጭ አገራት በማስገባት አገልግሎት የሚሰጥ ሆኗል። ይህንን አገልግሎት መጀመሩ ደግሞ ታማሚዎችን ከማገልገል ባሻገር ከአንገት በላይ ህክምና ድህረ ምረቃ መርሃ ግብር ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ሰልጣኞች ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር በማስተዋወቅና የሥራ ላይ ልምምድን በስፋት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
እነዚህንና መሰል መልካም ሥራዎችን በህከምናው መስክ ሲያከናውን አለም የደረሰበት ደረጃ ላይ ሊያደርሱን የሚችሉ በርካታ ልምዶችንም ለአገር ያመጣል። በእርግጥ ሥራዎቹ በዚህ ደረጃ ቢሰፉም በቦታ ጥበት ምክንያት ታካሚዎች በቀልጣፋና በምቹ ሁኔታ ማገልገል ተስኖት ቆይቷል። ስለዚህም ይህንን ችግር ለመፍታት አሁን ላይ ሆስፒታሉ በሁለት ቢሊየን 768 ሚሊየን 21 ሺህ ብር ጠቅላላ በጀት ከሦስት ኮንትራክተሮች ጋር በመፈራረም የሚያስገነባው (2B+G+8) የካንሰር ህክምና ማዕከል እና (B+G+8) የልብ ህክምና ማዕከል በአገልግሎቱ ላይ የሚታየውን የተደራሽነት ችግር በማቅለል የማይተካ ሚና ይኖረዋል። ታካሚዎች በምቹና ቀልጣፋ ሁኔታ እንዲገለገሉም ያደርጋል።
ግንባታው አሁን ላይ የሲቪል ስራ ፊዚካል አፈፃፀም 80 በመቶ መድረሱን ደግሞ የሆሰፒታሉ የምህንድስናና ግንባታ ዳይሬክተር ኢንጂነር አማኑኤል ሕይወት ይገልጻሉ። ሆስፒታሉ ተጨማሪ የድንገተኛ አደጋ ህክምና ማዕከል ፕሮጀክት በአቤት ሆስፒታል ለመገንባትም 8ሺ600 ካሬ ቦታ ተረክቦ በዝግጅት ላይ ስለመሆኑም ያነሳሉ።
ሆስፒታሉ እያስገነባ የሚገኘው ከ1ሺህ በላይ አልጋ ያለው ብሔራዊ የካንሰር፤ የልብ እና ከሆድ ዕቃ ጋር ተያያዥ (የአንጀት፣ ጨጓራ፣ ጉበት) ህክምና ማዕከል ሲሆን፤ በ6ሺህ 800 ካሬ በላይ ያረፈው ብሔራዊ የካንሰር ህክምና ማዕከል በየክልሉ ከሚገኙት የካንሰር ማዕከላት የገዘፈና ለጨረር ህክምና የሚሆን 5 ባንከር ያለው ነው። በጨረር ህክምና ለካንሰር ህክምና አገልግሎት የሚውለው ባንከር ጣሪያ ማልበስ ብቻ ነው የቀረው። የካንሰር ህክምና ማዕከሉ ከ337 በላይ አልጋ ያለው ሲሆን፤ ከኖርማል ራድዮሎጂ ዩኒት፣ ኤም አርአይ፣ ሲቲ ስካን በተጨማሪም ኒውክላር ሜዲሰን ያለው መሆኑን አብራርተዋል። በሌላ በኩልም በመደበኛ ኢሜጂንግ የማይታዩ የካንሰር ዓይነቶችን በግልጽ ለማየት የሚያስችሉ በኮንክሪት የተሰሩና የተለየ ቦታ የሚቀመጡ ቴክኖሎጂዎች መካተታቸውም ታውቋል።
እንደ ኢንጂነር አማኑኤል ማብራሪያ፤ በ1ሺህ 900 ካሬ ላይ ያረፈው ባለ ስምንት ወለል ህንጻ የልብ ህክምና ማዕከል ፕሮጀክትም እራሱን ችሎ ከ316 በላይ አልጋ፤ 15 አይሲዩ እና 15 ሲሲዩ አልጋዎች እንዲሁም አራት የቀዶ ጥገና፤ ሁለት ካትላብ እና 10 የማገገሚያ ክፍሎች አሉት። ምድር ቤት ( ቤዝመንት) እና ባለ ስምንት ወለል ያለው ህንጻም ይገኝበታል።
በ1ሺህ 400 ካሬ ላይ ያረፈውና የአንጀት፣ ጨጓራ፣ ጉበትና ተያያዥ ህክምና ማዕከል የሆነው ደግሞ 184 አልጋዎች፣ ስድስት የጨጓራ ምርመራ (ኢንዶስኮፒ) ክፍል አለው። ይህም በተመሳሳይ ምድር ቤት (ቤዝመንት) እና ስምንት ወለል የያዘ ህንጻ ነው። ሙሉ ከአንገት በላይ ህክምና ከቦታ ችግር ጋር ተያይዞ ራሱን ችሎ ሊገነባ ባለመቻሉም 115 አልጋዎች ያሉት የራሱ የቀዶ ጥገና ክፍል (ኦፕሬሽን ሩም) ያለው፣ በአንዱ ብሎክ ተተክቷልም ብለዋል ኢንጅነሩ።
ፕሮጀክቱ ከሦስት ኮንትራክተሮች ጋር በተደረገ ስምምነት እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን፤ ከዋና ሲቪል ኮንትራክተሩ ጋር በአንድ ቢሊየን 689 ሚሊየን በላይ ገንዘብ ተፈራርሞ የተጀመረ ነው። ከአለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ ደግሞ የአንድ ዓመት ኮንትራት ከባማኮን ኢንጂነሪንግ ጋር በመፈራረም ከካንሰር ህክምና ጋር የተያያዙ ዘመናዊ የኔትወርክ ዝርጋታ፣ በኔትወርክ የተደገፈ የህንፃ ማኔጅመንት ሲስተም፣ ነርስ ኮል ሲስተም፣ አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ሥራዎችን እና የማጠናቀቂያ ሥራዎችን ጨምሮ በ789 ሚሊየን ብር እየሰራ ይገኛል።
ከሐምሌ 2013 እስከ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም ለማጠናቀቅ 289 ሚሊየን 773 ሺህ ብር የፈረመው ደግሞ ኪቢሽ ኮንስትራከሽን ሲሆን፤ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራውን እየሰራ ይገኛል። ፕሮጀክቱ ከዋጋ ንረት አንጻር የሲሚንቶና የብረት ችግር በመጠኑ ተግዳሮት ሆኖበታል። በተለይም ጨረር ለመከላከል የሚሰራው ባንከር ግንባታ ጣራ የማልበስ ሥራ ተቆራርጦ የማይሞላና እስከ 5ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ የሚፈጅ ኮንክሪት በአንድ ጊዜ መሙላት ስለሚያስፈልገው ለዚህ የሚሆን ግብዓት ያስፈልጋል። በዋናነት ግን የመጨረሻ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ከ700 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ዕቃዎች ሙሉ በሙሉ ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው በጤና ሚኒስቴር በኩል ከሶስት ወር በፊት 15 ሚሊየን ዶላር ለብሔራዊ ባንክ የድጋፍ ደብዳቤ ተጽፎ በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑም አስረድተዋል ኢንጅነሩ።
በሌላ በኩልም በአሁኑ ወቅት የድንገተኛ አደጋ ህክምና ማዕከል የቅዱስ ጰውሎስ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ አካል በሆነው አቤት ሆስፒታል በአነስተኛ ህንጻ በኪራይ ትልቅ አገልግሎት እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን፤ በቀጣይ ግን 8ሺ 600 ካሬ ከጉለሌ ክፍለ ከተማ መሬት በመረከብ የድንገተኛ አደጋዎች ህክምና ማዕከል ሜጋ ፕሮጀክት ግንባታ ዲዛይን ተጠናቆ ከሶስት ወር በኋላ ግንባታው የሚጀመር ይሆናልም ብለውናል።
ዛሬ ላይ የደረስንበት የህዝብ ቁጥር በተገቢው ሁኔታ ለማገልገል እንደዚህ አይነት ግንባታዎች እጅግ በጣም ወሳኝ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከግንባታው ባሻገር የባለሙያው ሙያዊ ብቃት ላይ መሰል ሥራዎች መሰራትም ያስፈልጋል። እናም ሆስፒታሉ ይህንን በማድረግ በኩል ትልቅ አቅም ያሉት ኢንጅነሩ፤ ዓለም የደረሰበትን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታሳቢ ያደረጉ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችና ግብዓቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራትም እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 24/ 2015 ዓ.ም