ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ትምህርት ጥሩ ነው? በጣም ደስ ይላል የሚል መልስ እንደሰጣችሁኝ አምናለሁ። ጎበዝ የሆነ ተማሪ በምንም መልኩ አያማርርም። ምስጋናን ሁልጊዜ ያስቀድማል። በተጨማሪም ሳይጨናነቅ ትምህርቱን ያጠናል፤ ትምህርት ቤት ውስጥም ቢሆን ከትምህርቱ ውጭ ምንም አያደርግም። በአግባቡ ትምህርቱን ይከታተላልም። እናንተ ደግሞ እንደዚህ አይነት ልጅ እንደሆናችሁ እርግጠኛ ነኝ።
ልጆች ዛሬ ለየት ያለ ጉዳይ ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ። ምንድነው እሱ? ካላችሁኝ መልሴ በጣም ብልህና መልካም ስነምግባር ያለው ልጅ እንዴት መሆን ይቻላል የሚለውን ማስረዳት ነው። ይህንን ደግሞ በተግባር ያሳዩ ልጆች ናቸው የሚነግሯችሁ። ልጆቹ ወንድምና እህት ሲሆኑ፤ በትምህርታቸው በጣም ጎበዞች ናቸው። በተለይ ትንሽዬው ልጅ እጅግ የሚገርም ብቃት ያለው ነው። ኢራ ማሙሸት ይባላል። የሦስት ዓመት ከዘጠኝ ወር ልጅ ሲሆን፤ እንግሊዝኛ ቋንቋን አቀላጥፎ ይናገራል። አማርኛና ኦሮምኛም ይችላል።
ከአቅም በላይ የሆኑ ሥራዎችን ሲያከናውን ብታዩት ቤተሰቡ እድሜውን ተሳስቶ ነው ትላላችሁ። ምክንያቱም ከእሱ እድሜ በላይ ያሉትን ልጆች በትምህርት ያግዛቸዋል። በተለይም በእንግሊዝኛ ትምህርት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎችን ሳይቀር ያስጠናል። ለሌሎች ሰዎች ያለው አክብሮትም እጅግ የሚገርም ነው። ወደ ቤተሰቦቹ ቤት ለጥየቃ የሚመጡ ሰዎች የእርሱ ቤተሰቦች እንደሆኑ ነው የሚያስበው። ስለዚህም ያለውን ሁሉ ተካፍለው እንዲመገቡ ይፈልጋል።
ልጆች ኢራ ምን መሆን እንደሚፈልግ ታውቃላችሁ? ስፓይደር ማን መሆን ነው። ክንፍ ስለሌለው እንደማያደርገው ቢያምንም መብረር በጣም ይወዳል። ይሁንና መንጠላጠልና ሌሎች ከስፓይደር ማን ጋር ያሉ ነገሮችን ማከናወን ይፈልጋል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ በየጊዜው ልምምድ ያደርጋል።
የኢራ እህት ራማ ማሙሸት ሌላኛዋ ያነጋገርናት ብልኋና መልካሟ ልጅ ስትሆን፤ በሀርድ አካዳሚ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነች። ለእንስሳትና እጽዋት ልዩ ፍቅር አላት። በዚህም የወደፊት ህልሟ ዚዎሎጂስት መሆን ነው። ምክንያቱም እንስሳት መታደን የለባቸውም፣ ቦታቸውም በተለያየ መንገድ ሊመነጠርባቸው አይገባም የሚል አቋም አላትና የእነርሱን መብት ማስጠበቅ ላይ መስራት ትፈልጋለች።
ልጆች ራማ እንስሳትና እጽዋት ሲፈጠሩ አላማ አላቸው ባይ ነች። ምክንያቱም እነርሱ ካሉ ዓለማችን ውብ ትሆናለች። በተጨማሪም እነርሱ ካሉ የአየር ንብረት ለውጥ አያስቸግረንም የሚል እምነት አላት። ደስ ይላል አይደል ሀሳቧ ? ራማ ትምህርቷን ስታጠና የተለየ ዘዴ ትጠቀማለች። ይህም የተማረቺውን ዓይኗን ጨፍና ርዕሱን ብቻ በመያዝ ማስታወስ ነው።
ራማ ከሰዎች ጋር አብሮ መሥራት እጅግ ከሚያስደስታቸው ልጆች መካከል ነች። አብሮ መሥራት ጭንቀትን ያስወግዳል፣ አዲስ ሀሳብን ለማምጣት ያስችላል፣ የተማርነው እንዳይጠፋብን እድል ይሰጠናልም ትላለች።
ልጆች ራማን አንድ ነገር ጠይቀናት ነበር። ምን መሰላችሁ መልካምነት እንዴት ይዳብራል የሚል ነው። እርሷም እንዲህ ብላናለች። የተለያዩ መጸሐፍትን ስናነብ፣ ጠቃሚ ፊልሞችን ስናይና የቤተሰብ ምክርን ተቀብለን ስንተገብረው ነው። በማንበባችን ውስጥ ሁልጊዜ በራስ መተማመናችንን እናዳብራለን። ይህ ከሆነ ደግሞ ዝቅተኝነት አይሰማንምና መልካም እንሆናለን።
ልጆች ራማ ለእናንተ የምታስተላልፈው ትልቅ መልዕክት አለ። ይህም ጥሩ አንባቢ ሁኑ የሚል ሲሆን፤ ለማንበብ ደግሞ አቅዱ። በተጨማሪም እንስሳትንና እጽዋትን ውደዱ። ምክንያቱም እነርሱን በመንከባከብ ውስጥ ደስተኝነትን ታገኛላችሁ። ጤናማ አየርን ትተነፍሳላችሁ ትላለች።
ልጆች ሁለቱም ልጆች ደስ የሚል አስተሳሰብ አላቸው አይደል? መቼም ይህንን እንዴት አዳበሩት ማለታችሁ አይቀርም። መልሱ አንድና አንድ ነው። ወላጆቻቸው በጣም ጥሩና ለሌሎች የሚደርሱ ስለሆኑ ነው። ሁለቱም መምህራን ናቸው። በአካባቢያቸው ያሉ ልጆችን ቤታቸውን ክፍት አድርገው ያስተምሯቸዋል። ይህንን ሲያደርጉላቸው ደግሞ ነጻነታቸውን ሰጥተው ነው። እቃ ቢሰብሩ አይቆጧቸውም፣ ምንጣፍ ቢያበላሹም አይገርፏቸውም። መልካምነትን እየሰጧቸው ያስተምሯቸዋል። እናም እነ ራማም ይህንን እያዩ ስላደጉ ሁልጊዜ ለሰው መልካም መሆንን ብቻ ያስባሉ።
መልካም ስብዕና የሚዳብረው መጀመሪያ በራስ ተነሳሽነት በሚደረጉ ጥረቶች ነው። ፍላጎትን መሰረት አድርጎ ሁልጊዜ በጎ በጎ ነገር ማድረግ ባህሪ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ልቀይረው ቢባል እንኳን አይቻልም። ስለዚህም ገና ከአሁኑ መልካም አሳቢ ብቻ መሆንን ልመዱ። የመልካም ባህሪ መገለጫ ምንድነው? ካላችሁ ለሌሎች ያላችሁ አመለካከት ቅን መሆን፣ ለራሳችሁ የምትሰጡት ግምት ጥሩ መሆን፣ መንፈሳዊ እሴታችሁን ለመገንባት የምትጥሩ ከሆነ፣ ለሥራ ያላችሁ አመለካከት ማለትም መከባበር፣ ጨዋነት፣ ይቅር የማለት ችሎታችሁ፣ ልግስና፣ ምስጋና፣ መስተንግዶ፣ ፍትህ፣ የዋህነት፣መታዘዝ፣ ታማኝነት፣ ቅንነት፣ እውነተኝነት፣ ጥንቁቅ መሆን፣ ፈጣንና ቁርጠኛ መሆን ናቸው።
ልጆች ሁለተኛው መልካም ስነምግባራችንን የምናዳብርበት መንገድ ከቤተሰባችንንና ከማህበረሰቡ በምናገኘው መልካም ምልከታ ነው። እንደምታውቁት ሰው ብቻውን መኖር አይችልም። ከህብረተሰብ ውጭም አይሆንም። እናም ከልጅነት ጀምሮ በሰፈር ውስጥ ያላችሁ አቀባበል መልካም ስብዕናን ያላብሳችኋል። ትምህርት ቤትና መንፈሳዊ ቦታዎች ላይ ያለው ሁኔታም እንዲሁ መልካም መሆንን ከሚያለማምዳችሁ መካከል አንዱ ነው።
በእነዚህ ቦታዎች ላይ ከላይ የጠቀስኩላችሁን ባህሪያት በመላበስ መልካምነትን ማዳበር አለባችሁ በማለት ለዛሬ ሀሳቤን ጨረስኩ። በሚቀጥለው ጊዜ ሌላ ጉዳይ ይዤላችሁ የምቀርብ ሲሆን፤ ለዛሬ እንሰነባበት። መልካም ሰንበት!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ኅዳር 25/ 2015 ዓ.ም