እንደመግቢያ
ሰውየው የቋንቋ ባለፀጋ ናቸው፤ አማርኛ፣ እንግሊዘኛ፣ አረብኛ እና ትግርኛ ቋንቋ አቀላጥፈው ይናገራሉ፤ ይግባባሉ። እንደ አሎሎ ብረት የጠነከሩ ናቸው፤ በ12 ዓመታቸው ብረት እያገላበጡ አድገዋል። ለበርካታ ዓመታት ከቤተሰብ ርቀው በባዕድ አገር ኖረዋልና በዚህ ልባቸው ደንዳና ነው።አፍቃሪ ናቸው፤ ስለአገራቸው ፍቅር ሲሉ አገራቸው ለማልማት መጥተዋልና፡፡
ልበ ቀና ናቸው፤ ሚሊዮን ብሮችን በጅተው ለወጣቶች መዝናኛ ማዕከላትን ይገነባሉ፡፡ የህግና የደህንነት ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳቸው ነው፤ ለዚህም ምስክር የሚሆናቸው መንግስት ባለሃብቶች በማስተባበር በ90 ቀናት ውስጥ የሚተገብረውን ሰው ተኮር ፕሮጀክት ታሳቢ በማድረግ እራሳቸው መንግስትን ምን ልሥራ ብለው ጠይቀው ፖሊስ ጣቢያ እና ሁለት የወጣት ማዕከል በራሳቸው ወጪ የገነቡ በጎ ፈቃደኛ ናቸው።ፍትህና ሥርዓት ከሁሉ ይቀድማል፤ የምድርም ገዥ ህግ ነው ለሚለው እሳቤያቸው ማሳያ ይሆን ዘንድ ደግሞ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዘመናዊ ፖሊስ ጣቢያ እየገነቡ ነው፡፡
ገና በልጅነታቸው ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል።በጠንካራ ዲሲፕሊን አድገው በወቅቱም ውድ በተባለው ሳንፎርድ ትምህርት ቤት ከነጮች ጋር ተምረው ያነሰ ሳይሆን የበለጠ ውጤት አስመዝግበው ወላጆቻቸውን አስደስተዋል።ነገን አሻግሮ የማየት ህልማቸው ትልቅ ነበርና ገና በለጋ ዕድሜያቸው ከሥራ ጋር ተቆራኝተው አድገዋል፡፡
እእእ! ሰውየው በአገር ቀልድ አያውቁም።ለእርሳቸው ምቾት ማለት በአውሮፓ አሊያም ደግሞ በሀብት ድልቅቅ ባሉት አገራት መዘዋወርና መኖርም አይደለም።ይልቁንም አቅማቸው በፈቀደው ሀብትና እውቀት ስለአገር ሲባል የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ነው።የዛሬው የዚህ አምድ እንግዳችን የሕይወት ገፃቸውን ዓባይን በጭልፋ ዓይነት ልናወጋችሁ ወደድን።
ከአስመራ-አዲስ አበባ- ለንደን
የተወለዱት በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ነው።እስከ ስድስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአስመራ ከተማ በአንድ የጣሊያን ትምህርት ቤት ነው።ከዕለታት በአንዲት ቀን ስድስተኛ ክፍል ትምህርት ተዘግቶ ወደ ውጭ ወጣ ብለው ከእኩዮቻቸው ጋር ኳስ ይጫወታሉ።ከዚያን በፊት በጥብቅ ሥነ-ሥርዓት ስለሚመሩ ብዙም ከቤት አይወጡም ነበር፡፡
አባታቸው ከ17 ዓመታቸው ጀምሮ የሚሰሩት ጎንደር ነው።በሂደት ደግሞ ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል።ታዲያ ኳስ ወደ ውጭ ወጥተው ሲጫወቱ ጥሩ ነገር አልጠበቃቸውም።እናታቸው ቆጣ ብለው ተናገሩ፤ ‹‹እኔ ልጆቹን መቆጣጠር እየከበደኝ ስለሆነ መላ እንበላቸው›› ብለው ለአባታቸው ተናገሩ።በዚህን ጊዜ እነመንሱር ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ግድ ሆነ፤ በሸገር ከተሙ።ትምህርታቸውንም በሳንፎርድ ትምህርት ቤት ቀጠሉ።
ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በዚሁ ትምህርት ቤት ከተማሩ በኋላ ወደ እንግሊዝ አገር አምርተው ለሁለት ዓመት ‹‹ኤ ለቨል›› የሚባል ኮርስ ወሰዱ።በመቀጠል ወደ ‹‹ሲቲ›› ዩኒቨርሲቲ ገብተው በሲቭል ምህንድስና አራት ዓመት ተምረው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ።
ለምን አልነግድም?
ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የተለያዩ ሥራዎችን ሰርተዋል። ኢንጂነር መንሱር “ቤተሰቦቼ በሙሉ በንግድ ውስጥ ያለፉ ሆነው ሳለ እኔ ስለምን ተቀጥሬ እሰራለሁ” ብለው ራሳቸውን ጠየቁ፤ በጥያቄም ብቻ አልቀሩም “የራሴን ስራ ዛሬውኑ እጀምራለሁ አሉ”፤ አስበው አሰላስለውም ወደ ተግባር ቀየሩት።ከወንድማቸው ጋር ተመካክረው ‹‹ዲጂታል አድቨርታይዚንግ›› ሥራ ጀመሩ።በዚህም ሥራ በርካቶችን ተዋወቁ፤ ብዙ ሥራም ሰሩ።ይህ ሥራቸው ግን ብቻውን ደስታ አልሰጣቸውም።አቅማቸውና እውቀታቸው ለብዙ ነገር ይገፋፋቸው ጀመር ።ልባቸው ደግሞ “መንሱር ሆይ ከዚህም በበለጠ መሥራት ትችላለህ” ሲል ከውስጥ ይጎተጉታቸዋል።ታዲያ ኢንጂነር መንሱር ነፍስያቸው የምትለውን ለማዳመጥ ተገደዱ።
ወደ አገር ቤት
ያደጉባት ከተማ አዲስ አበባ፤ የተማሩበትን ትምህርት ቤት ሳንፎርድ፤ አገሬ የሚሏት ኢትዮጵያን ሊረሱ አልቻሉም።ልባቸው ወደ ኢትዮጵያ ብረር! ብርርር በል፤ ክንፍ ብሎ አስቸገራቸው።አላመነቱም ከውጭ አገር የቀሰሙትን እውቀት፣ ሰርተው ያገኙትን ጥሪት ቋጥረው በፈረንጆች አቆጣጠር 2015 ወደ አዲስ አበባ መጡ።ቤተሰቦቻቸው ከጥንትም ጀምሮ ያለፉበትና ይሠሩት የነበረው ሥራ የብረት ንግድ ነው።እርሳቸውም ወደዚሁ የሥራ ዘርፍ ተቀላቀሉ።ቃሊቲ አካባቢ ከሞይንኮ ጀርባ ‹‹ኮርቴክስ›› በሚል ስያሜ እ.ኤ.አ 2015 የብረት ፋብሪካ አቋቋሙ።በዚህን ጊዜም 30 ሚሊዮን ብር ከራሳቸው ካፒታል ሲሆን፤ 30 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከባንክ በተገኘ ብድር ነበር ሥራው የተጀመረው።
ከ60 ሚሊዮን ወደ ግማሽ ቢሊዮን
የብረት ሥራ በአቅም ከፍ ያለ ካፒታል ይፈልጋል።ሥራው እየተቀላጠፈ ሲሄድ የንግድ ሽርክና ፈለጉ።በዚህን ጊዜ በተለያዩ አገር ያሉ ጓደኞቻቸውን በልባቸው ማሰስ ጀመሩ፤ ዓለምን በአራቱም ማዕዘናት ዞሩ።እንግሊዝ፣ ሳውድ አረቢያ፤ ጆርዳን የሚገኙ ጓደኞቻቻውን አማከሩ፤ በጉዳዩም ላይ በዝርዝር መከሩ። የጀመሩት ሥራ አዋጭ መሆኑን ባስረዱም ጊዜ ጓደኞቻቸው አብረን እንስራ የሚለውን ሐሳብ ተቀብለው ፋብሪካውን የበለጠ ማጠናከር ጀመሩ።ከእንግሊዝ፤ ከጆርዳን፤ ከሳውድ አረቢያ በመጨመር ሰዎችን በመጨመር ሥራው ማቀላጠፍ ጀመሩ።የካፒታል መጠኑም ከ60 ሚሊዮን ብር በእጅጉ ብልጫ አሳይቶ ወደ ግማሽ ቢሊዮን ብር አሳደጉት።በዚህን ጊዜ በርካታ ምርት ማምረት ብቻ ሳይሆን በጥራትና ብዛት ማምረቱንም ተያያዙት።ገበያው ደራ፤ ደንበኛውም ጎረፈ፤ ስራውም ተቀላጠፈ፡፡
የውጭ ምርት መተካት
አሀዱ ተብሎ ኢንቨስትመንቱ ሲጀመር ከቻይና የገቡ ማሽኖች ነበሩ።በኋላ ግን በብረት ሥራ ከሚታወቁት ጣሊያንና ቱርክ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር ውስጥ አስገቡ።በሽርክና የሚሰሩትም በብረት ዘርፍ ዓመታትን የሰሩ ነበሩ።በተለይ አንደኛው ሱዳን፣ ኤሜሬት፣ ጋና እና ሳውድ አረቢያ ፋብሪካ ያለው በመሆኑ ስለገበያው ሁኔታ በሚገባ መረዳት ችሏል። ይህ ደግሞ ከማሽን ጀምሮ እስከ ግብዓት አቅርቦት ያለውን ሰንሠለት በሚገባ የሚረዳ ሰው በመሆኑ ሥራውን የበለጠ ቀልጣፋ አደረገላቸው።በፋብሪካው ሥራቸውን ‹‹ሀ›› ብለው ሲጀምሩ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መቶ በመቶ አገር ውስጥ በመተካት ነበር። ከጥሬ ዕቃ በስተቀር ከቻይና፤ ቱርክና ዩክሬን ይመጣ የነበረው ሙሉ ለሙሉ ቀርቶ በአገር ውስጥ መተካት ቻሉ።በአሁኑ ወቅትም ድርጅታቸው ኮርቴክስ 300 ዓይነት ፕሮፋይሎችን ይሰራል።ቀደም ሲል ግብዓቶች ከውጭ ሲመጡ ከመበላሸት በዘለለ በኪሎም ላይ ቅሸባ የተለመደ ነበር።ይህን ግን አሁን ተረት ሆኗል፡፡
ውጭ አገር ሲባል…
ማን እንደ አገር የሚለውን ምስክር ለመሆን ኢንጂነር መንሱር ጥሩ አብነት ናቸው።መሰደድ ማለት ለእኔ ከባድ ነው።ከምንወደው ባህል፣ ቤተሰብና አገር መራቅ በእውነቱ ሳስበው ከባድ ነው።ምንም ምቾት ቢኖር አገሬን የሚል የልብ ሰቆቃ አለ።
በእርግጥ በርካቶች አገሬን ላልማ ብለው ሲመጡ የሚታዩ ቢሮክራሲዎች፣ ውጣ ውረዶች ፈተናዎች ተስፋ ሊያስቆርጡ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ውጭ አገር ኖረው የመጡት ሁሉም ነገር እንደዚያው ውጭ አገር እንዳዩት እንዲሆን መፈለጋቸው ከሲስተሙ ጋር እንደሚያጋጫቸው መታዘባቸውን ይናገራሉ።ዳሩ ግን ሁኔታዎች ቢመቻቹ ማን ከአገሩ፤ ከአፈሩ እና ከምድሩ ርቆ መኖር ይፈልጋል፤ ሲሉ ኩራትም ራትም በአገር መሆኑን ያስረግጣሉ።
እንግሊዝ አገር ሳለሁ
የተማሩበት ትምህር ቤት የነጮች ነው። ዳሩ ግን የነጮች የበላይነት የሚባለው ነገር በፍጹም ተጽዕኖ እንዲፈጥርባቸው አይፈልጉም፤ ወላጆቻቸውም ኮትኩተው ያሳደጓቸው በጨዋ ኢትዮጵያዊ ክብርና ወኔ በመሆኑ ማጎብደድን ከቶውም አይዋጥላቸውም፤ ግን የሰው ልጆች ስለሆኑ ብቻ ሁሉንም ያከብራሉ፡፡
ኢንጂነር መንሱር ሳንፎርድ ትምህርት ቤት እየተማሩ ሳሉም፤ ‹‹አንተ ከማንም ሰው አታንስም›› የሚለው የአባታቸው ምክር ከአዕምሯቸው ሁሌም አይጠፋም።በዚህም የተነሳ በተማሪነት ሕይወታቸው ተፅዕኖ ተላቀው መማራቸው ለስኬታቸው ሚስጥር አንዱ መሆኑን ይናገራሉ።እንግሊዝ አገር ሳሉም ፖሊስ መንገድ ላይ ያስቆማቸው ሁለት ቀን ብቻ ነው፤ ሌሎችን ላይ ግን ብዙ ፍዳ ይደርሳል።ኢንጂነር መንሱር ሙሉ ትኩረታቸው ሥራቸው ላይ ብቻ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ እርሳቸው የሚኖሩበት ሰፈር ሙሉ ለሙሉ ነጮች የነበሩና ከለንደን ወጣ ያለ መንደር ቢሆንም ሌሎች የገጠማቸው ችግር እርሳቸውን አልገጠማቸውም፤ ቢገጥማቸውም ቦታ አይሰጡትም፡፡
በ12 ዓመቴ የጀመርኩት ሥራ
የመንሱር አባት ከጥንትም የሚሰሩት ብረት ንግድ ነበር።ታዲያ እርሳቸውም ከሰኞ እስከ ዓርብ ትምህር ቤት ውለው ቅዳሜ እና እሁድ ከአባታቸው ጋር ሆነው ብረት ያገላብጡ ነበር።በዚህን ጊዜ ዕድሜያቸው 12 ዓመት ነበር።ታዲያ ከዚህ ዕድሜያቸው ጀምሮ የብረትን የንግድ ሥራ ባህሪና አዋጭነት እውቀት ቀሰሙ።ይህ በለጋ ዕድሜያቸው ወላጆቻቸውን ለማገዝ ይሰሩት የነበረው ስራ ግን እስከ ጎልማሳነታቸው ድረስ ተከትሎ እርሳቸውም ከብረት ንግድ ከፍ አድርገውት ወደ ፋብሪካ ተከላ አስመነደጉት፡፡
በኢትዮጵያ የተለመደው አንዱ የጀመረው ቢዝነስ ሌላውን በተመሳሳይ ሁኔታ መጀመሩ ዕድገት አያመጣም የሚል አቋም አላቸው።አንዱ ዳቦ ቤት ከከፈተ ሌላው ይከተላል።ይህ ግን ኢትዮጵያን አልጠቀመም፤ ሥራ ፍላጎት፤ በዘርፉ እውቀትና ለአገር የረጅም ጊዜ ህልም ያለው መሆን አለበት የሚል ጥልቅ እሳቤ አላቸው።እርሳቸውም በማያውቁት ሙያ ላይ ከመሰማራት ይልቅ በሚወዱትና እውቀት ባዳበሩበት ዘርፍ የገቡበት ምክንያትም ይኸው ነው፡፡
እዚህ አገር ይላሉ ኢንጂነር መንሱር፤ በርካቶች ገንዘብ ብቻ ስላላቸው ዘው ብለው በማያውቁት ሙያ ውስጥ ገብተው ስራውን ያበላሻሉ።ታዲያ ይህ አገርንም ግለሰቡንም የሚጎዳ ተግባር ነው።ቢሆን ቢሆን ፈቃድ ሲሰጥ አንድ ግለሰብ ሙያው ላይ ያለው ዕውቀት፤ ልምድና ትምህርት ደረጃ ቢታይ ኢትዮጵያ በተጠቀመች ነበር ሲሉ ቁጭታቸውን ይገልፃሉ።
እኔ አንዳንድ ጓደኞች አሉኝ። አንደኛው አንድ ቶን ቡና 4ሺ ዶላር ሌላው ደግሞ 1ሺ800 ዶላር ይሸጣሉ።ያለው ልዩነት ሲታይ ለአገሪቱ ትልቅ ኪሳራ ነው።ይህም በሙያ እና በሙያተኞች ባለመመራቱ የመጣ ነው።ሌሎች አገራት ደግሞ የኢትዮጵያን ቡና በዝቅተኛ ገንዘብ ገዝተው በብዙ እጥፍ አትርፈው ይሸጣሉ።ይህም እየሆነ ያለው ‹‹ብራንዲንግ›› ላይ በደንብ ባለመሰራቱ ነው።አንድን ሥራ ረገጥ አድርጎ በጥንቃቄ ካልተሰራ ትርጉም የለውም።እስከ ዛሬ ትኩረት ባለመሰጠቱ ‹‹ብራንዲንግ›› በኢትዮጵያ ዋጋ አልባ ሆኗል።ሌሎች ግን የኢትዮጵያን ምርት ገዝተው እንደገና ‹‹ሪ-ብራንድ›› አድርገው በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ይሆናሉ።ይህ ባይሆን መልካም ነው።እኔም ገንዘብ ስላለኝ ብቻ በማላውቀው ሙያ መግባት ያልፈለኩት ለዚህም ጭምር ነው ይላሉ ሙያና ሙያተኛ እንዲገናኝ ያላቸውን መሻት ሲገልፁ፡፡
የምፅዋ ትዝታ
እስከ ስድስተኛ ክፍል ብዙም ከቤት መውጣት አይፈቅዱላቸውም ነበር።ግን አባታቸው በእረፍት ወቅት ወደ ምፅዋ ይወስዷቸው ነበር። “ገና ከቤታችን ግማሽ መንገድ ስንሄድ የምፅዋ ሽታ ያውደናል” ይላሉ። በዕዝነ ልቦናቸው ከምፅዋ ዳር ሄድ መለስ እያሉ የልጅነት ጊዜያቸውን ያስታውሳሉ።የባህሩ ሽታ አይረሳቸውም፤ የሰፈሩ ትዝታ ውል ይልባቸዋል።ታዲያ እዚህም እዚያም ያደጉባት አገራቸው ከኤርትራ ጋር በተጋጩ ጊዜ ክፉኛ ማዘናቸውን ያስታውሳሉ።መነጋጋር ቢቻል በሁለቱ ህዝቦች መካከል የነበረው ፍቅርና ሰላም ለሌሎችም ይተርፍ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡
ከትዝታቸው ማዕድ ተዝቆ የማያልቅ ነገር አላቸው።አሁንም ከአባታቸው ጋር ወደ ምፅዋ የተመላለሱበት መንገድ ትዝ ይላቸዋል፤ የውሃው ከፍና ዝቅ የሕይወትን መስመር ያስታውሳቸዋል፤ በምፅዋ ዙሪያ የሰዎች ሽር ብትን ዛሬም በትዝታ ስቅዝ አድርጎ ወሰድ መለስ ያደርጋቸዋል፡፡ አይ ምፅዋ! እያሉ ከልጅነት የትዝታ ማህደራቸው ገፆችን እየነጠሉ ትልቅ የሕይወት ምዕራፍን በሕሊናቸው ይቃኛሉ።
ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ሲታረቁ
የኤርትራ እና ኢትዮጵያ ጉዳይ ሲነሳ የማስበው መጀመሪያም ሁለቱ አገራት መጣላት አልነበረባቸውም።ግን ደግሞ ሲታረቁ የነበረኝ ስሜት ላቅ ያለ ነው።በአውሮፓ ምድር በኢኮኖሚው፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ትስስራቸው የተጠናከረ በመሆኑ አይጋጩም።እኛ ዘንድ ግን ይህ ትስስር ባለመፈጠሩ እየተጋጨን ነው። በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የነበረው ፀብ ብዙም አይገርምም።ምክንያቱ ደግሞ አሁንም በየሰበቡ በየመንደሩ እየተጋጨን ነውና ይላሉ።ይህ በጣም የተሳሳተ አካሄድ ነው።እኛን የሚያወጣን ሥራ ፣ ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት ነው ሲሉም ምክራቸውን ጣል ያድርጋሉ።
የፖሊስ ጣቢያ እና ወጣት ማዕከል የምገነባው
የሙስና እና ፀጥታ ጉዳይ በጣም አሳሳቢ ነው።የደህንነት ችግር ካለ ወደፊት መሄድ አንችልም።ከዳቦ በፊት ሕልውና ይቀድማል።በተለይ ከውጭ ለሚመጡ አልሚዎች ይህ ቀዳሚው ጉዳይ ነው።እኛ መጀመሪያ የተሰጠን ምገባ ማዕከል እንድንገነባ ነበር።ግን ፖሊስ ጣቢያውን መገንባት የፈለግነው ለደህንነት ቅድሚያ ስለምንሰጥ ነው ይላሉ፡፡
ኢንጂነር መንሱር ስለ አገራቸው ሲባል ልባቸው ስስ ነው።እናም ስለ አገር የሚሰጥ ነገር ሰጠሁ አይባልም፤ አገራችን ለእኛ ከምትችለው በላይ ሆናለች የሚል እምነት አላቸው።ታዲያ በአገር ውስጥ ደግሞ የፀጥታ ተቋማት ሚና በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ይገነዘባሉ።ይህንንም ስለሚያስቡ ፖሊስ ጣቢያ እኛ መገንባት አለብን ብለው ነው ወደ ሥራው የገቡት፡፡
ፖሊስ ጣቢያ ስለምን ያረጀ ያፈጀ አሰራር ይከተላል፤ የሰዎችን ሰላምና ደህንነት የሚጠብቁ ፖሊሶች የሥራ ቦታ እና አሰራሩስ ለምን ማራኪ አይሆንም ሲሉም ይጠይቃሉ።ታዲያ ይህም በመሆኑ አሁን እየገነቡት የሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ውብና ማራኪ ለማድረግም እየተጉ ነው ያሉት።
ፖሊስ ጣቢያ ለእኛ ከአደጋ የሚከላከል ተቋም ነው።ፖሊስ ጣቢያ ሰዎች የሚፈሩት ሳይሆን ወደው ጉዳያቸውን የሚፈጽሙበት መሆን አለበት።የሥራ ሥነ-ምህዳሩ ጥሩ የሆነ ፖሊስ ጣቢያ ብቁ ባለሙያዎችንና ዘመናዊ አሰራሮችን ለመተግበር ዕድሉን ይሰጠዋል የሚል አቋም አላቸው።
35 ሚሊዮን ብር ለመከላከያ፣ ህዳሴ ግድብና 90 ቀን ሰው ተኮር ፕሮጀክት
ኢንጂነር መንሱርና ድርጅታቸው አሁን ብቻ ሳይሆን ድጋፍ በተጠየቁ ጊዜ ሁሉ የሚቻላቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል።ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ለአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታና ለሌሎችም 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።ዳሩ ግን አልፎ አልፎ ድጋፍ ሲያደርጉ ለማን ድጋፍ እንዳደረጉ እና ምን እንደተሰራበት በግልጽ ባለማወቃቸው በመስጠታቸው ባይፀፀቱም ብዙ ምቾት አይሰጣቸውም።ብዙ ጊዜ ለድጋፍ ብር ሰጥተን ደረሰኝ ሳይሰጠን ቅር እንሰኛለን ይላሉ።አሁን የመጣው የ90 ቀናት ሰው ተኮር ፕሮጀክት ግን ለእኛ የመጣ ነው።ይህ ኃላፊነት ተሰምቶን የምንሰራውና በዚያው ልክ የምንመሰገንበት ወይንም የምንወቀስበት ይሆናልም ይላሉ፡፡
በ90 ቀናት ሰው ተኮር ፕሮጀክትም በአቃቂ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ለመገንባት ከ12 እስከ 15 ሚሊዮን ብር በጅተዋል።ሁለት የወጣት ማዕከላትን ለመገንባት ደግሞ በጠቅላላው 9 ሚሊዮን ብር በላይ መድበዋል።በአጠቃላይ ለፖሊስ ጣቢያ እና ወጣት ማዕከላት ግንባታ 25 ሚሊዮን ብር ወጪ ለማድረግ እርሳቸው በበላይነት የሚመሩት ድርጅት ወስኖ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አካሄድ
ኢንጂር መንሱር ለዓመታት በኖሩበት እንግሊዝ አገር ብዙ ነገሮችን አይተዋል፤ ልምድ ቀስመዋል።ከምንም በላይ ለነገሮች የሚሰጡት ትኩረትና የተስተካከለ የሥራ አካባቢ ለመፍጠር የሚጓዙበት አካሄድ ብዙ እንደጠቀማቸው ይናገራሉ፡፡
ሰው በሚሰራበትና በሚውልበት ቦታ ጭምር አስተሳሰቡ ይቀረፃል፤ የሚል ዕምነት አላቸው።ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተቋማት ውብ መሆን አለባቸው የሚለውን ፍልስፍናቸውን ኢንጂነር መንሱርም በትልቁ ይጋሩታል።ይህም በመሆኑ ነው ውብ ፖሊስ ጣቢያ እና ሁለት የወጣቶች ማዕከላትን ሙሉ ወጪ እና ዲዛይንና ግንባታ አጠናቆ ለማስረከብ የወሰኑት።ከዚህም በተጨማሪ መስጠት ትልቅ ደስታ ይሰጣል።በተለይም ለአገር የሚሰጥ ነገር ደግሞ ደስታው እጥፍ ነው የሚል እሳቤ አላቸው።በመሆኑም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አካሄድ በሌሎችም ዘንድ ቢዘወተር መልካም አርዓያ ስለመሆኑም ይመሰክራሉ፡፡
የቸገረን ነገር
መንግስት የሰጠንን አደራ ለመወጣት እኛ ጊዜ አናባክንም የሚሉት ኢንጂነር መንሱር ነገር ግን አሁን ለሚያከናውኑት ግንባታ ብዙ ችግሮች ይፈትኗቸዋል።የግንባታ ግብዓቶች በየወቅቱ መጨመርና የገበያው አለመረጋጋት ራስ ምታት ሆኖባቸዋል። እንደ አገርም ይህ የሚያሳስብ ስለመሆኑም መጠቆም ይፈልጋሉ።አንዳንዶች ደግሞ ለዚህ ጉዳይ ድጋፍ አድርጉ እያሉ መምጫቸውና መድረሻቸው ሳይታወቅ አንዳችም ብጣሽ ደረሰኝ ሳይሰጡ ድጋፍ! ድጋፍ! አድርጉ እያሉ ይጨቀጭቋቸዋል፡፡ ይህም ለከት የለሽ ነገር ህጋዊ አሰራር ያልተከተለ ድጋፍ አድርጉ የሚለው ነገር ቢቀር ደስታቸው ነው።
ድርጅታቸው አያሌ ሥራዎችን እያከናወነ ቢሆንም የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት፣ የማስፋፊያ ቦታ ችግር፣ የውጭ ምንዛሪ በሚፈለገው ልክ አለመገኘት ዋንኛ ፈተና ሆኖባቸዋል። በእርግጥ ሁሉም እንደ አገር የመጡብን ችግሮች በመሆናቸውም በሂደት ይቃለላሉ የሚል ተስፋ አላቸው። አገሪቱ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታም የሚጠበቅ መሆኑን ይናገራሉ። ደቡብ ኮሪያ፣ ህንድና የመሳሰሉት አገራትም በዚህ ሂደት ያለፉ ስለመሆናቸው ይጠቁማሉ።ከምንም በላይ ግን ያስቸገራቸው ነገር ባንክ አካባቢ ያለው ‹‹ሴኩሪቲ›› ጉዳይ እንደሆነ ይገልፃሉ።በባንክ አካባቢ ዲጂታል ዘዴ ተጠቅመው የሚያጭበረብሩ አካላት ለሥራቸው ፈተና ሆነውባቸዋል። ከዚህ በተረፈ ግን እንደዚህ መሬት ላይ ወርዶ ለሚሰራ የተሰካ ሥራ ድጋፍ ማድረግ ያስደስታቸዋል።ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፉ ስራዎችም ሕያው ምስክር ይሆናሉና እንኮራባቸዋለን፤ ለልጆቻችንም የመልካም አርዓያ መገለጫ እንሆንበታልን ይላሉ።
ምንም እንኳን አንዳንድ ሙስናና ምቾት የማይሰጡ አሰራሮች ቢጎረብጣቸውም፤ የቢዝነስ ሸሪኮችም መሰል ድጋፎችን ለማድረግ ደስተኞች ናቸው።በተለይም ለነገው ትውልድ በሚሆን ሥራ ላይ ወደኋላ እንደማይሉና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ወጪ ለሚሆን ገንዘብ ሁሌም ዝግጁ ስለመሆናቸውም ይመሰክሩላቸዋል።
የፖሊስ ጣቢያውና የወጣቶች ማዕከል ግንባታ ራሳችን ወጪውን ሸፍነን ራሳችን ፕሮጀክቶቱን መርተን ስለምንሰራው ውጤቱም አስደሳች እንደሚሆን አስባለሁ፤ ሸሪኮቼም ገንዘባቸው የት እንደደረሰ ስለሚረዱት ተቃውሞ የላቸውም ይላሉ። በአሁኑ ወቅት ምርታችን ጥሩ ገበያ እያገኘ ቢሆንም፤ ሌሎች ግን በስማችን መነገድ ጀምረዋል፤ ምንም እንኳን ደንበኞቻችን የእኛን እቃ ለይተው ቢያውቁም። ችግሩ ግን ይህንን ጭምር ለማዛባት የሚተጉ መኖራቸው መሆኑን በማዘን ጭምር ይገልጻሉ፡፡
ዕቅድ
በአሁኑ ወቅት ሥራችን እየሠራን ቢሆን ትልቅ አቅም ያለው ኤሌክትሪክ እንፈልጋለን።ስምንት ሜጋ ዋት አቅም ያለው ኤሌክትሪክ ጠይቀናል።በቀጣይ ብረት ራሳችን አቅልጠን ራሳችን በኮይል የሚመጣውን ብረት አምጥተን አቅልጠን መሥራትና የውጭ ምንዛሪ ማምጣት እንፈልጋለን።በአገሪቱ ውስጥ ትልቅ ኢንዱስትሪ ባለቤት መሆንም ህልማችን ነው።ዘመናዊ ማሽኖችንም ወደ ሥራ ማስገባት የማያባራ ዓላማችን ነው።ወጪ ቆጣቢ ቴክኖሎጂ እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መቀነስ ለይደር የማይተው ጉዳያችን ነው ይላሉ።በአሁኑ ወቅት 200 ሰራተኞች አሉ፤ በቀጣይ ወደ 500 እስከ 600 በማድረስ ቢያንስ የተወሰኑ ዜጎች በእኛ ምክንያት ዳቦ እንዲበሉ እንፈልጋለን ባይ ናቸው።
መልዕክት
ሰውን ከመርዳትና ከመስጠት የሚገኘውን ደስታ ብዙዎቻችን አናውቅም። ወጪውን እንጂ ገቢውን አናሰላም። ይህም በመሆኑ የሚሰጡ እጆች ይስጡ፤ የሚሰሩትም ጥረት ያድርጉ ባይ ናቸው። ታዲያ ይህ ሲሆን አገር ታድጋለች፤ ድህነትም ይጠፋል ይላሉ። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት መቆሙ ብዙ ተስፋ የሚሰጥ ነው። ኢትዮጵያም በሀብት የበለፀገች በመሆኗ ትንሽ እውቀት ከተጨመረ ለሌሎችም መትረፍ ስለሚቻል መትጋት ይገባል የሚለው የማሳረጊያ መልዕክታቸው ነው።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ኅዳር 25/ 2015 ዓ.ም