ብዙ የሥነ ጽሑፍ ሰዎችን አከራክሯል። በሥነ ጽሑፍ መድረኮች ሁሉ ስሙን ማንሳት ግዴታ የሆነ ይመስል ስሙ ይጠራል። ስሙ ተደጋግሞ የሚጠራበት ምክንያት ደግሞ ‹‹አማርኛው ይከብዳል›› የሚል ነው።
የሥነ ጽሑፍ አብዮተኛው ዳኛቸው ወርቁን ዛሬ ልናስታውሰው ነው። ዳኛቸው ወርቁ በአጻጻፉ ብቻ ሳይሆን በግለሰባዊ ባህሪውም አፈንጋጭ ነው ይባላል። ፈላስፋ ነው። ከዘመኑ ቀድሞ የሚያስብ ነው።
ሐዲስ አለማየሁ እና ዳኛቸው ወርቁ የሚደነቁበትና የሚታወሱበት ምክንያት፤ በዚያ የፊውዳል ዘመን፣ በዚያ ወግ አጥባቂ ማህበራዊ ሕይወት ውስጥ፣ በዚያ ልማዳዊ ነገሮች አይነኬ በሆኑበት ዘመን ውስጥ ሆነው ‹‹ጉዱ ካሳ (ካሳ ዳምጤ)›› እና ‹‹አደፍርስ›› የተባሉ ገጸ ባህሪያትን ፈጥረው አዲስ የባህልና ፖለቲካ አብዮት መቀስቀሳቸው ነው።
ለዛሬው የምናስታውሰው 28 ዓመታትን ወደ ኋላ መለስ ብለን የአደፍርስን ደራሲ ዳኛቸው ወርቁን ነው። አደፍርስ የመጽሐፉ ስም ሲሆን ዋና ገጸ ባህሪው አደፍርስ የተባለው ተራማጅ አስተሳሰብ የያዘ ፈላስፋ ነው።
ዳኛቸው የተወለደው ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ዘመን በ1928 ዓ.ም ነው። አባቱ አቶ ወርቁ አውሮፓ ኖረው ስለነበር ለቀለም (ዘመናዊ ትምህርት) ከፍ ያለ ግምት የሚሰጡ ሰው ነበሩ። ከ1936 ዓ.ም. እስከ 1942 ዓ.ም. ድረስ በተወለደበት አካባቢ፣ በደ ብረ ሲና፣ አብዬ ትምሕርት ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምሕርቱን ተከታተለ። በዚያም ሳለ ገና በአሥራ ሦስት ዓመቱ «ያላቻ ጋብቻ ትርፉ ሐዘን ብቻ» የተሰኘች ተውኔት ደርሶ ተውኗል።
በ1943 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንዲሁም በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤቶች ተማረ። በዚህ መሐል ግን ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ደብረ ሲና በመመለስ ልዩ የነበሩትን የአባቱን ሃሳቦች እና የእናቱን የማለዳና የምሽት ተረኮች ማዳመጥ ላይ አተኮረ። ወደ ሥነ ጽሑፍ የሚወስደውን መንገድ እንዲያውቅ ያደረጉትም እነዚህ ከወላጆቹ የቀሰማቸው ዕይታዎችና ትረካዎች እንደሆኑ ታሪኩ ያስረዳል። ሳይሳካለት ቀረ እንጂ ዳኛቸው ከእናቱ አንደበት የቀዳቸውን ተረቶች እየሰነደ የማሳተም ራዕይ እንደነበረው ይነገራል።
ዳኛቸው ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ወደ ደብረ ብርሃን ሄዶ መኖር ጀመረ። ‹‹ሰው አለ ብዬ›› የተሰኘውን ተውኔቱን የጻፈውም በዚህ ወቅት ነበር። ተውኔቱ የታተመው በ1950 ዓ.ም ነው። ዳኛቸው ትምህርቱን ለመቀጠል ወደ አዲስ አበባ ቢመለስም በሕመም ምክንያት መቀጠል ሳይችል ቀርቶ ወደ ደብረ ሲና ተመለሰ። ከሕመሙ ካገገመ በኋላ ያቋረጠውን ትምህርቱን ለመቀጠል ወደ አዲስ አበባ ቢመለስም በድጋሚ በመታመሙ ምክንያት ወደ ቤተሰቦቹ ተመለሰ። ከዳነ በኋላም የመምህርነት ሥልጠና ወስዶ በመመረቅ በአዲስ አበባና በሐረር አስተማረ። በዚህ ጊዜም ‹‹ሰቀቀንሽ እሣት›› የተሰኘ ትያትር ደርሶ እንዲታይ አደረገ። በተለያዩ ጋዜጦች ላይም ስላነበባቸው መጻሕፍት ምልከታዎቹን ለማስነበብ በቃ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (በወቅቱ ስያሜው ‹‹ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ››) ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ለማስተማር ሲወስን፤ ዳኛቸው ከመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች መካከል አንዱ ሆነ። በ1953 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን መማር ጀመረ። የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሳለ በዩኒቨርሲቲው በረዳት መምሕርነት አገልግሏል። ከዩኒቨርሲቲው ተመርቆ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በወቅቱ የተማሪው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ ከዘመነኞቹ የኮሌጁ ገጣሚዎች ከነታምሩ ፈይሳ፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ አበበ ወርቄ፣ ይልማ ከበደ፣ ኢብሳ ጉተማ፣ ኃይሉ ገብረዮሐንስ፣ መስፍን ሃብተማርያም፣ … ጋር እንደ «ወጣቱ ፈላስማ» በመሳሰሉ ግጥሞቹ የለውጥ ሃሳቡን ያስተጋባ ገጣሚም ነበር። በአራት ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታውም ‹‹እምቧ በሉ ሰዎች›› በሚል ርዕስ የተሰባሰቡ ትግል ቆስቋሽ ግጥሞችን ጽፏል።
በ1956 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቆ ከ1957 ዓ.ም. እስከ 1961 ዓ.ም. ድረስ እዚያው ዩኒቨርሲቲው ውስጥ በመምህርነት ያገለገለ ሲሆን «ትበልጭ» የተሰኘ ተውኔት ጽፎ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ለመድረክ አብቅቷል። በመቀጠልም ለተጨማሪ ትምህርት ወደ አሜሪካ አቀና። በ1962 ዓ.ም. በአሜሪካ ኦሃዮ ዩኒቨርሲቲ ‹‹የፈጠራ ሥነ ጽሑፍ አጥንቶ በመመረቅ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ›› የሚል ማዕረግ አገኘ።
ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ እስከ 1965 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋ መምህርነት አገለገለ። ዳኛቸው ከነጌታቸው ኃይሌ፣ አብርሃም ደመወዝ፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ ኃይሉ ፉላስ … ጋር በመሆን ‹‹የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል››ን ያደራጀ እንዲሁም ወጣት የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎችን በማፍራት አስተዋጽዖ ያደረገ ምሁር ነው።
ዳኛቸው ባነሳቸው በሳል የለውጥ ሃሳቦችና የተራቀቀ ሥነ ጽሑፋዊ የአቀራረብ ስልት የተደነቀውን፣ የኢትዮጵያን የዘመናዊ ልብ ወለድ ሥነ ጽሑፍ በእድገት ምዕራፍ ያሸጋገረውንና «አደፍርስ» የተሰኘውን ልብ ወለድ መጽሐፉን በ1962 ዓ.ም. በማሳተም ታላቅ ጠቢብነቱን አስመስክሯል።
‹‹አደፍርስ›› ብዙ የተነገረለትና ዛሬም ድረስ አነጋጋሪ የሆነ መጽሐፍ ነው። ከዳኛቸው ጋር በቅርበት የሚተዋወቁት ደራሲ ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም ‹‹ዳኛቸው ወርቁና መጽሐፎቹ›› በተሰኘ ጽሑፋቸው ‹‹ … ‹አደፍርስ› በርካታ ምሁራንን በሰፊው ያነታረከ መጽሐፍ ስለሆነ እኔም ተጨማሪ ንትርክ ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ አይደለሁም። ስለምንነቱ ጥቂት ሳልል ግን ለማለፍ አይቻለኝም። ‹አደፍርስ› በሌሎች ልብ ወለዶች የምናየው ዓይነት አንድ ወጥ የሆነና የጐለበተ ፈጠራ ታሪክ የለውም። በዚህ ፈንታ ቁርጥራጭ ትርኢቶች ነው የሚታዩበት። ትረካውን ይፋትንና ጥሙጋን ከጣርማ በር ተራራ ላይ ሆነው ሲመለከቱት ምን እንደሚመስል የሙዚቃ ቃና ባለው ቋንቋ ይጀምራል … በዚህ ክፍል ያለው ድንቅ ትርኢት በመድረክ ላይ የሚታይ ትርኢት እንጂ ሌላም አይመስል። ታሪኩ በዚሁ ይቀጥላል ብለን ስንጠባበቅ ሳለን የመድረኩ መጋረጃ ተዘግቶ ይከፈትና ሌሎች ባህርያት ሲጨዋወቱ እናያለን … ከዚህ ቀደም እንዳልኩት መጽሐፉ ከልብ ወለድነት ይልቅ ወደ ድራማነት የተጠጋ ነው … አንዳንዴ አስቸጋሪ ቢሆንም በውብ ቋንቋ የተደረሰ ድራማ።
‹‹አደፍርስ›› የአማርኛ ሥነ ጽሑፍን ካደፈረሱ ልቦለዶች አንዱ ሆነ፤ አዲስ መንገድ ይዞ መጣ፤ መንገዱ ከተለመደው ያፈነገጠ የሆነባቸው (የመሰላቸው) ወገኖች ክፉኛ ተቹት፤ የነቀፌታ አለንጋቸውን ሰነዘሩበት። ‹‹ለሙያው ቅርብ ነን›› የሚሉ ጸሐፍት እንኳን በ ‹‹አደፍርስ›› ሰበብ ወዳጅነታቸው ደፈረሰ። ‹‹ልብ ወለዱ ድንቅ ነው›› የሚሉ ሁሉ ተወገዙ። የመጽሐፉ አከፋፋይ ‹‹የመጽሐፉ ዋጋ ተወደደ … ቋንቋውም ከባድ ነው›› ብሎ ለዳኛቸው ነገረው። ዳኛቸውም ‹‹ … ‹ዋጋው በዛ፣ ተወደደ› ባይሉ ኖሮ አልጨምርም ነበር … እስካሁን ድረስ አንባቢውን ለማበረታታት ብዬ ነው አምስት ብር፣ አሥር ብር ስል የቆየሁት፤ አሁን ግን የመጽሐፉ ትክክለኛ ዋጋ ባይሆንም፤ የሚፈልገው ብቻ በእጁ እንዲያስገባው …›› ብሎ የመጽሐፉን ዋጋ 15 ብር አደረገው። በዚህ ድርጊቱ ብዙዎች ተገረሙ። ዳኛቸው በዚህ ብቻ ሳያበቃ አከፋፋዩን ‹‹መጽሐፎቼን ከዚች ደቂቃ ጀምሮ መሸጥ አቁም። አሁን ጥቂት ቀናት እሰጥሃለሁ። ያሰራጨሃቸውን መጽሐፍት በአስቸኳይ ሰብስበህ አስረክበኝ!›› ብሎ አዘዘው።
ዳኛቸውም መጽሐፎቹን ይዞ ወደ ቤቱ ገባ፤ ይህም ዜና በየአንባቢው ጆሮ ገባ። አንዳንዶች ግን ‹‹መጽሐፎቹን ሰብስቦ አቃጠላቸው›› ብለው አስወሩ፤ ጻፉም፤ እውነቱ ግን ይህ አልነበረም። በሕዝቡ ምላሽ ያልተደሰተው ዳኛቸው መጽሐፉን ሰብስቦ ቤቱ አስቀመጠው እንጂ አላቃጠለውም። እነደራሲ ሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም እንኳን ዳኛቸው መኖሪያ ቤት ሄደው ነው አንዱን ቅጂ በ15 ብር የገዙት።
እንደ አቤ ጉበኛ ያሉ ደራሲዎች ደግሞ የልቦለዱ ረቂቅነት በፍጹም ሊዋጥላቸው ስላልቻለና መጽሐፉ በአንዳንድ ምሁራን ዘንድ እየተሰጠው ያለው አስተያየት ደስ ስላላሰኛቸው ለ‹‹አደፍርስ›› የመልስ ምት የሚሆንና ‹‹ጐብላንድ አጭበርባሪው ጦጣ›› የተባለ መጽሐፍ ጽፈው እስከማሳተም ደርሰው እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል። ‹‹ተሳላቂ ነው›› የተባለለት ይህ ድርሰት ‹‹በዳኛቸው ‹አደፍርስ› እና በሰለሞን ደሬሳ ‹‹ልጅነት›› ላይ ያነጣጠረ ነው›› ይባላል።
ስለ ‹‹አደፍርስ›› ከተፃፉ ሂሳዊ ጽሑፎች መካከል በአንዱ ላይ እንዲህ ተብሎ ተጠቅሷል። ‹‹ … አደፍርስ ደፋር ነው፤ ሃይማኖትን ይሞግታል፤ ነባር አሰራርን ይቃወማል። ዓላማው የተኙትን ለማንቃት ነው፤ ማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ደዌ ለመንቀል። ግን ይጋጫል፤ በየሄደበት የነገር እንካ ሰላንቲያ ይከፍታል፤ ለብዙ ዘመናት ጸንቶ የቆየውን ሃይማኖታዊ አካሄድ በዜሮ ሊያባዛው ይፈልጋል … ››
የዳኛቸው ወርቁ ሌላው ዐቢይ ሥራ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ደርሶት እንግሊዝ አገር የታተመውና ‹‹The Thirteenth Sun›› የተሰኘው መጽሐፍ ነው። ይህ ስራው በብዙ የአውሮፓውያን ቋንቋዎች ተተርጉሞ ታትሟል። የትውልድ የአስተሳሰብ ግጭት የዚህ መጻሕፍ ፈትለ ነገር ነው። ደራሲ ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም እንደፃፉት፣ መሠረተ ሃሳቡ ከ‹‹አደፍርስ›› ጭብጥ እጅግም የራቀ አይደለም። በጥንታዊት ኢትዮጵያ አስተሳሰብና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ አስተሳሰብ (በቀድሞው ትውልድ እምነትና በዛሬው ትውልድ አመለካከት) መካከል ባለው ግጭት ላይ የተገነባ ልብወለድ ነው። ‹‹በእኔ አስተያየት በትረካው ረገድ ‹The Thirteenth Sun› ከ‹አደፍርስ› ላቅ ያለ ሲሆን በቋንቋው ውበት ግን ‹አደፍርስ› ይበልጣል›› ብለዋል። መጽሐፉ እስከዛሬ ድረስ በታላላቅ የምዕራባውያን የፈጠራ ጽሑፍ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በማስተማሪያነት እያገለገለ ይገኛል። ይህ ድርሰት የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ በዓለም አቀፍ መድረክ ያስተዋወቀ ስራ ነው።
ከአምሳሉ አክሊሉ (ዶክተር) ጋር በመሆንም ‹‹የአማርኛ ፈሊጣዊ ንግግሮች›› የሚል (ከሁለት ሳምንት በፊት እዚሁ ጋዜጣ ላይ የሰራነው ማለት ነው) እጅግ ጠቃሚ መጽሐፍ ጽፈው ለቋንቋው እድገት ከፍ ያለ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ‹‹የጽሑፍ ጥበብ መመሪያ›› የምርምር መጽሐፍም ጽፎ በበርካታ ቅጂዎች ታትሟል። ከዚህ ባሻገርም ለሀገሪቱ ቋንቋ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ባላቸው «የማርክሲዝም ሌኒንዝም መዝገበ ቃላት» እና «የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት» በመሳሰሉ ጥልቅና ምጡቅ ሥራዎች ዝግጅት ላይ በመሳተፍ ምሁራዊ ግዴታውን የተወጣ ኢትዮጵያዊ ነው።
ዳኛቸው ከመጽሐፍቱ በተጨማሪ በወቅቱ ይታተሙ በነበሩት ‹‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ››፣ ‹‹የኢትዮጵያ ድምጽ›› እና ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጦች ላይ የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ የተመለከቱ ስራዎችን በማቅረብና የወጣት ደራሲያን ሥራዎችን በመሔስ ለሀገሪቱ ሥነ ጽሑፍ ዕድገት ምሁራዊ ኃላፊነቱንና ተልዕኮውን ተወጥቷል።
ዳኛቸው በባህርይው ለየት ያለ እንደነበር ወዳጆቹ ሁሉ ይናገራሉ። ‹‹አፈንጋጭና የተለየ ነው›› ይሉታል። በቀላሉ ተግባቢ አይደለም። ከጥቂት ደራስያን በቀር ከብዙዎች ጋር የሚግባባ አይደለም፤ በራሱ ላይ የዘጋ፤ ከሕዝብ ጉባዔ ተነጥሎ ለብቻው ሱባዔ የገባ ሰው ነው። የሀገሩን እምነትና ባህል ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ለሥራ ነገን የማያውቅ፣ ለውጥ ፈላጊ፣ አገር ወዳድ፣ ስለሀገር ኋላ ቀርነት ሁሌ የሚቆረቆር ነው።
እንግዳ ባህርይውን ተቋቁመው፣ የጓደኝነት ድንበር ሳይጥሱ ከልብ የቀረቡት ደግሞ ‹‹… ሊያጡት የማይገባ፣ የዕውቀት ሎሌ ነው። ለወዳጅነት የተከፈተ ልብ ያለው ሰው ነው … ዳኛቸው ለሀቅ ሽንጡን ገትሮ ስለሚከራከር ከውሸት ጋር ማኅበር ከሚጠጡ፣ ፅዋ ከሚያነሱና ብርጭቆ ከሚያጋጩ ጋር ሕብረት አልነበረውም … ቀጠሮ ሰጥቶ በቀጠሮው ቦታና ሰዓት የቀጠረው ባለጉዳይ በተባባሉት ሰዓትና ቦታ ካልተከሰተ አምስት ደቂቃ እንኳ ሣይታገስ ወደ ጉዳዩ ይሄዳል … አንድ ወዳጁ በሌላው ላይ ሴራ ሲጠነሰስ ከተመለከተ ወይም ‹እየጠነሰሰ ነው› ብሎ ከጠረጠረ ተራራ በሚያክል ኩርፊያ ያስተናግደው ይሆናል …›› ይሉታል።
አንጋፋው ደራሲ ሰለሞን ደሬሳ ‹‹ … ከእኔ ጋር ወዳጆች ነበርን። ‹ልጅነት› ታትማ ስትወጣ በመጠኑ ቁጣ ወረደባት የማስታውሰው የምስጋና ጽሑፍ ያገኘሁት ከዳኛቸው ወርቁ ብቻ ነው። የደረሰኝ የምስጋና ጽሑፍ የቄስ ጽሕፈት ይመስል ነበርና የእሱ መሆኑን ያወቅሁት በኋላ ስንቀራረብ ነው፤ አልፈረመበትም ነበር። እንደአጋጣሚ ደግሞ ‹አደፍርስ›ን አግኝቼ ሳነብ ነበር ‹ማነው ‹ልጅነት›ን የጻፈው?› ብሎ ሲፈልግ የተገናኘነው። በጣም በጣም ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሣይሆን የትም ቦታ ከማደንቃቸው ጸሐፊዎች ዳኛቸው አንዱ ነው – በሁሉም ሳይሆን በ‹አደፍርስ› እና በ‹The Thirteenth Sun› በማለት ስለነበረው ባህርይና ችሎታ ይናገራል።
ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ደግሞ ‹‹ … አማርኛ ስሜትን የመግለጽ አቅም እንዳለው ዳኛቸው ወርቁ አሣይቶኛል … ይገርመኛል! ዳኛቸው ለብዙዎች እሾህ ነበር፤ እሾህ መልኩን እሾህ ገጹን ነው የሚያሳያቸው፤ ወይም ያሳየናል የሚሉት፤ ለእኔ ግን ጽጌረዳ ውበቱን ጽጌረዳ መልኩን ነው ያሳየኝ፤ ተመቻችተን ነበር፤ ልብ ለልብ ተግባብተን፤ ነፍስ ለነፍስ ተዋደን ነበር›› በማለት ስለዳኛቸውና ስለወዳጅነታቸው ተናግሮ ነበር።
‹‹አደፍርስ›› ልብ ወለዱ ከዩኒቨርሲቲው አካዳሚ ጋር ግንኙነቱን ያደፈረሰበት ደራሲ፣ የሥነ ጽሑፍ መምህር፣ ገጣሚ እና የተውኔት ጠቢብ ዳኛቸው ወርቁ፣ ዩኒቨርሲቲውን ለቆ መጀመሪያ በጥቁር አንበሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ኋላ ደግሞ በፈረንሳይ ኮሌጅ እስከ 1966 ዓ.ም. የአማርኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ አስተማረ። በኋላም በኢትዮጵያ ደረጃዎች መዳቢ ድርጅት በትርጉም አዋቂነት፣ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነትና በኢንዱስትሪ ፕሮጀክት አገልግሎት ሹምነት ለ15 ዓመታት ያህል አገልግሎ፣ በ1983 ዓ.ም. ጡረታ ወጣ። ኅዳር 22 ቀን 1987 ዓ.ም. በድንገት አርፎ ሥርዓተ ቀብሩ በተወለደበት ደብረ ሲና ከተማ ተፈጽሟል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 25/ 2015 ዓ.ም