በአገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚሳተፉ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የሚካፈሉበት የአፍሪካ አገራት ቻምፒዮን ሺፕ (ቻን) በመጪው የፈረንጆቹ ዓመት ለሰባተኛ ጊዜ ይካሄዳል። የውድድሩ አዘጋጅ ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር አልጄሪያ ስትሆን፤ በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ወር ይጀመራል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በበላይነት የሚመራው ይህ ውድድር 18 ቡድኖችን ያሳትፋል። በዚህ ውድድር ተካፋይ መሆናቸውን ካረጋገጡ አገራት መካከልም አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ ይታወቃል።
ቻን የአገር ውስጥ ሊጎችን ከማሳደግም ባለፈ የእግር ኳስ በቂ ችሎታ እና አቅም እያላቸው በአገር ውስጥ ክለቦች ብቻ የተወሰኑ ታዳጊና ወጣት ተጫዋቾች ለሌላው ዓለም የመታየት ዕድልን የሚያስገኝ ውድድር ነው። አዘጋጇን አገር አልጄሪያን ጨምሮ በየቀጠናው በተከናወኑ የማጣሪያ ውድድሮች፤ ሞሮኮ፣ ሊቢያ፣ ሴኔጋል፣ ሞሪታኒያ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ጋና፣ ኮትዲቯር፣ ኮንጎ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ ካሜሩን፣ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ማዳጋስካር፣ አንጎላ እና ሞዛምቢክ አልፈው ውድድራቸውን ለማድረግ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
አገራቱ በአምስት ምድብ የተከፈሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከአዘጋጇ አልጄሪያ፣ ሊቢያ እና ሞዛምቢክ ጋር ተደልድላለች። ይህንን ተከትሎም ቡድኑ ቅድመ ዝግጅቱን ለመጀመር አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለተጫዋቾቻቸው የመጀመሪያ ዙር ጥሪ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በመጪው ጥር ወር/2015ዓም ለሚካሄደው ውድድር ቅድመ ዝግጅት እንዲረዳ እና ተጫዋቾች በየክለባቸው በውድድር ላይ እያሉ ተገቢውን ክትትል እና ዝግጅት ለማከናወን እንዲረዳ እጩ የተጫዋቾች ዝርዝር ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም አሰልጣኙ ለ42 ተጫዋቾች ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ በቀጣይ ደግሞ የ28 ተጫዋቾችን ዝርዝር እንደሚያሳውቁ እና እጩ ተጫዋቾችም የዝግጅት ጊዜው እስኪጀምር ድረስ አቋማቸውን በመጠበቅ ውድድራቸውን እንዲያከናውኑ አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር እስከ ታህሳስ 17/2015ዓም እየተካሄደ እንደሚቀጥል በመሆኑ፤ ብሄራዊ ቡድኑ ከታህሳስ 18/2015ዓም ጀምሮ ለቻን ውድድር ቅድመ ዝግጅቱን የሚጀምርም ይሆናል።
በተጫዋቾች ዝርዝሩም መሰረት ባህርዳር ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ መቻል ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ድሬዳዋ ከተማ ግብ ጠባቂዎችን ማስመረጣቸው ታውቋል። በተከላካዮች በኩል ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አራት ተጫዋቾችን፤ ፋሲል ከነማ፣ ሃድያ ሆሳዕና እና ባህርዳር ከተማ ሁለት ሁለት እንዲሁም ሲዳማ ቡና አንድ ተጫዋች ተመርጠዋል። አማካዮች ደግሞ ከፋሲል ከተማ ሶስት፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ሲመረጡ፤ ከኢትዮጵያ ቡና፣ መቻል፣ አዳማ ከተማ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ሲዳማ ቡና እና ባህርዳር አንድ አንድ ተጫዋቾቻቸው በዝርዝሩ ላይ ተካተዋል። በአጥቂ በኩል መቻል፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ ሁለት ሁለት ተጫዋቾቻቸውን፣ ሲዳማ ቡና፣ አዳማ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ ባህርዳር ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ደግሞ አንድ አንድ ተጫዋቾቻቸውን በብሄራዊ ቡድኑ ተካተውላቸዋል።
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመሩት ዋሊያዎቹ በማጣሪያ ጨዋታዎች (በምስራቅና መካከለኛው ዞን) የደቡብ ሱዳን እና ሩዋንዳ አቻውን በመግጠም አንድም ግብ ሳያስተናግድ ነገር ግን 6 ግቦችን አስቆጥሮ ወደ መድረኩ እአአ ከ2016 በኋላ ዳግም መመለሱ ይታወቃል። ኢትዮጵያ ለቻን ስታልፍ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን፤ እአአ በ2014 እና 2016 ተሳትፎዎቿ ከምድቧ ማለፍ አልቻለችም ነበር። አሁን ግን ቡድኑ ከቀደሙት ሁለቱ ተሳትፎዎቹ የተሻለ ውጤት የማስመዝገብ ሃላፊነት እንዳለበት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በቅርቡ ውላቸውን ባደሱበት ወቅት በፌዴሬሽኑ በኩል እንደተጣለባቸው የሚታወስ ነው።
በየሁለት ዓመቱ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ሞሮኮ እአአ የ2018 እና 2020 በተከታታይ ቻምፒዮን የሆነች ሃገር ናት። የቻን ውድድር ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳታፊዎችን ቁጥር አሳድጎ በ18 ብሄራዊ ቡድኖች መካከል ከጥር 5 -27/2015 ዓ.ም ድረስ የሚከናወን ይሆናል። በኳታሩ ዓለም ዋንጫ ከምድቧ ማለፍ ያልቻለችው አልጄሪያ ለዚህ ውድድር ማካሄጃነት አራት ስታዲየሞችን አዘጋጅታለች።
አዲስ ዘመን ህዳር 23/2015