ድንጋይ ይመስላል፤ የተፈለጠ ድንጋይ፤ በውስጡ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኝ ውድ ሀብት የያዘ ነው ብሎ ለመገመት ጥቂትም ቢሆን ስለከበሩ ማዕድናት ግንዛቤ ያለው ሆኖ መገኘትን ይጠይቃል።
ከላይ የሚታየው የማእድኑ ነጩ ክፍል ቶሎ እይታ ውስጥ ይገባል፤ ዋናው፣ አብረቅራቂው፣ ደማቅ የወይን ጠጅ ቀለም ያለው ቀልብን በእጅጉ የሚስበው የማእድኑ ክፍል ግን ከውስጥ ነው ያለው። ይህ አብረቅራቂ የከበረ ማዕድን እሴት ተጨምሮበት ለቀለበትና ለአንገት ጌጣጌጥ ፈርጥ አገልግሎት እንዲውል ተደርጎ ለገበያ ተዘጋጅቶም እዚያው ተመለከትኩ።
ይህንና ሌሎችንም የከበሩ ማዕድናትን በጥሬውና እሴት ጨምረው ለውጭ ገበያ በማቅረብ በላኪነት ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ መሐመድ ነዚብ አብረቅራቂው የወይን ጠጅ ቀለም ያለው ይህ የማእድን አይነት አመቲስት እንደሚባልና በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ሻኪሶ እንደሚገኝ ይገልጻሉ። የሻኪሶ ምድር ጋርኔት የሚባል ማእድን መገኛም ነው።
በአካባቢው ስም የተሰየመውን የወሎ ኦፓልና ኤመራልድ የተባለውን ማዕድንም አቶ መሐመድ በጥሬውና እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ። አማራ ክልል ደላንታ አካባቢ የሚገኘው ኦፓል በሌላው የዓለም ክፍልም ይታወቃል።
አቶ መሐመድ ኢትዮጵያ በምድር ውስጥ በርካታ በረከቶች እንዳሏት የበለጠ ግንዛቤ ያገኙት የማእድን ሀብቱን በመላክ ሥራ ላይ ከ15 ዓመታት በላይ በቆዩባቸው ጊዜያቶች እንደሆነ ይገልጻሉ። ‹‹የማዕድን ሀብቱ ሻኪሶ ቦረና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች በስፋት ይገኛል። በማህበረሰቡ ውስጥ በቂ ግንዛቤ ባለመኖሩ ጥቅም ላይ ውሎ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ የማዕድን ሀብት እንደዋዛ እየታየ ነው። እየረገጥነው፤ እየሄድንበት ነው ሲሉም በቁጭት ይናገራሉ።
ልማቱ የሚከናወነው ስለማዕድን ሀብት ሰፋ ያለ ግንዛቤና እውቀቱ ባላቸው እንዳልሆነና በዘመናዊ መሳሪያ ወይንም ቴክኖሎጂ አለመታገዙን ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳም አልሚውም ሆነ በውጭ ገበያ ላይ የተሰማራው በሚፈለገው ልክ ተጠቅሞ ራሱንም ሆነ የአገር ኢኮኖሚን በሚያሳድግ መልኩ ውጤት እንዳላስገኘ ያስረዳሉ።
በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የማዕድን ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ላይ ያዩዋቸው አገር በቀል የወርቅ ማጠቢያና እና ሌሎችም ማሽኖች ለልማቱ ተስፋ የሚሰጡ ሆነው እንዳገኙዋቸውም ተናግረው፣ ወደፊት በዘርፉ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻልም ይናገራሉ።
አቶ መሐመድ በአልሚውና በላኪው መካከል የሚደረገው ግብይትም በድርድር እንደሚፈጸም ገልጸዋል። እስካሁን ባላቸው ተሞክሮም ይህን አይነቱን ግብይት የሚያካሂዱት በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ ከህንድ ከሚመጡ ደንበኞቻቸው ጋርም ነው። ወደፊት ወደተለያዩ የዓለም አገራት ገበያ በማፈላለግ ምርቱን ለማቅረብ የተዘጋጁትም በዚሁ የድርድር ሥርአት ነው።
ነፃ የገበያ ሥርአት የተከተለው ግብይት ምርቶችን በውድ ዋጋ በመሸጥ የተሻለ ገቢን በማስገኘት ጥቅሙ የጎላ መሆኑን አቶ መሀመድ ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ የማዕድን ሀብት በሌላው ዓለም ተፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ የመነሻ ዋጋ ሳይኖረው በድርድር ለውጭ ገበያ ማቅረቡ ግን ጉዳቱ እንደሚያመዝን ነው ያስገነዘቡት።
በአገር ደረጃ የመነሻ መሸጫ ዋጋ እንደሚያስፈልግ ለውጭ ገበያ በማቅረብ በሥራው በቆዩ በአንዳንድ የከበሩ ማዕድናትና ጌጣጌጥ ላኪዎች በቅሬታ ይነሳ እንደነበር ይታወሳል። በዚሁ ጉዳይ ላይ ከወራት በፊት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር መድረክ ከነበራቸው ላኪዎች ጋር በተደረገ ውይይት የከበሩ ማዕድናትና ጌጣጌጥ በአገር ደረጃ የመሸጫ መነሻ ዋጋ መውጣት እንዳለበት ስምምነት ላይ መደረሱም ይታወቃል።
በላኪነት ዘርፍ ላይ የተሰማሩት ሌላው ያነጋገርናቸው ቡምሪንግ የተባለ የማዕድንና ጌጣጌጥ ላኪ ኩባንያ ባለቤት አቶ መከተ ላቀው በአውስትራሊያ ዳይመንድ የተባለውን የማዕድን አይነት ለጌጣጌጥ በማዋል ሰፊ ተሞክሮ ባለው ኩባንያ ውስጥ ሰርተዋል፤ በዘርፉም ተሞክሮ ማካበት ችለዋል።
ወደ አገራቸው መጥተው ዘርፉን ከተቀላቀሉም ሁለት ዓመታት ሆኗቸዋል። ዘርፉን ሊያግዝ የሚችል የቴክኖሎጂ ትምህርትም እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ መከተ፣ ልምድና ክህሎታቸውን ብቻ አይደለም ይዘው ወደ አገር ቤት የመጡት። በአውስትራሊያ ይሰሩበት በነበረው ኩባንያ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውለውን ከመሬት ውስጥ ተቆፍሮ የወጣውን ማዕድን ፖሊሽ ወይንም ማዕድኑን ብቻ ጥርት አድርጎ በቅርጽ የሚያወጣና ለመቁረጫ አገልግሎት የሚውሉና ሌሎችንም ለማዕድን ሥራ የሚያገለግሉ መለስተኛ መሣሪያዎች ይዘው በመምጣት ነው ኩባንያቸውን ያቋቋሙት።
ወደ አገራቸው ይዘው የመጡትን ተሞክሮ፣ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ለራሳቸው ብቻ አልተጠቀሙም፤ በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ላይ ለሚገኙ በማካፈል ጭምር ዘርፉ በጋራ እንዲያድግ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ። በተለይም ተሞክሮን የማካፈል ፍላጎት እንዳላቸውና ብዙ ጊዜያቸውንም ለእዚህ አላማ እንደሚያውሉ ይናገራሉ።
በነዚህ ዓመታትም አጌት፣ የወሎ ኦፓል፣ አጃራ፣ ኦብሲዲያ ኤመራልድ ሩቢ ሳፋየርና ሌሎችም ለጌጣጌጥ የሚውሉ ማዕድናትን ለጌጣጌጥ በሚውል መልኩ በማዘጋጀት ወይም ፖሊሽ በማድረግና እሴት የተጨመረበት ጌጣጌጥ ለውጭ ገበያ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ በአውስትራሊያ የማዕድን ልማትና እሴት የተጨመረበት ምርት ለገበያ ለማቅረብ ያለው ሂደት ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው አሰራር ጋር ፍጹም ይለያል። በአውስትራሊያ አልሚው በልማቱ ሥራ ላይ እንዳይጎዳ ከሚደረገው የጉዳት መከላከያ ጥንቃቄ ጀምሮ ልማቱ በቴክኖሎጂ ታግዞ ነው የሚከናወነው። በአልሚው በቁፋሮ የተገኘው ማዕድንም ፖሊሽ የሚሆነው በዘመናዊ መሳሪያ በመታገዝ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ልማት ከባህላዊ አሰራር የተላቀቀ እንዳልሆነ ነው በአጭር የሥራ ቆይታቸው የታዘቡት።
ዘርፉ በዘመናዊ አሰራርና በዘርፉ ባለሙያዎች እንዲከናወን ማድረግ አሁንም አልረፈደበትም የሚሉት አቶ መከተ፣ እርሳቸውም በሥራና በትምህርት በውጭ አገር ያገኙትን ተሞክሮ ይዘው ወደ አገር ቤት በመምጣት በሥራው ሲሰማሩ ለውጥ ለማምጣት ከራሳቸው ለመጀመር በማሰብ እንደሆነ ነው ያጫወቱን።
የማእድን አልሚው ደህንነት መጠበቅ እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ። የአልሚው ደህንነት ካልተጠበቀ ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት ያስገኛል ተብሎ የሚጠበቀውን ገቢ ለማግኘት እንደሚያስቸግር ነው የገለጹት።
እርሳቸው እንዳሉት፤ በማዕድን ፍለጋ ወቅት በሚከናወነው የቁፋሮ ሥራ በሚያጋጥም የተራራ ናዳ እና በሌሎችም ከሥራ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች አልሚው ለጉዳት ሊዳረግ ይችላል። በዚህ ረገድ መንግሥት ልማቱ በሚከናወንበት አካባቢ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በመሥራት ንቃተ ህሊናን ከፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህ ካልሆነ ገንዘቡን ይዞ ወደ ልምቱ የሚገባው ባለሀብትም ቢሆን ለደህንነት ትኩረት አይሰጥም። በነበረው ነው የሚቀጥለው።
የማዕድን ልማቱም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ካልታገዘ ማዕድኑ ይሰባበራል። ይህ ደግሞ የጥራት መጓደል ያስከትላል። ማዕድኑ በቁፋሮ ሲሰባበር መጠኑ ያነሰ ምርት ነው የሚገኘው። በዚህ ወቅት መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት እነዚህን ሁሉ ክፍተቶች የሚቀርፍ እንደሚሆን ተስፋ አድርገዋል።
አቶ መከተ ኩባንያ በማቋቋም ወደ ሥራው የገቡበት ወቅት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት እንዲሁም በዓለም ላይ በተከሰተው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያቶች የዘርፉ እንቅስቃሴ የተቀዛቀዘበት ነበር፤ አገር ችግር ውስጥ በምትወድቅበት ጊዜም ቢሆን ባለሀብቱ መስራት እንዳለበት አስገንዝበው፣ ስራው በመንግሥት ላይ ብቻ የሚጣል መሆን እንደሌለበት ነው የገለጹት። በችግሩ ወቅትም ኩባንያቸው ሥራውን አንዳላቋረጠ ተናግረዋል። በአጠቃላይ ዘርፉ የበለጠ ውጤታማ መሆን የሚችለው አገር ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ሲኖር እንደሆነ አመልክተዋል።
ማዕድን ሚኒስቴር ኤክስፖ በማዘጋጀት አልሚውንና ላኪውን እንዲሁም ቴክኖሎጂ አቅራቢውን በማገናኘት ዘርፉን ለማነቃቃት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴም በዘርፉ የተሰማራው የበለጠ እንዲሰራ፣ የውጭና የአገር ውስጥ አዳዲስ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የሚያግዝ ሆኖ እንዳገኙት የሚናገሩት አቶ መከተ፣ ደማቅ ብለው በገለጹት የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ላይ መሳተፋቸው እንዳስደሰታቸውም አስታውቀዋል።
ኤክስፖው ከገበያ ትስስር ባለፈም በዘርፉ የተሰማራውን እርስበርስ በማስተዋወቅ ጥሩ ተሞክሮ የተገኘበት ሆኖ ነው ያገኙት። ኤክስፖው በዓመት ሁለቴና ሶስት ጊዜ ቢካሄድ የውጭ ገበያንና ኢንቨስትመንት ለመሳብ ጠቃሚ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በማእድን ዘርፍ በኢኮኖሚ የሚያጋጥማትን የውጭ ጫና ለመቋቋም የሚያስችል በቂ ሀብት አላት የሚሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ባህሩ ይርጋ ናቸው።በአገሪቱ አልምቶ ወደ ጥቅም የሚቀይራቸው እጆችን የሚጠብቁ የማዕድን ሀብቶች እያሉ በእርስ በርስ ግጭት የልማት ጊዜ መባከኑን በቁጭት ይገልጻሉ።
በትግራይ ክልል እጅግ ውድ ዋጋ የሚያወጣ ሳፋየር የተባለ ማዕድን መኖሩን በመጠቆም፣ በአካባቢው ላለፉት ዓመታት በተካሄዱት ጦርነቶች ሳቢያ የማእድን ሀብቱ ጥቅም ሳይሰጥ መቆየቱን ይገልጻሉ። ማዕድን የሀብት ምንጭ እንደሆነ ግንዛቤ የተያዘውና በመንግሥት ትኩረት የተሰጠው በቅርብ ጊዜ አንደሆነም ነው የገለጹት።
ኤመራልድ፣ ሞርጋናይት፣ ሩፒ፣ ቶፓዝና ሌሎችንም የማዕድን አይነቶች ከሻኪሶ፣ቦረናና ከሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች በመግዛት ለውጭ ገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ዘርፉ ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነም ይናገራሉ።
በቅርቡ በኢትዮጵያ በተካሄደው የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የማዕድን ሀብት ለኢኮኖሚው እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ዝቅተኛ ነው፤ ልማቱ ላይ በመሥራት ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል።
‹‹ኢትዮጵያ በውስጧ የያዘችውን ሚስጥር ገና አናውቀውም›› ሲሉም ጠቅሰው፣ ተመራማሪዎች ጠንክረው ከሰሩ ለግብርናው፣ ለኢንዱስትሪው፣ ለግንባታው ለሌሎችም የኢኮኖሚ ዘርፎች ግብአት የሚውል እምቅ የማእድን ሀብት አገሪቱ እንዳላት አስታውቀዋል። ይህን በማልማት በግዥ ከውጭ የሚገባውን የማእድን ምርት መተካት እንደሚቻል በተለያየ ጊዜ ከሚሰጡ መረጃዎች መገንዘብ ይቻላል ብለዋል።
ፕሬዚደንቷ የማዕድን ሀብት አላቂ እንደሆነ ግንዛቤ መያዝ እንዳለበት ጠቁመው፣ የማእድን ሀብቱን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ ገና ያልተነካ ሀብት እንዳላትና ለማልማት የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ትምህርት ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።
‹‹የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ የማእድን ሀብቱ ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያዊ ሀብቱን ጠንቅቆ እንዲያውቀው ብቻ ሳይሆን፣ ተንከባክቦና ጠብቆ ጥቅም ላይ የሚውልበትንና ከዘርፉም ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ያግዛል›› ሲሉም ፕሬዚደንቷ መናገራቸው ይታወሳል።
ፕሬዚደንቷ ኢትዮጵያ የበርካታ የማዕድን ሀብቶች ባለቤት እንደሆነች የማያውቁ አገራት መኖራቸውንም የአፍሪካ ልማት ባንክ ባዘጋጀው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ መጥቀሳቸውን አስታውሰው፣ አንዳንድ የመድረኩ ተሳታፊዎች ያነሳቸው ከነበሩ ጥያቄዎች ከኢትዮጵያ ውጪም የኢትዮጵያን የማእድን ሀብት የማወቅ ጉጉት መፈጠሩን መገንዘብ መቻላቸውን ጠቅሰዋል።
ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ሌላው ዓለም የኢትዮጵያን የማእድን ሀብት በተገቢው ሁኔታ እንዲያውቀው አለመደረጉን እንደሆነም አመልክተዋል። በዚህ ረገድም ብዙ ሥራ እንደሚቀር ያሳያል ብለዋል።
ውስጣዊ ችግሮች እየተፈቱ እንደሆነና በዘርፉ የሚሰማሩ ኢንቨስተሮች እንደሚመጡ ተስፋ ያደረጉት ፕሬዚዳንቷ፣ በዘርፉ የሚስተዋለውን ህገወጥነት በመከላከልና ህጋዊ መስመር በማስያዝ ረገድም ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። መንግሥት ለዘርፉ የተለያዩ ድጋፎችን በመስጠት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴም አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት የዘርፉን እምቅ ሀብት እና ሀብቱን ለማልማት በሚደረገው ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሚገባ እየተገነዘበ፣ መፍትሄያቸውንም እያመላከተ ይገኛል። በአገር በቀል ኢከኖሚ ሪፎርሙ የአስር አመት መሪ እቅድ የማእድን ዘርፉን ከአምስቱ የምጣኔ ሀብቱ ምሰሶዎች አንዱ ማድረጉንም ከዚሁ አኳያ መመልከት ይቻላል።
ከላኪዎቹ መገንዘብ እንደቻልነው ለአንዳንድ አገራት የእድገት ምንጭ የሆነው የማዕድን ሀብት በኢትዮጵያም ቢገኝም፣ አሀገሪቱ ይህን እምቅ ሀብት በተገቢው መንገድ ባለማልማቷና እሴት የተጨመረበት አገልግሎት ለገበያ አቅርባ መጠቀም ባለመቻሏ እሳቸው ቁጭት አድሮባቸዋል።
በአልሚዎቹ፣ በላኪዎችና በመንግሥት በኩል በአብዛኛው እየተከናወነ ያለው ተግባር እሴት ያልተጨመረበት ጥሬ እቃ በመላክ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህም አገርን ሳይሆን ሌሎች አገሮችን ነው የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርገው፤ ይህ ሁኔታ መቀየር ይኖርበታል። ቁጭት አንድ ነገር ነው፤ ብቻውን ግን ፋይዳ የለውም፤ ማእድኑን ለማልማት በሁሉም ወገን የተፈጠረው ተነሳሽነት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ህዳር 23/2015