አሁን ላይ የፍሳሽ አወጋገዱ በሁለት መንገድ አገልግሎት ይሰጣል። የመጀመሪያው በተሽከርካሪዎች አማካኝነት ፍሳሽ ከየቤቱ የማንሳት ሂደት ነው። ይህም የውሃና ፍሳሽ ባለ ሥልጣን ባሉት ተሽከርካሪዎች አማካኝነት በሌላ በኩል ደግሞ በግል በሚሳተፉ አካላት ተግባራዊ ይደረጋል፡፡
30 በመቶ የሚሆነውን በመኪና የሚነሳውን ፍሳሽ የሚሰበስቡት የግል ተቋማት ሲሆኑ፤ 70 በመቶው ደግሞ በውሃና ፍሳሽ ባለ ሥልጣን የሚሰራ ነው። ፍሳሽ ከየቤቱ በመኪና የሚሰበሰበውም በአነስተኛ ታሪፍ ነው የሚሉት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የፍሳሽ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ተስፋለም ባዩ ናቸው። እርሳቸው እንደሚገልጹት፤ ሆኖም ግን ፍሳሽን በመኪና የመሰብሰብ አገልግሎት በሂደት ይቀንሳል፤ ቀስ በቀስም ፍሳሽን በመኪና የመሰብሰብ ሥራ ይቆማል።
ኢንጂነር ተስፋለም፤ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የውሃም ሆነ የፍሳሽ መሠረተ ልማት ግንባታዎች የፋይናንስ ምንጫቸው ከየትም ቢሆንም በፕሮጀክት ትግበራ በኩል የእድገት ሥራ በመሰራት ላይ ነው፡፡ ዋና መስሪያ ቤት ደግሞ በአጠቃላይ የስትራቴጂ ሥራዎችን እየመራ ይገኛል፡፡ አሁን ላይ እየተሰሩ ካሉ ሥራዎች መካከልም ዘመናዊ የፍሳሽ አሰባሰብ ስልት አንደኛው ነው ይላሉ፡፡
‹‹የአዲስ አበባ ከተማን ፍሳሽ በመኪና እያነሱ አገልግሎት መስጠት የባለ ሥልጣኑ ስትራቴጂክ ግብ አይደለም፡፡›› የሚሉት ኢንጂነር ተስፋለም፤ ይህ ለጊዜው የሚተገበር እንጂ በዋናነት የስትራቴጂክ ግቡ ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያን በመገንባት አገልግሎት መስጠት መሆኑን ያብራራሉ፡፡
የውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን እንደ ስትራቴጂክ እቅድ ይዞ የሚሰራው ከተማዋን በመስመር በማገናኘት ፍሳሽ ከየቤቱ በመስመር እየተሰበሰበ ወደ ማጣሪያ ጣቢያዎች እንዲሄድ ማድረግ ነው፡፡ ለአዲስ አበባ የሚመጥነው አገልግሎትም እንዲህ ዓይነቱ ነው፡፡ ዓላማውም በዘመናዊ መንገድ እንዲጣራ ማድረግ ነው፡፡ ይህ እውን እንዲሆንም ባለሥልጣኑ በርካታ መሠረተ ልማቶችን እየሰራ ይገኛል ይላሉ፡፡
የዘመናዊ ፍሳሽ አሰባሰብን በመስመር ዝርጋታ ተግባራዊ ለማድረግ፤ በከተማዋ ያሉት የቤት ግንባታዎች ማስተር ፕላን ሊኖራቸው ይገባል። ያለ እቅድ በተሰሩና በየጊዜው በሚፈርሱ አካባ ቢዎች ላይ እንዲህ ዓይነቱን ዘመናዊ የመስመር
ዝርጋታ ለማበጀት አይቻልም፡፡ ከዚህም በዘለለ ፍሳሹ በመስመር ተጓጉዞ ወደ ማጣሪያ ጣቢያው እንዲደርስ በውሃ የሚሰሩ መጸዳጃ ቤቶች ያሉባቸው አካባቢዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ደረቅ የሚባሉ መጸዳጃ ቤቶችን በመስመር ማጓጓዝ አደጋች ነው፡፡ ሥራውም እንዲህ ዓይነት ቅድመ ሁኔታዎች በተሟሉባቸው አካባቢዎች ተግባራዊ ይደረጋል ይላሉ፡፡
በከተማዋ ዘመናዊ የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት በተማከለና ባልተማከለ መልኩ የሚከናወን ሲሆን፤ የተማከለው እንደ ቃሊቲ ዓይነት የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ዓይነቱ ነው ይላሉ፡፡ ይህም ከተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ፍሳሽ ተሰብስቦ በአንድ ላይ የማጣራት አገልግሎት የሚካሄድበት ስልት ነው፡፡ ያልተማከለው የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት ደግሞ በየአካባቢው በርካታ የማጣሪያ ጣቢያዎች ተገንብተው አገልግሎት የሚሰጡበት ሂደት ነው፡፡
አዲስ አበባን በሦስት ተፋሰስ በመክፈል ማለትም የቃለቲ፣ የምሥራቅና የአቃቂ ተፋሰሶች በሚል እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ናቸው፡፡ አዲስ አበባ በእነዚህ ተፋሰሶች የተከፈለችው አንድ አካባቢ ላይ የሚገኝ ፍሳሽ በመሬት ስበት ሥነ ዘዴ አማካኝነት ተሰብስቦ ወደ አንድ የማጣሪያ ጣቢያ ማምጣት እንደሚቻል ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡
እስከ ሰባት ክፍለ ከተማዎችን የሚይዘው የቃሊቲ ተፋሰስ ትልቁ ተፋሰስ ነው፡፡ በቀን 100ሺ ሜትር ኪዩብ የማጣራት አቅም ያለው የቃሊቲ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ተመርቆ ሥራ ከጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው ነው፡፡ ግንባታው ከዓለም ባንክ በተገኘ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እና ከመንግሥት በተመደበ የአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የተካሄደ ሲሆን፤ ግንባታው በ2008 አጋማሽ ላይ ተጀምሮ በተቀመጠለት ጊዜ መሠረት ተጠናቅቋል፡፡
ከአስሩ ክፍለ ከተሞች የካ፣ ቦሌ በከፊል፣ አቃቂ በከፊል፣ ንፋስ ስልክ በከፊል፣ ብቻ ነው ወደ እዚህ ማጣሪያ ጣቢያ ፍሳሻቸውን መልቀቅ የማይችሉት። የተቀሩት ሰባቱ ክፍለ ከተሞች ግን ፍሳሻቸው በዘመናዊ መንገድ ወደ ቃሊቲ የማጣሪያ ጣቢያ ይደርሳል ተብሎ የሚታሰብ መሆኑን ተናግረው፤ በዚህ በኩል ፍሳሽ በመስመር ተቀብሎ በማስተናገድ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የከተማዋን ነዋሪ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ እንደሚገመት ይገልፃሉ።
ባለ ሥልጣኑ ከሦስቱ ተፋሰሶች ይልቅ ትኩረት ሰጥቶ ሥራውን የጀመረው በትልቁ የቃሊቲ ተፋሰስ ነው፡፡ ግንባታው ሲመረጥም ብዙ ሕዝብን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ በመታሰቡ ጭምር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን ወደ ፊት ተገንብተው አገልግሎት የሚሰጡት የምሥራቅ ተፋሰስ 80ሺ እንዲሁም አቃቂ 60ሺ፣ ጨፌ 25 ሺ ሜትር ኪዩብ በማሰባሰብ የማጣራት አቅም ይኖራቸዋል በሚል የታቀደ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
የቃሊቲ የማጣሪያ ጣቢያውና የ18 ኪሎ ሜትር በየሰፈሩ የተዘረጋ መስመር በዓለም ባንክ ገንዘብ ተመድቦለታል፡፡ የዓለም ባንኩ ፕሮጀክት ሥራውን ሙሉ ስለማያደርገው በመንግሥት በጀት ደግሞ የ28 ኪሎ ሜትር ከፍተኛ መስመር እና 80 ኪሎ ሜትር የመለስተኛ የፍሳሽ መስመር ዝርጋታ ፋይናንስ ተደርጓል፡፡ ፕሮጀክቱ በግሪክ ኮንትራክተር የተሰራ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ይህ ማጣሪያ ጣቢያ በራስ አቅም ሙሉ ለሙሉ ሥራ እየሰራ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት፡፡
ግንባታው በሚከናወንበት ወቅት በአካባቢው የሚገኘውን የቀለበት መንገድ ሳያበላሽ ውስጥ ለውስጥ ቁፋር በማከናወን የመስመር ዝርጋታው በስኬት ተሰርቷል፡፡ በማጣሪያ ጣቢያው ላይ 52 ቋሚ ሠራተኞችና 25 የቀን ሠራተኞች በአጠቃላይ 77 ሠራተኞች ሥራ ተፈጥሮላቸው በማጣሪያ ጣቢያው ውስጥ በመስራት ላይ ናቸው በማለት ሥራው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
ይህ ፕሮጀክት ከተማዋን የዘመናዊ የፍሳሽ አወጋገድ ስልትን ተጠቃሚ ያደርጋታል፡፡ ጽዱና ውብ በማድረግ ረገድም ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ከተሞች በዓለም አቀፍ ውድድር ዘመናዊ ከሚያስብላቸው መስፈርቶች አንዱ ምን ያህል የዘመናዊ ፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት እየተተገበረ እንደሆነ የሚያሳይ በመሆኑ አዲስ አበባን ዘመናዊ ከተማ ያስብላታል፡፡ ሥራው የተቋሙንም ገቢ ይጨምራል፡፡
ከዚህ በፊት የተለያዩ ፍሳሾች ማጣሪያ ጣቢያ ባለመኖሩ በየወንዙ ይለቀቅ ነበር፡፡ በእርግጥ ይህ አሁንም ሙሉ ለሙሉ ባይቆምም የተወሰነውን ማቅለል ተችሏል፡፡ ይህንን በማስቀረት በርካታ ፍሳሽ ወደ ጣቢያው እንዲጓዝ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ከጤና አኳያ የራሱን ድርሻ እየተወጣ ያለ ጣቢያ ነው፡፡
በተለይ ከዚህ ቀደም ፍሳሽ ሳይጣራ በቃሊቲ ወንዝ ላይ ይለቀቅ ስለነበር ወንዙ በሚያቋርጥባቸው በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች የዚህ ሰለባ ተጋለጭ የነበሩ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግን ወደ ወንዝ የሚለቀቀው ፍሳሽ የተጠራ በመሆኑ ነዋሪዎችም ለመስኖና ሌሎች ልማቶች እየተጠቀሙበት እንደሚገኙም ነው የሚናገሩት፡፡
እንደምክትል ሥራ አስኪያጅ ገለፃ፤ ያልተማከሉ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች ተሞክሮን በተመለከተ
በተለይ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ እስካሁንም በስምንት የጋራ መኖሪያ ቤት ሳይቶች 12 የሚሆኑ የዘመናዊ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች ተሰርተው ሁሉም አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ 27ሺ ሜትር ኪዩብ የማጣራት አቅም አላቸው፡፡
ስለዚህ አዲስ አበባ በእንዲህ ዓይነት አሠራር ውስጥ በቀጣይ የተሻለች ትሆናለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የጨፌ ማጣሪያ ጣቢያ በመንግሥት የሚሰራ ሲሆን፤ 12ሺ 500 ሜትር ኪዩን ማጣራት የሚችል ነው፡፡ ይህም ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ የምሥራቅ ተፋሰስ ከዓለም ባንክ ፋይናንስ ስለተገኘለት የጥናት ዲዛይን የሚሰራ አማካሪ ቅጥር በሂደት ላይ ነው፡፡ ሁሉም የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች በግንባታ በሂደት ላይ ናቸው፡፡
ነገር ግን መስመሮቹ ቢዘረጉም ከየቤቱ ጋር ማገነኘት መሠረታዊ ሥራ አለ፡፡ በዚህ ሥራ ውስጥ የሚያጋጥመው አንዱ ፈተናም መስመሮችን ከየቤቱ መጸዳጃ ጋር ማገናኘቱ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ በሦስት መንገዶች ይሰራል፡፡ ጠቀሜታውንና የሰለጠነ ከተማ መገለጫ መሆኑን ለሕዝቡ ግንዛቤ በመፍጠር፣ በማበረታታትና አልፎም ተርፎም ለውጥ የማይመጣ ከሆነ በግዳጅ ፍሳሹን በመስመር እንዲገናኝ ማድረግ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2011
በአዲሱ ገረመው