ለሁለት ወራት የዘለቀው እና ከአምስት ቀን በፊት ጫፍ መድረሱ ሲነገርለት የቆየው የሱዳን ተቃውሞ እ.አ.አ በ1989 በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዙትን ፕሬዚዳንት ኡመር አልበሽርን ከስልጣናቸው አስወግዷል።
ሱዳናዊያን አልበሽርን በቃዎት በማለት ላለፉት ሁለት ወራት አደባባይ በመውጣት ከአገሪቷ የፀጥታ አካላት ጋር በመጋጨት ጭምር ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ደግሞ ወደ አገሪቷ የመከላከያ ሚኒስቴር በማቅናት ጦሩ ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ ሲያደርጉ ታይተዋል።
ይህንን ተከትሎም የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትሩ አህመድ አዋድ ኢብን ህዝቡ በትግስት እንዲጠብቃቸው ሲያሳስቡ ቆይተው፤ በመጨረሻም ፕሬዚዳንት አልበሽር ከስልጣናቸው መነሳታቸውንና ጦሩ አገሪቷን ለሚቀጥሉት ሁለት አመት እንደሚያስተዳድራት ለዚህም የሽግግር መንግስት መቋቋሙን ይፋ አድርገዋል። ሚኒስትሩ አገሪቷን ወደመረጋጋት ለመመለስም ለቀጣዮቹ ሶስት ወራት የሚቆይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን አስታውቀዋል።
መከላከያው ፕሬዚዳንቱ መልቀቃቸውን ይፋ ከማድረጉም በፊት ተቃዋሚዎች አልበሽር እንደሚለቁ ተረድተው እጅግ ተደስተው እንደነበር የአልጀዚራ ዘገባ ያሳያል።
በሰሜን ሱዳን እ.አ.አ በ1944 ከአርሶ አደር መወለዳቸው የሚነገርላቸው በሽር በ1973 ግብፅ ከእስራኤል ጋር ባካሄደችው ጦርነት ላይ ከግብፃውያን ጋር በመሆን የውትድርናውን ዓለም መቀላቀላቸው ይነገርላቸዋል።
አንድነት ያላት ሱዳንን ለማቆየት ፅኑ ፍላጎት እንደነበራቸው የሚነገርላቸው አል በሽር፤ ለሰላም ሲባል በህዝበ ውሳኔ ደቡብ ሱዳናውያን ነፃ አገር እንዲሆኑ እድል መስጠታቸውም ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2011
በ ምህረት ሞገስ