ሙስና አጀንዳ በሆነ ቁጥር አንድ ተደጋግሞ የሚነሳ ነገር አለ፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሀብት መጠን ይለካል የሚል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የፓርላማ ንግግር ዕለት ጀምሮ ዛሬ ድረስ ሙስና የመገናኛ ብዙኃኑ አጀንዳ ሆኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል ደግሞ የሀብት መጠናቸው ከገቢያቸው በላይ የሆኑት ላይ ምርመራ ይደረጋል በማለቱ ዜናው ሲዘዋወር ነበር።
የኔ ትዝብት ለምን ምርመራ ይደረግባቸዋል? የሚል አይደለም። ዘርፈው የከበሩ የትኛውም ባለሥልጣናት ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው። ይህ ሙስናን የመታገል አጀንዳ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እና ሁላችንም ከመንግሥት ጎን ቆመን ልንተባበረው የሚገባ ነው።
የኔ ትዝብት ከመንግሥት ባለሥልጣናት የሀብት መጠን ጋር ተያይዞ በቀልድም ሆነ በቁም ነገር የሚነሱ ልማዳዊ አመለካከቶች ላይ ነው። መንግሥት የራሱ መለኪያ እና መመርመሪያ መንገድ ስላለው ሙሰኛን የሚያጣራበትን መንገድ ለራሱ እንተወው።
ዳሩ ግን የብዙዎቻችን ልማዳዊ አመለካከት የመንግሥት ሠራተኛ ሲባል የግድ ድሃ እና ቀጫጫ መሆን ያለበት ይመስለናል። ምንም የሌለው ድሃ ነው ከተባለ እንደ ትክክለኛ የሕዝብ አገልጋይ ሀቀኛ ነው የሚታይ። በተቃራኒው የራሱ ውድ መኪና ያለው፣ ሰውነቱ ወፈር ያለ ከሆነ ‹‹ከሕዝብ ዘርፎ›› ነው የሚባል። ሰውየው መለካት ያለበት የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ከመወጣትና ከሙስናም የጸዳ መሆኑን በማወቅ እንጂ በአካላዊ ሰውነቱ እና በሚገለገልባቸው ነገሮች የጥራት ደረጃ መሆን የለበትም።
አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን በልጆቹ፣ በወንድሞቹም ሆነ በየትኛውም የቅርብ የቤተሰብ አባል አማካኝነት ብልጥ የቢዝነስ ሰው ከሆኑ ሀብታም መሆን አይችልም? ትልቅ ንግድ ቤት ቢከፍት ለሕዝቡስ ሆነ ለአገሪቱ ገጽታ አይጠቅምም?
ከመንግሥት ባለሥልጣንነት ውጭ ያሉ ነጋዴዎችን የተነሱበትን ነገር በጣም እናደንቃለን። በየመገናኛ ብዙኃኑ ዝናቸው ይነገርላቸዋል። ከ200 ብር ተነስቶ ነው፣ ከዶሮ ተነስቶ ነው፣ ቆሎ ከመሸጥ ተነስታ ነው… እየተባለ ይመሰገኑበታል። ከትንሽ ነገር ተነስቶ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ የሚያስመሰግን ስለሆነ ማለት ነው።
ታዲያ እንዲህ ከሆነ በሺዎች የሚቆጠር ደሞዝ የሚያገኝ አንድ ባለሥልጣን ጎበዝ የቢዝነስ ሰው ከሆነ ሀብታም መሆን አይችልም ወይ? እንዲያውም የሚያገኘውን ደሞዝ፣ አበልና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ውስኪ ከሚራጭበት ወደ ቢዝነስ ቢቀይረው ለአገርም ይጠቅማል።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ ሁላችንንም ፈገግ ያሰኘ አንድ የክፍል ጓደኛችን የተናገረው ነገር ትዝ አለኝ። ፈለግ ያሰኘን ቀልድ ሆኖ ሳይሆን የልጁ አስተያየት ከሁላችንም ለየት ያለ አተያይ ስለነበር ነው። ነገሩ እንዲህ ነው።
የሆነ ‹‹አሳይመንት›› ተሰጠን። የተሰጠን ሥራ በግቢው ውስጥ አስገራሚ ሕይወት ያላቸውን ሰዎች ወይም አስተማሪ የሆነ የሕይወት ታሪክ ያላቸውን ፈልጎ በቃለ መጠይቅ የሕይወት ታሪካቸውን መሥራት ነው። ዕቅዱ ተሰጥቶን ያገኘናቸውን ሰዎች ይሆናሉ አይሆኑም የሚለውን ለመምህራችን እያቀረብን ከመምህሩም ከተማሪውም አስተያየት እየተሰጠበት ነው።
አንደኛው ቡድን ያቀረበው በግቢው ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ከአትክልተኝነት ጀምሮ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ሲያገለግሉ የቆዩ ሽማግሌ ናቸው። የተመረጡበት ምክንያትም ለበርካታ ዓመታት አገልግለው በከፍተኛ ድህነት ውስጥ እየኖሩ መሆኑ ነው። ይሆናል አይሆንም በሚለው ላይ ተወያዩበት ተባልን።
አሳይመንትነቱን ልተወውና በሰውየው ሕይወት ላይ የሁላችንም ሀሳብ ተመሳሳይ ነበር። ይህን ያህል ዓመት ዩኒቨርሲቲውን ያገለገሉ ሰውየ እንዲህ መቸገር የለባቸውም፤ ዩኒቨርሲቲው ቤትም ሊሰጣቸው ይገባል አልን።
ይህኔ አንደኛው ልጅ (ሁሌም እንደመፈላሰፍ ያደርገዋል) እጁን አወጣና አስተያየት መስጠት ጀመረ። ‹‹የእኝህን ሰውየ የሕይወት ታሪክ ስትሰሩ የቁጠባ ባህላቸውንም ጠይቋቸው፤ ይህኔ እልም ያሉ ሰካራም ቢሆኑስ? ገንዘባቸውን ያባከኑት በመጠጥና በሌሎች አልባሌ ነገሮች ቢሆንስ? ዩኒቨርሲቲው እኮ እንደማንኛውም ሰራተኛ ይሆናል የከፈላቸው፤ እና እርሳቸው አባካኝ የሆኑ እንደሆነ ዩኒቨርሲቲው ምን ያድርግ?›› አለ። በወቅቱ ብንስቅም እየቆየ ሲሄድ ግን ‹‹እውነቱን እኮ ነው›› ማለትም ጀመርን።
ሽማግሌውን ታታሪ ሰራተኛ እና የግቢው ከፍተኛ ባለውለታ ያደረግናቸው ስለተቸገሩ ሳይሆን አይቀርም። ብዙ ጊዜ ልብ ብላችሁ ከሆነ በምቾት ውስጥ ያለ ሰው ምንም ያህል ለተቋምና ለአገር ውለታ ቢውል ተመስጋኝነቱ ትንሽ ነው። ተመችቶት የሚኖር ሰው የሚሰደበውና የሚወቀሰው ይበልጣል። በአንፃሩ ተቸግሮና ተጎሳቁሎ የሚኖር ደግሞ ሰነፍ ቢሆን እንኳን ተመስጋኝ ነው። ነገሩን ካየነው ግን የሥራ ትጋት ስለተቸገሩ ብቻ ላይሆን ይችላል። ምክንያቱ ደግሞ ሀብት ያላቸው ሰዎች ከህዝብ አጭበርብረው ነው ያገኙት የሚል እሳቤ ስላለ ነው።
አሁንም ደግሜ የማሳስበው ነገር ሌብነትን እያበረታታሁ አይደለም። ዳሩ ግን የአንድ ሰው ጎስቋላ ሕይወት መኖር በራሱ የሰውየውን ሀቀኝነት አያሳይም ነው። በተመሳሳይ የሰውየው ምቹ ኑሮ መኖርም ሌብነቱን አያሳይም ነው። አንድ ትልቅ ባለሥልጣንም ሆነ የቀበሌ ኃላፊ የሚጠቅመኝ የምፈልገውን አገልግሎት በፍጥነት እንዳገኝ ካስደረገልኝ፣ አግባብነት የሌለው ክፍያ እንዳልከፍል የሚያደርግ ሥርዓት ከዘረጋልኝ እንጂ የራሱ መጎሳቆል አይደለም የሚጠቅመኝ።
እንደማንኛውም ሰው በታክሲ እየሄደ፣ ተራ ምግብ ቤቶች ውስጥ እየተመገበ፣ ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸውን አልባሳት እየለበሰ፤ ዳሩ ግን የሚመራው መስሪያ ቤት ጉዳዬን የሚያዝረከርክብኝ ከሆነ፣ መክፈል የሌለብን ገንዘብ የሚያስከፍለኝ ከሆነ፤ ይህ ሰውየ ሥልጣኑን በአግባቡ አልተወጣም ነው የሚባለው!
ከላይ የጠቀስኳቸውን የሕዝብ አገልግሎቶች በአግባቡና በፍጥነት እንዲያገኝ የሚያደርግ ሥርዓት ከፈጠረልኝ በራሱ ገንዘብ ለምን ቁርስ ቢሾፍቱ፣ ምሳ ባህርዳር፣ እራት ሐዋሳ እየሄደ አይበላም።
በእርግጥ በሕዝብ ገንዘብ (በመስሪያ ቤቱ በጀት ማለት ነው) የሚያደርገው ከሆነ ነውር ብቻ ሳይሆን በህግም የሚያስጠይቅ ጥፋት ነው። ዳሩ ግን በራሱ (ከኪሱ ማለት ነው) በሚያደርገው መዘነጥም ሆነ መመገብ ኃላፊነቱን በአግባቡ ከመወጣቱ በላይ መሆን የለበትም።
በሌላ በኩል ሁልጊዜ ሽር ሽር እና ሁልጊዜ ቅንጡ ሕይወት ፍለጋ ብቻ ከሆነ ምናልባትም ሥራ ሊበድልም ይችላል፤ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ከሚወጣበት ሰዓት ላይ ይሸራረፋል ማለት ነው። ስለዚህ በራሱ ገንዘብም ቢሆን ከሥራ ሠዓቱ ላይ የግል ፍላጎቱን ለማሟላት መንቀሳቀስ የለበትም።
ከዚያ ውጭ ግን የሀቀኝነት እና የታታሪ ሰራተኛነት መገለጫው ድሃ መሆን አይደለም፤ ይሄ ድህነትን ማበረታታት ነው። መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ሙስናን መከላከል ሲያቅተው ሰዎች ለፍተው ያገኙትን ነገር ሰርቀው ነው ብሎ መጠርጠር ስንፍና ነው። ምናልባትም የሕዝብን ንብረት እየመዘበረ ድሃ የሚሆን ባለሥልጣንም ይኖራል።
ስለዚህ ከመንግሥትም ሆነ ከሕዝብ የሚጠበቀው ሙስናን መከላከል፣ ሥርዓቱን ማስተካከልና ተጠያቂነትን ማስፈን እንጂ ንግድ ቤት ያለውን ሁሉ እንደ ሌባ ማየት አይደለም፤ ይህ ልማዳችን ሊቀረፍ ይገባል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/ 2015 ዓ.ም