ሕይወቷን ሙሉ ለጥበብ የሰጠች ነች። ይሄን ሕይወቷን የሚያጣፍጥላትን ሰላም አጥብቃ በመሻቷ በሰላም ግንባታ ዙርያ ሳታሰልስ ስትሰራ ቆይታለች። መላውን ኢትዮጵያውያን ስትደርስ የቆየችበትና‹‹ኢንተርሬይዝ ፒስ ፒውልዩጋግ›› የተሰኘው ተቋም ምስክር ይሆናታል። በተለይ በህፃንነቷ ስታገለግል ካደገችበት ሰንበት ትምህርት ቤት የወረሰችውን መንፈሳዊ መንገድ ተጠቅማ የወጣቶችን አእምሮ ራሳቸውንና አገራቸውን በሚጠቅሙበት ቅንነት መቅረጽን ተክናበታለች።
ሥራቸው በርካታ አንቱ የተሰኙ አባላትን ያበረከተው የፍካት ወጣት ደራሲያን መስራችም ነች። የህፃናትን ጨምሮ ግለ ታሪክና ሌሎች መጽሐፎችን ጽፋለች። ማናት ካላችሁኝ አሁን ላይ ከሌሎች አጋሮቿ ጋር በመሆን ‹‹ቶኔቶር ኢትኤል›› የተሰኘ መልቲ ሚዲያ በማቋቋምና ስቱዲዮ በመገንባት ፊልምና ቲያትርን ጨምሮ የተለያዩ የጥበብ ሥራዎቿን ለሕዝብ በማቅረብ ላይ የምትገኘው ደራሲና ጋዜጠኛ እመቤት ዘውዴ ነች። እመቤት የጥበብ ሥራዎች ልብ በሚነኩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው።
ለወላጆቿ የመጀመሪያ ሴት ልጅ የሆነችውና ከ15 ዓመታት በላይ በጋዜጠኝነት ሙያ ስትሰራ ያሳለፈችው እመቤት በፖለቲከኛ አባቷ እሥር ምክንያት ገና በጨቅላነቷ የቤት ውስጥ ኃላፊነትን በመሸከም መፈተኗ አብዛኞቹ የጥበብ ሥራዎቿ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያጠነጥኑ ተፅዕኖ ያደረገባት መሆኑን የጥበብ አጋሮቿ ሲናገሩላት ይደመጣል።
በዕለታዊ አዲስ፤ በዘ-ፕሬስ፤ በኢትዮ ኒውስ ጋዜጦች አብዝታ ማህበራዊ ሥራዎችን ስትሰራ የኖረችው ዓይናማዋ እመቤት ዘውዴ በጋዜጠኝነት ሙያ ከሰራችባቸው ዓመታት አብዛኞቹን ዓይነስውራን ላይ አተኩራ ነው ስትሰራ የቆየችው። ውለታዋ የመጀመሪያ የሆነውን የብሬል ጋዜጣ ለዓይነስውራን እስከማሳተም ይዘልቃል። እኛም ለዛሬ እመቤትን ግድ ብሏት ለዓይነስውራን ባበረከተቻቸው ሥራዎች ዙሪያ ተወስነን ያካፈለችንን ልናካፍላችሁ ወድደናል።
እመቤት እንዳጫወተችን ሁላችንም የሰው ልጆች በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ነው የምንኖረው። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ እንደመኖራችን የአንዳችንን ችግር አንዳችን መረዳታችን አንዱ የማህበረሰብ መስተጋብር መገለጫችን ነው። እናም እመቤት በዚህ መስተጋብር ውስጥ ሆና በአገራችን የዓይነስውራን ትምህርት በሚፈለገው ደረጃ አለመስፋፋቱን ስታስተውል ቆይታለች። ከዚህ የተነሳ ብዙዎቹ ዓይነስውራን በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውና ተጠቃሚነታቸው ለማነስ መገደዱን አስተውላለች። ማመልከቻ የሚያጽፉትም ሆነ የሚያስነብቡት ዓይናሞችን በመለመን እንደሆነም ታዝባለች። በብሬል የተፃፉ መጽሐፎቶችና ጋዜጦች ባለመኖራቸውም ብሬል የተማሩትም የግንዛቤ አድማሳቸውን በንባብ እንዲሁም በመስማት ሳይቀር የሚያሰፉበት ሁኔታ አለመኖሩም እንዲሁ ስታስተውል ነው የኖረችው።
ይሄ ሁሉ በአፍሪካ የመጀመርያው የሆነውንና ኢትዮ ኒውስ ብሬል ጋዜጣ የተሰኘውን የዓይነስውራን ብሬል ጋዜጣ እንድታዘጋጅና እንድትመሰርት አሳስቷታል። በተለይ ደግሞ ጋዜጣውን እንድታዘጋጅ በዋናነት ምክንያት የሆናት በኢትዮጵያ ዓይነስውራን ማህበር ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት በመሆን ተቀጥራ የምትሰራበት አጋጣሚ ነበር። አጋጣሚው ዓይነስውራኑ የመረጃ እጥረት እንደነበረባቸው ፍንትው አድርጎ ሊያሳያት የቻለበትን ሁኔታ እንደብዙዎቻችን ዓይናሞች ከንፈር በመምጠጥ በትዝብት ብቻ አላለፈችውም። ችግራቸውን ችግሬ ብላ በመያዝ ፈጥና ወደ መፍትሄው ነው የገባችው።
በተለይ አዳሪ ትምህርት ቤት የሚማሩ ወንድና ሴት ዓይነስውራንን ጨምሮ በሌሎች ቦታዎች የሚማሩና የሚኖሩ ዓይነስውራን የአኗኗር መስተጋብር በእጅጉ ያሳስባት ነበር። እንዴት ቢባል ወንዶቹና ሴቶቹ ከአዳሪ ትምህርት ቤት በሚወጡበትም ጊዜ በአንድ ቤት ውስጥ ሰብሰብ ብለው ነው የሚኖሩት። እነዚህም ሆነ ሌሎቹ በአንድ ጣራ ሥርም ያድራሉ። ነገር ግን ስለ ስነተዋልዶ ምንም ዓይነት ግንዛቤ አልነበራቸውም። በመሆኑም እርስ በእርስ በጓደኝነት የተያያዙት ጥንዶች ጥንቃቄ የጎደለው የግብረሥጋ ግንኙነት ያደርጋሉ። በዚህ ምክንያት ሴት ዓይነሥውራን ላልተፈለገ እርግዝና ይጋለጣሉ።
አንዲት ዓይነስውር ሴት በዚህ ሁኔታ አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ደጋግማ ላልተፈለገ እርግዝና ትጋለጣለች። በልጅነቷም የብዙ ልጆች እናት ለመሆን ትገደዳለች። የልጅ እናት በመሆኗ ምክንያት ትምህርቷን ታቋርጣለች። ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችም ትጋለጣለች። የሚደርስባት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እየከፋ ሲመጣ ልጆቿን ይዛ ልመና እስከመውጣት ትደርሳለች። የቤት ኪራይ የምትከፍለው ስታጣ ከነልጆቿ ጎዳና እስከማደርም ትገደዳለች። ይሄ ደግሞ ቤተሰቧንም እሷንም ለበለጠ የከፋ ችግር ይዳርጋል።
ብዙ ዓይነሥውራን ሴቶች በዚህ ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ። በተለይ አዳሪ ትምህርት ቤት ይማሩ የነበሩት ከአዳሪ ትምህርት ቤት በሚወጡበትና ወንድና ሴት በመሆን በጋራ ቤት ተከራይተው በሚኖሩበት ጊዜ የመረጃ እጥረቱ የሚያደርስባቸውን ችግር ልቧን ነካው። ሴቶቹ ባልተፈለገ እርግዝናና ወሊድ ምክንያት ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውና በዚሁ ምክንያትም ለተለያዩ ችግሮች ከመጋለጥ አልፈው ለልመና እስከመውጣት መድረሳቸውን መረዳቷ ውስጧን ከነከናት። ወንድ ጓደኞቻቸው ግን በፊናቸው ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ ያለምንም እንቅፋት እስከመጨረሻው ዳር ያደርሳሉ። ዩኒቨርሲቲም ገብተው ሥራ ላይ እስከመሰማራት ይዘልቃሉ።
ሆኖም ይሄኔ የልጄ እናት ባለቤቴ ወይም ገደኛየ ብለው ወደ እነሱ አይመለሱም። ሁሉም በሚባል ሁኔታ ይተዋቸዋል። እራሳቸውን ከቻሉ በኋላ ወደ አይናማ ሴቶች ይሄዳሉ። ይሄ ለእነርሱ ከዓይናሞች ጋር ተጋግዞ ሕይወታቸውን ለዘለቄታው መምራት የሚያስችል ቢሆንም ለተካዱት ሴት ዓይነስውራን መገለልን ስለሚያስከትል ተስፋ ያስቆርጣል። መፈጠራቸውንም የሚጠሉበትን ሁኔታ ያስከትላል።
እመቤት ይሄ በጥንዶቹ መካከል የተፈጠረው ክፍተት ከግንዛቤ ጉድለት የመጣ መሆኑን ተረዳች። ቀደም ሲል መረጃ ቢኖራቸው ኖሮ ሁለቱም ልበ ብርሃን ስለሚሆኑ ችግሩ እንደማይከሰትም አሰበች። ሀሳቧ በወቅቱ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ዓይነስውራንን የመረጃ ተደራሽ በማድረግ ችግሩን የሚቀርፍ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳታፊነታቸውንና ተጠቃሚነታቸውን የሚያሰፋና የሚያጠናክር መሆን እንዳለበትም አቀደች። ጋዜጠኛዋና ደራሲዋ እንዲሁም የሁለገብ ጥበብ ባለሙያዋ እመቤት በዚሁና በዓይነስውራን የመረጃ እጥረት ጥናት አጠናች። በጥናቱ መሰረትም በኢትዮጵያ ዓይነስውራን ማህበር ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የስነ ተዋልዶ ስልጠና እንዲዘጋጅ ተደረገና መንገዷን አሀዱ አለች። ለጠቅ አድርጋም ‹‹የዓይነ ስውራን ድምፅ›› የተሰኘ የቀለም መጽሔት በማዘጋጀት የመረጃ ተደራሽ ልታደርጋቸው ሞከረች። እመቤትን ይሄም ስላላረካት ዓይነስውራን በራሳቸው አማካኝነት በቀጥታ የመረጃ ተደራሽ የሚሆኑበትን መንገድ ስታሰላስል ቆየች።
ለእመቤት ኢትዮ ኒውስ ጋዜጦች ላይ መሥራቷ የብሬል ጋዜጣውን ለዓይነስውራኑ ለማዘጋጀት እንደመንደርደሪያ ሆኗታል። እራሷ እንደምትናገረው በተለይ በኢትዮ ኒውስ ጋዜጦች ሥር አንዷና ዋንኛዋ የሆነችውን ኢትዮ ኒውስ ጋዜጣ መመስረቷና ዋና አዘጋጅ ሆና መስራቷ ኢትዮ ኒውስ ብሬል ጋዜጣ ለህትመት ብርሃን ለማብቃት ጥሩ መደላድል ፈጥሮላታል።
የዓይነስውራን የመረጃ እጥረት ችግር ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ለመፍታትና የመረጃ ተደራሽነታቸውን ለማስፋት በ1996 ዓ.ም ኢትዮ ኒውስ የብሬል ጋዜጣን ማሳተም ጀመረች ። የኢትዮ ኒውስ የብሬል ጋዜጣዋ የበላይ ጠባቂ ደግሞ የቀድሞው የኢፌዴሪ መንግስት ፕሬዚዳንትና ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ነበሩ። ፕሬዚዳንቱ የጋዜጣው የበላይ ጠባቂ ሊሆኑ የቻሉበት የራሳቸው ምክንያት ነበራቸው።
እመቤት ከዚህ ከዓይነስውራን ብሬል ጋዜጣ መጀመር ጋር ተያይዞ ስለብሬል ወደ ኢትዮጵያ አገባብና አጀማመር እንዲሁም ዶ/ር ነጋሶ የበላይ ጠባቂ ሊሆኑ ስለቻሉበት ጉዳይም በምጥኑ አጫውታናለች። የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ የብሬል ተማሪ ማን እንደነበረም በአስገራሚ መልኩ አውግታናለች።
እንደ ደራሲና ጋዜጠኛዋ እመቤት ዘውዴ ኢትዮ ኒውስ የብሬል ጋዜጣ በእሷ መሥራችነትና አዘጋጅነት ለህትመት ብርሃን ከመብቃቱ በርካታ አሥርት ዓመታት በፊት ብሬል ወደ ኢትዮጵያ የገባበት ሁኔታ ነበር። የገባው በሚሲዮናውያን አማካኝነት ሲሆን የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ የብሬል ተማሪና ሰልጣኝ ደግሞ ዓይነስውሩ የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ አባት ቄስ ጊዳዳ ሶለን ነበሩ። ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የኢትዮ ኒውስ ብሬል ጋዜጣ የበላይ ጠባቂ የሆኑትም በዚሁ አባታቸው የመጀመርያው የኢትዮጵያ ብሬል ተማሪ ከመሆናቸው ጋር ይሰናሰላል። የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ አባት ቄስ ጊዳዳ ሶለን በብሬል ከሰለጠኑ በኋላ የብሬል ትምህርት በኢትዮጵያ እየተስፋፋ መጥቶ በርካታ ኢትዮጵያውያን ዓይነስውራንን ተደራሽ ያደረገበት ሁኔታም በአገራችን ተፈጥሯል።
በዚህ ምክንያት እሷ በ1996 ዓ.ም መስርታ ታሳትመው የነበረው ኢትዮ ኒውስ የብሬል ጋዜጣ እንደ አገር በርካታ አንባቢዎችን ማግኘት መቻሉንም እመቤት ትገልፃለች። ለዓይነስውራን ማህበር፤ ለዩኒቨርሲቲዎች ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ለተለያዩ ተቋማት በስፋት ይሰራጭ የነበረ መሆኑንም ታወሳለች። እንደ አገር በየክልሎች ማዳረስም ጥረት ተደርጓል። በእሷ ዘንድ ጋዜጣዋን በአፍሪካና በዓለም ተደራሽ የማድረግ ሀሳብም ተሰንቆ ነበር።
ይሁንና የበላይ ጠባቂው ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በተለያዩ የአገር ጉዳዮች በመጠመዳቸው ሊደረግለት የሚገባው ድጋፍ አልተደረገለትም። ለሕትመት ወጪው ድጋፍ የሚያደርጉ የተለያዩ ተቋማት እጃቸው እየታጠፈ መጣ። በግሏ ጥሪት ብቻ ማሰንበቱ አልሆነላትም። በመሆኑም ወጪው ከፍተኛ በመሆኑ ከስድስት ወራት በላይ በሕትመት ላይ ያልቆየውን የኢትዮ ኒውስ ብሬል ጋዜጣን በሕትመት ጎዳና ማስቀጠል አልተቻላትም። እመቤት በዚህ መልኩ የኢትዮጵያ ብሬል ጋዜጣ ከህትመት ቢወጣም ዘመኑ ከደረሰበት ፈጣን ቴክኖሎጂ አንፃር በተለየ መልኩ ዳግም የዓይነስውራኑን የመረጃ እጥረት በሚቀርፍ መልኩ ለማስቀጠልም ሀሳብ እንዳላትና በዚሁ ዙሪያም እንቅስቃሴ እያደረገች እንደምትገኝ ታነሳለች።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/ 2015 ዓ.ም