ወቅቱ በገጠር አዝመራ የሚሰበስብበት ነው፤ እናም ሥራ ይበዛል። በዚህ ወቅት ከተሜው ወደ ገጠር ቢሄድ ሊመለከት የሚችለው ሰብስቡኝ ሰብስቡኝ የሚል በማሳ ላይ የደረሰ ሰብልና አርሶ አደሩ አዝመራውን ለመሰብሰብ የሚያደርገውን ርብርብ ነው።
በኢትዮጵያ በቆየው የግብርና ሥራ ባህል መሰረት አርሶ አደሩ በዚህ ወቅት አዝመራ ያጭዳል፤ይከምራል፤ ይወቃል። ውቂያ ለማካሄድ ራሱን የቻለ ዝግጅት ማድረግ ይገባል። ይህ አይነቱ ዝግጅት ምርት አንዳይባክን፣ ጥራቱ እንዳይጓደል፣ወዘተ ፋይዳው ከፍተኛ ነው።
እህሉ የሚወቃበት አውድማ በጥንቃቄ መዘጋጀት ይኖርበታል፤ ለእዚህም አውድማው በእበት ተለቅልቆ በሚገባ እንዲዘጋጅ ይደረጋል። ይህን ማድረግ ደግሞ የሴቶች ድርሻ ነው። የአካባቢው ሴቶች ተሰባስበው ወይንም በደቦ አውድማውን በእበት ለቅልቀው ለውቂያው ዝግጁ ያደርጋሉ።
የተከመረው አዝመራ በአውድማው ላይ ይደረግና በሬዎች አፋቸው ታስሮ እንዲመላለሱበት ይደረጋል። ውቂያው በሚገባ እየተከነወነ እያለ አዝመራው በመንሽ እየተገለበጠ ፍሬው ከገለባው እስከሚለይ ድረስ በሚገባ አንዲወቃ ይደረጋል።
መንሽና ላይዳ የአርሶ አደሩ የውቂያ ወቅት ዋነኛ የግብርና መሣሪያዎች ናቸው። የተወቃው አዝመራ ገለባና ፍሬ በመንሽ በቅድሚያ ይለያል፤ ገለባው ከተለየ በኋላ አሁንም በመንሽና በላይዳ/ ትልቅ ማንኪያ ይመስላል/ ለንፋስ ይሰጣል። በዚህም እህሉ ከገለባው ይለያል።
ጤፍ ሲሆን ደግሞ እንደ ሰፌድና ማራገቢያ የሚመስሉ ቁሳቁስ እብቁ ይለያል፤ ጤፉን ከእብቁ ለመለየት አንደ ጥራጥሬው መንሽም ላይዳም ጥቅም ላይ አይወሉም። በሰፌድና በመሳሰሉት ነው ጤፉ ከእብቁ እንዲለይ የሚደረገው።
እንዲህ ባለው ባህላዊ መንገድ የደረሰው አዝመራ እየተሰበሰበ፣ እየተወቃ ነው ወደ ጎተራ እንዲገባ ሲደረግ የኖረው። አሰራሩ እጅግ ኋላ ቀር ነው፤ የሐገራችን ግብርና ስራ የግብርናውን ሥራ የሚያቀላጥፍ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ጊዜን በመቆጠብ፣ ድካምን በመቀነስ ተጠቃሚ ከሆኑ ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር በእርግጥም እጅግ ኋላቀር ሆኖ ቆይቷል።
ግብርናውን ከዚህ አይነቱ ኋላቀር አሰራር ለማውጣት በተለያዩ መንግስታት ሙከራዎች ተደርገዋል፤ በንጉሱ ዘመን በባለርስቶች ከዚያም በደርግ ዘመን የመንግስት እርሻ በባሌና አርሲ በትራክተር እና በኮምባይነር የታገዘ የሰፋፊ ግብርና ስራዎች ይካሄዱ አንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
የግብርና ሥራው በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ፣ ወንዝ በመጥለፍና ግድብ በመሥራት የመስኖ ልማትን ለማካሄድ ጥረቶች ተደርገዋል። በመስኖ ልማቱም ጎዴ መስኖ እርሻ፣ አልዌሮ መስኖ ግድብ፣ ጣና በለስ ፕሮጀክት፣ ከሰም መስኖ ግድብ፣ ተንዳሆ መስኖ ግድብ፣ ፈንታሌ ቦሰት መስኖ እርሻ፣ ወለጪቲ ቦፋ፣መገጭ፣ርብና ጊዳቦ መስኖ ግድብ፣ አርጆ ደዴሳ ግድብ፣ኩራዝ ፕሮጀክት፣ወልቃይት ወይንም ዛሬማ ግድብ ለመስኖ ልማት ለማዋል ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።
ከእነዚህ ለመስኖ ልማት ከተዘጋጁ ግድቦች አብዛኞቹ ለስኳር ልማት የታቀዱ ነበሩ። አንዳንዶቹም ከአትክልት ልማት የዘለለ ብዙም ስራ ያልተሰራባቸው ናቸው። በእዚህ የተነሳም እቅዱ ወደ ሥራ ተተግብሮ እንደ ሀገር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ እህል ራስን ለመቻል የሚደረግ ጥረትን በማገዝ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አልተመዘገበም።
የግብርና ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ለአርሶ አደሩ ለማስተዋወቅና ተጠቃሚ አንዲሆን ለማደረግም ተሞከሯል። የሕብረት ስራ ማህበራት፣ በግብራናው ስራቸው አንቱ ተብለው ተሸላሚ እስከመሆን የደረሱ አርሶ አደሮች የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ጥሩ ተነሳሽነት ቢያሳዩም፣ ግብርና አንደ ሀገር ከሚያስፈልገው ቴክኖሎጂ አኳያ ግን ብዙ ተሰርቷል የሚያሰኝ ሁነታ አልነበረም። በተለይ የግብርናው ዘርፍ ለሜካናይዜሽን ተግባር የሚያስፈልገውን የፋይናንስ አቅርቦት የሚቀርብበት ሁኔታ አልነበረም። ሀገሪቱም ለግብርናው ዘርፍ ፋይናንስ የማይቀርብባት ተብላም በባለሙያዎች ስትተች ኖራለች።
ከጥቂት አመታት ወዲህ ግን መንግስት ግብርናው ላይ በስፋት እየሰራ ይገኛል። ግብርናው በየአመቱ ምርትና ምርታማነቱ እያደገ ቢመጣም የሐገሪቱን ፍላጎት በማመቋላት በኩል ግን ብዙ እንደሚቀረው ታምኖበት እየተሰራ ነው። ውጤታማነቱ በሚገባ የተረጋገጠው የኩታ ገጠም እርሻ እየተስፋፋ ነው፤ የመስኖ እርሻ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ይገኛል።ሜካናይዜሽን ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቶታል። ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ ምርት እስከመሰብሰብ ያለው ሂደት በሜካናይዜሽን ወይም በትክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን በመንግሥት በልዩ ትኩረት እየተሰራበት ነው።
በሀገሪቱ በመኸር አርሻም ሆነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሰፋፋ በመጣው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የግብርና ሜካናይዜሽን እየተሰፋፋ ይገኛል። በትራክተር በማረስ፣ በኮምባይነር አዝመራ በመሰብሰብና በመውቃት የመስኖ ልማትን በስፋት በማከናወን በኩል ሀገሪቱ ታምር እያሳየች ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት ግለሰቦችና ማህበራት የእነዚህ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎች ባለቤት እየሆኑ ናቸው። መሳሪያዎቹ በኪራይ ጭምር ሊገኙ የሚችሉበትን ሁኔታም አነዚህ አካላት እያመቻቹ ይገኛሉ። በእዚህ የምርት ዘመን እየተመለከትን ያለውም ይህንኑ ነው።
በሀገሪቱ ግብርና ሜካናይዜሽን በአጠቃላይ፣ በእዚህ የምርት ዘመን በሜካናይዜሽን መሳሪያዎች እየተካሄደ ስላላው የግብርና ስራ በተለይ ያነጋገርናቸው በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ሜካናይዜሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ በረከት ፎርሲዶ እንዳሉት፤ የምርት ዘመኑ የመኸር ግብርና ሥራ ከፍተኛ የሆነ የመሬት ስፋት ለግብርና ሥራ የዋለበት ሲሆን፣በመደበኛ በዝናብ ወቅት ከሚከናወን የግብርና ሥራ በተጨማሪ በመስኖ ጭምር የልማቱ ሥራ የተጠናከረበት ነው። በቅድመ ዝግጅት ግብርና እና በድህረ ምርት አሰባሰብ ከፍተኛ የሆነ የቴክኖሎጂ ወይንም በዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች የመጠቀም ፍላጎትም ታይቷል።
በተለይም ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ የግብርና ሜካናይዜሽን ፍላጎት እየጨመረና አቅርቦቱም እያደገ መጥቷል። በየግላቸው እንደ ትራክተር፣ ኮባይነር ሀርቨስት (ሰብል አጭዶ የሚወቃ መሣሪያ)፣ሌሎችም የግብርና ቴክኖሎጂ ገዝተው የኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ ተፈጥረዋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተናጠል አንድና ከዚያ በላይ የሜካናይዜሽን መሣሪያ ያላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች በማህበር ተደራጅተው በጋራ አቅም ፈጥረው አገልግሎቱን እንዲሰጡ በማስተባበር በተወጣው ሚና ከ270 በላይ የሆኑ አባላትን የያዘ ኢትዮጵያ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ሰጭዎች ማህበር ተመስርቶ የተናበበ ሥራ እየተሰራ ነው፤ ይህም በዘርፉ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
አገልግሎት አቅራቢዎችም በየግላቸው አገልግሎት ሲሰጡ ያጋጥማቸው የነበረውን ችግርና ከመንግሥትም የሚፈልጉትን ድጋፍ ለማግኘት እንዳስቻላቸው በማህበር ተደራጅተው በጋራ መሥራት ከጀመሩ ወዲህ መገንዘብ ተችሏል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ለግብርናው ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ ከማህበሩ አባላት ጋር ቀድሞ ምክክር ያደርጋል።
ቅድመ ምክከሩም የአገልግሎት ጥራት እንዲጠበቅ የአሰራር ሥርአቱን ተከትለው እንዲያከናውኑ ለማስቻል ነው። ነዳጅ ለመቆጠብ ሲባልና በችኮላ በእርሻ ወቅት በሚያስፈልገው የጥልቀት መጠን መሬቱን ያለማረስ ሁኔታ እንዳይፈጠር፣ በሰብል መሰብሰብና መውቃት ወቅትም በተመሳሳይ በሚሰጠው የቴክኖሎጂ አገልግሎት በአግባቡ እንዲከናወን፣አገልግሎት ሰጭዎቹ ገቢ የሚያገኙት አርሶ አደሩ ምርታማነቱ ሲጨምር እንደሆነ፣አገልግሎታቸውም ወቅታዊ የዋጋ ሁኔታን ያገናዘበ እንዲሆን ሚኒስቴሩ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይሰራል። ወጭ ቆጣቢ የሆነ አሰራር እንዲጠቀሙና የግብርና መሳሪያ አጠቃቀም ላይም ሥልጠናም ይሰጣል።
ምክክሩ አገልግሎት ተጠቃሚው አርሶ አደርም አገልግሎቱን ከማግኘቱ በፊት ማወቅ ስላለበት ቅድመሁኔታ ግንዛቤ እንዲኖረው ይደረጋል ሲሉ አቶ በረከት ይጠቄማሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ በተለይም ስለቴክኖሎጂ አጠቃቀሙና የቴክኖሎጂውን ጥቅም በተመለከተ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው በመንግሥት በጀት በተለያዩ ፕሮግራሞች በሚደረግ ዝግጅት በአርሶ አደር ማሳ ላይ ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ ያለውን ሂደት የተግባር ትምህርት እንዲያገኝ ይደረጋል። ይህም የሚከናወነው ከክልሎች ጋር በመሆን ነው።እንዲህ ያለ ቅድመዝግጅት ችግሮችን ቀድሞ ለመፍታትና ሥራውንም የተቀላጠፈ ለማድረግ ጠቃሚ ሆኖ በመገኘቱ ያልተቋረጠ ምክክር ይደረጋል።
በዚህ የምርት ዘመንም ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱን አቶ በረከት ይናገራሉ። በአሁኑ ጊዜ ከነዳጅና ከመለዋወጫ ዋጋ ጋር በተያያዘ የአገልግሎት ዋጋ ጭማሪ ስለሚኖር የተጋነነ ዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር በምክክር መድረክ መግባባት ላይ ተደርሶ ነው ወደ ሥራ የተገባው ሲሉ ይገልጻሉ። በተጨማሪም እንደ ሀገር ከፍተኛ ጭማሪ ያለው የምርት ዝግጅት በመደረጉ አገልግሎት ሰጭዎቹ በአንዱ አካባቢ ሥራቸውን እንዳጠናቀቁ ወደሌላው በመሄድ አገልግሎታቸውን እንዲያቀላጥፉ የማነቃቂያ ፕሮግራምም መካሄዱንም ይገልጻሉ።
አስቀድሞ ምርት በሚደርስበት ኦሮሚያ ክልል አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ጠቅሰው፣ በመቀጠልም ወደ ደቡብ ክልል እንዲሄዱ መደረጉን ተናግረዋል። ከዝዋይ፣መቂ፣ቆሴ፣ስልጤ፣ሐዲያ፣ጉራጌ ይዘው ነው በክልሉ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ የሚገኙት። ወደ ሶማሌ ክልልም የሚንቀሳቀሱ አሉ ይላሉ።
ባለፈው ሳምንትም ሚኒስቴሩ የአገልግሎት ሰጪዎችን ተወካይ ወደ አማራ ክልል ይዞ በመሄድ በአካባቢው እንዲሰሩ የማነቃቂያ ሥራ መሰራቱን አስታውቀዋል። በዚህ መልኩ እየተሰራ ባለው የመኸር ሰብል አሰባሰብ በምርት ዘመኑ ወደ1800 ኮባይን ሀርቨስተር(ማጨጂያና መውቂያ ማሽን)፣በከፊል በአርሶአድር ጉልበት የተከናወነውን ሥራ የሚያግዝ 13ሺ የመውቂያ ማሽንም በሥራ ላይ መዋሉን አስታውቀዋል። በኪራይ አገልግሎት ከቀረቡት ከነዚህ ቴክኖሎጂዎች በተጨማሪ አርሶ አደሩ በራሱ አቅም አነስተኛ በሆኑ ማሽኖች በመጠቀም ጉልበቱንና ጊዜውን በመቆጠብ እየሰራ መሆኑን ይገልጻሉ።
በማህበራት ከሚቀርቡ አገልግሎቶች በተጨማሪ አቅም ያለው አርሶ አደርም የማረሻ፣ማጨጃና መውቂያ ቴክኖሎጂዎችን ለአካባቢው አርሶ አደር በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲያደርግ እየተሰራ መሆኑንም ነው አቶ በረከት የጠቀሱት። ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት የግብርና ቴክኖሎጂዎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በግዥ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡትንና በማህበር ተደራጅተው አገልግሎት ከሚሰጡ በተገኘ መረጃ ላይ የተሰመሰረተ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
የግብርና ሜካናይዝሽን ቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት ይፈልጋል ያሉት አቶ በረከት፤የሥራ መሳሪያዎቹን በግብርና ሥራው ላይ ለማዋል በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ ሚኒስቴሩ ማሰልጠኛ ተቋም አቋቁሞ በአጭር ጊዜ ስልጠና ባለሙያዎች እያበቃ መሆኑንና በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛም በቴክኖክና ሙያ (ቲቤቲ) በደረጃ(ሌብል) እንዲሰለጥኑ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ግብርናው በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ አስረድተዋል።
ለግብርናው አገልግሎት የሚውለት መሳሪያዎች ከቀረጥ ነጻ ከውጭ እንዲገቡ፣በሀገር ውስጥ የተፈጠሩ አነስተኛ የቴክኖሎጂ አምራች ኢንዱስትሪዎችም የጥሬ ዕቃ ግብአት ከቀረጥ ነጻ ከውጭ እንዲያስገቡ በመንግሥት እንዲበረታቱ መደረጉ አጠቃቀሙ እንዲጨምር ካደረጉ ተግባራት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት እንደሚያመለክት ተናግረዋል።
በግብርና ሜካናይዜሽን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረው ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እንደሚኖረውና ተከታታይ ሥራም እንደሚያስፈልግ ይታመናል። አቶ በረከት ይህን አስመልክቶም ሲናገሩ በቴክኖሎጂ ታግዞ የተገኘውን ውጤት በቁጥር ለማስቀመጥ ጥናት ይፈልጋል ብለዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ካለው ነባራዊ ሁኔታ በሜካናይዜሽን በኩል መልካም ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው። እንደ ሀገር ወደ 13 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለግብርና ሥራ እየዋለ እንደሆነ ይገመታል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ወደ 75 በመቶ የሚሆነው ለሜካናይዜሽን የግብርና ሥራ ምቹ ነው። በቴክኖሎጂው በመጠቀም ቀደም ሲል በማምረት ሂደት ያጋጥም የነበረውን ወደ 30 በመቶ ብክነት ወደ አምስት በመቶ ለማውረድ በአስርአመት መሪ እቅድ ውስጥ ተካትቷል። ጥቅም ላይ እየዋለ ባለው ቴክኖሎጂ ብክነቱን በምን ያህል ማስቀረት እየተቻለ እንደሆነ የጥናት ሥራ ይፈልጋል።
በእስካሁኑ ሂደት ስለነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችም አቶ በረከት እንደገለጹት፤ በጠንካራ ጎን ከሚጠቀሰው አንዱ በግብርና አመራረት ላይ የአርሶ አደሩ ግንዛቤና የእውቀት ደረጃ ከፍ ብሏል። በግብርና ኤክስቴንሽን የሚሰጠውን ምክርና አገልግሎት በመጠቀም ገበያ ተኮር ምርት ለማቅረብ የሚያደርገውም ጥረት የሚሰጠውን ምክር ተግባር ላይ በማዋል እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ያሳያል። ለአብነትም በአማራ ክልል በክላስተር የአዘራር ዘዴ በመጠቀም እየተገኘ ያለው ውጤት ወይንም የምርት ቁመና አበረታች ነው። ደቡብ ጎንደር መተማና ቋራ አካባቢዎች ወደ 250ሺ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ አኩሪአተር ተመርቷል።
ይህም አግሮ ኢንደስትሪውን ወይንም አቀነባብሮ ለተጠቃሚው የሚያቀርበውን ኢንዱስትሪ ለመመገብ ታስቦ በአካባቢው የተጀመረ ልማት ነው። ልማቱ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ለማስቻል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሰሞኑ መረጃ ለመሰብሰብ ወደ ሥፍራው ሄዶ ነበር። አገልግሎት ሰጪዎች ወደ ስፍራው በመሄድ አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎት በማሳየታቸው በቅርቡ የደረሰውን የአኩሪ አተር እንደሚሰበስቡ ይጠበቃል።
ካላቸው የመሬት ስፋት ወይንም ከተነሳሽነትና ፍላጎት ጋር በተያያዘ የግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም አካባቢ ከአካባቢ ልዩነት ሊኖር ይችላል። በዚህ ላይም አቶ በረከት በሰጡት ማብራሪያ የሜካናይዜሽን አቅርቦቱ ተጠናክሮ ከመቀጠሉ በፊት ቀደም ሲልም ተሞክሮው ባለባቸው አካባቢዎች በተሻለ መንቀሳቀስ፣ፍላጎትም መጨመር ጋር ተያይዞ የስርጭት ከፍ ማለት በመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍል ኦሮሚያ፣ደቡብ፣አማራ ክልሎች ይስተዋላል። አሁን ላይ በአርሶ አደሩ በኩል እየታየ ያለው ቴክኖሎጂውን የመጠቀም ፍላጎት ቴክኖሎጂውን ጥቅም ላይ የመዋል ተከታታይነት ያሳያል።
አርሶ አደሩ ቀደም ሲል መሬቱን አርሶ ለመከስከስ ብቻ ነበር ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ፍላጎት የነበረው ያሉት አቶ በረከት፣ በአሁኑ ጊዜ ግን በመስመር መዝራትን፣በሰው ጉልበት የሚካሄደውን የፀረተባይ መርጨት ስራን የመሳሰሉ ሰፋፊ ተግባሮችን የሚያከናወኑ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ነው። የበጋ መስኖ ልማት የአርሶ አደሩን በግብርና ሜካናይዜሽን የመጠቀም ፍላጎት እንዲጨምር አድርጎታል። በአርሶ አደሩ የተፈጠረው መነቃቃትና ከዝናብ ጥገኝነት ተላቅቆ አመቱን ሙሉ ለማምረት እንዲችል የቴክኖሎጂ አቅርቦቱ መጠናከር ይኖርበታል።
በግብርና ሜካናይዜሽን ታግዞ ስለተከናወነው የምርት አሰባሰብ ሁኔታ አቶ በረከት ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በየጊዜው ባለው የመረጃ መለዋወጥ ትክክለኛውን መረጃ ለማስቀመጥ እንደሚያዳግት ተናግረዋል። የመኸሩ ምርት መሰብሰብ ቢጀምርም በአብዛኛው ግን ከተያዘው ህዳር ወር ጀምሮ ነው የመሰብሰቡ ሥራ የሚጠናከረው ብለዋል።
የግብርና ሜካናይዜሽን ሥራውን ለማጠናከር በሚኒስቴር መሥሪያቤቱ ዳይሬክቶረት ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከተገባ ከሰባት አመት በላይ እንደሆነው የጠቆሙት አቶ በረከት፣ የፖሊሲ ድጋፍ የሚፈልጉ ሥራዎችን ከተበጣጠሰ አሰራር በመውጣት በተጠናከረ መልኩ መሠራት ከጀመረ ግን ሶስት አመት እንደሆነው ይገልጻሉ። በዚህ ጊዜ ውስጥም ከተቋማዊ አደረጃጀት ጀምሮ ለውጥ የታየባቸው ሥራዎችን ማየት ተችሏል ብለዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2015