ሄርሜላ ተሾመ ትባላለች:: የሃያ አራት ዓመት ወጣት ናት:: ነፍስ ካወቀችበት ማለትም ከሰባት ዓመቷ ጀምራ ከእናትና አባቷ በወረሰችው የፋሽን ዲዛይነርነት ሙያ ተሰማርታ ላለፉት አስራ ሰባት ዓመታት እየሠራች እንደምትገኝ ትናገራለች:: ከቤተሰቧ በተረከበችው ሙያ ላይ ዕውቀትና ክህሎት ጨምራ፣ በዘመናዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ታግዛ ሥራውን የበለጠ አጠናክራ በውጤታማነት ለማስቀጠል ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጨርቃ ጨርቅና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በ2013 ዓ.ም (በኮቪድ ወረርሽኝ የተነሳ ወደ2014 ዓ.ም የተዛወረ) በፋሽን ዲዛይንና ቴክኖሎጂ ተመርቃ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች::
በአባቷ አቶ ተሾመ ስሜ እና እናቷ ብስራት ጣሰው የተመሠረተው “ኤም.ኬ ዲዛይንና ዲኮር” ከተመሠረተ አሁን ላይ ሃያ ስምንተኛ ዓመቱን ይዟል:: ከሰባት ዓመቷ ጀምራ ላለፉት አስራ ሰባት ዓመታት በእናትና አባቷ ደርጅት ውስጥ በፋሽን ዲዛይነርነት እየሠራች የምትገኘው የ24 ዓመቷ ወጣት ሄርሜላ፤ “ድርጅታችን ከእኔ ዕድሜ በላይ ከሃያ ሰባት ዓመታት በላይ በዘርፉ ተሠማርቶ እየሠራ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም ነው” ትላለች:: በዋነኝነት በባህል አልባሳት ስፌትና ዲዛይን ሥራ ላይ ተሰማርቶ እየሠራ መቆየቱን የምትናገረው ዲዛይነር ሄርሜላ አሁን አሁን ግን በባህላዊ ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ አልባሳት ስፌትና ዲዛይን ላይ ጭምርም እየሠሩ መሆናቸውን ትገልጻለች::
ከስፌትና ዲዛይን እንዲሁም ሽያጭ በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት በተለይም ለልዩ ልዩ ሁነቶች የሚሆኑ ባህላዊና ዘመናዊ አልባሳትን በማከራየት፣ የተለያዩ ሁነቶችንና አውደ ርዕዮችን በማዘጋጀትና ለዚሁ የሚሆኑ ባህላዊና ዘመናዊ አልባሳትን በሽያጭና በኪራይ በማቅረብ ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ትናገራለች:: የምርቶቻቸውን የገበያ ተደራሽነት በተመለከተም ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ገቢ ያላቸውን ደንበኞች ሁሉንም ባማከለ መንገድ ሁለገብ ምርቶችን በማምረትና በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ትናገራለች::
ወጣቷ ዲዛነር ሄርሜላ፤ “በቀጣይ መሥራት የምፈልገው በልዩ ሁነትና በዓላት ወይንም መርሃ ግብሮች ጊዜ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ሰዓትና በየትኛውም ቦታ መለበስ የሚችሉ በዘመናዊ መንገድ ተሰፍተው የተዘጋጁ የባህል አልባሳትን ለኢትዮጵያውንና ለአፍሪካውያን ብሎም ለዓለም ማቅረብ ነው” በማለት የወደፊት ራዕይዋን ትናገራለች:: ይሁን እንጂ የኅብረተሰቡ የባህል አልባሳትን ለዘወትር የመጠቀም ፍላጎትና ባህል በጣም ዝቅተኛ መሆንና ገበያው በተወሰኑ ድርጅቶች ብቻ መያዙ እርሷም ሆነ ድርጅቷ ለሰነቁት የወደፊት ራዕይ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን በስጋትነት ታነሳለች::
ለአብነትም የአገር መከላከያ ሠራዊት አልባሳትና ጫማዎች፣ ቦርሳዎች፣ የተማሪዎች ዩኒፎርም አልባሳትና ቦርሳዎች፣ የተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች አልባሳትና ጫማዎች፣ ለተለያዩ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች የሚያስፈልጉ እንደመጋረጃ ዓይነት አልባሳትና ጨርቆችን… የማምረትና የማቅረብ ዕድል የተሰጠው ለጥቂት የአገር ውስጥና የውጭ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራች ድርጅቶች መሆኑን ታነሳለች::
“እናም የቱንም ያህል ባህላዊና ዘመናዊ አልባሳትን በምርጥ ዲዛይንና በጥራት ብናመርትም የገበያ ዕድሉ የሚሰጠው ሁሌም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ትልልቅ የአገር ውስጥና የውጭ አምራቾች ብቻ ከሆነ በመካከለኛና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የምንገኝ አምራቾች እንዴት ተወዳዳሪ መሆን እንችላለን? እንዴትስ ወደከፍተኛ አምራችነት መሸጋገር እንችላለን?” ትላለች:: ስለሆነም መንግሥት ድጋፍ ባያደርግልን እንኳን ቢያንስ የገበያ ዕድሉን ለእኛም ሊሰጠን ይገባል ትላለች::
ለአንድ አምራች ለሕልውናው መቀጠልም ሆነ ወደቀጣዩ የእድገት ደረጃ ለመሸጋገር ዋነኛው ነገር ገበያ መሆኑን የምታመላክተው ዲዛይነር ሄርሜላ መንግሥት የገበያውን ሁኔታ ካመቻቸላቸውና ዕድሉን ከሰጣቸው የእርሷና ቤተሰቦቿን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማሩ የመሥራት አቅም ያላቸውና ወደከፍተኛ ደረጃ ማደግ የሚችሉ ሌሎችም በርካታ ድርጅቶች መኖራቸውን ትጠቁማለች:: በገበያ በኩል ያለው ከተፈታ ከኅብረተሰቡ አመለካከትና ባህል ጋር በተያያዘ ያለው ቀሪው ተግዳሮት በአንድ ጊዜ ባይሆን ቀስበቀስ በሂደት መፍታት የሚቻል መሆኑንም ታመላክታለች:: ይህንን ለማድረግም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ሚና ያላቸው መሆኑንም ታስረዳለች::
ለዚህም ከራሳችን መጀመር አለብን ትላለች:: መጀመሪያ መንግሥትና የአገራችንን ዜጎች አምነውብን ዕድሉን እንዲሰጡንና ምርቶቻችንን እንዲገዙን ማድረግ ይገባናል:: ከዚያም በእኛው የተሠሩና የተመረቱ “በኢትዮጵያ የተመረቱ” የሚሉ ባህላዊም ሆኑ ዘመናዊ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርቶቻችንን ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ብሎም ለአውሮፓና ለመላው ዓለም መላክ እንችላለን ትላለች ወጣቷ ባለራዕይ ዲዛይነር ሄርሜላ ተሾመ::
የባህል ልብሶቻችን የሚሠሩበት ጨርቅ ጥራና የሚሰፉበት ክር ጥንካሬም ለዘወትር ልብስነት ተመራጭ እንዳይሆኑ አንደኛው ተግዳሮት መሆኑንም ነው ዲዛይነር ሄርሜላ የምታመለክተው:: ይህንን ችግር ለመቅረፍም የእርሷና የቤተሰቧ ድርጅት የሆነው ኤም.ኬ ዲዛይንና ዲኮር በመፍትሔ አማራጭነት የያዘው ጨርቆቹን ከውጭ በማስመጣትና በአገር ውስጥ ሰፍቶ ለገበያ ማቅረብ ነው:: ለዚህም ብራንዲንግ ላይ ትኩረት አድርጎ ለመሥራት መወሰኑንም ታመላክታለች::
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2015