በኢኮኖሚያቸው በከፍተኛ ደረጃ እያደጉ ያሉት ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ሕንድና ደቡብ አፍሪካ ትብብራቸውን ልማታቸውንና ደኅንነታቸውን የሚያጠናክርላቸውን ብሪክስ የተሰኘ ተቋም ከመሠረቱ ዓመታት ተቆጥረዋል። እነዚህ ሀገሮች በቅርቡ ደግሞ ኢትዮጵያን፣ ግብፅን፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትን ጨምሮ ሌሎች ሀገሮችን በአባልነት ይዘዋል።
ጥምረቱ ሀገሮቹ ኢኮኖሚያቸውን የሚያሳድጉበት፣ ለምርቶቻቸው ገበያ ለመክፈትና ለማፈላለግ በትብብር የሚሠሩበት፣ በአጠቃላይ የገበያ ትስስራቸውን የሚያስፉበት የትብብር መድረክ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በማኅበራዊ ዘርፎችም እንዲሁ በጤናና በትምህርት እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂም ጭምር ትስስር በመፍጠር ልማታቸውን የሚያሳልጡበትም እንደሚሆን ይጠበቃል።
በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት 2024 በጥር ወር ኢትዮጵያም የዚህ ጥምረት አባል መሆኗ ይታወሳል። ኢትዮጵያ የዚህ ጥምረት አባል መሆኗ ከጥምረቱ መሥራቾች ጋር ብቻ ሳይሆን አባላት ጋርም በተለይ በምጣኔ ሀብት ረገድ የሚኖራትን ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክርላት ይታመናል።
በተለያዩ የምጣኔ ሀብቱ ዘርፎች ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችለው የዚህ ጥምረት መሥራቾችና በፋሽን ኢንዱስትሪያቸውም ቀላል የማይባል ገንዘብ የሚዘዋወርባቸው ናቸው። በዚህም ባሕልን፣ ማንነትን ለመግለጽ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እንዳለውም ይታሰባል። ይህንን ሀሳብ ለማጎልበት እና የጥምረቱ አባል ሀገራት በዘርፉ ላይ ያላቸው እንቅስቃሴ ውጥነትን የተከተለ እንዲሆን የሚያስችል መድረክ በቅርቡ ተካሂዷል ።
መድረኩን አስመልክቶ የወጣ መረጃ እንዳመለከተው፤ ይህ ብሪክስ የፋሽን የተሰኘ መድረክ በሞስኮ ባሳለፍነው ሳምንት እ.አ.አ ከጥቅምት ሦስት እስከ አምስት ለሦስት ቀናት ነው የተካሄደው። በዓለም አቀፍ ደረጃ እወቅና ካላቸው የፓሪስ ፋሽን ሳምንት እንዲሁም የሚላን ፋሽን ሳምንት ተከትሎ የተካሄደው ትልቅ የፋሽን መድረክ መሆኑ ተነግሮለታል። ከ100 በላይ የሚሆኑ ከተለያዩ ሀገራት የተወጣጡ ተሳታፊዎች እንደተገኙበት የተጠቆመ ሲሆን፣ ይህም ብሪክስ በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ እያሳየ ያለው ተፅዕኖ የተንጸባረቀበት ተብሏል።
በመድረኩም በፋሽን ኢንዱስትሪው እየታየ ስላለው ለውጥ ውይይት ተካሂዷል። በዚህ መድረክ ላይ በየዓመቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚዘጋጀው የ‹‹ሀብ ኦፍ አፍሪካ ፋሽን ሳምንት›› መሥራች እና አዘጋጅ የሆነችው ማሕሌት ተክለማርያም ኢትዮጵያን ወክላ ተሳትፋለች ።
በወቅቱም ‹‹የብሪክስ ዓለምአቀፍ የፋሽን ፌዴሬሽን›› ይፋ ተደርጓል። ፌዴሬሽኑ በአባል ሀገራት የሚገኙ የፋሽን ፈጠራዎችን በአንድ በማምጣት፣ የተለያዩ ንድፈ ሀሳቦችን እና ልዩ ልዩ ባሕላዊ መግለጫዎችን የሚያቀርብ እና አዳዲስ ጽንሰ ሀሳቦችን እና ፈጠራዎችን ለዓለም አቀፍ ፋሽን ኢንዱስትሪ የሚያስተዋውቅ መሆኑም ተገልጿል።
የፌዴሬሽኑ መመሥረት ዋና ዓላማም በአባል ሀገራቱ በተለያዩ የፋሽን ዘርፎች ላይ የተሠማሩ ኢንዱስትሪዎችን ማጠናከር፣ የተለያየ ችሎታ እና ተሰጥዖ ያላቸውን ዲዛይነሮች መደገፍ፣ የባሕል ልውውጥን ማበረታታት፣ የጋራ የሆነ የግብይት መስመርን መፍጠር ነው ተብሏል ።
የሞስኮ ምክትል ከንቲባ ናታሊያ ሰርጉኒና የብሪክስ ዓለም አቀፍ የፋሽን ፌዴሬሽን መመሥረት ለብሪክስ ትልቅ ስኬት መሆኑን አስታውቀዋል። የፋሽን ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን መመሥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሳታፊ ለሆኑት ሀገራት ቁልፍ ጉዳይ የሚጋሩበት መድረክ ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ ከበርካታ ሀገራት የተውጣጡ በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ላይ የሚሠሩ፣ የፋሽን ሳምንት አዘጋጆች እንዲሁም የፋሽን ትምህርት ቤት ባለቤቶች፣ ዲዛይነሮች ተገኝተዋል። በብሪክስ ዓለምአቀፍ የፋሽን ፌዴሬሽን አባል ከሆኑት ሀገራት መካከልም ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ስፔን፣ አሜሪካ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ማሌዢያ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ ይገኙበታል።
ኢትዮጵያን ወክላ በመድረኩ የተገኘችው የሀብ ኦፍ አፍሪካ ፋሽን ሳምንት መሥራች እና አዘጋጅ ማሕሌት ተክለማርያም በመድረኩ ላይ ንግግር አድርጋለች። መድረኩን አስመልክተን ያነጋገርናት ማሕሌት ዝግጅቱ በፋሽን ኢንዱስትሪው ከሚሠሩ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ጋር ለመገናኘት እና ትውውቅ ለመፍጠር ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጻለች።
‹‹ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር እንደመሆኗ በዚህ ዓለም አቀፍ የፋሽን ፌዴሬሽን ላይም አባል ሆናለች። ፌዴሬሽኑ በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ የተማሩ ባለሙያዎችም ሆኑ ነጋዴዎች ከሌሎች ሀገራት አቻዎቻቸው ጋር ያላቸውን የገበያ ትስስር በእጅጉ እንዲያሳድጉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በሀገራችን በመነቃቃት ላይ ለሚገኘው የፋሽን ዘርፍ እድገትም የራሱ የሆነ ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖረዋል›› ስትል ገልጻለች።
የብሪክስ ዓለም አቀፍ የፋሽን ፌዴሬሽን መቋቋም በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ራዕይ ያላቸውን የፋሽን ኢንዱስትሪው የፈጠራ ባለቤቶች ሥራዎቻቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያሳዩ እና እውቅና እንዲያገኙ ከመሥራት ባሻገር የፋሽን ኢንዱስትሪው በሚኖረው የአመራረት ሒደት በተፈጥሮ ላይ እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚያመጣው አሉታዊ የሆነ ተፅዕኖን በመቀነስ ረገድም የራሱን ሚና ሊጫወት እንደሚችል በመድረኩ ላይ ተገልጿል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም