የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንትን ባሳለፍነው ሳምንት በተለያዩ ኩነቶች አካሂዷል። የቱሪዝም ሳምንቱ ከመስከረም 21 ጀምሮ ለሶስት ቀናት የተካሄደ ሲሆን፣ የቱሪዝም ኤግዚቢሽንን፣ የሆቴልና የሆስፒታሊቲ ዘርፉን ለማበረታታትና ትብብር ለመፍጠር ያስቻለና ምርት አቅራቢ ድርጅቶች ምርቶቻችን ለገበያ ያቀረቡበት እና ያስተዋወቁበት መድረክ ሆኖ አገልግሏ ።
በዚህ የቱሪዝም ሳምንት ማብቂያ ላይ የቱሪዝም ሽልማት እና እውቅና የመስጠት ሥነ-ሥርዓትም ተካሂዷል። በቱሪዝም ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት ፣ ቡድኖችና ግለሰቦች የእውቅና ሽልማቶች ተበርክቷል።
የወይዘሪት ቱሪዝም ኦሮሚያ የቁንጅና ውድድር በቱሪዝም ሳምንቱ ማብቂያ ላይ ተካሂዷል። በመድረኩም ለቀጣዩ አንድ ዓመት የኦሮሚያ ክልልን የቱሪዝም ሀብቶች የምታስተዋውቅ የኦሮሚያ ቱሪዝም አምባሳደር ምርጫ ተካሂዷል።
በዚህ መድረክ ላይ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ፣ የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ዱጋ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ታዋቂ ሰዎች እንዲሁም ባለፉት ዓመታት የተደረጉ የወይዘሪት ቱሪዝም ኦሮሚያ ውድድር አሸናፊዎችም ታድመውበታል።
በዘንድሮው የወይዘሪት ቱሪዝም ኦሮሚያ ውድድር በርካታ ሞዴሎች መሳተፋቸውና ውድድሩ ከሁለት ወር በፊት መጀመሩም ተጠቁሟል። በዚህም በተለያዩ መስፈርቶች የተመረጡ ተወዳዳሪዎች የቀረቡ ሲሆን፣ በጽሁፍ እና የቃል ፈተና ተወዳድረው ያሸነፉ 14 የሚሆኑ ተወዳዳሪዎች ለመጨረሻው ዙር የወይዘሪት ቱሪዝም ኦሮሚያ እጩ ሆነው መቅረባቸውም በመድረኩ ተገልጿል።
በኦሮሚያ የቱሪዝም ሳምንት መዝጊያ ሥነሥርዓት ላይ ውድድራቸውን ያደረጉ እጩዎች፣ በፋሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ በተሰማሩ እንዲሁም የኦሮሚያን ኪነጥበብ እና ባህል በማስተዋወቅ ድርሻ ባላቸው አካላት ነው የተዳኙት።
ተወዳዳሪዎቹ በመድረኩ ላይ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚዘወተሩ ባህላዊ አልባሳትን በመልበስ እና ስለባህሉ ገለጻ በማድረግ ራሳቸውን አስተዋውቀዋል። ከውድድሩ ተሳታፊዎች መካከል በቅድሚያ ዳኞች አስር ተወዳዳሪዎችን የለዩ ሲሆን፣ በቀጣይም ተወዳዳሪዎች የለበሱት የባህል ልብስ የሚገለጽበትን የጭፈራ ሥርዓት በመድረኩ እንዲያሳዩ ተደርገዋል።
ወይዘሪት ቱሪዝም ኦሮሚያ የምትመረጥበት መስፈርት ውጫዊ ውበት ብቻ አይደለም፤ ውስጣዊ ውበት ወይም እውቀትም መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ ተወዳዳሪዎች ለባህላቸው የሚሰጡት ቦታም ከግምት እንዲገባ እንደሚደረግ ተመልክቷል።
ዲዛይነር ፍርዶሳ ዩሱፍ ወይዘሪት ቱሪዝም ኦሮሚያን ለመምረጥ የዘንድሮውን ጨምሮ ለአራት ዓመታት የተካሄዱትን የወይዘሪት ቱሪዝም ኦሮሚያ ውድድሮችን በዳኝነት ከመሩት መካከል ናት። የኦሮሚያ ባህል አልባሳት ባህሉን በጠበቁ መልኩ ዲዛይን በማድረግ እና ከሀገር ውጪ እንዲሁም በተለያዩ ሀገራት በማስተዋወቅ ግንባር ቀደም ከሚባሉ ዲዛይነሮች ትጠቀሳለች።
በዘንድሮው የኦሮሚያ የቱሪዝም ሳምንት መዝጊያ መድረክ ላይ በቱሪዝም ዘርፉ የክልሉን የቱሪዝም ሀብት በማስተዋወቅ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የዘርፉ ተዋንያን ክልሉ ባዘጋጀው የቱሪዝም ሽልማትም ዲዛይነር ፍርዶሳ ልዩ ተሸላሚ ሆናለች።
የፋሽን እሳቤ በብዙዎች ዘንድ የሚኖረው አመለካከት የተለያዩ ነው ያለችው ዲዛይነሯ፣ ባህላዊ አልባሳትን ዘመኑን በሚመስል መልኩ ሠርቶ ማቅረብ እና ማሳየት ሲነሳ ባህሉ የሚጠይቀው የአለባበስ ሥርዓት ፈር ሊለቅ ይችላል የሚለው የብዙዎች ስጋት መሆኑን ታመለክታለች።
‹‹ ፋሽን ለእኔ ማንነቴን የምገልጽበት ነው ብዬ ነው የማስበው፤ ሰው ደግሞ ክብር የሚሰጠን መጀመሪያ ለራሳችን ባህል እኛው ክብር ስንሰጠው ነው ብዬ አምናለሁ። እኔ ባህል አይቀየርም የሚል እምነት አለኝ፤ በተለያየ መድረክ ባህሉንና ክብሩን በጠበቀ መልኩ ማሳየት ማስተዋወቅ እንችላለን፤ አቀራረባችን ዘመናዊ ለማድረግ በሚል የምናከናውነው ተግባር ባህሉን የለቀቀ የሚያደርገው መሆን የለበትም›› ብላለች።
የፋሽን ኢንዱስትሪ የአንድ ሀገር ባህል እና ማንነት የሚገለጽበት ታላቅ መድረክ ነው›› ስትል አብራርታም፣ ከዚህ አኳያ ገና ብዙ ሥራ እንደሚቀር ዲዛይነር ፍርዶሳ አስታውቃለች። ‹‹የእኛ ሀገር ባህል ልዩና ሰፊ ነው፤ በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚኖረው አስተዋጽኦ ሀገርን እንዲያስተዋውቅ ለማድረግ በብዙ መንገዶችን መጠቀም ይቻላል›› ስትል አመልክታለች።
የወይዘሪት ኦሮሚያ ቱሪዝም የቁንጅና ውድድር ባህልና አለባበስን ለፋሽን ኢንዱስትሪው በስፋት ለማስተዋወቅ እንደሚረዳም ገልጻ፣ ‹‹ እንደዚህ አይነት መድረኮች መዘጋጀታቸው አንድም ባህላችንን እናስተዋውቅባቸዋለን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የቱሪዝም መዳረሻችንን እናሰፋባቸዋለን፤ ስለዚህ መቀጠል አለባቸው ›› ብላለች።
የዘንድሮው 2017 ዓ.ም የወይዘሪት ቱሪዝም ኦሮሚያ አሸናፊ ለመሆን ከተወዳደሩ 14 ተወዳዳሪዎች መካከል ደራርቱ ተስፋዬ አሸናፊ ለመሆን የበቃች ስትሆን፣ ለአንድ ዓመት ያህል የኦሮሚያ ቱሪዝምን የምታስተዋውቅ አምባሳደር ናት። በውድድሩ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ለወጡ አሸናፊዎችም እውቅና እና የገንዘብ ሽልማት በመድረኩ በተገኙት የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ዱጋ ተበርክቶላቸዋል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም