የአትሌቲክስ ስፖርት ሩጫን፣ ዝላይና ውርወራን የሚያጠቃልል ስፖርት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ትኩረቱን ያደረገው በሩጫ ላይ ያውም በረጅምና መካከለኛ ርቀቶች ላይ ብቻ ነው፡፡ አገሪቷ ለስፖርት አስፈላጊ የሆኑ ጸጋዎች ቢኖሯትም በአግባቡ እየተጠቀመችበት ግን አይደለም፡፡
አስቀድሞ የምትታወቅበት የረጅም ርቀት ውድድርም ቢሆን በተቆራረጠና ተተኪዎች እንደየወቅቱ በማይገኙበት ሁኔታ ቀጥሏል፡፡ በቅርቡ ኦሊምፒክ እና የዓለም ቻምፒዮና ውድድሮች ላይ የአገራቸውን ስም በድል ሲያስነሱ የቆዩ አትሌቶች ፊታቸውን ወደ ጎዳና ላይ ሩጫዎች እየመለሱ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ለማሳያ ያህልም አልማዝ አያና፣ ገንዘቤ ዲባባ እና ለተሰንበት ግደይ ማንሳት ይቻላል፡፡ በእርግጥ እነዚህ አትሌቶች አገሪቷ በምትታወቅበት ማራቶን ውጤታማ ሊያደርጓት ይችላሉ፡፡ ይሁንና አሁን ላይ በእነሱ እግር የሚተኩ አትሌቶች መኖራቸው አጠራጣሪ ነው፡፡
በመላው አገሪቷ በርካታ ፕሮጀክቶች፣ የማሰልጠኛ ማዕከላትና አካዳሚዎች እንዲሁም በግላቸው የሚንቀሳቀሱ ታዳጊና ወጣቶች ቢኖሩም የመተካካቱ ነገር ግን በሚፈለገው ልክ አይደለም፡፡ ይህ ሁኔታ ታዲያ የስፖርት ቤተሰቡን ስጋት ላይ የሚጥል ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ዓለም ትኩረቱን በአጭር ርቀቶች እና የሜዳ ተግባራት ላይ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያ በተለይ የምትታወቅባቸው የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶችም ከበርካታ ውድድሮች ላይ መሰረዛቸው ለዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡ በመሆኑም ከጊዜው ጋር ለመራመድ እንዲሁም ከስፖርቱ ከሚገኘው ጥቅም ተቋዳሽ ለመሆን በእነዚህ ስፖርቶች ላይ አተኩሮ መሥራት አስፈላጊ ስለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡
በዚህ ላይ ከትምህርት ቤት እና ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ ካሉ አሰልጣኞች አንስቶ እስከ ታላላቅ የስፖርት ሳይንስ ምሁራን ድረስ ድርሻ አላቸው፡፡ በአትሌቶች ምልመላ፣ የስልጠና ሂደት፣ አመጋገብ፣ በውድድሮች ላይ ስለሚከተሏቸው ቴክኒኮች እና ሌሎች ጉዳዮች ላይም በበቂ እውቀትና ሳይንሳዊ ዘዴ ካልተመራ ውጤታማ ሊያደርግ አይችልም፡፡ በዚህ ረገድ ስፖርቱን የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ፕሬዚዳንቷ ረዳት ኮሚሽነር ጀኔራል ደራርቱ ቱሉ ትጠቁማለች፡፡
አገሪቷ ከምትታወቅባቸው ርቀቶች ባለፈ ውጤታማ ተሳታፊነትን ለማጠናከር ሲባል ፌዴሬሽኑ የአጭር ርቀት፣ ዝላይ እና ውርወራ ቻምፒዮናን ለብቻው በየዓመቱ በመደበኛነት ያዘጋጃል፡፡ ከዚህ ውድድርም በምሥራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ የማሳተፍ ፍላጎት ቢኖርም ለተሳታፊነት የሚያበቃ ሚኒማ ማሟላት ግን አዳጋች ሆኖ መቆየቱንም አንጋፋዋ አትሌት ታስታውሳለች፡፡ በመሆኑም የውድድር ዕድሎችን በማስፋት፣ የሚኒማ ማሟያ በማዘጋጀት እንዲሁም በክለቦች ውስጥ ካሉ አትሌቶች ሻል ያሉትን በእነዚህ ውድድሮች ለማሳተፍ ይሞከር ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀደም ይደረግ እንደነበረው የተሻሉ አትሌቶችን በቀጣና ውድድሮች ላይ ማሳተፍ አልተቻለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ፌዴሬሽኑ የኤሌክትሮኒክስ ሰዓት መቁጠሪያ መሣሪያ ጥቅም ላይ በማዋሉ አጠጋግቶ በውድድር ማሳተፍ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍም ፌዴሬሽኑ የተለያዩ መንገዶችን ሲጠቀም ቆይቷል፤ አሁን ግን እንደመፍትሄ ያስቀመጠው በዘርፉ የተሻሉ አሰልጣኞችን ከውጭ አገራት ጭምር ማስመጣትን ነው፡፡ ከአውሮፓ እና አሜሪካ ባይሆንም በአፍሪካ ልምድ ያላቸውን ከናይጄሪያ፣ ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ሌሎች አገራት በማስመጣት ልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ይሞከራል፡፡ አቅም ከፈቀደ ደግሞ በአሰልጣኝነት ለማምጣት ማቀዱንም ፕሬዚዳንቷ ጠቁማለች፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 19 ቀን 2015 ዓ.ም