ልብ በጥላቻ ተሞልቶ፣ ቂም ነፍስ አውጥቶ ሆድ ውስጥ እየተላወሰ፤ እኛነት ጠፍቶ በእኔነት አይነ እርግብ አይን ከተጋረደ፤ የትናንትን ለመማሪያ ሳይሆን ለመማረሪያ እየተነሳሳ ሰው ሲቆሳሰል ሲደነቋቆል ከመመልከት የላቀ ምን የሚያሳቅቅ ነገር አለ። ዛሬም ከዚህ መንገድ ተላቅቀን፣ ትናንትን ላናነሳ ደግሞ ወደ ኋላ ላናይ ውሾን ያነሳ ውሾ ተባብለን ዳግም ለሰላም እጃችንን ስናነሳ በልባችን ውስጥ አንዱ ጥግጋት ላይ ቂም ላለመኖሩስ ፈትሸን ይሆን ብዬ እጠይቃለሁ።
እኛ በትናንት የይደር ጥላቻ አቁሮ ዛሬን መለኮታዊ ኃይል ተአምር እንዲደረግ የምንለምን፤ ትናንት የተሠሩትን ስህተቶች መተቸት እና መጥቀስ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ ላይ እንዳይደገሙ ማድረግ ብልህነት ላይስ አበክረን ለመሥራት ምን አስበናል?፤ የሚለውን ሁላችንም ለራሳችን ልንመልስ የተገባ ነው። ምክንያቱም እነዚያ ያለፉትን ችግሮች እየተመለከትን ዛሬ ተመሳሳይ የችግር የመሥራት ያላለቀ በደል ውስጣችን ተቀብሮ እየተቸገርን እንገኛለን።
ዘረኝነት እና የጎሳ አቀንቃኞችን እያወገዝን በሌላ አንፃር የዘረኝነት እና የጥላቻ ችግኞችን አካባቢያችን እየኮተኮቱ እና ውሃ እያጠጡ የሚያበቅሉ እና ከስሩ እንዳይጠፋ የሚንከባከቡትን እንደምንስ ተመልክተናቸው ይሆን? በዚህ ረገድ እኛም እሳቤና ምግባራችንን መፈተሽ ይኖርብናል። ምክንያቱም መንፃት መፅዳት ከሥሩ ነው። መተውም ይቅርታም ከልብ ነው። ጥፋትን አምኖ ይቅርታን መጠየቅም የሚጀምረው ከራስ ነው። እነ ጎሳ ከላዮችን እንቃወማለን እያልን በአደባባይ እየጮህን ቤታችን ስንገባ የጎሰኞች አድናቂ ሆነን በቤታችን ጠረጴዛ ዙሪያችን ለእነሱ እድገት እና መልካም ምኞት ብርጭቆ እያጋጨን ነገራቸው እኮ እያልን የምንስቅ ከሆነ የችግሩ መሠረቶች እኛ ነን እናም ልንፈወስ ይገባል እላለሁ።
የዘር ትብታብ በሌሎች ላይ እየጠላን ሰዎች በነፃነት ሃሳባቸውን በሚገልፁበት አንድ ነጥብ ላይ አንተ እንደዚህ ስለሆንክ ነው፤ የእከሌ ጎሳ ስለሆንክ ነው ብለን ልንፈርጅ ስንነሳ ያ የጎሰኝነት ጥቁር መንፈስ ያለው እና የተመሠረተው እኛ ልብ ውስጥ እንደሆነ ልናውቀው ይገባል። ሰው መርጦ ወዶ ባልተወለደበት ዘሩ አንቋሻሽ፤ ሰው ያለጥፋቱ አንድ ላይ በአንድ ማህበር ፈራጅ፤ የራሳችን ዓይን ላይ የቆመ የስህተት ምሰሶ ሳይታየን የሰው ዓይን ጉድፍ ጠራጊ፤ ለዚህኛው አሽቃባጭ ለሌላው አለቅላቂ፤ እርቅ ይሁን ሲባል የሚጎረብጠው እነ ጭር ሲል አልወድም ባዮች ቂም ይዞ ፀሎት ለቅፅፈት ነውና ነገሩ ልብ እንበል እላለሁ።
ሰላምን መርጠን እርቅ ከሆነ ምርጫችን፤ የሄድንበትን የስህተት መንገድ አርመን እና ይቅር ተባብለን፤ ኅብረተሰብ እና ሌሎችን ያላቸውን ልዩነት ጠንቅቀን አውቀን፤ ይቅርታ በሚል የፈውስ ቃል የውህደት ሥራ ልንሠራ ይገባል አላለሁ። በአንፃሩ ደግሞ የዛሬ የበደል ገንቦ ናጭዎቻችን ሊቀቡን የተዘጋጁት ቅቤ ኖሯቸው ሳይሆን ያው ኢትዮጵያን ቢቻላቸው በእምነት እና በአመለካከት የእነሱን ፈር እንድትይዝ አልያም እየተናጠቅን እና እየተባላን እንድንኖር ነውና ልብ ልንል ይገባል እላለሁ።
በደል በደልን ወላጅ፣ ቂም ቂምን አስከታይ ነውና የደም ታሪክን በይቅርታ አድርቀን ከቂምና ከጥላቻ የነፃን እንድንሆን ይሁን። እኔነት ወድቆ ቀርቶ በእኛነት መንፈስ እጅ ለእጅ ብንያያዝ ዳግም ወደ ኋላ የመለስናትን አገራችንን ከፈጠኑት በላይ አፍጥነን የምንመኛትን ታላቅ አገር እንድናይ ቂም አብቅቶ ሰላም ይሰፈን፤ ሁሉም በይቅርታ ይተሳሰር።
ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከተው፣ በጊዜ ሂደት ያፈረስነው የማህበራዊ ትስስር ገመድ ከማጥበቂያው ላልቶብናል፤ እንደ ድሮ ተቻችሎ የመኖር መንፈሳችን በተለያየ ቁስል ጠባሳ ሆኖ ቀርቷል፤ ጠባሳችን ይሽርልን ዘንድ የበላነውን እርም እንመላለስ። የወገን ለቀሶ ለቅሷችን ሆኖ እንባችንን እንተባበስ። ህመሙ ያላንኳኳው ጓዳ ያልደረሰበት ደጅ የለምና በበቃ ይብቃ ቃል በይቅርታ ይታለፍ።
ቀን ጠባቂ ጠልፎ ጣይ ገመዳችንን ለአንድነት ገመድ ማጥበቂያ ለመተሳሰሪያ ይሁንልን፤ የጥላቻ ዓይኖቻችንን በፍቅር ዓይን መልሰን ሁላችን የፈረሰውን ያንተ ትብስ አንቺ መንፈስ ለቸገረው ደራሽ በጋራ ለሚሆን መደጋገፍ ልባችን ይቅና። ከሁሉ በላይ የቀን ጠባቂነት መንፈስ ከውስጣችን ይውጣ። እኛ ሰው ብቻ ነን፤ እናም ሰው ብቻ እንሁን፤ ማነኝ ምንድነሽ ከየት ነህ ወዴት ነህ የሚለው ቋንቋ ይብቃ፤ እርስ በእርስ መጠፋፋት የትናንት የከትናንት ወዲያ ታሪካችን በቂም ጉዳና፣ በመነጣጠን መንገድ እንዲያስጉዘን አንፍቀድለት፤ ክፉን ከመድገም መተሳሰብን መተሳሰርን አብሮነትን ለሚሰብኩቱ ቅድሚያ እንስጥ።
የትናንት ቁስልን ብናነሳ ብንጥል ከቁስለት ያለፈ የሚያተርፍልን ነገር ላይኖረን ለምን ራስን ማቁሰል የመጀመሪያ አማራጫችን አናድርግ። ነገን ጥሩ ማድረግ እየቻልን በትናንት ትዝታ ውስጥ የእውር ድንብር መዳከርን ተልቅ አማራጭ እንደሆነ ማሰባችንን እናቁም።
ትናንት ኢኮኖሚያችንን አድቅቆ፤ ሰዋችንን ያለ ሀብት ንብረት አስቀርቶ፤ የበርካቶችን ሕይወት አስከፍሎን፤ ሳቅም ለቀሶም እስኪጠፋብን ግራ አጋብቶን ሄዷል። በቃ ሄዷል፤ ትንሽም ብትሆን የታየችንን የሰላም ጭላንጭል ተንከባክበን ወደ ወጋገን ካልለወጥናት የከፈልነው ዋጋ በእጥፍ ይጨምራል፤ ስለዚህ ጊዜው በይቅርታ መታጠብን ይሻል። ለትውልድ የምናወርሰው ቁርሾ እንዳይኖር በይቅርታ በቃ እንባበል፤ ፈጣሪ የሚወደውን በየእምነታችን አድርገን የጀርባው ይቅርና የፊታችንን እያፀዳን ወደከፈታው እንራመድ። እርምጃችን በእውቀትና በጥበብ ይሁን፤ በጥበብ የተመራ ትውልድ አይደለም ይህን የዛሬ መከራችንን ማለፍ በህብረት ተራራን መናድን ያውቅበታል።
ትናንት በጠፋው ጥፋት ዛሬ ላይ ያልታመመ ባይኖርም፤ ይበልጥ የተጎዱትን ለማገዝ መወሰን ያስፈልገናል። ወገን ለወገን ነውና ነገሩ ያለንን በመሰንዘር ነጋችንን እናጥራ። ለልጆቻችን የምናወርሰው ቂም አይኑር፤ አገርን በፀና መሠረት ላይ በማኖር በእኛ ዘመን ዳግም ጥፋት ላይመጣ ቃል ገብተን በይቅርታ አንታጠብ። ካለ ይቅርታ ሰላም የልብ ቂምን ይዞም የተሻለ ነገን ማሰብ አይጠበቅም። ቂም ይዞ ፀሎት ለቅስፈት ነውና ነገሩ፤ ካለ ይቅርታ ሰላምን አንናፍቅ። በይቅርታ እንታረቅና አገራችንን በጋራ እናሻግር። ለዛሬው አበቃሁ፤ ሰላም!
ብስለት
አዲስ ዘመን ህዳር 18 ቀን 2015 ዓ.ም