በቤተሰቡ ላይ የወደቀው ዝምታ አስፈሪ ነው። ድንጋጤው ከቤተሰብም አልፎ ጎረቤት ደርሷል። ወዳጅ ዘመድም በሰማው ነገር እየተከዘ ነው። «እውን ወይንስ ቅዠት» የሚለው የሁሉም ጥያቄ ነው። ያልተፈታ እንቆቅልሽ ሆኖ በሁሉም አእምሮ ውስጥ ይመላለሳል። ለማስተዛዘን የማይመችም ጉዳይ ሆኗል። አስደንጋጭ አሟሟት። በቁም ያሉትን አንገት ያስደፋ።
በዝምታ፣ ጨዋ በሚል መጠሪያ ወይም በቤት ልጅነት መድብ ውስጥ ብትመደብ ተቃውሞ የማይቀርብባት ወጣት። አንድ ቀን ራሷን ለማጥፋት ወስና አድርጋው ተገኘች። ታላቅ ድንጋጤ። በቤተሰቡ ውስጥ የሆነው ምን እንደሆነ ግልጽ የሚሆንለት ሰው እንዲጠፋ ያደረገ ክስትት። በለቅሶ ቀናት ውስጥ ኀዘን ከቤተሰቡ ሊወጣ አልቻለም። «እንዴት ሆነ?» የሚለውን ጥያቄ ሊመልስ አቅም ያለው ሰው አልነበረም። ግን ሆነ!
ለማጽናናት የሚመጣ ሰው ተመሳሳይ ታሪኮችን እያነሳ ማውራቱ የተለመደ ነውና መሰል ታሪኮች ከየአቅጣጫው ተሰሙ። ተመሳሳይ ታሪክ መብዛቱ ለቤተሰቡ ግን ጉዳዩ እንቆቅልሽ ሆኖ ከመቆየት ሊያስቀር አልቻለም። ፖሊስ ፍንጭ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ከብጣሽ ወረቀት ያለፈ ሊሆን አልቻለም። ሟች ያስቀመጠችው ማስታወሻ ልብን በሚነኩ ቃላት የተከተበ ነው። እንዲህ ይላል «የሚሰማው ያጣ ሰው ይህን አደረገ። ኃላፊነቱ በራሴ ነው። በአጠገባችን ያለውን ሰው እንወቀው ደግሞም እናድምጠው። » ይላል። ፖሊስ እያንዳንዱን ቃል እየመነዘረ አንዳች የወንጀል መስመር ይገኝ እንደሆን ሞከረ። ብጫቂ ማስታወሻው ከአንድ የወንጀል ክስተት ይልቅ የሕይወት መስመር ግራ መጋባት ሊሆን እንደሚችል ወደ መደምደሙ ነው። የበዛው የቤት ሥራን ለቤተሰብ የተወ።
በሥራ በብዙ ተጠምደው ለቤተሰብ ሁሉ እንዲሞላ የሚተጉ እናትና አባት ራሳቸውን እየወቀሱ የሞትን መንገድ ለራሳቸው ተመኙ። እንዴት ይህ ሆነ? እንዴት? አሁንም እንዴት? የሚለው ጥያቄ ቀጥሏል።
መሰል ታሪኮችን ካለንበት ቤት በተወሰነ ርቀት ላይ ሊገጥመን እንደሚችል ጸሐፊው ያምናል። በዙሪያችን ድምጻቸው ሊሰማ የሚገባ ነገር ግን ያልተሰሙ ሰዎች አሉ። ድምጻቸውን ሊያሰሙ ፈልገው ያልተሳካላቸው ሰዎች በገባቸው መንገድ ሕይወትን ሊፈልጉ ይማስናሉ፤ የስህተት መንገድንም ጨምሮ። አብረን እንደ ቤተሰብ፣ አብረን እንደ አካባቢ፣ አብረን እንደ ማህበረሰብ አብረን እንደ አንድ አገር ሕዝቦች ወይንም እንደ ሰው እየኖርን ያልተሰሙ ድምጾች መኖራቸው ያሳዝነናል።
ዛሬ የምናነሳው ሃሳብ ያልተሰሙ ድምጾችን ስለመስማት ነው። ከዙሪያችን ተነስተን በሁሉም ኃላፊነት ባሉብን መስመሮች ሁሉ። ሌሎችን ከማድመጥ በፊት የሚቀድመውን ራስን ማድመጥን በማስቀደም።
ራስን ማድመጥ
ያለንበት ዘመን «የመርካት አለመርካት» ተቃርኖ ዘመን ነው ልንል እንችላለን። በአንድ በኩል ሕይወትን ለማቅለል የሚረዱ እርካታን የሚፈጥሩ የብዙ ጥረቶች የሚደረጉበት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተቃራኒው የውስጥ እርካታ ጥፋት የሰዎችን ሕይወት ትርጉም አልባ ያደረገበት። ‘የሰው ልጅ ከእዚህ በኋላ እንዴት በቴክኖሎጂ ሊያድግ ይችላል?’ ተብሎ እስኪታሰብ ድረስ ቴክኖሎጂው አስደማሚ ሆኗል። በግንኙነት መስመሩ የሰው ልጅ ከዓለም አንዱ ጫፍ ከሌላኛው ጫፍ ጥርት ባለ መንገድ በቀላል ዋጋ በፍጥነት ማገናኘት ተችሏል። አንድ ዕቃ ከአንድ አቅጣጫ ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመውሰድ ትርጉም ባለው ሁኔታ አሠራሩ የተቀየረበትም ሆኗል። እውቀት ለማግኘት እንዲሁ የሚደረገውን ጉዞ ቴክኖሎጂ ተአምር በሚባል ሁኔታ ቀይሮታል። የእኒህ ነገሮች ድምር ውጤት የሰውን ልጅ አኗኗር በመሠረታዊ ደረጃ በአወንታዊ መልኩ የቀየሩት መሆኑን እንረዳለን። ነገርግን በውስጣዊ እርካታ ማጣት የሚበላሸው በዝቷል። ራስን ማድመጥ ካለመቻል የሚነሳ ህመም።
ሰው ወደ ውስጡ መመልከት እንዳይችል የሕይወት ዘይቤን ከፈጣሪ በማዞር ወደ ራስ ለማድረግ የሚደረገው ትግል ከፍተኛ ነው። የሰው ልጅ በፈጣሪ ላይ የሚያደርገውን መደገፍ እንደ ደካማነት በመቁጠር በራሱ ያለፈጣሪ ለመቆም የሚያደርገው ሙከራን አስተውለናል። ‘ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር እናደርጋለን ’ በሚል አመለካከት ለፈጣሪ ጀርባን ለመስጠት የተሄደባቸው ዘመኖችም እሩቅ አይደሉም። የሰው ልጅ በዚህም ተባለ በእዚያ የውስጥ እርካታው ጉዳይ ሚዛን ላይ ሆኖ መፍትሄን በሚሻበት ወቅት ላይ ሆኖ ሰሚ ስላጡ ድምጾች እናስባለን።
እርካታን በገንዘብ ውስጥ፣ እርካታን በትምህርት ውስጥ፣ እርካታን በስልጣን፣ እርካታን በሌሎችም ነገሮች ውስጥ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ወደ ውጤት እንዳላመጣን ጸሐፊው በማመን ከቁስ ባሻገር ስለሚገኝ እርካታን እያነሳን ነው። ራስን በማድመጥ ውስጥ ስለሚገኝ እርካታ፤ ድምጽ ልንሆንላቸው ስለሚገቡ ድምጽ በመሆን ከራስ ባሻገር በመሄድ ስለሚገኝ እርካታ።
እርካታ ያጣው ቱጃር
በፕሮቴስታንት እምነት ውስጥ መንፈሳዊ መነቃቃት/ሪቫይቫል ታሪኮች ውስጥ ከሚጠቀሰው መካከል አርጅንቲና አገር የሆነው አንዱ ነው። ከአንድ ሪቫይቫል ጀርባ በልዩ ሁኔታ እግዚአብሔር የሚያስነሳቸው ሰዎች እንዳሉ ይታመናል። ከአርጀንቲናው ሪቫይቫል ጀርባ እርካታ ያጣን አንድ ሰው እናገኛለን። እርካታን ፍለጋ በብዙ ቁሳቁስ ውስጥ ራሱን ፈለገ፤ ፍለጋው በቁስ ውስጥ አለመሆኑንም አረጋገጠ። ይህ ሰው ካርሎስ አናኮንዲያ ይባላል።
አርጀንቲና ከ1982 ጀምሮ በእዚህ ሰው አገልግሎት የተነሳ በሪቫይቫል ውስጥ እንደሆነችም ትቆጠራለች። ካርሎስ አናኮንዲያ ከድሃ ቤተሰብ የተወለደ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ በንግድ አማካኝነት ባለጸጋ ለመሆን የበቃ ሰው ነው። በገንዘብ ላይ ገንዘብን እየጨመረ በሄደ ቁጥር በውስጡ ያለውን ጥያቄ መልስ እየሰጠ እንደሚሄድ ያምን ነበር። በተጨባጭ ግን ሳይሆን ቀረ። «ከገንዘብ ክምችት ባሻገር ጭፈራ ቤት ቢኖረኝ እኮ እርካታዬን አመጣዋለሁ» ብሎ በማሰብ በውድ ዋጋ የጭፈራ ቤት አስገነባ። ነገርግን አሁንም በውስጡ ላለው ጩኸት ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም። ያልተደመጠው ጩኸት ያመጣው የፈጠረው እርካታ ማጣት። አሁንም ሌላ ሙከራ ባለቅንጦ ቤት ባለቤት መሆን። እጁ ላይ ያለው ገንዘብ ይህን ለማድረግ የሚያስችለው ነበረና በበቂ ሁኔታ ገንዘብ የፈሰሰበትን ቤትም አስገነባ። አሁንም ለውጥ የለም። በአውሮፓ ጎዳናዎች ላይ በቅንጡነታቸው የተዘመረላቸውን መኪኖቹ አምጥቼ ብነዳቸው አለ፤ እነርሱንም አስመጣና ከሀብቱ ዝርዝር ውስጥ አደረጋቸው። አሁንም አዲስ ነገር የለም።
የውስጡ ነገር እርካታ ከማጣት ወደ ፍርሃት አደገ። ሀብቴ በአንዴ ቢጠፋስ የሆነ ነገር ቢገጥመኝስ የሚለው ፍርሃት ያስጨንቀው ጀመር። የሞት ፍርሃት ወረረው። ነፍሱ አንዳች የታዳጊ ያለህ ማለት ጀመረች። በእዚህ ጊዜ ከውጭ ይልቅ ወደ ውስጥ ሲመለከት በውጫዊ ቁስ ሊሞላው ያልቻለው አካል መኖሩን ተመልክቶ ለመንፈሳዊ ሕይወት ስፍራን ሰጠ። የጀመረው ጉዞም የሪቫይቫል መነሻ ሆነ።
እርካታ ያጣው ቱጃር ውስጡን ለማድመጥ የሄደበት ርቀት ለብዙዎቻችን ትምህርት አለው። በሃይማኖቶች ውስጥ የምንማረው ትምህርት ወደ ውስጣችን መመልከት እንዳለብን የሚያስገነዝብ ነው። ወደ ውስጥ መመልከት፤ ራስን ማዳመጥ። ቁስ የማያረካው ውስጣዊ አካላችንን ፈልገን በማግኘት ማዳመጥ መቻል። ራስን ማድመጥ ተከትሎ ሌሎችን ማድመጥም ይከተላል።
ሌሎችን ማድመጥ
«ከአሜሪካ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል ዘርዝር ብትባል የማንን ስም ትጠቅሳለህ? ፕሬዚዳንቶቹን ትጠቅስ ይሆን? ወይንስ ማይክል ጆርዳንን? ወይንስ ቢል ጌትስን? እኔ ግን በዝርዝርህ ውስጥ ኦፕራ ዊንሬን እንድትጨምር እጠይቅሃለሁ።» ይላሉ ጆን ማእክስዌል ናቸው። ስለ ኦፕራ ሲጽፉም «ኦፕራ በ1985 እ.አ.አ በተግባር የማትታወቅ ተራ ዜጋ ነበረች። በቺካጎ አካባቢ ስርጭት ባለው የጠዋት ሾውን በመምራት ለአንድ አመት ወደ መድረክ ስትወጣ ትኩረት መሳብ ጀመረች። የእርሷ ስኬት ጀርባ ያለው ጉዳይ የመናገር አቅሟ ጥሩ መሆኑ እንደሆነ በብዙ ሊታሰብ ይችላል፤ በእርግጥ ትክክል ነው። በልጅነት ወቅት ማለትም የሁለት አመት ልጅ እያለች በቤተክርስቲያን መድረክ ላይ ንግግር አድርጋ ምእመናኑ ጥሩ ተናጋሪ ነሽ ብለዋት እንደነበር ታስታውሳለች። ነገር ግን ከመናገር በላይም የማዳመጥ አቅሟም ትልቅ ነው። ከዘወትር ልምዷ መካከል ዋናው ለመማር ያላት ፍላጎት ነው። የጸሐፊያንን ጥበብ በንባብ ውስጥ እንደሚገኝ በማዳመጥ ውስጥ በሰዎች ውስጥ ያለውን ጥበብ ለማግኘት ትወዳለች። ሰዎች እንዴት እንደሚያስቡና እንደሚሰማቸው ለማወቅ ልብወለድ መጻሕፍትን፣ የግልታሪኮችን ወዘተ ለማወቅ ትጥራለች። የአድማጭነት አቅሟ የሥራዋን መስመር አሳድጎታል። በተግባርም በቴሌቪዥን መስኮት የምታቀርበውን ፕሮግራም ተወዳጅነት ጨምሮታል። ጉዳዮቹን ለአየር ለማብቃት በተከታታይነት ነገሮችን መመልከት እና ማድመጥ ትወዳለች። ወደ ፕሮግራሙ የምታቀርባቸውን ባለሙያዎች፣ ጸሐፊዎች፣ አርቲስቶች በትኩረትና ከውስጥ በሆነ መስማት ታደምጣቸዋለች። ኦፕራ ባላት የአድማጭነት አቅም ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ተርታ እንድትሰለፍ ሆናለች። እርሷ የዓለማችን ከፍተኛው የመዝናኛ ዘርፍ ተከፋይ ባለሙያዎች ተርታ ትመደባለች፤ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚገመትም ሀብት አላት። በአሜሪካ ብቻ የሳምንቱ ሰላሳ ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ የእርሷን የቴለቪዥን ፕሮግራም ይከታተላል። »
ሌሎችን ማድመጥን የቻለበት ሰው ለራሱም የቀናው መንገድ ላይ እንዲገኝ ያግዘዋል። «ማንን ላዳምጥ?» የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ በመመለስ የሚጀምር ከሆነ።
ማንን ላዳምጥ?
በተግባቦት ትምህርት ውስጥ መደማመጥ ያለውን ትልቅ ቦታ እንረዳለን። ከመናገር በፊት ማድመጥ መቻል እንደ ብልሃትም ይወሰዳል። ብዙ የሚያደምጥ ብዙ ከሚያወራም በንግግሩ ከሚመጣ አደጋም የተጠበቀ መሆኑ ግልጽ ነው።
«ማንን እናዳምጥ?» የሚለው ጥያቄ በዙሪያችን ያሉትን በአግባቡ እንድንቃኝ ዕድልን ይሰጠናል። ራሳችንን ባለብን ኃላፊነት ውስጥ ሆነን ዙሪያችንን ስንመለከት ማንን ማድመጥ እንዳለብንም እንድንወስን ያደርገናል።
ሁሉንም ሰው ማድመጥ አንችልም፤ ነገር ግን ከኃላፊነት የሚመነጭ አድማጭነት የግድ ሊደመጡ የሚገባቸውን አካላት እንድንለይ ያደርገናል። ከኃላፊነት የሚመነጭ አድማጭነት ውጤታማ አድማጭነት ነው። በትዳር ውስጥ ያለ አባት ሚስቱን እና ልጆቹን ማድመጥ መቻል የግድ ሊያደርገው የሚገባ አድማጭነት ነው። ከኃላፊነቱ የሚመነጭ አድማጭነት። ተቋም የሚመራ ግለሰብ ሠራተኞቹን፣ ደንበኞቹን፣ አቅራቢዎቹን፣ የመንግሥት አካላትን ወዘተ ለማድመጥ ጆሮውን ሲከፍት የግድ መሆን ያለበት አድማጭነት ነው፤ ከኃላፊነት የሚመነጭ አድማጭነት። ከእዚህ በመነሳት የአድማጭነት አቅማችንን ምን ይመስላል?
በኃላፊነት ውስጥ የሚሆን ማድመጥ ሁሉንም ነገር ተቀብሎ ማስተናገድ ማለት አይደለም። ነገር ግን ከኃላፊነት የሚወጣው አድማጭነት የወሰድነውን ኃላፊነት ዳር ማድረስ እንድንችል ዕድልን የሚሰጥ ነው።
አንድ አባት እየመራሁ ነው ብሎ የሚያስበውን ቤተሰብ ካላደመጠ ማንን ሊያደምጥ ይችላል? የቤተሰቡ አባላት ያሉበትን ሁኔታ የማያውቅ በፈጠረው በራሱ ዓለም ውስጥ ብቻ የሚኖር ከሆነ እርሱ አስቸጋሪ ይሆናል። አብረው እየኖሩ አብረው ወጥተው እየገቡ ነገርግን አንዱ ሌላውን የማያውቅበት ሕይወት በመግቢያችን ላይ ላነሳነው ዓይነት ገጠመኝ ይዳርግም ይሆናል።
ማንን ላዳምጥ የሚለው ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ እንዲያገኝ የትስስር ሕግን ማሰብ ተገቢ ነው።
የትስስር ሕግ
ማድመጥን በተመለከተ ጆን ማእክስዌል «የትስስር ሕግ» ብለው የሚያነሱትን ነጥብ እንመ ልከት። አንድ ሰው የሚከተሉትን ሰዎች እጅ ለሥራ ከመጠየቁ በፊት ልባቸውን ማግኘት አለበት። ያንን «የትስስር ሕግ» እንለዋለን። መሪው የግለሰቡን ልብ ከመንካቱ በፊት በግለሰቡ ልብ ውስጥ ያለውን ነገር ማወቅ አለበት። ማወቅ የሚችለው ግን ማድመጥ በመቻል ነው።
በደካማ ሰዎች ዘንድ መስማት ያለመፈለግ ዝንባሌ አለ። የአሜሪካን ማኔጅመንት አባት ተብሎ የሚጠቀሰው ፒተር ድራከር 60 በመቶ የሚሆነው የማኔጅመንት ችግር ስህተት ያለበት ግንኙነት ነው ይላል። ግንኙነትን መሠረት ካደረግ የማኔጅመንት ችግሮች መካከል ደግሞ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ደካማ የማዳመጥ ችግር ነው።
ትኩረትን የሚፈልጉ በርካታ ድምጾች በዙሪያችን አሉ። የማዳመጥ ጊዜን እንዴት ማሳለፍ እንዳለብን ስናስብ ውጤታማ ለመሆን ሁለት የማዳመጥ አላማዎች ልብ ማለት አለብን እነርሱም ከሰዎች ጋር ትስስርን ለማድረግ እና ለመማር ዝግጁ መሆን።
የትስስር ሕግን ከኃላፊነት የሚመጣ ማድመጥ ካልነው ነጥብ ጋር አገናኝተን ስናስበው ማንን ማድመጥ እንዳለብን በግልጽ እንረዳለን። በእዚህም ምክንያት ለሚከተሉት ሰዎች ጆሮን መክፈት የግድ ይላል፣
1. ተከታዮችን ማድመጥ
ልጆች በልጅነት ወቅታቸው የአባትና እናት ተከታዮች ናቸው። በተለያየ ጉዳይ መሪዎች ካሉ ተመሪዎች ደግሞ እንዲሁ ይኖራሉ፤ ተከታይ ልንላቸው የምንችል። ጥሩ የሚባሉ መሪዎች ከተከታዮቻቸው ጋር ግንኙነት ሲያደርጉ የሥራ ጉዳይን ከመፈጸም ያለፈን ግንኙነት ያደርጋሉ። እንደ ግለሰብ እያንዳንዱን ሰው ስሜት ለማዳመጥ ይሞክራሉ። ተከታዮች ወደ ውጤት እንዲደርሱ አስከታዩም ኃላፊነቱን መወጣት እንዲችል ያደርጋል። ከኃላፊነታችን የሚወጡ ተከታዮቻችንን ከልብ ማድመጥ መቻል ራሳችንን ከጥፋትም የሚጠብቀን መሆኑን መረዳት አለብን።
2. ግል-መካሪ የሆንክላቸውን ሰዎች፣
በሀገራችን ግለ-መካሪነት/mentoring ትኩረት ተሰጥቶት የሚሠራ አይደለም። ነገርግን አንዳንዴ በሃይማኖት፣ በሙያ፣ በጉርብትና፣ በማህበራዊ መስተጋብር ወዘተ ምክራችንን ፈልገው አጠገባችን የሚገኙ ሰዎች አሉ። እኒህ ሰዎች መደመጥን ይፈልጋሉ። እኛ የመናገር ዕድል ስላገኘን ሰዓቱን በሙሉ ተቆጣጥረን እኛ ብቻ እያወራን የምንመልሳቸው እንዳይሆን ማሰብ አለብን።
የግል-መካሪ ሊኖረው የማይገባ አንድ ም ሰው የለም በተለይም መሪዎች። የግል-መካሪ ከሌለን ዛሬ ነገሳንል እንፈልግ። ግለ-መካሪ ስንሆን ደግሞ ግል-መካሪ የሆንላቸውን ሰዎች በማድመጥ ውጤታማ ግንኙነት እንዲኖረን እናድርግ።
3. ደንበኞችን ማድመጥ
ከቤተሰብ አልፈን ወደ ሥራው ዓለም ስንሂድ የሥራው ዓለም ደንበኛ በሚባሉ ሰዎች ላይ በደንብ የተደራጀ ነው። ተቋማት ደንበኛዬ ብለው ያሉትን ሊያገለግሉ በብዙ ይደክማሉ። ደንበኞች አድማጭ ካገኙ በሹክሹክታ መናገር ይችሉበታል። የሚያደምጣቸው ካጡ ሌላ አማራጭ ካለ ይሄዳሉ፤ አማራጭ ካጡ ግን ይጮሃሉ። ችሮኪ የተባለሰው እንዲህ አለ «በሹክሹክታ የሚነገርህን አዳምጥ ይህን ካደረክ በቁጣ ውስጥ ሆኖ የሚጮህ ሰውን ከመስማት ትድናለህ። » ከራሳቸው ሀሳብ ውጪ የደንበኞቻቸውን ስጋት፣ ቅሬታ እና ሃሳብ የማይሰሙ መሪዎች በእውነቱ አስገራሚዎች ናቸው። ቢልጌት Business @ the Speed of Thought በተሰኘው መጽሐፉ ላይ «እርካታ ያልተሰማቸው ደንበኞች ሁልጊዜ ስጋት ናቸው እንዲሁም ዕድል። » ማለታቸውን ብናነሳ ሃሳባችንን ያጠናክርልናል።
አድማጭ ለመሆን ተግባራዊ እርምጃ
ዛሬ በእጃችን ሳለ ወደ አድማጭነት ለማደግ እንድንጠቀም ተግባራዊ ነጥቦችን በመጠቆም እናጠቃልል። ንድፈሃሳባዊ ነጥቦችን በአንድ በኩል ይዘን በተጨባጭ እንዴት መተግበር እንችላለን የሚለውን ማሰብ አስፈላጊ ነው።
* ልብንና ጆሮን እኩል መስጠት – ትኩረት መስጠት ለብዙ ነገሮች አስፈላጊ ነው። ባለንበት ዘመን ትኩረት የሚነጥቁ የበዙ ነገሮች አሉ። ትኩረትን የሚነጥቁ ነገሮች ባሉበት ሁኔታ በተበታተነ ትኩረት ውስጥ ማድመጥን በተግባር ማድረግ አስቸጋሪ ነው። ማድመጥ ውጤታማ መሆን እንዲችል ልብንና ጆሮን እኩል መስጠታችንን እርግጠኛ መሆን አለብን። ልጃችንን እያናገርን በአንድ በኩል ቲቪ እየጮኸ በሌላ በኩል ሞባይላችን አስሬ እያናገርን ወዘተ ውጤታማ መደማመጥ ማድረግ አንችልም። ሰዎች ሁካታ በሌለበት ድባብ ውስጥ የተሰማቸውን ለመናገር ይበረታታሉ በአግባቡ በመደመጣቸው ውስጥም ደስታን ያገኛሉና ልብንና ጆሮን እኩል በመስጠት ውስጥ እንዲሆን ማድረግ ወሳኙ የተግባር እርምጃ ነው። በትኩረት ውስጥ ስንሆን አጀንዳ ተኮር፣ መረጃ ተኮር ወይንም የሆነ ይዘት ተኮር ሆነን ሙሉ ትኩረታችን ጉዳዩ ላይ ይሆናል። ከእዚህ በተጨማሪ ግን ስሜት ተኮር የሆነ ድባብን ይፈጥራል። ለመደመጥ አስፈላጊ የሆነ።
*ጊዜን መመደብ – ጊዜ ውድ የሆነበት ጊዜ የተረፈ መሆኑን በሚያሳብቅ በተቃርኖ ዘመን ውስጥ አለን። ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ ትርኪምርኪ ሲቃርሙ የሚውሉበትን ሁኔታ ስናይ ጊዜ ተረፈ እንላለን፤ ለመልካም ነገር እርስበርስ ለመደማመጥ ጊዜ ሲጠፋ ደግሞ የተቃርኖውን ሌላኛውን ገጽታ እናገኛለን። ቤተሰብህን፣ ተከታዮችህን፣ ደንበኞችህን፣ ተፎካካሪዎችን እና የግል-መካሪህን ለመስማት ጊዜ ትመድባለህ? እኒህ አካላት በመደበኛነት በካላንደርህ ውስጥ ከሌሉ ለእነርሱ ትኩረት አልሰጠህም ማለት ነው። በየዕለቱ፣ በየሳምንቱ ወይንም በወር ውስጥ ከእነዚህ ጋር የምትገናኝበትን ጊዜ አስቀምጥ። ይህን ማድረግ ለማድመጥ የሰጠኸውን ቦታ ያሳያል። ስለሆነም ሁለተኛው ተግባራዊ እርምጃ ዛሬውን ልታደምጣቸው ለተገቡት ጊዜ መመደብ ነው።
*በሰውዬው ጫማ ውስጥ መሆን – አድማጭነትን ተቀብለህ በጊዜ ሰሌዳህ ላይም መድበህ ያንን ሰው ስታገኘው በእርሱ ጫማ ውስጥ በተግባር መሆን አለብህ። ይህን ለማድረግ ሰውዬውን ከግንኙነታችሁ በፊት አስበው፤ ስለ እርሱ ልትሰበስብ የምትችለውም መረጃ ይኑርህ። ጥሩ አድማጭ የመሆን ቁልፉ የጋራ መቆሚያ ቦታን ማግኘት መቻል ነው። ግለሰቡን ለማወቅ በምታደርገው ጥረት ውስጥ የጋራ መቆሚያ ቦታን ማግኘት ትችላለህ። በተጨማሪም በሚኖርህ ግንኙነት ወቅት ከግለሰቡ ራሱ በመጠየቅ በሰውዬው ጫማ ውስጥ መሆንን ልትለመድ ትችላለህ። በሚቀጥለው ጊዜ ከልጅህ ይሁን ከሠራተኞችህ ወይንም ከደምበኞችህ ጋር ስትገናኝ ስለግለሰቡ የግል ሕይወት አራት ወይንም አምስት ጥያቄዎች ልትጠይቀው ሞክር። ማን እንደሆነ ልታውቀው ሞክር በመካከላችሁ ትስስርን ለመፍጠር ይረዳሃልና።
ዛሬ በዙሪያችን፣ በአካባቢያችን፣ በከተማችን፣ በአገራችን፣ በዓለማችን ‘የአድማጭ ያለህ’ የሚሉ ድምጾች በርክተዋል። ኃላፊነት-መር አድማጭነትን መነሻ አድርገን በማድመጥ እንትረፈረፍ ዘንድ ይህ ተጻፈ። መልካም አድማጭነት!
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/ 2015 ዓ.ም