በህመም እየተሰቃዩ አልጋ ይዘው በቤትም ይሁን በየሆስፒታሉ ያሉ ሰዎች ከምንም በላይ የሚፈልጉት «ፈጣሪ ይማርህ» የሚላቸውን ጠያቂ ነው። ይህ ቃል በውስጡ ብዙ ነገር የያዘ በመሆኑም በታማሚዎቹ ላይ የሚፈጥረው የስነ ልቦና ጥንካሬ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
በተለይም ራቅ ካለ አካባቢ ለህክምና የመጡ ብሎም አካባቢያቸውም ላይ ሆነው ጠያቂ ተመልካች ወገን የሌላቸው በርካቶች አይናቸው ከሚቁለጨለጭበትና በልባቸው ከሚያዝኑበት ነገር አንዱ ጠያቂ ማጣታቸው ነው። በመሠረቱ አንዳንድ ጥሩ ልምድ ያላቸው ሰዎች የማያውቁትን የታመመን ብቻ ሳይሆን የታሰረን ሰውም እየሄዱ የሚጎበኙ አሉ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ሃምሳ አለቃ ዘሪሁን ደጋጋ አንዱ ናቸው።
ሃምሳ አለቃ ዘሪሁንን ያገኘናቸው በአለርት ሆስፒታል የታካሚዎች መንፈሳዊ የህክምን ቀን በማለት በየዓመቱ በሚያዘጋጀው የጥየቃ ፕሮግራም ላይ ነው። ሃምሳ አለቃ ዘሪሁንን ለየት የሚያደርጋቸው ቀኑን ምክንያት አድርገው ሳይሆን በግቢው የተገኙት ሁሌም የማያውቋቸውን በሽተኞች እየዞሩ ፈጣሪ ይማራችሁ የማለት ልምድ ስላላቸው ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ሃምሳ አለቃ ዘሪሁን በቅርቡ ለአንድ ወር ያህል በሆስፒታል ተኝተው ህክምና ሲያገኙ ቆይተው ወደሙሉ ጤንነታቸው ተመልሰው ቤታቸው ገብተዋል። ያም ተጨምሮ አሁን ላይ አስታማሚና ጠያቂ የሌላቸው ወገኖች የፈጣሪን ፈውስ አግኝተው ከበሽታቸው አገግመው ቤታቸው ይገቡ ዘንድ በተወሰኑ ቀናት ልዩነት «ምህረቱን ይላክላችሁ» ሊሉ በሆስፒታሉ ይገኛሉ።
ሃምሳ አለቃ ዘሪሁን «እኛ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለን ኢትዮጵያውያን ነን። ሌላው መገለጫችን ደግሞ እርስ በእርስ የምንተዛዘነውና የምንጠያየቀው ነገር ነው፤ በመሆኑም እኔም በሚመቸኝ ቀንና ሰዓት እየመጣሁ ወገኖቼን ፈጣሪ ምህረት ይላክላችሁ ማለት ለእኔ ቀላል ለሰዎቹ ግን ትልቅ ዋጋ ያለውና በመንፈስም በአካልም የሚያጠነክራቸው በመሆኑ ሕይወቴ እስካለም ድረስ ይህንን ዓይነቱን ተግባር አጠናክሬ እቀጥልበታለሁ» ይላሉ።
ሃምሳለቃ ዘሪሁን ሁሉም ሰው ይህንን ነገር ልምድ ቢያደርገው የሚያዝን የሚተከዝ አይኖርም በማለት ሀሳባቸውን ይሰጣሉ።
«የሃይማኖት አባቶች ጉብኝት ለታካሚዎች ፈውስ ጉልህ አስተዋጽዖ አለው» በሚል አለርት ሆስፒታል ለአምስት ተከታታይ አመታት ይህንን ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። በዚህም ብዙ ጥቅሞች ስለመገኘታቸው ይነገራል። የሃይማኖት አባቶች በየመኝታ ክፍሉ እየተዘዋወሩ «ፈጣሪ ይማራችሁ» ሲሉም በህሙማን ላይ የሚታየው መንፈሳዊ ደስታና የመፈወስ ስሜት በእውነት ላቅ ያለ ነው። በተለይም አስታማሚ የሌላቸው በተለያዩ ምክንያቶች ቦታው ላይ የተገኙ ሁሉ ይህንን የፈውስ በረከት ለማግኘት አቅማቸውን ሁሉ አሟጠው ቀና ሲሉ ማየት ደስታው የተለየ ነው።
ከደብረ ቢታንያ አቡነተክለሃይማኖትና ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተክርስቲያን የመጡት ቀሲስ ለይኩን ብርሃኑ እንደሚሉት አለርት ሆስፒታል ከሌሎች ሁሉ ለየት የሚያደርገው ከሚሰጠው ስጋዊ ህክምና ጎን ለጎን ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማኑ የመንፈስም ህክምና ያሻቸዋል በማለት በየዓመቱ የሃይማኖት አባቶችን እየጠራ ጸሎት እንዲደረግ «እግዚአብሔር ይማራችሁ» እንዲባሉ ያደርጋል፤ ይህ በእውነቱ በጣም አስደሳች ነው በሰዎቹ ላይ የሚፈጥረውንም ደስታ እየተመለከትነው ነው ።
«እኛ ገብተን ማጥንት ስናጥን መስቀል ስናሳልማቸው ከአልጋቸው መነሳት ያቃታቸው ህሙማን ሳይቀር ተነስተው እልል እያሉ የሚያሳዩት ደስታ በቃላት የሚገለጽ አይደለም ። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሁሉም በየእምነታቸው መቼ ቤተክርስቲያን ሄጄ መስቀል ተሳልሜ ማጠንት ሸቶኝ ብለው የሚመኙ መሆናቸው ነው እነዚህን ሰዎች እግዚአብሔር ይማራችሁ ማለት ለእነሱም ተስፋ ነው» ብለዋል።
ህክምና የሚጀምረው ከአእምሮ ነው የሚሉት ቀሲስ ለይኩን እነዚህ ሰዎች በዚህ መልኩ መጎብኘታችን ከፍ ያለ ጠቀሜታ ያለው ነው ሌሎች ሆስፒታሎችም ይህንን አካሄድ ቢከተሉት ለሚያክሟቸው ህሙማኖቻቸው ከፍ ያለ ጥቅም አለው በማለት ይመክራሉ።
ካርዲናል አቡነ ብርሃነ እየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ዕለቱን አስመልክተው ሲናገሩ የሃይማኖት አባቶች ህሙማንን ጎብኙ ብሎ አለርት ሆስፒታል ሲጠራን ላቅ ያለ ደስታ ተሰምቶኝ ነው የመጣሁት።
ሆስፒታሉ ሰፊና ብዙ ዘርፎች ያሉት ታካሚዎቹም በዚያው ልክ ቁጥራቸው ላቅ ያለ ነው። እነዚህን ህሙማን በቦታው ላይ ተገኝቶ መጠየቅ አስታማሚዎችን በርቱ ማለት ደግሞ ጥቅሙ ከምንም በላይ ላቅ ያለ ነው በማለት ይናገራሉ።
የሃይማኖት አባቶች ምእመኖቻችንን ማስተማር በምግባር ማነጽ ትልቁ ሥራችን ነው፤ ከዚያ አልፎ ደግሞ ችግር߹ ህመም߹ ጉስቁልና ሲደርስባቸው ከጎናቸው ሆነን አይዟችሁ ያልፋል ፈጣሪ ይርዳችሁ ይማራችሁ ማለት ደግሞ ይጠበቅብናል። ሆስፒታሉም ይህንን የሰው ልጆችን የሚቀይር የሚያረጋጋና የሚያጽናና ተግባር በየዓመቱ ማዘጋጀቱ ሊያስመሰግነው እንደሚገባም ተናግረዋል።
«ወንጌሉ የታመመን ጠይቅ» ይላል የታመመን የምንጠይቀው ደግሞ እቤቱ አልያም በየሆስፒታሉ ነው። ይህንን ባደረግን መጠን ፈጣሪያችንን ያዘዘንን ተወጥተናል ማለት ነው ። ስለዚህ ሁሉም ምዕመን ዛሬ ጤነኛ ቢሆን ነገ ተራው ሲደርስ ታማሚ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለምና በተቻለ መጠን አወቅነው አላወቅነው ሳንል የታመመን መጎብኘት ልምዳችን ልናደርግ ይገባል ሲሉም መክረዋል።
የሚፍታህ መስኪድ ዋና ኢማም ሼህ መሀመድ ፈትህ አለርት ሆስፒታል የሁላችንም ነው፤ በተለይም በዚህ መልኩ የሁሉንም እምነት ተወካዮች ጠርቶ ህሙማንን ጎብኙልን በዱኣ አስቡን ማለቱ ሊያስመሰግነው የሚገባ ነገር ነው።
ምን ጊዜም ሰዎች ስንታመም ስጋዊ ፈውስን ፈልገን ወደ ሆስፒታሎች ብንሄድም ልባችን ያለው እምነታችን ላይ የፈጠረን አምላክ ጋር ነው፤ በዚህ መልኩ ደግሞ ታማሚው የእምነት አባቱ ያለበት ቦታ ድረስ ቀርቦ ፈጣሪ ይማርህ “አላህ ያሽር” ሲለው የሚሰማው ፈውስ እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። በመሆኑም ሆስፒታሉም በዚህ መልኩ መሄዱ ሥራውን ውጤታማ ያደርግለታል ለሌላውም አርዓያ ሊሆን የሚገባ ሥራ ነው።
የእኛ ጸሎት ለታማሚው ብቻ ሳይሆን ጥበቡን ገልጦላቸው ህክምና ለሚሰጡት ባለሙያዎች በሙሉ ነው፤ በመሆኑም በሆስፒታሉ መጥተው ህክምና ላይ ያሉትን ህክምና በመስጠት ላይ ያሉ ባለሙያዎችም አላህ ጥበቡን ይግለጽላቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት አገልጋይ መጋቢ ሰለሞን ተስፋዬ እንዳሉት ደግሞ ፈጣሪያችንም ያለው «ታምሜ አልጠየቃችሁኝም፤ ታርዤ አላለበሳችሁኝም ነው» የት ነው ታመህ ያልጠየቅንህ ብለው ሲጠይቁትም «የታመሙትን አልጠየቃችሁም» የሚል ምላሽ ነው የሰጣቸው፤ በመሆኑም ሰውን ታሞ መጠየቅ ጌታ እየሱስ ያስቀመጣቸው ዋና ነገሮች ናቸው ይላሉ።
በሌላ በኩልም እንደ ሰውም ሆነ እንደ ሃይማኖት አባት በየሆስፒታሉ በአጋጣሚ እንኳን ገብተን ስንጠይቅና ፈጣሪ ይማራችሁ ስንላቸው ሃይማኖታችንን እንኳን ሳያውቁ በአንድ ቃል «አሜን» ነው የሚሉት ይህ የሆነው ደግሞ የፈጣሪ ስም የማጽናነት የመፈወስ ኃይሉ ከፍ ያለ በመሆኑ ነው። ስለዚህ ይህችን አንድ ቃል ተናግረን ሰዎችን ከህመማቸው የምንፈውስ ከሆነ በየጊዜው በየሆስፒታሉ ያሉ ወገኖቻችንን ሄደን የመጎብኘት ልምድ ይኑረን ይላሉ ።
«የተቸገሩ በተለይም የታሰሩና የታመሙ ሰዎችን መጠየቅ ትልቅ ዋጋ የሚያሰጥ ነገር ነው፤ በመሆኑም እግረ መንገዳችንን እንኳን ወደ ሆስፒታሎች ጎራ እያልን የታመሙትን የተጨነቁትን ወገኖቻችንን እግዚአብሔር ይማራችሁ አስታማሚዎችንም ብርታት ይስጣችሁ ብንል በምድር ከፍ ያለ እርካታ በሰማይም ዋጋው ትልቅ ነው፤ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አለርት ሆስፒታልም ከሚሰጠው ስጋዊ ህክምና ባሻገር ሰዎች በመንፈስም ሊታከሙ ይገባል ብሎ ይህንን ዓይነቱን ሥራ በየዓመቱ አለማቋረጥ ማካሄዱ ሊያስመሰግነው ለሌሎች ሆስፒታሎችም አርዓያ ሊሆንበት የሚገባ ሥራ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሽመልስ ገዛኸኝ እንዳሉት በተለያየ ሆስፒታል ከተራ ሠራተኝነት ጀምሮ በኃላፊነት ደረጃ ሠርቻለሁ በዚህን ያህል ህሙማን ከስጋዊ ህክምና ጎን ለጎን መንፈሳዊ ፈውስ ያስፈልጋቸዋል ብሎ የሠራ አላየሁም፤ አለርትም በዚህ በጣም ልዩና ሊመሰገን የሚገባው ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል።
እኛ የስጋ ህክምና የማስታገሻ መድኃኒት ልንሰጥ እንችላለን፤ እናንተ ደግሞ መንፈሳዊውን እና ትልቁን ለሰው ልጆች ሁሉ አስፈላጊ የሆነውን ህክምና የምትሰጡ ናችሁ፤ በዚህ ልክ እናንተም ወደኛ መጥታችሁ መሥራታችን ሆስፒታሉ የተሟላ ህክምና የሚሰጥ ተቋም ያደርገዋል ይላሉ።
ወደፊትም ይህ መሰሉ ሥራ በዓመት አንዴ ከመሆን አልፎ ሁለቴና ሦስቴ ይሠራል፤ እኔ ለቦታው አዲስ ነኝ ነገር ግን ጅምሩ ጥሩ በመሆኑ ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን መንገድ በበኩሌ አመቻቻለሁ ብለዋል።
እናንተ በዚህ ተገኝታችሁ መጎብኘታችሁ የፈውስ አገልግሎት መስጠታችሁ ሆስፒታሉ የእኛ ነው ህሙማኑም የእኛው ናቸው ብላችሁ መምጣታችሁ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው ወደፊትም ጸሎት ልመናችሁ እንዳይለየን ይላሉ።
ከሰላሌ የመጡት ታካሚ ወይዘሮ መሠረት በቀለ እግራቸው ተቆርጦ ሰፊ ህክምናን እየተከታተሉ ነው ። በዚህ መልኩ የናፈቃቸውን የሃይማኖት አባቶች ድምጽ የተኙበት ድረስ መጥቶ መስማታቸው ህመማቸውን እንዲረሱ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ።
«በሽተኛ የሰው ዓይንና ድምጽ በተለይም እግዚአብሔር ይማርህ የሚለውን ቃል አብዘቶ ይናፍቃል፤ እንደእኛ ራቅ ካለ አካባቢ የመጣ ሰው ደግሞ ጠያቂም የለውም፤ በዚህ መልኩ ሃይማኖት አባቶች መጥተው ስለጎበኙን የተሰማኝ ደስታ ወደር የለውም፤ በሽታዬንም ረሳሁት» በማለት ከፍ ባለ የደስታ ስሜት ውስጥ ሆነው ሀሳባቸውን ገልጸዋል።
አቶ ደረሰ አዳሙ ከደራ ወረዳ የመጡት የስጋ ደዌ ህመም ታማሚና ለህክምና ብቻቸውን የመጡ ናቸው። ለአገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ ቢሆኑም በተለይ የሃይማኖት አባቶች በዚህ መልኩ መጥተው ሲጎበኟቸው እጃቸውን ይዘው አይዞህ በርትታ ትድናለህ ማለታቸው በጣም እንዳስደሰታቸው ነው የተናገሩት።
አቶ ደረሰ ሆስፒታሉ ከሚሰጠን ህክምና ጎን ለጎን በዚህ መልኩ በእምነታችን እንድንጽናና ያደረገው ጥረት ሌሎች ቦታዎች ያላየነው በጣምም የሚያስመሰግን ነው በማለት ሀሳባቸውን ይገልጻሉ።
አለርት ሆስፒታል «የታካሚ መንፈሳዊ የህክምን ቀን» ብሎ በዚህ መልክ የሃይማኖት አባቶችን አሰባስቦ ማስጎብኘቱ በህሙማኑ ላይ ከፍ ያለ የደስታና የእረፍት ስሜት ሲፈጥር ተመልክተናል ። ሌሎች ሆስፒታሎችም ከሚሰጡት የስጋዊ ህክምና ጎን ለጎን ይህንን ተሞክሮ ቢወስዱት መልካም መሆኑንም ለመግለጽ እንወዳለን።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/ 2015 ዓ.ም