ወጣት ነው፤ በሥራና በትጋት የሚያመን ትጉህ ወጣት። ለፍቶ ጥሮ ግሮ የማግኘት ትርጉም የገባው ወጣት ቢኒያም ሴካሞን በስራው ባፈራው ሀብት ከራሱ አልፎ ለበርካቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ለትልቅ ለትንሹ ታዛዥ እና ሥራውን አክባሪ የሆነው ወጣት ዘወትር ቀኑን የሚ ጀምረው በፀሎት ነው።
ቢኒያም ዛሬም እንደልማዱ ከእንቅልፉ የተነሳው በሰላም መዋልን ተመኝቶ ነው፡፡ ፀሎቱን አድርሶ ፈጣሪውን አመስግኖ አካላዊ እንቅስቃሴ ቢያደርግም ምንም የመነቃቃት መንፈስ ሊሰማው አልቻለም። ጊዜው የእንቁጣጣሽ አጋማሽ የመስቀል በዓል መቃረቢያ ሳምንት መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም ነበር፡፡ ክረምቱ እየተገፈፈ ፀሃይ መድመቅ ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡ የዛን ቀንም ቀኑ ደመቅ ብሎ ጀማምሯል።የመስከረም ወር የአዲስ አመት መጀመሪያ ነውና ብዙዎች በአዳዲስ እቅድና በተስፋ የሚጀምሩበት ወር ነው።
ምንም ብሩህ ቀን ቢሆንም የቢኒያም የደስታ መንፈስ ሊቀሰቅስ አልቻለም፤ ድብርት ተሰምቶታል፡፡ ማልዶ ከቤት መውጣት አልፈለገም፡ ፡ መልሶ ሊተኛ ካሰበ በኋላ በጣም እንዳይጫጫነው በመስጋት ያገኘውን መፅሄት ሲያገላብጥ ቆየ። እንደምንም ራሱን አነቃቅቶ አረፋፍዶ ቁርሱን ተመግቦ እንደልማዱ ቡናውን ጠጥቶ ዘመናዊ መኪናውን እያሽከረከረ ከቤቱ ወጣ፡፡
የዝርፊያ ዕቅድ
ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ ህግን የማስከበር ሀላፊነት የተጣለባቸው የህግ አስከባሪዎችም በየደረጃው ሀላፊነታቸውን ለመወጣት ስምሪት ይዘው ተንቀሳቅሰዋል። ሆኖም ግን ሁሉም የፍትህ አካል ሀላፊነቱን በሚገባ ይወጣል ብሎ ማሰብ አልፎ አልፎ የማይቻልበት ሁኔታ ያጋጥማል። መስከረም 11 ቀን 2014 የሆነውም ህግ ለማስከበር የተሰማሩ አካላት በሙያቸውና ሙያው በሚጠይቀው ስነምግባር ዙሪያ አልነበሩም። የፀጥታ አስከባሪ የመሰሉት ወንጀል ለመፈጸም የተዘጋጁ የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ናቸው ።በጋራ ሆነው በእለቱ ስለሚፈጽሙት ውንብድና መዶለት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡ ፡ ምክትል ሳጅን አዲስ አለም አባተ ቢሻቶ ፤ ዋና ሳጅን ሚሊኪያስ አበራ ማሞ፤ ሳጅን ኤልያስ ታፈሰ እና ዳዊት በልሁ ከሌሎች ግለሰቦች ጋር በመሆን ከማን ምን እንዴት እንደሚዘርፉ ተመካከሩ። ምን ቢያደርጉ የተሳካ ዘረፋ ሊያከናውኑ እንደሚችሉ ቁጭ ብለው ዓቅደው ተዘጋጅተው ነው የመጡት ።
በተሰማሩበት የህግ ማስከበር ሂደት ውስጥ የተመለከቱትን የወንጀል ልምድ በሙሉ በመቀመር ለእነሱ የዘረፋ ሂደት ይጠቅመናል ብለው የሚያስቡትን እቅድ ከማውጣት አልፈው የስራ ድርሻ ተከፋፍለዋል። ለዝግጅታቸው ተግባራዊነት መንግስት ለደንብ ማስከበር ያገለግላቸዋል ብሎ የሰጣቸውን መሳሪያና አልባሳት ለእኩይ ሥራቸው ማስፈፀሚያ እንደሚያደርጉት ተማምነዋል።
በመንገድ ላይ…
ሊዘረፉ ዕቅድ ከተያዘባቸው መካከል ወጣት ቢኒያም አንዱ ነው፡፡ ቅድመ ዝግጅት አድርገው ጥርሳቸው ውስጥ አስገብተው ሲከታተሉት ከራርመዋል፡፡ መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 4፡00 ሰዓት አካባቢ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ልዩ ቦታው ኔክሰስ ሆቴል ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ በአሳቻ መንገድ ላይ እየጠበቁት መዘግየቱ አሳስቧቸው ተስፋ ለመቁረጥ በማመንታት ላይ እያሉ፤ የቢኒያም መኪናን ከሩቅ ተመለከቱ፡፡
ቢኒያም ከቤቱ ሲወጣ የኮረኮንች መንገዱን እየገሰገሰ አለፈው፡፡ ጉዞውን በቀጥታ ወደ ኔክሰስ ሆቴል መንገድ አደረገ፡፡ ብዙም ሳይርቅ ደብል ጋቢና ፒካፕ የፖሊስ መኪና በተጨማሪ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-47692 ኦ.ሮ ዶሊፊን መኪና የቢኒያምን መኪና መከተል ጀመሩ፡፡
ፍጥነቱን ቀንሶ መንዳቱን ቀጠለ፡፡ እየተጠጉት መሆኑን ሲያውቅ ግራ ተጋብቶ በቀስታ መኪናውን ጥግ አሲይዞ አቆመ። የሚከተሉት መኪናዎች ትተውት አልሔዱም ጭራሽ ከፊትና ከጎን መንገድ ዘግተውበት ቆሙ፡፡ ነገር ግን መኪኖቹን ሲመለከት የፖሊስ መኪና መሆናቸው ብቻ ሳይሆን መኪናዎቹ ውስጥ ያሉት ሰዎችም የደንብ ልብስ የለበሱ መሆናቸውን ሲያረጋግጥ ተስፋ አደረገ፡፡ ብዙም ስጋት እንዳይሰማው ለማድረግ ለመረጋጋት ቢሞክርም፤ ከመኪናው ውስጥ የሚወርዱት ሰዎች አኳኋን ግን ግራ የሚያጋባ ሆነበት።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ኔክሰስ ሆቴል አካባቢ ተገኝተው ትርዒቱን ሲያዩ የነበሩ ሰዎች፤ የፖሊስ ዳብል ጋቢና ፒካፕ መኪናን በማየታቸው ቢኒያም ወንጀለኛ ሆኖ እየተያዘ መሆኑን አልተጠራጠሩም፡፡ ቢኒያም በበኩሉ ጥርጣሬና ስጋት እየተከታተሉ ቢፈታተኑትም ራሱን ተቆጣጥሮ ከተሽከርካሪው ሳይወጣ ባለበት የሚሆነውን መከታተል ጀመረ፡፡
የፖሊስ ዳብል ጋቢና ፒካፕ መኪና እያሽከረከረ ቢኒያምን ሲከተል የነበረው ዋና ሳጅን ሚሊኪያስ ምክትል ሳጅን አዲስ አለም ፣ ሳጅን ኤልያስ ታፈሰ፤ እና ሌሎች ወንጀል ፈጻሚዎች ጋር አብረው በመኪናው የመጡት በሙሉ ከመኪና ወረዱ፡ ፡ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-47692 ኦ.ሮ የሆነ ዶልፊን መኪና እያሽከረከረ የነበረው፤ ዳዊት በልሁም እንደሌሎቹ ከመኪናው ወርዶ ወደ ቢኒያም መኪና ተጠጋ፡፡ መኪናቸውን ከቢኒያም መኪና አጠገብ አቁመው ምክትል ሳጅን አዲስ አለም የፖሊስ የደንብ ልብስ ለብሶ መጥሪያ የሚመስል ወረቀት እያሳየ ሽጉጥ ወደ ቢኒያም ግንባር ደቀነ፡፡ ሳጅን ኤልያስ ታፈሰ ደግሞ፤ ለቢኒያም ‹‹ከመኪናው ውረድ አንተ ሀገር አፍራሽ ጁንታ›› በማለት ከመኪናው አስወረደው።
በካቴና ሁለት እጁን በማሰር በፖሊስ መኪና አስገቡት፡፡ ‹‹የመኪናዬ በር ስላልተዘጋ ልዝጋው ፍቀዱልኝ›› አላቸው፡፡ ‹‹እንደውም ውረድ›› በማለት፤ እጁ በካቴና እንደታሰረ በራሱ መኪና ከኋላ ወንበር በማስገባት ሌላኛው ወንጀል ፈጻሚ የቢኒያምን መኪና እያሽከረከረ ምክትል ሳጅን አዲስ አለም በቢኒያም ግንባር ላይ ሽጉጥ በመደቀን ‹‹እንቀሳቀሳለሁ ብትል እገልሃለው፣ የምጠይቅህን ብቻ መልስ ፡፡ ›› በማለት፤ መኪናውን እና እርሱን ፈትሸው የዋጋ ግምታቸው 70 ሺህ ብር የሚገመት ሁለት ዘመናዊ ሳምሰንግ ስልኮች ፣ ከተለያዩ ባንኮች ተፅፎ የተፈረመባቸው የ200,000 ብር እና የ350,000 ቼኮች፣ የመኪና ቁልፍ እና የተለያዩ ሰነዶችን ወሰዱ፡፡
በቢኒያም ጭን ላይ ሽጉጥ በመደቀን ‹‹ብልትህን ነው የማወጣልህ›› በማለት እያስፈራሩ ወደ ጉርድ ሾላ አቅጣጫ መኪናውን እየነዱ ወሰዱት፡፡ እየወሰዱት እያለ ፤ ‹‹ዝቅ በል ካቴናውን ሰው እንዳያየው›› በማለት መኪናውን ወደ ሰዓሊተ ምህረት አቅጣጫ ሲያሽከረክሩ ስራ አመራር አካባቢ ማርያም ባቡር መሻገሪያ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ፤ ትራፊክ መንገዱን በማጨናነቁ ምክንያት መኪናው ፍጥነቱን ቀነሰ፡፡ ቢኒያም እጁን በካቴና እንደታሰረ የመኪናውን መስኮት በመክፈት እጁን እና አንገቱን ወደ ውጭ በማውጣት የድረሱልኝ ጥሪ አሰማ፡፡ ጩኸቱን አቀለጠው፡፡
የአካባቢው ህብረተስብ ሲሰበሰብ በመስኮት ዘሎ በመውጣት ‹‹ሌቦች ናቸው አፍነውኝ ነው አስጥሉኝ›› ሲል ወንጀል ፈፃሚው፤ ከመኪናው በመውረድ ‹‹በወንጀል ተፈላጊ ነው›› በማለት ይዞ መልሶ ወደ መኪናው ውስጥ ሊያስገባው ሲሞክር በአካባቢው የነበሩ ፖሊሶችና ሌሎች ሰዎች የደንብ ልብስ የለበሰውን ወንጀለኛ ተባብረው ያዙት፡፡
የፖሊስ ምርመራ
የህግ አስከባሪነት ሀላፊነትን ተቀብለው ለረዥም አመታት ሲያገለግሉ የቆዩት እነዚሁ ግለሰቦች የተሰጣቸውን ሀላፊት ያለአግባብ በመጠቀም ህዝቡን ማሸበር ዋነኛ ተግበራቸው ካደረጉት መቆየታቸው በፖሊስ ምርመራ ተረጋገጠ። በዚህ ተግባራቸው የመዲናዋን ሰላማዊ ሰዎች ሀብት ንብረት ከመቀማት አልፎ በማስፈራራት የስነ ልቦና እና የአካል ጉዳት ማድረሳቸውም ታወቀ።
የፖሊስ ምርመራው እንደሚያሳየው በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የውንብድና ተግባር ሲፈፅሙ ከለላ ያደረጉት ህዝብ የጣለባቸውን ሀላፊነት ነበር። ለስራቸው ቅልጥፍና ሲባል የተሰጣቸውን የደንብ ልብስ ከስራ ውጪ በመጠቀም በህግ ማስከበር ሰበብ ሰዎችን ሲያስፈራሩና፤ ለወንጀላቸው መሸፈኛ ይሆን ዘንድ የፖሊስ ማዘዣ ወረቀትን በማስመሰል ያለአግባብ ሰዎችን ሲያንገላቱ ቆይተዋል።
ዳዊት በልሁ ፣ ሳጅን ኤልያስ ታፈሰ፤ ሌላው ወንጀል አድራጊ በዶልፊን መኪናው ካመለጡት መካከል አንዱ ክትትል ሲደረግባቸው በሽጉጥ ሌላ ተበዳይንም እያስፈራሩ ጥርሱን በቦክስ በመምታት ጥርሱ እንዲደማ በማድረግ ይዘውት በመጡት የፖሊስ መኪና የኋላ ወንበር ካሰገቡት በኋላ የዋጋ ግምቱ 11,000 ብር የሆነ ሞባይል 5,000 ጥሬ ገንዘብ ፣ መንጃ ፍቃድ እና የባንክ ደብተር ከኪሱ አውጥተው መውሰዳቸው ታወቀ፡፡
ሌላውን እንደቢኒያም ዓይነቱን ተበዳይን ይዘው በላምበረት ወደ ሲቪል ሰርቨስ አቅጣጫ ከወሰዱት በኋላ ሲቨል ሰርቪስ ሲደርሱ ያልተያዘው ግብረ አበራቸው አንገቱን ይዞ ከመኪናው በማስወረድ ጥለውት መሄዳቸው ተረጋገጠ።
ምርመራውን መሰረት በማድረግ ምክትል ሳጅን አዲስ አለም ህጋዊ ፍቃድ ሳይኖረው የጦር መሳሪያ ይዞ የተገኘ እና ሰዎችን ለማስፈራራት የተጠቀመ በመሆኑ በፈፀመው ከባድ የውንብድና እና ህገ- ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት ወንጀል ተከሰሰ፡፡ እርሱ ብቻ አይደለም፤ ወንጀል ፈፃሚዎቹ ጓደኛሞች ከባድ የውንብድና ወንጀል እንዲሁም ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት ወንጀልን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ በመተላለፋቸው በፍትህ ሚኒስቴር ቦሌ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ዐቃቤ ህግ ክስ ተመሰረተባቸው፡፡
ውሳኔ
ተከሳሾች በችሎት ቀርበው ክሱ ደርሷቸው ከተነበበላቸው በኋላ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ተጠየቁ፡፡ 4ቱም ተከሳሾች ‹‹ድርጊቱን አልፈፀምንም ጥፋተኛም አይደለንም›› ሲሉ ቃላቻውን ሰጡ።
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የተከሳሾችን ጥፋተኝነት የሚያስረዱ ምስክሮች፣ የሰነድ፣ ገላጭ እና የኤግዚቢት ማስረጃዎችን በበቂ ሁኔታ ለችሎቱ አስረዳ፡፡ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾችን እንዲከላከሉ ብይን ቢሰጥም፤ በዐቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ክስ እና ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሾች በተከሰሱባቸው ክሶች የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላለፈባቸው።
በዚህም መሰረት ተከሳሾች ከዚህ በፊት የጥፋተኝነት ሪከርድ የሌለባቸው፤ የቤተሰብ አስተዳዳሪ የቅጣት ማቅለያዎች ተይዘውላቸው 1ኛ ተከሳሽ ምክትል ሳጅን አዲስ አለም አባተ ቢሻቶ የ12 ዓመት ከ3 ወር ፅኑ እስራት እና 2,000 ብር ተፈረደበት፡፡ ሁለተኛ ተከሳሽ ዋና ሳጅን ሚሊኪያስ አበራ ማሞ ፤ ሶስተኛ ተከሳሽ ሳጅን ኤልያስ ታፈሰ የ12 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደባቸው፡፡ የመጨረሻውና 4ኛ ተከሳሽ ዳዊት በልሁ በ9 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/ 2015 ዓ.ም