አያ ቢተው ይባላሉ፤ለፍተው ለሥራ ካበቋ ቸውና እያስተማሯቸው ካሉት ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ጋር በአዘቦት ቀን በአንድ ላይ ሰብሰብ ብለው እየተ ጨዋወቱ ነው። የሚያዩትና የሚሰሙት ትዝብትም፣ ግርምትም፣ቁጭትም ፈጥሮባቸ ዋል፡፡ የአገራቸው ጉዳይ ከልባቸው ተሰንቅሮ እረፍት ቢነሳቸው በቤተሰብ ጨዋታቸው መካከል አንስተውታል፡፡
መምህር ታለጌታ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪዋ አለሚቱ እንደ ቅደም ተከተላቸው የእድሜ ጠገቡ አያ ቢተው ልጅና የልጅ ልጅ ናቸው። ውይይቱን አድምቀው ታል፡፡ የስም መመሳሰል ከተፈጠረ ታስቦበት እንዳልሆነ ይያዝልኝ እያልኩ ጭውውታቸውን እንደወረደ ጋበዝኳችሁ፡፡ መኮምኮም የእናንተ ፋንታ ነው፡፡
አያ ቢተው፡- ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› ብለው አበው የተረቱት መሬት ጠብ አላለም፡፡ ጉብል እስከ አዋቂ በወሬ የሰከረ፣ በወሬ የተምታታ ይሁን? ወሬን በወሬነቱ አድምጦ ከማን ሰማኸው? የትስ አገኘኸው? ብሎ መጠየቅ ነውር ነው እንዴ? እንዲህ ሆኖ አረፈ ወጉ? ንፋስ ሲያመጣው መቀበል፤ንፋስ ሲነሳ መሸኘት። በፌስቡክ ጉሊት ከሚነፍሰው ጋር ገለባ ሆኖ አብሮ መንፈስ። አይጣል እቴ!
መምህር ታለጌታ፡- ምነው? ምን ገጥሞህ ነው? አያያ። (አባቱን የሚጠራበት ስም ነው) እንዲህ ሆድ ያስባሰህ።
አያ ቢተው፡-ሰማህ ልጄ አገር መስታወት ነው። ተጠንቅቃችሁ፣ ወልውላችሁ ያዙኝ ይላል። እንደ ቀልድ ባረባ ቦታ አስቀምጠህ፤ አለያም በአቧራ ሲለወስ እያየህ ያልሰተርከው መስታወት እንደፈለከው ትክክለኛ መልክህን ሊያሳይህ ይሳነዋል፡፡ አገርህም እንደዚያው ነች። እንደቀላል ሥሟን ማጉደፍ ለመወልወል ያስቸግራል፡፡ አገርህንና አይንህን በዋዛ አታስነካ፡፡ መተኪያቸው ይቸግርሃል፡፡ በአገር መስታወት ውስጥ ማን የሚታይ መስሎሃል?
መምህር ታለጌታ፡- ድሮ ልጅ እያለሁ ‹አብወ ለድ› ብስኩት ልገዛ ሳላስፈቅድ ከኪስህ ገንዘብ አሹልኬ ስወስድ ተቆጥተህ የምታሳየኝን ፊት ነው ዛሬ ያየሁብሀ። እንዲህ ለብሶት የዳረገህን ጉዳይ ለምን አትነግረኝም፡፡
አያ ቢተው፡- አየህ አገር ሲከፋት ብሶቷ የሚታየው በእኛ ፊት መጥቆር ነው፡፡ አገር በውሸት ስትታመስና ሠላሟ ሲናጋ የሚናጋው የእኛ ኑሮ፣ የእኛ ሰላም ነው፡፡ አለመታደሌ ሆኖ እነሱ በዋሉበት ሳልውል ቀርቼ ይሁን እንጃ ጆሮዬ በየቀኑ የሚሰማውና የሚያደምጠው ሟርት ብቻ ሆነ፡፡ እንዴት ሰው ካላጣው ማሟረቻ በአገሩ ያሟርታል፡፡
‹‹አንድ አይና በአፈር አይጫወትም›› አሉ፡፡ ሌላ መጠለያ ያለን ይመስል እንዴት አንሳሳላትም፡፡ መረን ትቶ ከአሳሩ መራቅ፣ መሸሽ አይቻል፡፡ በአገር የሚመጣ እንዴት ዘራፍ አያስብልም፡፡ በጠላሸት በተጥሞረሞረና በጠቆረ ነጠላ ማጌጥ የለም፡፡ ወተት መስሎ መታየት ይናፍቃል፡፡
መከበርም አይታሰብ፡፡ በአገርም ያው ነው፤ ያውም ይብሳል፤ ቀና ብሎ እኩል ማያ አይን ያሳጣል፤ ምላስ እንዳልፈታ ሕጻን አንደበት ጉልበት አጥቶ ይንተፋተፋል፡፡ አገር መስታወት የጨበጠች ዕለት ከፊት ለፊቷ የሚታዩት የእናንተ የትውልዶቿ የሰከሩ ፊቶች ናቸው፡፡ እንጂማ ምን አብሰከሰከኝ፡፡
መምህር ታለጌታ፡- እንደ እናንተ ዘመን አገርን የሚወድ ትውልድ የለ ሆኖ ይሆን እንዴ? ተማሪዎቻችን ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ብዙ ነገር ያወቁ አድርገው ራሳቸውን ያስባሉ፡፡ በዚህ የተነሳ አሻግረው የሚመለከቱት ውጪ አገር ነው፡፡ ያ ይሆን?
ተማሪ አለሚቱ፡- ተማሪዎች የሚማሩት እኮ ዲቪ ለመሙላት ነው፡፡ ደግሞ እዚህ አገር ማን ተምሮ የተለወጠ አለ? ጋሼ ይሙት(በአያቷ ስትምል)፡፡ ፊዚክስ መምህራችንን ብታዩት ፈላጭ ነው‹(ጎበዝ ነው ለማለት ነው) በዚያ ላይ ጨዋ ነው፡፡ አምስተኛ ክፍል እያለሁ የለበሳትን ስኩዌር ሸሚዝ እስካሁን ድረስ አልቀየራትም። እና መማር ቢለውጥ እሱን አይለውጥም ነበር።
አያ ቢተው፡- አይምሰላችሁ ልጆቼ። አገሩን የሚወድ ትውልድ በየዘመኑ ይበቅላል፡፡ ዋናው ነገር አስተዳደጉ ነው። እየሰማችሁኝ ነው?
መምህር ታለጌታ፡- አዎ፡፡ በደንብ እንጂ። እያዳመጥን ነው።
አያ ቢተው፡- በዚች ምድር ላይ ያልዘሩት አይበቅልም። ያልዘሩትን የሚያጭዱም አይኖሩም። ካሉም ደግሞ ርባና ቢስ ናቸው፡፡ እናም ‹‹ተማሪው ማንን ይመስላል ቢሏችሁ አስተማሪውን፤ አገር ማንን ይመስላል ከተባላችሁም መሪውን›› ነው መልሱ፡፡
ተማሪዎቻችሁ የእናት አገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ክብር ያውቁታል? ሲወጣና ሲወርድ ያለውን ክብርስ? መዝሙሩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ በሚያስረቀርቅ ድምጽ ያዜሙ ታል?
ተማሪ አለሚቱ፡- ጋሼ አንተ የምትለው የድሮውን ነው? እሱኮ አሁን የለም ቀርቷል፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ሲወጣና ሲወርድ እኛ ትምህርት ቤት ቀስ ተብሎ ነው የሚኬድ። አስተማሪዎቻችንም፣ርዕሰ መምህራችንም እንደኛ ቀስ ብለው ነው የሚራመዱት፡፡
እኔ እስካሁን ሳይንቀሳቀስ ቀጥ ብሎ የሚያከብር አላየሁም፡፡ በሰልፍ ላይም የዜግነት ክብር መዝሙር መዘመር ግዴታ አይደለም፡፡ የፈለገ ይዘምራል፤ ያልፈለገ ዝም ቢልም ችግር የለውም፡፡
አንድ ቀን የሥነ ዜጋና ሥነምግባር አስተማ ሪያችንን በጣም ረበሽነው፡፡ ከዚያ‹‹ የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ቆሞ በደንብ የዘመረ 10 ማርክ እጨምርለታለሁ›› አለ፡፡ 56 ታችንም ጸጥ ነው ያልነው፡፡ 38 ተማሪዎች ሞክረው አንዳቸውም አልቻሉትም፡፡ ቲቸርየ ለነገ ተለማምደነው እንድንመጣ አስጽፈን አልነው፡፡ ብዙ ሳያስብበት ‹‹እሺ›› ብሎ ጀመረልንና መካከል ላይ አራት መስመር ብቻ ጽፎ ጠፍቶት ቀጥ አለ፡፡ ከዚያም ነቄ አልንበት፤እንዴት እንፋታው፡፡ አዘናግቶ ላሽ ሊል ነበር፡፡ ማቲስ (ሒሳብ) ክፍለጊዜ ገብቶ አስተማሪያችን ቆርቁሮ አስወጣው፤ ገላገለው፡፡
መምህር ታለጌታ፡- እሱስ እውነት ነው፡፡ እኛም አናደርግም፡፡ተማሪዎቹም እንዲያደርጉ የሚመክር አስተማሪ እስካሁን አላየሁም። ራሳችን አስተማሪዎችም ከልባችን አድርገን ማሳየት ነበረብን፡፡ እንደውም መምህር የሆንበትን እድል እየረገምን ከመዋል ባለፈ መቼ ወደነውስ እየሰራነው። መብላት ስላለብን ብቻ እኮ ነው የምናስተምረው እንጂ ተማሪው ሲቀልድ ነው የሚውለው፡፡
በቀደም እለት አንድ ተንኮለኛ ጋዜጠኛ የወራቱን እና የእለቱን ግጥምጥሞሽ እያሰላ ‹‹የካቲት 12፣ አርበኞች፣ድል ፍሬ…ወዘተ ተብለው በሚጠሩ ትምህርት ቤቶች ከች እያለ ጉድ ሰራቸው። ተማሪዎቹ የትም ህርት ቤታቸው ስም(መጠሪያ) መሆኑን እንጂ ከዚያ የዘለለ አንዳች ነገር የሚያውቁት እንደሌለ ገለጹ። የታሪክ አስተማሪዎችንም ለትዝብት እንደዳረጋቸው ሰምቻለሁ፡፡ እንደውም አንዱስ ‹‹ጥሩ ስትከፍሉኝ ጥሩ አስተምራለሁ›› ብሏል አሉ፡፡
አያ ቢተው፡- አያችሁ ታዲያ ተማሪዎቹ ከየትና ከማን ያዩ የሰሙትን ነው አገራቸውን፣ ሰንደቃ ቸውን፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ መዝሙር ሊያውቁ የሚችሉት፡፡
የአገር ፍቅር ከልጅነት ጀምሮ አብሮ የሚያድግና ሲነካ የሚቆጠቁጥ የአካላችን አንድ ክፍል እንጂ ዘሎ መጥቶ የሚሳፈር ውቃቤ ወይም ዛር አይደል። ልጆቻችን የአገር ፍቅር ስሜትን ከቤተሰቦቻቸው በተግባር አይተው መቅሰም ካልታደሉ በትምህርት ቤት ብቻ ሙሉ ሊያደርጉት አይችሉም፡፡ ልጆቻችን የእኛ ውጤቶች ናቸው፡፡ ከእኛ ከወላጆች በተግባር ያዩትን ከእኛ በላይ ሁነውት ያድጋሉ፡፡
ልጆች ሲያድጉ እናቴን፣አባቴን ያስቀይምብኛል ወይም ነውር ነው ብለው የማያደርጉት ወይም የተከለከሉት ተግባር እንዳለ ሁሉ አገርህን(አገርሽን) ያስከፋል፡፡አገራችሁ ትቆጣባችኋለች በሌላ በኩል ይሄን ብታደርጉ አገራችሁ ታመሰግናችኋለች ተብለው ያደጉት ተግባር ሊኖር ይገባል፡፡ በትምህርት ቤት ደግሞ ይበልጥ መጎልበት ይኖርበታል፡፡
ሕጻናት እኛ ቤተሰቦቻቸው በሰራናቸው ልክ የሚያድጉ ችግኞች ናቸው፡፡ በረጅም ጊዜ ስኬት ፍሬያቸው ሊታይ የሚችል፡፡
መምህር ታለጌታ፡- እናንተ ስታድጉ ሀሜት፣ስድብ፣ አሽሙር፣ጥላቻ ፍጹም ነውር የሆኑት እና የተወገዙት በምን መንገድ ነበር፡፡ አሁን እኮ ተማሪዎቻችን መክረናቸው እየሰሙን አይደለም፡፡
አያ ቢተው፡- አልቀበላችሁ አሉ? መጀመሪያ እናንተ ሁናችሁ ተግብራችሁ አርአያ ሁኑላቸው፡፡ ከዚያ ተማሪዎቻችሁ በራሳቸው ጊዜ እንዲሆኑ የምትፈልጉትን ሆነው ታገኟቸዋላችሁ፡፡
እንደው ይሄ መከረኛ ዘመን እያላችሁ ትደልቁበ ታላችሁ እንጂ ኮ ከዚህ በላይ ወርቅ የሆነ ዘመን ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡
ማሰልጠኛ ፍዳ ሳይከፈል፣መሳሪያ በየዕለቱ እየፈቱ በመወልወል ሳይሞሽሩ፣ መሳሪያ ከነዘሩ አብሪ ታጣፊ እያሉ ሳይዋትቱ፣ከሞቀ ቤቱ የሞቀ ጭን እንደታቀፉ ተንደላቀው ሹም ሽር ታይቶ ያውቃል? አሜኬላ ሳይለ ብሱ ቋጥኝ ሳይንተራሱ የአገርን አሜኬላ ለመንቀል ታስቦ ያውቃል፡፡ አይታሰብም ።
ችግሩ ለዘመናት ሲገረፍ የለመደ ሕዝብ ሆነና ቢያንስ ቆንጥጡኝ፣ስደቡኝ አለበለዚያ አደብ አልገዛም ማለቱ ነው። ቆዳው ነጻነትን መሸከም አይችልም፡፡አለመደም የሚሉም አሉ።‹‹የለመደ ልማድ ያሰርቃል ከማዕድ›› እንዳሉት አበው ሀሜትን፣ሽርደዳን፣ቂምን፣ጥላቻን በቡና ጠጡ የሰፈር ፕሮግራም መዝራትና ማቃቃር ሥራ ሆኖ ደመወዝ አስከፍሏል ይባላል፡፡ ዛሬ ከሥራ ገበታ ዝርዝር ሲሰረዝ በርካቶች ለአደገኛ ሥራአጥነት መዳረጋቸው ይነገራል፡፡ ፍጹም ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አሳፋሪና አስነዋሪ የሆኑ ተግባራትን ጭምር የተፈቀዱ ያህል መላመድ አልቸገረንም፡፡አላሳፈረንም፡፡
ማታለል ፣መዋሸት፣መስረቅ (ያውም የሚልሰው ካጣ) ከፖለቲከኛ እስከ ቤተ እምነት ጓዳ ዘልቀው ከተጣቡ ሩብ ክፍለ ዘመን አስቆጥረዋል፡፡ ጥሮ ግሮ ከመክበር በአቋራጭ ከደሃ ጎሮሮ መንትፎ ፎቅ መደርደር፣ መንደላቀቅ በአደባባይ ወግ ሆኗል፡፡ እነዚህን በእውን ማድረግ የቻልን ሰዎች ከድህነት የሚያላቅቅ ወኔን መላበስ ተስኖናል፡፡
ነገሩማ አያድርስ ነው፡፡ ክፉ አመል አመለኛውን ሳያጠፋ አይጠፋም፡፡ የሚባለው ሐሰት አይም ሰላችሁ። አሁን በጥሩንባ ከመለፈፍ ላልተላቀቅን ሕዝቦች ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎችን እንደ እድል ልንጠቀምባቸው በተገባ ነበር፡፡ እኛ ግን አሁንም የንትርክ አፈሙዝ መማዘዣ፣የሐሜት እና የጥላቻ መንዣ አድርገናቸዋል፡፡
መምህር ታለጌታ፡- ወሬን ወሬ ያነሳዋልና እዚህ ላይስ የሰማሁትን እኔም ላክልበት፡፡እነፌስ ቡክ ለእኛ አገር ከእድልነታቸው ይልቅ ጦሳቸውን አልቻልነውም። ሌሎቹ ምርታቸውን እና አገልግሎቶቻቸውን ያስተዋ ውቁባቸዋል። እኛ ደግሞ ክፋቶቻችንን፣መርዛማ ንግግሮ ቻችንን እንረጭ ባቸዋለን።ከክፋታችንና ከምቀኝነታችን የአስተሳሰብ የእድገት ደረጃ ሳንላቀቅ ፈጥነው መጥተውብን ነው፡፡ እኛ እኮ ገና ‹‹ኩብኩባ›› ደረጃ ላይ ነን ብሎ ከትከት አድርጎ ያሳቀንን የሥነ ሕይወት አስተማሪ አልረሳውም፡፡
በፖለቲካው መስክ ተከራክረህና ተወዳድረህ ልትደር ስባቸው ያልቻልካቸውን እንደ ዶክተር አብይ አይነት የልጅ አዋቂ ትንታግ መሪዎች ተግባር ከአፍ እና ከእጅ እየለቀምክ ጥላሸት በመቀባት ለፌስቡክ ጉሊት ቀርበው ይቸረችራሉ ይባላል፡፡
በአካባቢው በሚገኝ ትጉህ ነጋዴ ላይ ምቀኝነት ያደረበት ሙትቻ ነጋዴ አለያም የእሱ ቅጥረኛ ተከፋይ ሁለት ዘዴን በማጥመጃነት ይጠቀማል አሉ። የመጀ መሪያው የሐሰት ክስ መስርቶ ፍርድ ቤት እያመላለሱ ሥራ ማስፈታት ከተቻለም ንብረቱን ማሳገድ። ሁለተኛው ደግሞ የምርቶቹን ዝርዝር ከመርዛማ ቃላት ጋር ለፌስ ቡክ ጉሊት አቅርቦ ለሐሜት ንፋስ ማጋለጥ። በቀደዱለት ቦይ የሚፈሰው የፌስቡክ ጉሊት ተሰላፊ የጫኑትን ተሸክሞ ከመንጎድ በዘለለ ማላመጫም ማዳመጫም የላቸውም ይባላል፡፡
ተማሪ አለሚቱ፡- ይሄን ያህል ቀውስ ፈጥሯል እንዴ? ሁሉም ሰው ተለክፏል?
አያ ቢተው፡- ሰማችሁ ልጆቼ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ጥሬ እንዳየች ጅግራ ትውልዱ ወጥመድ ውስጥ ገብቷል፡፡ ‹‹ትዝብትህን ንገረን ካላችሁ ከሕጻናት እስከ አዋቂ ምሁር ነኝ ባይ ድረስ ‹‹መርዞ›› መርዛለች፡፡
በአይኑ ከሚያየው፣ በእጁ ከሚዳስሰው እውነታ በላይ የማህበራዊ ሚዲያ አማኝ፣ሰጋጅ፣ተከታይና ዘማች ትውልድ በርክቷል፡፡ ከእምነት ቦታዎቻችን በር እኮ አንድያችንን ጠቅልለን ስንሄድ ካልሆነ በስተቀር እግራችን ድርሽ አልልም ብሎናል፡፡
እናንተም እኔም ሁላችንም የፌስ ቡክ ጋሪዎች መሆናችንን እረሳችሁት? አሁን የእኛ መሪ ማን እንደሆነ ጠፍቶን ነው? ሆሆ…ሆሆ.. ‹‹ወደው አይስቁ›› ነበር ተረቱስ፡፡ ከየት አባቴ ሣቅ ላምጣ እንጂ፡፡ እንደውም ‹‹ወደው አያብዱ›› ብየዋለሁ፡፡
አዎ ንገረን ካላችሁ ‹‹አሁን እንደው ጆሯችን ቀጥ ብሎ ቆሞ ወሬ የሚያዳምጠውና የሚጠብቀው ከቤተ መንግስት ነው ወይስ ከፌስ ቡክ? መልሱን ከራሳችሁ ኪስ ፈትሹ፡፡
መሪዎቻችን እንዲህ አሉ ብለን ከምናጣቅስ ይልቅ ሺ ጊዜ ፌስቡክን አናነሳምን? ስለዚህ እስኪ ንገሩኝ? የእኛ መሪ ማን ነው? ሕዝብ መሪውን ይሰማል፣ ያዳምጣል፣ ይከተላል፣ አብሮ ይተማል፡፡ ስለዚህ እኛ እንዲህ ነን ወይ፡፡ እየተመምን ያለነው ከየትኛው መሪያችን ጋር ነው? የየትኛውን መሪያችንን ቃል በመፈጸም ላይ ነን? ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ ሁላችንም የፌስቡክ ነጋዴ ነን፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2011
በሙሐመድ ሁሴን