እቁብ በኢትዮጵያ ባህላዊ የገንዘብ ቁጠባ መንገድ ሆና ለረጅም ዓመታት አገልግላለች። ይችን ባህላዊ የገንዘብ መቆጠቢያ መላ ጉራጌዎች እንደጀመሯትም ይነገራል። በዚች ባህላዊ የገንዘብ ቁጠባ ስልት ሰዎች ቡድን ፈጥረው በየወሩ ገንዘብ ሰብስበው በየተራ እየወሰዱ የገጠማቸውን የገንዘብ ችግር ፈትተዋል። አሁንም በዚቹ እቁብ አማካኝነት ሰዎች ንግድ ይጀምራሉ። የህክምና ወጪያቸውን ይሸፍናሉ። የሚያስፈልጓቸውን የቤት እቃዎችንም ያሟላሉ።
በኢትዮጵያ ባንኮች እየበዙ መጡ እንጂ የአብዛኛው ማህበረሰብ የገንዘብ ቁጠባ መንገድ እቁብ ነበር። አሁንም ቢሆን በተለይ የገጠሩ ህብረተሰብ ሁነኛ የገንዘብ ቁጠባ ዘዴ እቁብ ነው። ከነተረቱም ‹‹ሰውን ሰው ያደረገው እቁብ ነው›› ይባላል። ይህም እቁብ በማህበረሰቡ ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነት ያለው መሆኑንና በድንገት ከሚያጋጥም ችግር መውጪያ መንገድ መሆኑን ያሳያል።
እስካሁን ድረስ እቁብ ባህላዊ መንገዷን ጠብቃ እዚህ የደረሰች ቢሆንም ታዲያ አሁን ላይ ግን በጥቂቱም ቢሆን ደረጃዋ ከፍ ያለ ይመስላል። ዘመናዊነትንም ተላብሳ ብቅ ብላለች። እንዴት? ያሉ እንደሆነ እቁቧን ለማዘመንና ደረጃዋንም ከፍ ለማድረግ በጋራ እየሰሩ ያሉ ወጣቶች ለዚህ ምላሽ አለን ይላሉ።
ወጣት አቤኔዘር እንግዳ ‹‹ውጆ›› የተሰኘና የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ላይ የሚሰራ መተግበሪያ ከፈጠሩ ወጣቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን የዚሁ ቴክኖሎጂ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኖ ያገለግላል።
እርሱ እንደሚለው ‹‹ውጆ›› በጉራጌኛ ቋንቋ እቁብ ማለት ሲሆን የቴክኖሎጂ ድርጅቱ ስም የፈለቀውም ከዚሁ የጉራጌኛ ቃል ነው። በቀደመው ታሪክ እቁብ ሸቀጥ ላይ ያተኮረና ሰዎች ግብይት የሚያካሂዱት እቃን በእቃ በመለዋወጥ ነበር። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሀገሪቱ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትና አሉታዊ የኢኮኖሚ ተፅእኖ ይታያል። እቁብም በባህሪው ለእቁብተኛው በግዜ ገደብ ገንዘብ የሚደርሰው በመሆኑ መጀመሪያና መጨረሻ ገንዘቡ ሲወሰድ እኩል ዋጋ ሊኖረው አይችልም። በዚህ መነሻነት አንድ ሰው የወጣለትን እቁብ ለምን ወደሸመታነት አይቀይረውም በሚል በውስጡ የኢ ኮሜርስ ፓላትፎርም በማጠቃለል የሚሰራ ‹‹ውጆ›› የተሰኘ መተግበሪያ በለፀገ።
የትምህርት እድል አግኝቶ በቻይና ሀገር እንደነበር የሚያስታውሰው ወጣት አቤኔዘር፤ እዛ በነበረው ቆይታ ‹‹ዊ ቻት›› የተባለ መተግበሪያ ማየቱንና በዚሁ መተግበሪያ አማካኝነት ሁሉንም የፋይናንስ ጉዳዮች በአንድ ላይ በማድረግ ሲጠቀሙበት መታዘቡን ያስረዳል። ይህንኑ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ በሀገር በቀል ሀሳብ ለምን ወደ ኢትዮጵያ አናመጣውም በማለት ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ስራውን እንዳስጀመረም ይናገራል።
እንደ ወጣት አቤኔዘር ገለፃ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ነው የተባለለት ይህ የፋይናንስ መተግበሪያ በውስጡ ሰዎች እቁብ እንዲጥሉ፣ ብድር እንዲያገኙና ሸመታ እንዲፈፅሙ ያስችላል።
በዚሁ መተግበሪያ አማካኝነት ሁለት ስራዎች የሚከናወኑ ሲሆን በመጀመሪያው ከቢዝነስ ድርጅቶች ጋር በመጣመር ለድርጅት ሰራተኞች እቁብ እንዲቀርብ ይደረጋል። በሁለተኛው ደግሞ ግለሰቦች፣ የቤተሰብ አባላትና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች እቁብ የመጀመር ሃሳብ ካላቸው ሶስትና አራት ሆነው ሲመጡ ከመካከላቸው አንዱ ለድርጅቱ እንደ ወኪል ሆኖ ያገለግላል። በዚህም ድርጅቱ ከሚያገኘው ሶስት ከመቶ የአገልግሎት ክፍያ እኩል ተካፍሎ ጥቅሙን እያገኘ ኃላፊነት ወስዶ የማህበረሰቡን እቁብ እንዲያሳልጥ ያደርጋል።
‹‹የእቁብ አሰባሰቡ ዲጂታል እንዲሆን በማሰብም ጭምር ነው መተግበራዊ የበለፀገው›› የሚለው ወጣት አቤነዘር እቁብ በባህሪው የተለያዩ እጥረቶች የሚታዩበት መሆኑን ይገልፃል። እቁብ በቀላሉ ተደራሽ አለመሆኑ፣ አቅምን ያገናዘበ፣ በሰአቱ ሊደርስ የማይችልና ትክክለኛነቱም አጠያያቂ መሆኑ ከእጥረቶቹ መካከል ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውንም ያብራራል።
እነዚህኑ እጥረቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት እቁብ ዲጂታላይዝድ ቢደረግ እጥረቶችን በመፍታት ረገድና ስራውንም በማቀላጠፍ በኩል ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ከሚል እሳቤ በመነሳት እርሱና ጓደኞቹ ስራውን እንደጀመሩት ያስረዳል።
የሀገሪቱ የፋይናንስ ሴክተርም ይህን ጉዳይ ቸል ያለው በመሆኑና በተለይ ደግሞ የጥቃቅንና አነስተኛ የቁጠባና ብድር ተቋማት በዲጂታል መንገድ ብድር ገና በቅርቡ የጀመሩ በመሆናቸው በዚህ ረገድ የሚታየውን ክፍተት ከመፍታት አኳያ የመተግበሪያው ሚና የጎላ መሆኑንም ይጠቅሳል።
ወደ 44 ከመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ህብረተሰብ ከዝቅተኛ እስከመካከለኛ ገቢ ያገኛል የሚል መረጃ በመኖሩ ለነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች መተግበሪያው አማራጭ የፋይናነስ አገልግሎት ሆኖ እንደሚያገለግል ወጣት አቤኔዘር ይጠቁማል።
የገንዘብ ንክኪውንም ከመቀነስ አኳያ የመትግበሪያው ሚና የጎላ መሆኑንም ጠቅሶ፤ ድርጅቱ ፕላትፎርሙን በድረገፅና በመተግበሪያ በማቅረብ ገንዘቡ በባንክ በኩል ለተጠቃሚው እንዲቀርብ የሚደረግ መሆኑንም ያስረዳል። የድርጅቱ ተግባር እቁቡን ማስተዳደር ብቻ መሆኑንም ነው የሚጠቁመው። መተግበሪያውን ያላወረደ ሰው ካለም በድረገፁ አማካኝነት እንዲጠቀም የሚያስችለው መሆኑንም ይገልፃል።
ወጣት አቤኔዘር እንደሚለው በአሁኑ ግዜ ድርጅቱ ከተለያዩ የቢዝነስ ድርጅቶች ጋር ስምምነት በመፍጠር ሰራተኞች በሚፈልጉት አማራጭ በመተግበሪያው በተጋጀላቸው ጥቅል አማካኝነት ከደሞዛቸው ውጪ አማራጭ የቁጠባ እቅድ እንዲኖራቸው እየሰራ ይገኛል። ከቢዝነስ ድርጅቶች ውጪ ያሉ ሌሎች ሰራተኞችም ከመካከላቸው አንዳቸው ወኪል ሆነው ይመዘገቡና ድርጅቱ ከሚያገኘው የአገልግሎት ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆኑና እቁቡን በማሳለጥ ረገድ ሃላፊነት እንዲወስዱ ይደረጋል።
የቴሌኮምና የኢንተርኔት መሰረተ ልማት እምብዛም ባልተስፋፋበትና የህብረተሰቡም የዲጂታል እውቀት እምብዛም ባለሆነበት በዚህ ጊዜ ባህላዊ የገንዘብ ቁጠባ መንገድ የሆነውን እቁብ በዲጂታል መንገድ ማሳለጥ የራሱ የሆነ ተፅእኖ አለው። ይሁንና ድርጅቱ እንዲህ አይነቱ ችግር በሂደት የሚፈታና የሚቀየር መሆኑን በማመን ስራውን እያከናወነ ይገኛል።
በተለይ የህብረተሰቡ የዲጂታል እውቀት ገና ያላደገ እንደመሆኑ የዲጂታል ግንዛቤን በህብረተሰቡ በማስፋትና አሁን እያደገ የመጣውን የዲጂታል መሰረተ ልማት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም እቁብን ጨምሮ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ የፋይናስ ስራት ለማስፋት ጥረት ይደረጋል። በተለይ ኢትዮ ቴሌኮም ለግል ባለሃብቶች በሩን ክፍት በማድረጉና ይህንኑ ተከትሎ መሰረተ ልማቱ የመስፋት እድሎች ስለሚኖሩ ውጣውረዱን መቋቋምና አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ ማቅረብ ይቻላል።
በአሁኑ ጊዜም ድርጅቱ ቀስ በቀስ እድገትና መሻሻሎች እያሳየ መጥቷል። ለጊዜውም ከ ‹‹ቻፓ›› እና ከ ‹‹ቴሌ ብር›› ጋር በመሆን እየሰራ ይገኛል። በሂደት ደግሞ እቁብን በቴክኖሎጂ የማሳለጥ ተግባር በሀገር ደረጃ መለያ እንዲሆን በማድረግ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ወደ ኬኒያ፣ ሩዋንዳና ጂቡቲ ጭምር እንዲሰፋ የማድረግ ውጥን አለ።
ጥናቶችም እቁብን ጨምሮ ፋይናስን በቴክኖሎጂ የማሳለጥ ተግባር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ተግበራዊ እየሆነ እንደሚገኝ ያሳያሉ። ሙሉ ስያሜውም /Rotating Saving And Credit Association/ ተብሎ ይጠራል። ከዚህ አንፃር ይህን ቴክኖሎጂ መለያ በማድረግ በኢትዮጵያ መስራት ከተቻለ በአህጉርና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚሰፋበት እድል አለ። የማህበረሰቡ የዲጂታል እውቀትም በጊዜ ሂደት እየተሻሻለ ይመጣል ተብሎ ይታሰባል።
እቁብን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የማሳለጡ ተግባር በአሁኑ ጊዜ በሙከራ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚናገረው ወጣት አቤኔዘር፤ በቀጣይ እ.ኤ.አ በ2023 አዲስ አመት ሙሉ በሙሉ ወደትግበራ እንደሚገባ ይጠቁማል። ከዛ በፊት ባሉት ጥቂት ወራት ግን እቁብን መሰብሰብና ከአገልግሎት ክፍያ ገቢ ማግኘት ብቻ ሳይሆን አጋር አካላትን በማሰባሰብ እቁቡ እስኪያልቅ ድረስ ደምበኞች ሸመታ እንዲፈፅሙ በማሰብ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ያመላክታል።
ለአብነትም ድርጅቱ ፈሬሽ ኮርነር፣ ብላክ ፐርፐዝ ኢትዮጵያና ሌሎች መሰል ድርጅቶች ጋር በአጋርነት እየሰራ እንደሚገኝ ይጠቅሳል። ወደፊት ደግሞ ደንበኞች እቁብ በመጣል እንደ አስቤዛና የቤት እቃዎችን የመሰሉ መሰረታዊ ሸመታዎችን በመተግበሪያው አማካኝነት እንዲከውኑ የማድረግ ውጥን መያዙንም ወጣት አቤኔዘር ይጠቁማል። በአሁኑ ጊዜ ግን እርሱና ጓደኞቹ እቁቧን ብቻ በማስጣል ቴክኖሎጂው ያስኬዳል ወይስ አያስኬድም የሚለውን የመሞከር ሂደት ላይ እንደሚገኙም ነው የሚጠቅሰው።
ቴክኖሎጂ ችግር መፍቺያ መሳሪያ ከሆነ ሰነባብቷል። የሰዎች ህይወትና የአኗኗር ዘይቤም በቴክኖሎጂ እየቀለለ መጥቷል። የሰዎችን የአኗኗር ሁኔታ ከማሻሻል በዘለለ ቴክኖሎጂ የሀገርን ኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድም ቁልፍ ሚና እየተጫወተ መጥቷል። መንግስትም በቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት በማድረግና በጀት በመመደብ የዜጎችን ህይወት ለማሻሻልና የሀገርን ኢኮኖሚም ለማሳደግ ብርቱ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
ለዚህም ቴክኖሎጂውን የሚመራና የሚቆጣጠር ተቋም ከመገንባት ጀምሮ ሌሎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራን የሚያግዙ ተቋማትን አቋቁሞ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል። በዚህ ረገድ ደግሞ ወጣቶች በቴክኖሎጂ ላይ አተኩረው በመስራት ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንደሚጠቅሙ ይጠበቃል።
ወጣት አቤኔዘርና ጓደኞቹ ሀገር በቀል የገንዘብ ቁጠባ መንገድ ከሆነው እቁብ በመነሳት በቴክኖሎጂ ተደግፎ እንዲሰራ እያደረጉ ያሉት ጥረትም ለዚህ ጥሩ ማሳያ በመሆኑ ሊበረታታና ሊደገፍ ይገባል። መንግስትም መሰል ተግባራትን ለመፈፀም ዝግጁ ለሆኑ ወጣቶች ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
እኛም ወጣት አቤኔዘርና ጓደኞቹ ቴክኖሎጂን መሰረት አድርገው እቁብ ላይ እየሰሩ ያሉትን ተግባር በማድነቅ በቀጣይ ስራቸው መሬት ላይ ወርዶ ከራሳቸው አልፎ በርካቶችን ሊጠቅም እንደሚችል ተስፋ እናደርጋለን። ሌሎች ወጣቶችም በእነርሱ ስራ ተነሳስተው ቴክኖሎጂን በመጠቀም ችግር ፈቺ ስራዎችን ይሰራሉ ብለን እናምናለን። በዚህም ከራሳቸው አልፈው ሀገራቸውንም እንደሚጠቅሙ ይታሰባል።
ሰላም!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 16/ 2015 ዓ.ም