ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ እንደ ችግር ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ የዕድሜ ተገቢነት ነው፡፡ የዕድሜ ገደብ ባላቸው አህጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የሚስተዋል ችግርም በሳይንሳዊ መንገድ ተረጋግጦ በርካታ የአፍሪካ አገራትን ከጨዋታ ውጪ ሲያደርጋቸው በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ኢትዮጵያም በዚሁ ችግር ውስጥ የምትገኝ አገር ስትሆን በውድድሮች ላይ በትክክለኛ ዕድሜያቸው የማይሳተፉ አትሌቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ፤ በጉዳዩ ላይ የሚደረገው ቁጥጥርም እንደላላ ቀጥሏል፡፡ በዚህም በትክክለኛ ዕድሜያቸው የሚወዳደሩ አትሌቶች ተጎጂዎች ሲሆኑ ስፖርቱም ተተኪ አልባ ሲሆን ተስተውሏል፡፡
ይህ አሳሳቢ የሆነ ጉዳይ በቅርቡ በተካሄደው 26ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ልዩ ትኩረት ከተሰጠባቸው አጀንዳዎች መካከል ቀዳሚው ነበር፡፡ የፌዴሬሽኑ የህክምና ባለሙያ ዶክተር አያሌው ጥላሁን በጉዳዩ ላይ ለጉባኤተኛው ገለጻ ሲያደርጉ፣ «የዕድሜ ተገቢነት ችግርን ሌላኛው የስፖርት አበረታች ቅመም ነው» በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ተናግረዋል። በቅርቡ አሰላ ላይ በተካሄደው የታዳጊና ወጣት አትሌቶች ውድድር ላይ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑ አትሌቶች ከዕድሜ በላይ የሆኑ እንደነበሩ የጠቆሙት ዶክተር አያሌው፣ የሚሊተሪ መሠረት ያላቸው የስፖርት ክለቦች ጭምር አትሌቶቻቸውን በእነዚህ ውድድሮች ላይ ማካፈላቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት እና በተተኪ ወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ አቅም ያላት አገር ብትሆንም የዕድሜ ተገቢነት ግን አሁንም ችግር ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ፌዴሬሽኑ ከ18 ዓመት እና ከ20 ዓመት በታች ዓመታዊ ውድድሮችን ሲያካሂድ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ያወጣበታል ነገር ግን ዓላማውን በትክክል ማሳካት አልቻለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዕድሜ ገደብ የሚካሄዱ ውድድሮች ላይ ክልሎችና ክለቦች ተገቢነቱን ሳይሆን ለሜዳሊያና የዋንጫ ተሸላሚነት ቅድሚያ ስለሚሰጡ መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል።
እንደአገር በስፖርት ትምህርት ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ባለሙያዎች ቢኖሩም በጉዳዩ ላይ ግን መፍትሄ የሚሆን ሃሳብ መሬት ማድረስም አልቻሉም፡፡ የሚመለከታቸው አካላትም ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ምክንያትም ተተኪ አትሌቶች እንዲሁም አገር እየተጎዳች ስለመሆኗም ዶክተር አያሌው ይጠቁማሉ፡፡ ሁሉም ክልሎች ላይ ከ16፣ 18 እና 20 ዓመት በታች ፕሮጀክቶችና ማሰልጠኛዎች እያሉ ውድድሮች ላይ ግን በሚፈለገው ልክ ታዳጊዎቹ ተሳታፊ እየሆኑ አይደለም። ፌዴሬሽኑም ቢሆን ችግሩን ተመልክቶ ከማለፍ ባለፈ እርምጃ አለመውሰዱ ለዕድሜ አጭበርባሪዎቹ እንደማበረታቻ እየሆናቸው ነው፡፡ በመሆኑም ጠቅላላ ጉባኤው መፍትሄ ላይ መድረስ አሊያም ውድድሩን ማስቆም ተገቢ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ደራርቱ ቱሉም የዕድሜ ተገቢነት ሊቆም ያልቻለ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ገልጻለች፡፡ ከዚህ ቀደም በታንዛኒያ ዳሬሰላም በተካሄደ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት ብታመጣም አትሌቶቹ ግን ከሌሎቹ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት በዕድሜ ልቀው የታዩበት እንደነበር አስታውሳለች፡፡ ይህ ሁኔታ በሌሎች ውድድሮች ላይም የታየ እና ከስፖርታዊ አበረታች ቅመሞች ተነጥሎ ሊታይ የማይችል ማጭበርበርም ነው፡፡ ነፃ ስፖርት በእኩል ዕድሜና በዕኩል ዓይን መካሄድ ስለሚገባው ችግሩን መቅረፍ ተገቢ መሆኑንም አመላክታለች፡፡
ጉዳዩ በብሔራዊ ደረጃም ሆነ በምሥራቅ አፍሪካ፣ በአህጉርና ዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ በስፋት የሚስተዋል መሆኑ በጠቅላላ ጉባኤውም ላይ አጀንዳ ሊሆን አስችሎታል፡፡ አትሌቶችን በውድድሮች ላይ የሚያሳትፉት ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ናቸው። እነዚህ አካላት ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ አድርገው እና ረጅም ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ለውድድር ከሄዱ በኋላ ማቋረጥና ወደመጡበት እንዲመለሱ ማድረግ ከባድ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ዓመት ጀምሮ ችግሩ ካልተቀረፈ የፌዴሬሽኑ አቅጣጫ የሚሆነው ክለቦች የማይካፈሉበትን ውድድር፤ በአገሪቷ ባሉት ከ37 በላይ ፕሮጀክቶች እና ከ8 በላይ የማሰልጠኛ ማዕከላት መካከል ማካሄድ ነው፡፡ በመሆኑም ጠቅላላ ጉባኤው ይህንን እንዲገነዘብ በማድረግ ከዚህ በኋላም ችግሩ የማይቀረፍ ከሆነም ፌዴሬሽኑ መሰል ውድድሮችን እስከመሰረዝ የሚደርስ ውሳኔ ላይ መድረሱን በፕሬዚዳንቷ በኩል አስታውቋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም