ከባለፈው ዓመት ነሐሴ 1 ጀምሮ በቢሾፍቱ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የጤና ስፖርት ማህበራት ውድድር ፍጻሜ አግኝቷል። ከ35፣ ከ40 እና ከ50 ዓመት በላይ ምድብ የዙርና የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ተደርገው ላሸነፉ ቡድኖች እውቅና እና የዋንጫ ሽልማት በመስጠት ውድድሩ ሲጠናቀቅ የመርካቶ አካባቢ ጤና ስፖርት ማህበር አጠቃላይ አሸናፊ መሆን ችሏል።
በቢሾፍቱ ስታድዬም ከ50 ዓመት በላይ በተደረገ የፍጻሜ ጨዋታ መርካቶ ጤና ስፖርት ማህበር የቢሾፍቱ አቻውን በመለያ ምት በመርታት ቻምፒዮን ሆኗል። በኦሊምፒክ ሜዳ በተደረገ ከ40 ዓመት በላይ መርሃ ግብርም መርካቶ ሳሪስን በማሸነፍ የምድቡ ባለ ድል ሆኗል።
ከ35 ዓመት በታች የተካሄደውን የዙር ጨዋታ ቢሾፍቱ ከተማ ጤና ስፖርት ማህበር በበላይነት አጠናቆ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል። ከሦስት ወራት ለበለጠ ጊዜ በቢሾፍቱ የተለያዩ ስታድዬሞች በተከናወኑ ጨዋታዎች በኮከብ ተጨዋችነትና ግብ አስቆጣሪነት ብሎም በኮከብ አሰልጣኝነት የተመረጡ ተሳታፊዎችም እንደ ውጤታቸው የተለያዩ የማበረታቻ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።
ዓመታዊ ውድድሩ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲስፋፋ የኢትዮጵያ ጤና ስፖርት ማህበርን ከመመስረት በተጨማሪ የውድድሮችን ቁጥር ማሳደግ ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት ተፈራ ደምበል ተናግረዋል።
ከውድድሩ አሸናፊዎች ባለፈ በምስጉንነታቸው ለተመረጡ ማህበራት፣ በትክክለኛ ዕድሜ ተሳታፊዎችን ላቀረቡ ቡድኖችና ለማህበሩ ፍሬያማነት ለተጉ በጎ ፍቃደኞች የቢሾፍቱ ከተማ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች እንግዶች የእውቅና ሰርተፊኬትና ሽልማት በመስጠት ዓመታዊ ውድድሩ ተጠናቋል።
ከ20 በላይ የጤና ቡድኖች በሦስት የዕድሜ ካታጎሪ ተከፍለው ላለፉት አስራ ሦስት ሳምንታት ሲወዳደሩ የቆዩበት ይህ የስፖርት መድረክ በየአመቱ ኅብረተሰቡ ስፖርት በመስራት ጤናውን እንዲጠብቅ ከማድረጉም ባሻገር በተጨዋቾች ዘንድ ቅርርብን በመፍጠር ወንድማማችነትን እና ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር ከመፍጠር አኳያ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተጠቁሟል።
የዘንድሮ ውድድር የአዲስ አበባ ጤና ቡድን አመራሮች፣ የውድድር ኮሚሽነሮች እና አልቢትሮች ከሌላው ጊዜ አንፃር ጨዋታዎቹን በጥሩ ሁኔታ በመምራት እንዳጠናቀቁም ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በ1986 ዓ.ም በሁለት ቡድኖች የተጀመረው የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ ዛሬ ላይ አርባ ሁለት ማሕበራትን እያሳተፈ ይገኛል። እነዚህ ማሕበራት በየአካባቢው ከዚህ ቀደም በስፖርቱ ውስጥ ያለፉ ግለሰቦችን ያካተቱ ሲሆን ቢሾፍቱ ላይ የሚያካሂዱትን ዓመታዊ ውድድርም በሦስት የዕድሜ ካታጎሪ ተከፍለው ያካሂዳሉ። ከ35 ዓመት በታች፣ ከ40 ዓመት በታችና ከ50 ዓመት በላይ ዕድሜ ላይ የሚገኙ የማሕበራቱ አባላት ውድድሮችን ያካሂዳሉ።
ሁሉም ውድድሮች የእግር ኳስን ሕግና ደንብ መሠረት አድርገው የሚካሄዱ ሲሆን፣ ከአስራ ሦስት ሳምንታት በላይ በሚፈጀው ፉክክር 208 ጨዋታዎች ይከናወናሉ። በዘንድሮው ውድድር አራት አዳዲስ ማሕበራት የተካተቱ ሲሆን፣ በመክፈቻው ዕለት ሃያ ያህል ጨዋታዎች በቢሾፍቱ ሰባት የተለያዩ ሜዳዎች ተከናውነዋል። እንደ አጠቃላይ ከሃያ ሺ በላይ ተመልካቾችም ይህን ውድድር ይከታተላሉ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2015