የማዋዣ ወግ፣
የባህርይ ጥናት ተመራማሪዎችና የአነቃቂ ንግግር ባለተሰጥዖዎች ዕንቁራሪትን አስመልክተው የሚጠቅሱት አንድ የተዘወተረ ምሳሌ አለ፡፡ ምሳሌው በትንሽ በትልቁ ዘንድ በሚገባ የሚታወቅ ቢሆንም ለዚህ ጽሑፍ ማጎልበቻነት የሚመጥን መስሎ ስለታየን ደግመን እናስታውሰዋለን፡፡ በሰሞንኛው የውሎ አምሽቷችን ተግባቦት (Communication) ዋነኛ አጀንዳ አድርገን እንደ ኅዳር ጭስ “እየታጠንበት” ላለው “የልብ ትርታችንም” የምሳሌው ዐውዳዊነት ገላጭ ስለሆነ ከርዕሰ ጉዳያችን ጋር በሚገባ የሚጎዳኝ ይመስለናል፡፡
“አንዲትን ዕንቁራሪት በሰፊ የብረት ድስት ገበቴ በተሞላ ውሃ ውስጥ ጨምረን እሳት ላይ ብንጥዳት ዘልዬ ካልወጣሁ ብላ ላትወራጭና ላትንፈራገጥ ትችል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ውሃው ለብ እያለ ሲሄድ በሙቀቱ ምክንያት ስለምትዘናጋ በፍል ውሃው ነፍራ እስክትገነትር ድረስ አብጣ ብትነረትም የድሎትና የተዝናኖት ውጤት ስለሚመስላት እየሞተች መሆኗ እንኳን ትዝ ላይላት ይችላል፡፡”
“ዕንቁራሪት ዝሆንን አክላለሁ ብላ ፈነዳድታ ሞተች” የሚለው ብሂል መነሻው ይህ ታሪክ ሳይሆን የሚቀር አይመስለንም፡፡ ካልሆነም ምሳሌውንና ብሂሉን ብናዛምዳቸው ክፋት የለውም፡፡ በአንጻሩም ያቺውኑ ዕንቁራሪት በፈላ ውሃ ውስጥ ብንከታት ሙቀቱና ፍላቱ እንግዳ ስለሚሆንባት ዘልዬ ካልወጣሁ ብላ አጥብቃ መንፈራገጧ አይቀርም፡፡”
የፍል ውሃ ዋናተኞቹ የሀገሬ ሙሰኞችና ሌቦች፤
የመንደርደሪያችንን ማዋዣ እዚሁ ላይ ገታ አድርገን ወደ ዋነኛው ጉዳያችን እንዝለቅ፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰሞኑ የፓርላማ ንግግራቸው ያስጨበጨበላቸውን አንድ ጉዳይ በግልጽነት ነግረው አደፋፍረውናል፡፡ ንግግራቸው ጭል ጭል የምትለው የተስፋችን ኩራዝ ደመቅ ብላ እንድትበራም ምክንያት የሆነ ይመስለናል፡፡ በቁርጠኝነት ይፋ ለገለጡትና በክፉ ነቀርሳነት ለሚመሰለው ሀገራዊ የሌብነት ፈተናችን ማስታገሻነት ለተሰጠው መንግሥታዊ ውሳኔ ባናመሰግን ባለ ዕዳ እንሆናለን፡፡ በተለየ ሁኔታ ግን “የማይታለፈው ቀይ መስመር ወደ ቀይ ምንጣፍነት መለወጡን” የገለጹበት አነጋገር በዚህ ጸሐፊ ግምት የዓመቱ ድንቅ ገለጻ ሆኖ ቢመዘገብ ይበዛበታል የሚባል ዓይነት አይደለም፡፡
እንደኛዎቹ ጉደኛ ሌቦች የሕዝብና የሀገር ሀብት በመዝረፍ የተካኑ የሌሎች ሀገራት መሰል የሌብነት ባለ ታሪኮች ይኑሩ ወይንም አይኑሩ ለማወቅና ለማነጻጸር ምርምርና ፍተሻ ማድረጉ እጅግም የሚጠቅም
አይደለም፡፡ መኖሩ ቢያጠራጥረንም “ሞልቶ” ብለው ለሚሟገቱ ተከራካሪዎች የውይይቱን በር ላለመዝጋት ሲባል ብቻ የሚያውቁትን ቢያሳውቁን ለዕውቀትም ሆነ ለጸሎት ሊረዳ ስለሚችል በየት ሀገርና እንዴት እንደሆነ ቢነግሩን አይከፋም፡፡ ይህንን የምንልበት አጥጋቢ ምክንያት ስላለን መከራከሪያችንን እናብራራለን፡፡ ብሶታችንን በነፃነት ዘርግፉ ስለተባልን “ሀገር ያወቃቸውን፤ ፀሐይ የሞቃቸውን” አንዳንድ “የአደባባይ ምሥጢሮችን” ብቻ ለማሳያነት ለመጠቋቆም እንሞክራለን እንጂ ችግሩን ሁሉ አሟጠን እንዘረዝራለን ማለት አይደለም፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በአንዳንድ አካባቢዎችና ጥቂት በማይባሉ የክልል ከተሞች ውስጥ “የሙስና ሠፈር” የሚባሉ አካባቢዎች መኖራቸውን መንግሥት “አልሰማሁም፣ አላወቅሁም” ብሎ የኢትዮጵያን ስም እየጠራም ሆነ ሕገ መንግሥቱ ላይ እጁን ጭኖ ቢምል ቢገዘት እንኳን ልንሰማው ቀርቶ ጉዳዬ ብለን ጆሯችንን ለመስጠትም ይቸግረናል፡፡ ምክንያቱም በሚገባ ያውቀዋል፡፡ መረጃውም በእጆቹ ላይ ናቸው፡፡
አልፎም ተርፎ የአካባቢዎቹ ስያሜ በሕግ የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ “የሙስና መንደር” እየተባለ በሕጋዊ ሰነዶች ሁሉ ላይ ሳይቀር የሚጠቀስላቸው አካባቢዎች ብዙዎች ናቸው፡፡ ጠቢቡ ባለሀገር “የጉድ ሀገር ገንፎ እያደር ይፋጃል” ማለቱን ወድጄለታለሁ፡፡ እናስ ለሌብነት እንዲህ ዓይነት ዕውቅና የሰጠ ሌላ ሀገር አለ ቢባል ማን ይቀበላል?
ሁለተኛ፤ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና አውራ ጎዳናዎች ላይ እየተንፈላሰሱ ጌቶቻቸውን የሚያንፈላስሱት ሽንጠ ረዣዥሞቹ አብዛኞቹ በምንትስ ብራንድ የሚታወቁት የፒክ አፕ መኪኖች (የጥቂት ላብ አደር ‹?› መኪኖችን ፍረጃው አይመለከትም) ስያሜያቸው የሙሰኞችና የደላሎች መባሉን መንግሥታችን አልሰማ ይሆን? ባለንብረቶቹስ እየመነዘሩ መኪኖቹን ንብረታቸው ያደረጉት የሕዝብ እምባ እየሰፈሩ መሆኑ አይታወቅምን? “ከኑግ ጋር የተገኘሽ ሰሊጥ አብረሽ ተወቀጭ” በማለት ጥቂት ጨዋ ንጹሐን አብሮ ስማቸው እንዳይነሳ አደራ እንላለን፡፡
“እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን” የሚለው ደርጋዊ ብሂል ዛሬም በሠላሳ ዓመቱ መልዕክቱ እንዳልደበዘዘ ስለምንጠረጥር የምንተነፍሰው የብዕራችንን ልጓም ገታ በማድረግ ነው፡፡ መንግሥት መረጃው የለኝም የሚል ከሆነ (እንደማይል ተስፋ በማድረግ) የትራንስፖርት ቢሮዎችን ዶሴ በመመርመር “ንጹሐንን እንዲያመሠግን፣ ዘራፊዎችን እንዲለይ፣ ግፉዓንን በፍትሕ እንዲዳኝ” አቤቱታ እናቀርባለን፡፡
ለመሆኑ ስሙ ቤትኛ፣ ተግባሩ እንደ ሰማይ የራቀብን የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ጉዳይስ ዝም ተብሎና ተድበስብሶ ሊያልፍ ይሆንን? ሀገር እንዲታደግ ከላይ እስከ ታችኛው የሀገሪቱ ዳርና ጠረፍ ድረስ በመንግሥት መ/ቤቶችና በልማት ተቋማት ውስጥ መዋቅሩ ተዘርግቶ የሀገሪቱ ሀብት ሲፈስለት የኖረው ኮሚሽን ዕድል ፈንታው ምን ሊሆን ነው? ጠይቁ ስለተባልን እንጠይቃለን፣ አትጠይቁ ከተባልንም ዝምታችንን እያመነዠግን ቀን እንገፋለን፡፡
በየሚዲያው ማስታወቂያ እያስነገረ ሲያደነቁረን የታገስነው “የፌዴራሉ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን” ወይ እንደ ስሙ ይጀግን አለያም ስሙን ለሰጠው አካልና ሀገር መልሶ በማስረከብ እንደ ፍጥርጥሩ ይሁን፡፡ ለምሳሌ፡- “የመንግሥት ሹመኞችንና የሕዝብ ተመራጮችን ሀብት እመዘግባለሁ እያለ እንዳልፎከረ ስለምን እንደ ቃሉ ሪፖርቱን በግላጭ ለሕዝብ ይፋ አላደረገም? የሰነፍ ዱላ ዘጠኝ ነው እንዲሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የመንግሥት ሠራተኞችንም ሀብት ጨምሬ እመዘግባለሁ ብሎ ምኞቱን ከፍ ማድረጉ
አይዘነጋም፡፡ እኮ ስለምን በመሐላ ጭምር የገባልንን የተስፋ ቃሉን ቅርጥፍ አድርጎ ሊበላ ቻለ? መልስ ባናገኝም መጠየቃችንን ሳናቆም “ልብ አድርጉልን” በማለት ለታሪክ እማኝነት እያስመዘገብን እናልፋለን፡፡
ከሰሞኑ የተቋቋመው “የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ” ጉዳይ ከዚህ በተግባር ሳይሆን በዕድሜ ርዝመት ካፈጀው ተቋም ጋር ያለው የስምና የተግባር መወራረስና መለያየት እስከ ምን ደረጃ እንደሆነ እስካሁን
አልተገለጸልንም፡፡ ግማሽ ሥልጣኑ ተገምሶ የተወሰደበት ተቋሙ የቀረው ከፊል ጎኑ “ሥነ ምግባር” የሚለው ብቻ እንደሆነ ባያስረዱንም ገብቶናል፡፡ ለማንኛውም አዲሱ ጎጆ ወጭ ብሔራዊ ኮሚቴ የት ድረስ እንደሚዘልቅ ለጊዜ ጊዜ ሰጥተን በትዕግሥት እንጠብቃለን፡፡ ሕዝቡ መረጃ እንዲያቀብል ተለይቶ የተሰጠው ባለ አራት ዲጂት 9555 የስልክ መስመርም እንደ ጓደኛው እንደ ኤሌክትሪክ አገልግሎቱ 905 ልሳኑ ተዘግቶ ዲዳ ሆኖ እንዳያበሳጨን ከወዲሁ ሕዝባዊ መልዕክታችን ይድረስልን እንላለን፡፡
ወደ ዕንቁራሪቷ ጉዳይ እንመለስና ከዚህ ክፉ የማኅበረሰብ ነቀርሳ ከሆነው የሌብነትና የሙስና ጉዳይ ጋር እያስተያየን ጥቂት እንቆዝም፡፡ ዛሬ በሀገሪቱና በሕዝቡ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው መቅኒውን የሚመጡት (ደሙ፣ ሥጋና አጥንቱማ ተግጦ ያለቀ ይመስላል) ክፉ የቀትር ጋኔን ሌቦች ዘረፋቸውን የጀመሩት ትናንት አይደለም፡፡ ሥራቸው እጅግ የረዘመና ሴራቸውም እጅግ የተወሳሰበ ነው፡፡ እንደ ዕንቁራሪቷ ፈነዳድተው እስኪሞቱ ድረስ ዘረፋውን የተለማመዱት ቀስ በቀስ ነው፡፡ ለዛሬው አበሳችን በይደር የተላለፈው አሳርም “ያኔ በዕንቁላሉ ጊዜ” ስላልተቀጡ፤ እንዲቀጡም ባለመፈለጉ እንጂ ከልብ ቢታሰብበት ኖሮ የሀገሪቱ መከረኛ ፊት እንደዛሬው ባልገረጣ ነበር፡፡ የሀገራችንን ሌብነትና ሙስና የምንመስለው በፍል ውሃ ዋና ነው፡፡ ይዋል ይደር እንጂ የፍል ውሃው ዋናተኛ ሌቦች ሕሊናቸውና መንፈሳቸው፣ ነፍስና ሥጋቸው ገንትሮ ወደ ሲዖል እንደሚወርዱ የምንመሰክረው የምድሩንም የሰማዩንም ፍርድ እያጣቀስን ነው፡፡
ብዕረኛው ወዳጄ ክፍሌ አቦቸር (ሻለቃ) እያነባ ከከተበልን ግጥሞች መካከል (እንባውን ሲያፈስ ያይን ምስክር ስለነበርኩ) ከዚህ መልዕክት ጋር በሚገባ የሚጎዳኙትን ዘለግ ያሉ ስንኞች እየመረጥሁ ላስታውስ፤
“አረማሞው የሚነቀል ማለዳ ነው ከቡቃያው፣
ከጥንቱ ነው ከችግኙ አበባውም የሚጠጣው፣
ጠማሞቱ የሚቃናው፡፡
እንጂማ፡- ኮትኳች ከሌለ አረም ነቃይ፣
ወሳጅ ከሌለ ተቀባይ፣ ጥሩም መጥፎውም አይታይ፡፡
ይኼው ነው የእኛም ነገር፣“ሀ” ሲባል “ሀ” ቢባል፣
ጅምሩ ቀድሞ ቢዳሰስ፣ ቀድሞ ቀድሞ ቢቀነጠስ፣
መፈልፈያው ቢደፈን፣ ሥሩ ማለዳ ቢበጠስ፣
ውስጥ ውስጡ የላይ ላዩ፣ቃርሚያው በወጉ ቢነሳ፣
ባልኖረ ባልነበረ የዛሬው ክምር አበሳ፡፡
ይኼው ዛሬም እንዲሁ፣ ለቆየን ችግር እርሾ ሆኖን፣
እንደ ጲላጦስ አንጡኝ የሚል የውስጡን በውስጡ ይዞ፡፡
የችግሩ “ችግር” ይህ ነው፣ ሽምቅታው ነው የበደለን፣
የሳመን ነው የነከሰን፣ የሳቀ ነው የገደለን፡፡
እና ጎበዝ! ያለፈው ቀድሞ አለፈ
ዛሬ ለነገ እንዲቀነስ፣ ድራ ድሩን ነው መበጣጠስ፣
“አስኳሉን” ነው መፈርከስ፡፡
እንጂማ፡- ቅርንጫፉማ ጭራሮ ነው፣
ግንዱ ሲቆረጥ የሚረግፍ፣ግንዱም ቢሆን ግንዲላ ነው፣
ሥሩ ሲነቀል የሚነጥፍ፡፡
የሚሆነው ዛሬ ይሁን፣ አይኑር “ይደር” የምንለው፣
“ከመፈቅፈቅ ማለቅለቅ” እንዲሉ ነውና አበው፡፡
የሀገራችን የሙስናና የሌብነት ታሪክ መልኩና ምስሉ በዚህ ግጥም ውስጥ ከተንፀባረቀው እውነታ የሚለይ አይደለም፡፡ ሌቦቹ ለብ ባለ ዘረፋ ውስጥ ሲዘፈቁ ሙቀቱ የተስማማቸውና ለብታው የተመቻቸው ገና በማለዳው እንዳልታዩ ስለታለፉ ነው፡፡ እውነቱ ግን ሌባ የሰረቀው የሚጣፍጠው ከጉሮሮው እስኪወርድ እንጂ ወደ ከርሱ ከዘለቀ በኋላ ለሕሊናው ካንሰር ሆኖ እንደሚያሰቃየውና እንቅልፍ ነስቶ እንደሚያባንነው በግልጽ
ይታወቃል፡፡ ለምን ቢሉ ሌብነት የፍል ውሃ ዋና ስለሆነ ውሎ አድሮ ማፈነዳዳቱ አይቀርም፡፡
ሌብነት ተዋራጅነት ነው፡፡ እንደዚህ ጸሐፊ እምነት ቢሆንማ መንግሥት በቀጥታ ያገባኛል በሚላቸው ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በየሃይማኖት ተቋማትም ውስጥ ሳይቀር በዐውዳቸው ልክ “የቤተ እምነቶች ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ” አቋቁሞ ፍተሻው ቢቀጥል ምንኛ መልካም በሆነ ነበር፡፡ ለመቶ ፐርሰንት ጥቂት ፈሪ ቁጥር ባለበት ሀገር “መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው” የሚለው ገደብ ሁሌም ይህንን ጸሐፊ ከሕሊናው ጋር እንዳሟገተው ዘልቋል፡፡
ሙስናን በተመለከተ “ውሻን ምን አገባው ከእርሻ” የሚሉትን ብሂል እያስታወሱ ከቶውንም ቢሆን መንግሥትን ይህ ጉዳይ አያገባውም ማለት የሚቻል አይመስለንም፡፡ ስመ እግዚሐርና ስመ አላህ እየተጠራ ከምዕመኑ የሚሰበሰበው ሀብት ለታቀደለት ጉዳይ እንዳይውል የሚያደርጉ ሁሉ በሀገራዊው ሕገ መንግሥት ብቻም ሳይሆን በሚመሩባቸው ቅዱሳት መጻሕፍትም ጭምር ሳይቀር የሕግ ድጋፍ ስለሚኖር ጉዳዩ መንግሥትን ሊያስፈራውም ሆነ ሊያሳፍረው አይገባም፡፡
በተለየ አትኩሮት ግን ከቀበሌ እስከ ዞንና ክልል ድረስ ባሉ እርከኖችና በአገልግሎት ሰጭ መንግሥታዊ ተቋማት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ፣ ሕዝብም አራት ዐይናማ በመሆን የየድርሻን ኃላፊነት መወጣት ቢቻል ሀገራዊ መከራችን ሸክሙ ሊቀል ይችል
ይመስለናል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር እዚህ ወይንም እዚያኛው ተቋም ውስጥ ሳልጉላላ ለያውም ተከብሬ ጉዳዬን ከውኜ ወጣሁ የሚል ዜና መደመጥ ሲጀምር ይህ ጸሐፊ ስዕለቱን ለፈጣሪ ምስጋናውን ለመንግሥት የሚያቀርበው በዕልልታ አጅቦ እንደሚሆን እነሆ ቃሉን በብዕሩ ያጸናል፡፡ ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2015