ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየአመቱ በሚያካሂደው የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ከሃያ ዓመታት በላይ በዘለቀ ጉዞው ከውድድር የዘለለ ስኬቶችን አስመዝግቧል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት ጋር በተያያዘ በተገደበ የተሳታፊዎች ቁጥር የተካሄደው ይህ እንደ ስሙ ታላቅ የሆነ ውድድር ዘንድሮ ከነ ሙሉ ግርማ ሞገሱ ተመልሶ አርባ ሺ ተሳታፊዎችን በመስቀል አደባባይ አፎካክሯል። ውድድሩ ትናንት ሲካሄድ በአረንጓዴ፣ቢጫና ቀይ የመሮጫ ካኒቴራዎች ያሸበረቁ ተሳታፊዎች አዲስ አበባን ገና በማለዳው ደምቃ እንድትታይ አድርገዋታል። ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ በርካታ የውጭ አገር ዜጎችም የውድድሩ ድምቀት በመሆን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከዓለም ምርጥ አስር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች አንዱ የተሰኘው በምክንያት መሆኑን አስመስክረዋል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሩጫም በላይ ነው። በዚህ ውድድር የኢትዮጵያ መልክ ከመሮጫ ካኒቴራዎቹ ጀምሮ ይገለጻል። የውድድሩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ሌሎችም ጥቅሞች በተደጋጋሚ የሚገለጹና ሁሉም የሚረዳው ነው። ከዚህ በዘለለ በውድድሩ ላይ የሚስተዋሉ የተለያዩ ትእይንቶችና ልዩ ድባብ ታላቁ ሩጫ የኢትዮጵያ ውበት እንዲሁም አንድነት መገለጫ ሆኗል።
ውድድሩ ከስፖርታዊ ኩነት የዘለለ መሆኑ ዛሬ እንደ አዲስ የሚነገር ባይሆንም ደረጃውና የሚሰጠው ትኩረት ከዓመት ዓመት እየተመነደገ መጥቷል። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በትናንቱ ውድድር ተገኝተው ሩጫውን ማስጀመራቸው ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በተለይም ለአዲስ አበባ ከተማና ሕዝብ ልዩ ትርጉም አለው። ከንቲባ አዳነች አበቤም በትናንቱ ውድድር ተገኝተው ከፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ጋር ሩጫውን በማስጀመር ባስተላለፉት መልእክት “አብረን ስንሆን እናምራለን ፤ ኢትዮጵያችንም ከፍ ትላለች፣ የከተማችን ድምቀትና ውበት የሆነው የ2015 ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የ 10 ኪሎ ሜትር ውድድርን አስጀምረናል፡፡
ታላቁ ሩጫ ለከተማችን ከስፖርታዊ ውድድርነቱም ባሻገር የአብሮነት፣ የሰላምና የፍቅር እንዲሁም የትብብር ተምሳሌት ጭምር ነው፡፡ የውድድሩ አዘጋጆች፣ በውድድሩ የተሳተፋችሁና አሸናፊ የሆናችሁ በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ፣ ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ” ሲሉ ተደምጠዋል። በተጨማሪም ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የቀድሞ አትሌቶች እና የዘንድሮው ውድድር ተጋባዥ እንግዳ ኬንያዊቷ የኦሊምፒክ የማራቶን አሸናፊ ፔሬስ ጄፕቺርቺር ተገኝተዋል።
የቀድሞ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሚያስ አየለ ሩጫውን በባዶ ዕግሩ መሮጡ የትናንቱ ውድድር አንዱ ክስተት ነበር። የታላቁ ሩጫ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተሳተፈችበትን ሁሉንም ሜዳሊያዎች አድርጋ የሮጠችው ተሳታፊም ሌላኛዋ የሩጫው ክስተት ሆናለች።
በታዋቂ አትሌቶች መካከል የተካሄደው ውድድርም በድንቅ ፉክክር ታጅቦ ሲጠናቀቅ የ2013 ውድድር አሸናፊው አትሌት አቤ ጋሻው ከአማራ ማረሚያ ዳግም አሸናፊ መሆን ችሏል። አትሌት አቤ ጋሻው በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሲያሸንፍ የዘንድሮው ሶስተኛ ድሉ ሆኖም ተመዝግቧል። እስከ ውድድሩ መጨረሻ ሜትሮች ድንቅ ፉክክር ማድረግ የቻለውና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ጠንካራ የ3ሺ ሜትር መሰናክል ተፎካካሪ በመሆን የሚታወቀው አትሌት ሃይለማርያም አማረ ከፌዴራል ማረሚያ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ አትሌት ገመቹ ዲዳ ከኢትዮኤሌክትሪክ ሶስተኛ ሆኖ አጠናቋል።
በሴቶቹ መካከል በተከናወነው እና ሌላ እልህ አስጨራሽ ፉክክር ባስተናገደው ውድድር ደግሞ አትሌት ትዕግስት ከተማ ኦሮሚያ ደንና ጥበቃ ኢንስቲትዩት በቀዳሚነት ስታጠናቅቅ፣ አትሌት መስታወት ፍቅር ከአዲስ አበባ ፖሊስ ሁለተኛ በመሆን ውድድሯን ጨርሳለች። እልህ አስጨራሽ ፉክክር ያደረገችው የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ አትሌት ፎቴን ተስፋዬ ደግሞ ሶስተኛ በመሆን አጠናቃለች።
በውድድሩ አንደኛ ለወጡት አትሌት አቤ ጋሻው እና ትዕግስት ከተማ እያንዳንዳቸው የ150 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በአምባሳደሮች ዘርፍ በሴቶች የተካሔደውን ውድድር በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር፣ በአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር እና በኢትዮጵያ የአየርላንድ አምባሳደር በቅደም ተከተላቸው መሰረት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል፡፡ በአምባሳደር ዘርፍ ተወዳድረው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለወጡት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2015