የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው ግብርና እምብዛም ውጤታማ እንዳልሆነ ይነገራል። ለዚህም እንደ ምክንያትነት ከሚነሱ ችግሮች መካከል ዛሬ ድረስ የዘለቀው በበሬ ከማረስ ያልተላቀቀ ኋላቀር የአስተራረስ ዘዴ መጠቀም፣ የምርታማነት አለመጨመር እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ። በዚህ የተነሳም ግብርናውን ወደ ተፈለገው የእድገት ደረጃ ማምጣት እንዳልተቻለ ሲነገር ቆይቷል። በተለይም ሀገሪቷ ሰላምና መረጋጋት በሌለባት በዚህ ወቅት የግብርና ዘርፉ ብዙ ጫና ውስጥ እንደሚገኝ ይታወቃል።
በዓለምም ሆነ በሀገራችን ያለው ጫና እየበረታ የመጣ ቢሆንም ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ጠንካራ ሥራዎች ለውጦች እየመጡ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። በዚህም በግብርና ልማት ከተጠበቀው በላይ ለውጥ እየታየ መሆኑን ለማሳየት የሚያስችል መረጃዎች ይፋ እየሆኑ ይገኛሉ። መንግሥትም የግብርና ምርትና ምርታማነት በመጨመር ረገድ ያከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት በየጊዜው እያሳወቀና እያስገነዘበ ይገኛል። ይህም ዘርፉን ለውጤት ለማብቃት የሚቀሩ ብዙ ሥራዎች ቢኖርም እምርታዊ ለውጥ እያሳየ ለመሆኑ ግን በርካታ አመላካቾች አሉ።
በተለይም በአሁን ወቅት በሀገሪቱ በተለያዩ ክልሎች እየተሰሩ ባሉት የልማት ሥራዎች የስንዴ፣ የሩዝ እንዲሁም ሌሎችም የአዕዝርት አይነቶች በማልማት እየታየ ያለው ለውጥ ይበል የሚያሰኝ ነው። በተለይ ስንዴን ከራስ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ መላክ (ኤክስፖርት) ማድረግ የሚቻልበት ደረጃ መድረስ እንዲሁም በሩዝ ምርት ደግሞ ከውጭ የሚገባው (ኢንፖርት) የሚደረገውን የሩዝ ምርት በማስቀረት እራስን ለመቻል እየተደረገ ያለው ጥረት የግብርናው ዘርፍ እያሳየ ያለው እድገት ቀላል የማይባል መሆኑንን ማሳያ ነው።
በዚህም ባለፈው ዓመት እድገት ከተመዘገበባቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱ የሆነው የግብርናው ዘርፍ ስድስት ነጥብ አንድ ፐርሰንት ዕድገት ማስመዝገቡ ተመላክቷል። ይህ ሁሉ የሆነው ደግሞ ሀገራችን ውስብስብ ችግር ውስጥ ባለችበት፤ ጫናው በበረታበት ሰላምና መረጋገት ባልሰፈነበት በዚህ ወቅት መሆኑ ለየት ያደርገዋል። በሀገራችን ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች በሙሉ አቅም ወደ ማምረት ተገብቶ በደንብ ምርትና ምርታማነትን ማስፋት ቢቻል ከዚህ የበለጠ እድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል ማሳያ ነው። የግብርና ዘርፍ እድገት ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በማስቀረት ከራስ አልፎ ለሌሎች መትረፍ እንዲሁም ወደ ውጭ በመላክ አቅምን ማሳደግ የሚቻል መሆኑን ማሳያ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባሳለፍነው ሳምንት 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የተናገሩት ይህንኑ የሚያጠናክር ነው። በተለይም የግብርናው ዘርፍ ያለበትን ደረጃና እያስመዘገበ ያለውን ለውጥና መሻሻል የሚያሳይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንደገለጹት በባለፈው ዓመት ከተመዘገበው ስድስት ነጥብ አራት በመቶ ዕድገት በዘርፍ ከፍለን ብናይ ግብርና ቀዳሚ እንደሆነ አንስተው ዘርፉ ስድስት ነጥብ አንድ በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን ሲገልጹ፤ በግብርና ዘርፍ ሁላችሁም በየምርጫ አካባቢያችሁ ስትሄዱ እንዳያችሁት በስንዴ እጅግ አበረታች ውጤት ተገኝቷል። ከስንዴ ባሻገር ብዙ ባንናገርለትም ሩዝ ከባለፈው ዓመት (2013 ዓ.ም) አካባቢ እስከ አምስት ሚሊየን ኩንታል ከውጭ እናስገባ ነበር። ዘንድሮ አማራ ክልል በሩዝ ምርት የጀመረውን ጥሩ ልምድ በኦሮሚያ እና በደቡብ አስፋፍተን ቢያንስ ስምንት ሚሊየን ኩንታል እንጠብቃለን። እንደ ስንዴ ለውጭ ገበያ ባንልክም ሩዝ ከውጭ ማስገባት (ኢንፖርት) ማድረግ አያስፈልገንም። በአገር ውስጥ ሩዝ ለማምረት የሚያስችል፤ በአገር ውስጥ የተመረተውን ሩዝ ለመጠቀም የሚያስችል ቁጥር እንዳለ ዘንድሮ ማየት ተችሏል።
ከዛ ባሻገር ግን በሩዝ ምርት ወደፊትም ኢትዮጵያ ከፍተኛ አቅም እንዳላት ትምህርት ተወስዶበታል። አንደኛ፣ ምርታማነቱ፤ ሰባ ሰማንያ ኩንታል በሔክታር የተገኘባቸው ቦታዎች አሉ። ከፍተኛ ምርታማነት አለው። ሁለተኛ፣ የሚጠቀምበት አካባቢም ከዚህ ቀደም በስፋት ለእርሻ አገልግሎት ያልዋሉ ቦታዎችንም ጭምር ማስፋት ስለሚቻል ሩዝ በሚቀጥሉት ዓመታት ልክ እንደ ስንዴው በከፍተኛ እምርታ ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችል እንደሚሆን ይጠበቃል። ዘንድሮ ግን ቢያንስ ከውጭ የምናስገባውን ለማስቀረት የሚያስችል ውጤት ተገኝቷል።
በቆሎም እንደዚሁ ነው። በበቆሎ ከፍተኛ ምርት እየተገኘ ነው። ስንዴ ስንዴ የሚባልበት ምክንያት ከዚህ ቀደም ስንዴ ስላልነበር በዚህ ማግኒቲውድ እና በስፋት ስለተሰራ እንጂ በቆሎ ላይም ያለው ውጤት እጅግ አበረታች ነው። ከፍላጎታችን በላይ የሆነ የበቆሎ ምርት በዘንድሮ ክረምት ተገኝቷል። በአትክልትም ያለው ጅማሮዎቹን ጥሩ የምታውቁት ነው፤ በቅርቡ አንድ ቦታ ላይ የዛሬ ሰባት ወር ተኩል ስምንት ወር የተተከለ ፓፓያ ከአንድ ግንድ እስከ ሰማኒያ እስከ ዘጠና ፍሬ የሚያበቅል ፓፓያ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሰባት ሔክታር ላይ የለማ ማየት ችያለሁ። በአትክልት ምርትም ኢትዮጵያ ከፍተኛ አቅም አላት። ጅማሯችን የግብርና ሴክተሩ ዕድገት እንዲያመጣ አድርጓል። ቡና ባለፉት አራት ዓመታት ከአራት ነጥብ ሰባት ቢሊየን በግሪን ሌጋሲ ውስጥ ከተቀመጠው ውጪ ከአራት ነጥብ ሰባት ቢሊየን በላይ አዳዲስ የቡና ችግኞች ተተክለዋል። ዘንድሮ በቡና ምርት ከ20 በመቶ በላይ ዕድገት ይጠበቃል።
እነዚህ ተደምረው ሲታዩ በኤክስፖርቱ በምግብ ራስን በመቻልም አጠቃላይ በማሳደግ ደረጃ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው። ግብርና ላይ የተጀመረው ሥራ ድጋፍ ካገኘ፣ የመንግሥት ቁርጠኛ አመራር ተጠናክሮ ከቀጠለ ኢትዮጵያን የዳቦ ቅርጫት ማድረግ የሚያስችል መሠረት እንዳለ ያመላክታል። ነገር ግን አሁንም ጅማሮ ነው። መሥራት ከሚገባን በእጅጉ ገና ሩቅ ነን ያለነው። ዋናው ፍላጎታችን ገበሬን እና በሬን መለያየት ነው። ገበሬ እና በሬ ከመሬት ጋር ባለ ከእርሻ ጋር ባለ ትስስራቸው ተላቀው በሌላ መንገድ ለምግብነት የሚውል የደለበ በሬ ማርባትና ማዘጋጀት የገበሬ ሥራ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ለእርሻ አገልግሎት በሬን እየገፉ ማረስ የሚቀርበት ደረጃ እስከምንደርስ በግብርና የተጀመረው ጥረት መቀጠል ይኖርበታል። ውጤቱ ተስፋ የሚሰጥ ቢሆንም ከዚህ አንፃር ብዙ ሥራ የሚጠበቅ ነው ሲሉ የግብርናው ዘርፍ ያለበት ሁኔታ አመላክተዋል።
በግብርና ምርቶችን ላይ እየተመዘገበ ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አበረታች እንደሆነና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያስረዱት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ተሾመ አዱኛ በበኩላቸው፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ የግብርና ምርትን በተለይም የስንዴን ምርት ኤክስፖርት ለማድረግ እያደረገች ያለው ጥረት በሀገሪቷ የኤክስፖርት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ነው ያነሱት። ኢትዮጵያ በአብዛኛው የምትታወቀው ቡናን ኤክስፖርት በማድረግ ቢሆንም አሁን ግን ስንዴን ኤክስፖርት ከማድረግ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የኤክስፖርት ባህሪ ይለወጣል።
እንደ ቻይና ያሉ ሀገራት ካየን የተለያየ አይነት ምርቶች ኤክስፖርት ማድረግ በመቻላቸው አሁን ያሉበት ደረጃ መድረስ ችለዋል። ስንዴን ኤክስፖርት በማድረግ ይህንን ታሪክ በማሻሻል በግብርና ምርት ውስጥ አዲስ ለውጥ እንዲመጣ እና ታሪካዊ እንዲሆን የሚያደርግ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል።
እንደ ዶክተር ተሾመ ገለጻ፤ አገሪቷ የማምረት አቅም አላት፤ ታመርታለች። ነገር ግን ብዙ ጊዜ ችግር የሚሆነው የገበያ አቅም ወይም ትስስር አለመኖሩ ነው። አብዛኛውን ጊዜ አምራቹ ገበሬ ከለፋ በኋላ በአንድ ቀን በሚወሰን ዋጋ ሞራሉ ይሞታል። በዚህ የተነሳ ከአውሮፓ ወይም ከአሜሪካ በሚመጡ እርዳታዎች የግብርና ምርታችንን ሲጎዳ ነበር። ይህንን መከላከል አልቻልንም። የአሁኑ የስንዴ ኤክስፖርት ግን ገበሬ ልፋት የሚቆጥርና ዋጋውን የሚያነቃቃው መሆን አለበት። በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ያላት አቅም ያሳያል። ነገር ግን ኢትዮጵያ በታሪክ የሚታወቀው የስንዴ ተረጂ በመሆኗ ነው። እንደዚህ አይነቱ ድክመት እኛ ባለመስራታችን የመጣ ነው። በአጠቃላይ አሁን ላይ የተጀመረው የስንዴ ኤክስፖርት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክ ያላትን ንግድ ትስስር የሚያስተዋወቅ ይሆናል። ጅምሩ ጥሩ በመሆኑ ከዚህ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
መንግሥት የጀመረው የስንዴን ኤክስፖርት በተገቢ ሁኔታ መመራት እንዳለበት የጠቆሙት ዶክተር ተሾመ፤ በኤክስፖርት ረገድ የሚታየው ድክመት ለዘርፉ የተቋቋመ ተቋም ባለመኖሩ ነው። በንግድና ቀጠናዊ ትስስር እራሱን የቻለ ኤክስፖርቱን የሚመራ ተቋም ያስፈልጋል። ኤክስፖርት በባህሪው መንገድ፣ ገበያ ማፈላለግ፣ ቴክኖሎጂ እና የመሳሰሉት ይፈልጋል። በየጊዜው ተወዳዳሪ መሆንንም የሚፈልግ እንደመሆኑ አንደኛው ጠንካራ የሆነ ተቋም ያስፈልገዋል፤ ሁለተኛ የሁለትዮሽ የንግድ ትስስር ማድረግን ይጠይቃል። ይሁን እንጂ አገሪቷ የፈረመችው የሁለትዮሽ የንግድ ትስስር በጣም ጥቂት በመሆኑና ጠንካራ ሥራ ባለመሰራቱ ተጎድተናል።
ከዚህ በኋላ ግን ስንዴን ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ምርቶችን ኤክስፖርት ማድረግ አለብን የሚሉት ዶክተር ተሾመ፤ ከዚህ የበለጠ ሥራ ለመሥራት የሎጂስቲክ ሥራዎች ማጠናከር እንደሚጠይቅ ይገልጻሉ። ሌላው ይህንን የኤክስፖርት ሥራ የሚሰራ የተለየ ተቋም ያስፈልጋል። ይህ ተቋም ጠንካራ የሆነ ኤክስፖርት የሚያደርጉ ተቋማቶችን ይለያል፤ ይደግፋል፤ ኤክስፖርት የት የት እንደሚደረግ ይለያል። ኤክስፖርት በሚያደርገው ምርት ላይ የተለያየ እሴት ጨምሮ ማቅረብ የሚቻልበት ሁኔታ የሚያመቻች መሆን አለበት። ለዚህም ሎጀስቲክ እና ፖሊሲ ያስፈልጋል።
‹‹ስንዴ ኤክስፖርት የሚደረገው በስፋት ስለተመረተ ብቻ ነው ወይስ እሴት ጨምረን ነው የሚለው መታየት አለበት››። ስንዴን ሁልጊዜ በጆንያ ብቻ አድርገን ኤክስፖርት ማድረግ የለብንም። እሴት በመጨመር እና የምናሽግበት መንገድ መለየት አለበት። ለምሳሌ ቻይናን ብንመለከት ከሰላሳና ከአርባ ዓመት በፊት የሩዝ እጥረት ነበረባት። አሁን የተሻለ መንገድ በመጠቀሟ ከዓለም 20 በመቶውን አቅርቦት መያዝ ችላለች። እኛ ገና የመጀመሪያችን በመሆኑ አጠናክረን መቀጠል ይጠበቅብናል። በተለይ አምራቹ መጠቀም አለበት። ነገር ግን አንዳንዴ እየሆነ ያለው ምንም ኤክስፖርት የማያውቅ አካል ብር ስላለው ብቻ ኤክስፖርት ሲያደርግ ይታያል። እንደዚህ አይነት ነገሮች ከእንግዲህ መቀረፍ ይኖርባቸዋል። ኤክስፖርት የሚያደርግ ሰው የኤክስፖርት ባህሪ ያለው፣ ተሰጥኦ እና ቴክኖሎጂ ያለው መሆን አለበት። ዝም ብሎ ብር አግኝቶ ብቻ የሚጠፋ መሆን እንደሌለበት ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሲታይ እኛ እያመረትን ነው ማለት አይቻልም የሚሉት ዶክተር ተሾመ፤ ምንም ትርፍ ያመረትነው ነገር የለም ይላሉ። ነገር ግን ይቺ ትንሽ ያመረትናት ምርት የተትረፈረፈች ይመስለናል። ነገር ግን በአግባብ መጠቀም ያስፈልጋል፤ ካልሆነ የጎንዮሽ ጉዳት አለው። ገበያን ከሚወስኑ ባህሪዎች ውስጥ አንዱ የተትረፈረፈ ምርት ነው። ካልሆነ ከገበያው ይወርዳል አቅራቢውን ይጎዳል፤ በዚያ ላይ ምርት በተፈለገ መጠን ውጤታማ እንዳይሆን ያደርጋል። የተትረፈረፈ ምርት በብዛት መኖር አለበት፤ ይህም ጥሩ ነው። ሆኖም ግን መቆጣጠርና መከታተል ያስፈልጋል። ቁጥጥር ወይም ክትትሉ በተለያየ መልኩ የሚገለጽ ሲሆን ዋጋው እንዳይወርድ አቅርቦቱ በማስፋት ገበያው በሁሉ ቦታ በማስፋት ማጠናከር ይጠይቃል። ለምሳሌ አውሮፓውያን የወተት ምርት የተትረፈረፈ ሲሆን መንግሥት ክትትልና ቁጥጥር አድርጓል። በዚህም አምራቹም እንዳይጎዳ ይሆናል። በመጨረሻም የአገሪቱ ኢኮኖሚ የበላተኛ በመሆኑን ጠቅሰው አምራቹ እንዳይጎዳ መንግሥት መደገፍ አለበት ይህ ካልሆነ ኢኮኖሚው አይቀየርም በማለት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2015