የዓለም ህዝብ የመግባቢያ ቋንቋ የሆነው የእግር ኳስ ትልቁ ውድድር ዓለም ዋንጫ፤ ዛሬ በአረብ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ይካሄዳል። ትንሿ አገር ኳታር እጅግ ከፍተኛ መዋለነዋይ ያወጣችበትን 22ኛውን የዓለም ዋንጫ በደማቅ ሁኔታ ታስጀምራለች። ባህላዊውን የአረብ ጎጆ ቅርጽ የያዘውና በሰሜን ዶሃ የተገነባው ግዙፉ የአል ባይት ስታዲየም ደግሞ የዛሬውን የመክፈቻ መርሃ ግብር ያስተናግዳል።
በዚህ ተናፋቂ በሆነው የዓለም ዋንጫ አዘጋጇ ኳታር ለመጀመሪያ ጊዜ የውድድሩ ተካፋይ ትሆናለች። ብራዚላውያን ደግሞ ስድስተኛውን ዋንጫ በማንሳት ክብረወሰኑን ከእጃቸው ላለማውጣት ይፋለማሉ። በቅርቡ ንግስታቸውን ያጡት እንግሊዛውያንም እአአ ከ1966 ወዲህ ያላነሱትን ዋንጫ ኳታር ላይ ለማንሳት ተስፋ አድርገዋል። የወቅቱ የዓለም የእግር ኳስ ኮከብና ጠበብቶች ሊዮኔል ሜሲና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ምናልባትም ከዚህ በኋላ በማይሳተፉበት በዚህ ውድድር በዋንጫ የታጀበ ታሪክ ለማስመዝገብ ወጥነዋል። ወጣት ተጫዋቾችም ብቃታቸውን ለማሳየት ለአገራቸውም ዋንጫውን ለማንሳት ጅማሬውን ዛሬ በሚያደርገው የዓለም ዋንጫ ተሰይመዋል።
ከዛሬ ጀምሮም ከ32 ብሄራዊ ቡድኖች የተወጣጡ ከ800 በላይ የእግር ኳስ ተጫዋቾች በስምንቱ የኳታር ስታዲየሞች የዋንጫ ፉክክራቸውን ያካሂዳሉ። እአአ የ2019 የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን ያስተናገደችው ትንሿ አገር ኳታር ይህንን ውድድር ተከትሎ ለስታዲየሞች፣ ለሆቴሎች፣ ለመንገድና ሌሎች መሰረተ ግንባታዎች ከ220 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር አውጥታለች። ይህ ደግሞ እስካሁን ከተካሄዱ የዓለም ዋንጫዎች መካከል ውዱ አድርጎታል።
እምብዛም የእግር ኳስ ታሪክ የሌላት ኳታር ሰባት ስታዲየሞችን ለዚህ ውድድር ያስገነባች ሲሆኑ፤ በጀርመናዊው አርክቴክት አልበርት ስፒር እና ባልደረቦቹ የተነደፉም ናቸው። ግዙፍና እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው ስታዲየሞቹ እያንዳንዳቸው ከ40ሺ እስከ 80ሺ ደጋፊዎችን የሚያስተናግዱም ናቸው። አስገራሚው ነገር ደግሞ አገሪቷ እጅግ ትንሽ ከመሆኗ የተነሳ በእያንዳንዱ ስታዲየም መካከል ያለው ልዩነት ከ60 ኪሎ ሜትር አይሰፋም፤ ሩቅ የሚባለው ብቸኛው ስታዲየም ርቀትም ቢሆን 90 ኪሎ ሜትር በመሆኑ ደጋፊዎች በቀላሉ የሚፈልጉትን ጨዋታ በቅርብ ርቀት ተመልክተው ወደ ሌሎች ስታዲየሞችም የመጓዝ እድልን የሚያስገኝላቸው ይሆናል።
ኳታር እጅግ ከፍተኛ የሚባል ሙቀት ያለባት አገር እንደመሆኗ ቀን ቀን ሙቀቱ በተለየ ሁኔታ ያይላል። ታዲያ ይህ ሁኔታ ውድድሩን በበላይነት ለሚመራው ፊፋም ሆነ ለእግር ኳስ ቤተሰቡ አሳሳቢ እንደመሆኑ ኳታር በተለየ ትኩረት የሰራችበት መሆኑን ነው ያሳወቀችው። ይኸውም በስምንቱም ስታዲየሞች የአየር ማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂዎችን ዝግጁ በመደረጋቸው በሜዳ ላይ ለተጫዋቾችም ሆነ ለተመልካች ስጋቱ የሚቀረፍበት መንገድ ተመቻችቷል።
በዚህ የዓለም ዋንጫ በፊፋ በኩል 36ዳኞች፣ 69 ረዳት ዳኞች፣ 24 የቪድዮ ዳኞች ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል። ካለፈው ጊዜ ለየት የሚያደርገው ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ዳኞች የተካተቱበት የወንዶች ዓለም ዋንጫ በመሆኑ ነው። እንስቶቹ ዳኞች ሶስት ሲሆኑ፤ ፈረንሳዊቷ ስቴፋኒ ፍራፖርት፣ ሩዋንዳዊቷ ሳሊማ ሙካንሳንጋ እና ጃፓናዊቷ ዮሺሚ ያማሺታ ናቸው። የዓለም ዋንጫ አስቀድሞ በሚካሄድበት የፈረንጆቹ በጋማ ወቅት በረሃማዋ ኳታር እጅግ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ የምታስተናግድበት እንደመሆኑ ፊፋ ወደ ህዳር ወር ሊቀይረው ችሏል። አጭሩ የዓለም ዋንጫ የተሰኘው የኳታሩ የዓለም ዋንጫ 64 ጨዋታዎችን በ28 ቀናት አካሂዶ ለማጠናቀቅ ነው የታቀደው። ኳሷ በአዲዳስ የተመረተች ሲሆን፤ መጠሪያውም ‹‹አል ሪህላ›› ጉዞው የሚል ትርጓሜ ያለው መሆኑም ታውቋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን እሁድ ኀዳር 11 ቀን 2015 ዓ.ም