ድሮ ድሮ ውይይት የምትባል የከተማ ውስጥ ታክሲ ነበረች። ተሳፋሪዎቹ ፊትለፊት እየተያዩ ከሹፌሩ ጋር በመስታወት ብቻ የሚተያዩባት ታክሲ። አንዳንዴ ቀስ ብሎ የሚጀመር ጭውውት እየሰፋ ሄዶ ተሳፋሪውን ሁሉ አሳታፊ ሆኖ ይገኛል። ተሳፋሪዎቹም አብረው ጉዞ የሚያደርጉ ሳይሆኑ ለስብሰባ የተቀመጡ ሰዎች ይመስላሉ። ፊትለፊት እየተያዩ የሚነጋገሩ ስለሆኑ ውይይቱ ይጦፋል። ወራጅ በሚኖር ጊዜ የሚገባውና የሚጫነው ውይይቱን መረበሹ ግን አይቀርም። ጨዋታውን ጀምሮ ሳይጨርስ መውረጃው ላይ የሚደርስ፤ ከውጭ የሚገባው አዲስ ተሳፋሪ ደግሞ በሞቀ ጭውውት ውስጥ የሚማገድበት ሁኔታ ሲሆን ውይይቱ እንደታሰበው ወጣ ገባ እያለ ይቀጥላል።
ውይይት በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ በስፋት በነበረች ጊዜ ከተደረጉ የውይይት ውስጥ ውይይቶች መካከል አንዱን ውይይት ለዛሬ መንደርደሪያ እናድርግ። ውይይቱ የተጀመረው ለህክምና ቀጠሮ ሄደው ዶክተሩ የለም ተብለው የተመለሱ እናት ብሶት ነበር። “እንዴት ዶክተር የለም” ተብሎ የህክምና ቀጠሮ ይሰረዛል በሚል ሁሉም በልቡ የያዘውን ቅሬታ እያወጣ በመሄድ ውስጥ ውይይቱ ተከፈተ።
አንዱ የህክምና ሰው የሙያ አጋሩ በፈጠረው ክፍተት ተበሳጭቶ እንዲህ አለ፤ “ይሄ እኮ ሙያዊ ግዴታን መወጣት አለመቻል ነው፤ እንዴት አንድ ሰው መሃላ ፈጽሞ የተረከበውን ሃላፊነት ችላ ብሎ ይገኛል። የእርሳቸው ህመም እኮ በአግባቡ ክትትል ካልተደረገበት አደገኛነቱን እንዴት ዶክተሩ ይዘነጋዋል፤ ይህ በጣም አሳዛኝ ነገር ነው።” በማለት ተናገረ።
ከህክምና ባለሙያው በመቀጠል የህግ ባለሙያ የሆነ ሰው ሃሳብ ሰጠ፤ “መልካም አስተዳደር እኮ በአንድ አገር ውስጥ መሰረት የማይዘው በተደራጀ ሁኔታ ለመብታችን ስለማንቆም ነው። ሁላችንም ችግራችንን በቡና ሰዓት ወይም እንዲህ በመሰለ የትራንስፖርት ላይ ካልሆነ በስተቀር በሌሎች የተደራጁ አሰራሮች ውስጥ አንታገልም። አሰራርን ተከትለን ቅሬታ በማቅረብ ሰዎች ሃላፊነት እንዲወስዱ ካላደረግን ችግሩ እየተፈታ ሳይሆን እየሰፋ ይሄዳል።” በማለት ሃሳቡን ሰጡ።
አንድ የእምነት አባት ደግሞ በመቀጠል “ልጆቼ የምትሉት በሙሉ ትክክል ነው፤ አንድ ነገር ግን ወሳኝ ይመስለኛል። ሰው በውስጡ የሆነውን ነው የሚሆነው። መልካም እሴት እንዲኖረው ሆኖ ያልተገነባ ሰው በህግም ሆነ በሌላ ነገር ብንሄድ በመሰረታዊነት ለውጥ ሊያመጣ አይችልም። በመልካም እሴት የተገነባ ሰው ከእሴቱ ውጭ ሲሆን የራሱ ጤንነት የታወከ ስለሚሆን ስለ ራሱ ሲል በመልካሙ መንገድ ላይ ይገኛል። ዛሬ እናንተ ልጆቻችን እኛ እናንተን ያሳደግንበት ውጤት ናችሁ። ችግሩ ዛሬ ታየ እንጂ በተጨባጭ የሆነው ትናንት ነው። ልጆቼ ትናንት በተጨባጭ የተሰራው ስራ ዛሬ እየታጨደ ነው፤ ዛሬ የሚዘራው ደግሞ ነገ ይታጨዳል። ነገሮች ከስር ከመሰረታቸው ካልተሰሩ ሁሉም ነገር በይድረስ ይድረስ መሰረታዊ ለውጥ ሊመጣ አይችልም። ዛሬ ስንቱ የመንግሥት ሃላፊ ነው በሃቀኛ መንገድ ተምሮ የትምህርት ማስረጃውን የያዘው። በሌብነት በተገኘ ትምህርት አማካኝነት በተገኘ የመንግሥት ሃላፊነት ላይ ተሁኖ እንዴት ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ባልተገባ መንገድስ በተገኘ ሥልጣን እንዴት ሕዝብን የሚቀይር ከስርቆት የጸዳ አሰራር ሊያመጣ ይችላል። እናም ልጆቼ ሁሌም ወደ መሰረቱ መመልከትን ልናፈጥን ይገባል። በመሰረቱ ላይ የሚሰራው ስራ ከሁሉም ነገር መቅደም አለበት። መሰረት ላይ ያልተሰራን ጣራው ላይ መስራት አይቻልም” አሉ።
ከሰሞኑን ኢትዮጵያ በሙስና እየገጠማት ያለውን ከፍተኛ ተግዳሮት ለማቅለል እንዲቻል መንግሥት በልዩ ሁኔታ ሊወስደው ስላሰበው እቅድ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ተረድተናል። ሙስናን በዘመቻም ለአገራችን የሚጨምረው ነገር እንዲኖር በዘለቄታም መሰረት ያለው ስራ እንዲሰራ መጋቢያዊ ነጥቦችን እናንሳ። ከዚህ ቀደም “ስቅለትን በየቀኑ” በሚል ርዕስ ስር በቀረበው መጋቢያዊ መልእክት ያነሳናቸውን ፍሬ ነገሮች ለሙስና በዘመቻ በሚሆን መንገድ አንስተን እንማርበት።
ራስን መስረቅ
“ሌባው ማንን ይሰርቃል?” ቢባል ትክክለኛው መልስ “እራሱን ነው” ። የሌብነት ድምር ውጤት ከራስ ላይ መስረቅ ቢሆንም በሌባው አዕምሮ የተሳለው ተቃራኒው ስለሆነ ሌብነቱን ባሳካ ጊዜ ውጤት ያስቆጠረ እንደሆነ ያስባል። ስለትንሹም ሆነ ስለትልቁ ሌባ አንስተን ብናወራ በጊዜ ሂደት ውስጥ ያለው ውጤቱ ከራስ ሰርቆ መገኘትን እንደሆነ እንረዳለን።
በትዳሩ ላይ የማገጠ ሰው የፈጸመው የመማገጥ ተግባር ዛሬ ነገ ታወቀብኝ እያለ በስጋት ውስጥ እንዲወድቅ ያደርገዋል። ነገርዬው የታወቀ ቀን ደግሞ በቤቱ ውስጥ የፈራው ነገር ሆኖ ይመለከታል። የፈራው በሆነ ጊዜ ሁሉም በቀረብኝ ሲል የሚቆጥራቸው የረዘሙ ቀናት ይወለዱበታል፤ የጸጸት ቀናት። በትዳሩ የማገጠው ሰው በስተመጨረሻ የሰረቀው ከማን ነው? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ ከራሱ እንደሆነ የሚገልጽ ነው። የራሱን የልብ መተማመን ማጣት፤ ሰላሙን መነጠቅ፤ የህሊና ወቀሳ ውስጥ መግባት ወዘተ የሚያሳየው በግላጭ ስርቆቱ ከራሱ መሆኑን ነው።
ከትዳር አልፈን ወደ መስሪያ ቤት እንሂድ በዋናነት ወደ ግዢ ክፍል። በሥራ ቦታው በግዢ ስራ ላይ የተሰማራ ግለሰብ በግዢ ሂደቱ ላይ በሌብነት ነገሮችን የሚያከናውን ቢሆን፤ በሌብነት እጁ ስለሚገባው እቃ ብሎ ያልሆነ ነገር እንዲገዛ የሚያደርግ ቢሆን፤ ይህ ሰው የሚሰርቀው ማንን ነው? ይህ ሰው ስለስራው በልበሙሉነት በባልደረቦቹ ፊት መመላለስ የማይችል መሆኑን ስናስብ፤ በቅርቡ ያሉ ሰዎች የሚያደርገውን የሚያውቁ እየመሰለው የሚገባበት መሳቀቅን ስንረዳ፤ የሌብነቱ ግብረአበር ከሆኑ ሰዎች ጋር ሲኖር በሞራል ጉዳይ ሃሳብ ለመስጠት ሲያስብ የሚሰማውን መሳቀቅ ለማሰብ ስንሞክር የምንሰጠው ምላሽ ሌብነት የሚጎዳው እርሱን መሆኑን እንገነዘባለን።
እኛ ሰዎች ስንገናኝ በነጻነት ሃሳባችንን የመለዋወጥ ፍላጎት አለን። ስለሞራል፣ ስለ ህግ የበላይነት፣ ስለ ስፖርት፣ ስለ እምነት፣ ስለ ትዳር ወዘተ አብሮ መነጋገርና መወያየት መቻል፤ የራስን ሃሳብ ጨምሮ በሰዎች ፊት ሙሉ ሆኖ መኖርን እንፈልጋለን። ይህ ግን በተግባር የሚሆነው በውስጣችን የሆነውን መሆን ስንችል ነው።
ለአንድ ሥራ ብቁ ያልሆነ ሰው በዘመድ በኩል ወይንም በሌላ እጅ መንሻ አንድ መስሪያ ቤት ውስጥ ቢቀጠር፤ ዛሬ ነገ ሚስጥሬ ታወቀ ከሚለው ስጋት ጀምሮ በብቃት ባልተገኘበት ስራ ውስጥ በሚፈጥረው ጉድለትና የስራ ጥራት ማነስ በስርቆት መንገድ ሰላሙን ማጣቱን እንገነዘባለን።
እንዲህ እያልን የበዙ የስርቆት ማሳያዎችን መደርደር እንችላለን። የስርቆትን ትርጉም በሚገልጸው ደረጃ አድርገን ስንመለከት መዳረሻው ተሰራቂው ጋር ስንደርስ ሌባው ባሰበበት ተቃራኒ ተሰራቂውን እናገኘዋለን። በእርግጥ ሌባው በዚህ ሂደት ውስጥ የሚያገኘው ነገር ይኖራል፤ ነገር ግን በመሰረታዊነት ሌባው ራሱ ተሰራቂ ነው። ሌባው ሰላሙን፣ ጤንነቱን፣ ከሰዎች ጋር ያለውን መስተጋብር፣ በልበ ሙሉነት አንድን ነገር ቀርጾ የመንቀሳቀስ አቅምን፣ እድገትን፣ የሞራል ልእልናን፣ ወዘተ የሚሰረቅ ነው። ሰዎች እኒህ ነገሮችን ከተሰረቁ ራሳቸውን በመጠጥና በአጉል ነገሮች ውስጥ የመደበቅ መንገድን የሚከተሉ ስለሆነ በቀኝ እጁ የተቀበለውን ገንዘብ በግራ እጁ ያወጣዋል። በጊዜ ሂደት የእኒህ ነገሮች የጤናና የቤተሰብ መዋቅርን የማዳከምና የማፍረስ እንዲሁም የሕይወትን አቅጣጫ የሚቀይሩ ሆነው ይገኛሉ። አዎን ሌባ ሌላውን ይሰርቃል፤ በዋናነት ግን ራሱን ይሰርቃል!
ወረቀት ላይ እና ምድር ላይ፤
አንዳንዱ ሌብነት ወረቀት ላይ ትክክል የሆነ ስራ ሆኖ ምድር ላይ ግን በተጨባጭ ሌብነት ሆኖ የሚገኝ ነው። ባለንበት ዘመን ሙያዊነት እያደገ የመጣበትን ሁኔታን በጉልህ እናስተውላለን። ስራዎችን በሚመለከተው ባለሙያ ለማሰራት ለባለሙያ የመክፈል ባህልም እየመጣ ነው።
ከሙያዊ እድገት ጋር አብሮ እያደገ የመጣው ሙያዊ የወረቀት ላይ ሌብነት ነው። ባልተገባ መንገድ የተዘረፈን ገንዘብ፤ ኦዲተር እንዳያገኘው በሚያስችል ሁኔታ ሙያን ተጠቅሞ ወረቀት ሲሰራለት እርሱ ወረቀት አገዝ ሌብነት ልነለው እንገደዳለን። አንድ ድርጅት የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓትን ተግብሮ ነገር ግን የቁጥጥር ሥርዓቱ ሌብነትን መያዝ እንዳይችል የሚያደርግ የወረቀት ላይ ሌብነት የበረከተበት ዘመን ውስጥም እንገኛለን። በዓለም አቀፍ ትልልቅ ተቋማት ላይ የሚሰሙ የምርመራ ሪፖርቶች የሚያሳዩን ሙያን ተገን ያደረጉ የበረከቱ ቅሌቶች/ scandals በተግባር እየተፈጸሙ መሆኑን ነው።
ወደ አገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስንመጣም የተለመደው የቁጥጥር ሥርዓትን አልፎ የሚሰራውን ስርቆት የአደባባይ ሚስጥር ነው። ለይስሙላ ሦስት ፕሮፎርማ ሰብስቦ ሦስቱም ግን በአንድ ነጋዴ አቅራቢነት የሚቀርብበት፤ ወረቀቱ ሙሉ ሆኖ መሬት ላይ ግን ስርቆቱ የሚከናወንበት አሰራር ነው። ሦስት ፕሮፎርማ ሰብስቦ የተሻለ ዋጋ ሊሰጥ የሚችልን ለማግኘት የተዘረጋውን ሥርዓት ከአንድ ነጋዴ ሶስት ፕሮፎርማ በማግኘት የቁጥጥር ስርዓቱ እንዳይሰራ ማድረግ እንደ ማሳያ ሊቀርብ የሚችል ነው።
የህክምና ባለሙያው ገቢውን ለመጨመር ሲል በሙያዊ መረዳቱ የማያምንበትን ምርመራ እንደሚያዝ የሚቀርበው ወቀሳም ሌላው የወረቀት ላይ ሌብነት ማሳያ ነው። በምህንድስና፣ በመንገድ ስራው፣ በባንኮች የብድር አሰጣጥ ሥርዓት ውስጥ ወዘተ የሚከናወነውን ስንመለከት የምናየው የወረቀት ላይ ሌብነት መዋቅራዊ እየሆነ መምጣቱን እንረዳለን። በተጨባጭ ይህ በሆነበት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ እየኖርን በዘመቻ ልንፈታው የምንችለው የሙስና ችግሩ የቱ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ተገቢነት ይኖረዋል።
የመንግሥት፣ የህዝብ እንዲሁም የግል ተቋማት እንዴት አድርገው የወረቀት ላይ ሌብነትን ለማስቀረት አስበው የማይሰሩ ከሆነ በወረቀት ጋጋታ ውስጥ ሌብነት ስር እየሰደደ፤ ለሌብነት የሚመች ከባቢ እየተፈጠረ ይሄዳል። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ መንገድ ላይ ሞባይል መንትፎ ከሚሮጠው ቀማኛ በከፋ ሁኔታ ከረባት አድርጎ፤ በንግግሩ መካከል የእንግሊዝኛ ቃል ጣል ጣል የሚያደርግ ወረቀት አገዝ ሌብነትን የሚያደርግ አንቱታ የተሰጠው ሰው ከፍተኛ ነው። ለአንድ ስራ ውል እስከመግባት ጀምሮ እስከ ውሉ አፈጻጸም ድረስ የወረቀት አገዝ ሌብነት በስፋት ይተገበራል። መፍትሔውን ማሰብ እንደ አገር በሌብነት ምክንያት የከፋው ላይ ከመድረስ በፊት ያግዛል።
የሌብነት መስፋት እንደ መንስኤ ከሚቀርቡት ነጥቦች መካከል የግብረገብ ትምህርት አለመኖር፣ የእምነት ተቋማት በተከታታዮቻቸው ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ ማሳደር አለመቻል፣ አገራዊው የሥልጣን አያያዝ ሂደት ከመነሻው በሌብነት ላይ የተመሰረተ መሆን፣ የኢኮኖሚ እድገት ውስንነትና የሰው ልጅ የሚካፈለው ሀብት እያነሰ መምጣት ወዘተ ተብሎ ይቀርባሉ።
የስልጣን መያዢያው መንገድ
ሌብነት በአገር ላይ ተጽእኖ እያሳደረ፤ የሕዝብ ብሶት ሆኖ ሲገኙ፤ እንዲሁም የአገሪቱ ቁንጮን ልዩ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ሆኖ ሲሰማ ትልቅ ውጤት ለማምጣት ስራውን የሚሰሩትን ሰዎች ማሰብ ያስፈልጋል። በዘላቂነትም ከሌብነት ጋር የሚደረገው ትግል ፍሬ እንዲኖረው ግብ አድርገው የሚሰሩቱ የተቀመጡበትን ወንበር ንጽህና መመልከቱ የግድ ይላል።
በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ ሁሉም ሥርዓቶች ተገጣጥመው በአንድ ሳንባ መተንፈስ ወደሚችሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ሕዝብ የሚተዳደርባቸው ሥልጣኖች በግልጽነትና ከሌብነት በጸዳ መንገድ መያዝ እንዳለበት ይታመናል፤ በአገራችንም ሕገመንግሥት ውስጥ ይህን ለማሳካት የሚያስችል ድንጋጌዎች ይገኛሉ።
ሕዝብን ማገልገያ ሥልጣን የሚሰራበት መንገድ በማህበረሰቡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ የሆነ ተጽእኖ ያለው መሆኑ ማህበረሰቡ የሚከተለው እሴትን በሰፊው ለመግራት እድልን ይሰጣል። በህዝብ ይሁንታ የተሰራ ስልጣን በህዝብ ይሁንታ እንደሚወርድ ሲታሰብ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴውም ከሌብነት የጸዳ የመሆን እድሉ ሰፊ እንደሆነ በርካታ የምርምር ስራዎች ያሳያሉ።
በየደረጃው ውሳኔ ሰጪነት የሚመነጭበት ሥልጣን ምንጩ ብቃት ሲሆን፤ መውጫና መውረጃው ነጥቡ ውጤት ሲሆን በጤናማ መንገድ ሥልጣንን ለመስራት የሚረዳ ሆኖ ይታያል። በጤናማነት ሥልጣን ባልተሰራበት ሁኔታ ግን የሚፈጠረው የሌብነት ደረጃ መዋቅራዊ እንዲሁም የብሮክራሲው አንድ አካል ተደርጎ ሊጠቀስም ይችላል።
ግልጽነት በሰፈነበት አሰራር ውስጥ ሌብነት እድል ስለማያገኝ ሌብነት እየቀጨጨ የመሄድ እድል አለው። ከዓለማችን የትናንት እንዲሁም የአሁን ዘመን ታሪክ የምንረዳው ሥልጣን በቤተሰብ ደረጃ በተያዘበት ሁኔታ ሥልጣን በእጁ ያለቤተሰብ ሥልጣንን እንዳሻው የመጠቀም እድሉ ሰፊ ስለሆነ ስርቆት በተቀናጀ ሁኔታ በቤተሰቡ ኔትወርክ ሊመራ እንደሚችል ነው። ግልጽነት በቤተሰቡ ቁጥጥር ውስጥ ስለሚገባ ማለት ነው። አምባገነን መንግሥታት ውስጥም በተመሳሳይ ሁኔታ ከቤተሰብ በከፋ ሁኔታ ገዢው ቡድን ሥርዓት ውስጥ ያሉ ሰዎች ሥልጣንን በመጠቀም በሌብነት ውስጥ በሙሉ አካላቸው ለመገኘት በሚያደርጉት ሂደት ሌብነት እውቅና የተሰጠው የተወሰኑ አካላት መብት ሆኖም ይገኛል። ሕዝብ በገዛ ፈቃዱ መሪውን የሚመርጥበትና የሚያወርድበት ሥርዓት እስካልተረጋገጠ ድረስ ሥልጣን የሚሰራበት መንገድ ለሌብነት የራሱን አስተዋጾ ማድረጉን ይቀጥላል።
ዛሬ እንደ አገር የገባንበት ብሮክራሲውን የተቆጣጠረው ሌብነት ላይ መፍትሔ እንዲመጣ ሥልጣንን በንጽህናና በግልጽ መንገድ የመያዝ ባህልን ለማዳበር መስራት ይኖርብናል። ወጣቶቻችንን ነገ አገራቸውን ወደ መልካም ለመምራት ህልም የሚያደርጉት ዛሬ ያለውን በመመልከት መሆኑን በመረዳት።
ትናንት ሌብነትን በስቅላት ፍርድ ለመከላከል የሞከሩ አሉ። በአገራችንም ሌብነትን መጸየፍ እንዲቻል ሌባው የሰረቀውን እየተናገረ በሕዝብ መካከል እንዲንቀሳቀስ ይደረግ እንደነበር ታሪካችን ይነግረናል። ያለፈው ትውልድ ሌብነት በተለያዩ መንገዶች ለመከላከል ያደረገው ጥረት ያመጣለትን ውጤት በመመርመር ለአሁኑ ሊወሰድ የሚገባውን ትምህርት ማግኘት ያስፈልጋል።
ሁሉም ሰው ከቤቱ ከስርቆት የጸዳ አገር እንድትኖረን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት። ራሳችን በራሳችን እየተሰረቅን ሁሌም ባለንበት እየረገጥን መኖር የለብንም። ሌባው የሰረቀውን ለማሸሽ ብዙ ርቀት ይሄዳል። እኛ ደግሞ ከስርቆት ለመትረፍና መሰረታዊ ነገራችንን ለማግኘት ስለ መሰረታዊ ለውጥ እንትጋ። ሰላም።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/ 2015 ዓ.ም